
ኢትዮጵያውያን ከጥንት እስከዛሬ ተፈትነዋል፤ ፈተናቸውን ግን በድል ተሻግረዋል። ይህ ተፈትኖ የማለፍ ምስጢሩ ደግሞ ከልብ የሆነ አንድነት፣ ወንድማማችነትና ፍቅር ነው። ይህ የሰው ልጆች እውነተኛ ገጽ፤ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ፣ የማንነትና ብዝሃነታቸው መገለጫ የዓለም ተምሳሌታዊ ስማቸው ነው። ይህ እውነተኛ የኢትዮጵያውያን ማንነት ነው፤ በፈተና እንዳይሸነፉ፤ በሴራ እንዳይጠለፉ፤ በእኩያን ትርክት እሴታቸውን እንዳይሸረሽሩ አድርጎ ዘመን ያሻገራቸው፡፡
ይሁን እንጂ ትናንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጉ ሕዝቦቿን ዝቅ ለማድረግ ብዙዎች ለፍተዋል፤ ጦር ሰብቀው ድንበር ጥሰው ገብተው ተዋርደው ተመልሰዋል፤ ሲሻቸው ማንነትን፣ ሲሻቸው ሃይማኖትን ተገን አድርገው ሊከፋፍሉና ሊያዳክሟቸው በብርቱ ጥረዋል፤ ለዚህም በብዙ መልኩ ሃብት፣ ጉልበት አፍስሰዋል። ይህ ሁሉ ሴራና ሃብት ግን ኢትዮጵያን ሊያወርዳት፤ ኢትዮጵያውያንንም ከፋፍሎ ሊያዋርዳቸው አልቻለም። ምክንያቱም ብዝሃነቱ እንዳይፈርስ በኢትዮጵያዊነት ታላቅ ገመድ ተዳውሮ ተሸምኗልና ነው፡፡
ይህ የብዙሃኑ እሴት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በጥቂት ብልጣብልጦችና የሴራ ተላላኪ ቅጥረኛ የሃይማኖትም ሆነ የብሔር ካባ ለባሾች ሲፈተን ማየቱ እየተለመደ መጥቷል። በተለይ ከለውጡ ማግስት እየተቀጣጠለ የመጣው አንድነትና ሕዝባዊ ወንድማማችነት የኢትዮጵያን የብልጽግና መንገድ በእጅጉ የሚያፋጥነው መሆኑን የተገነዘቡ የውስጥም የውጭም ኃይሎች ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ለመከፋፈልና ለማባላት የሚያስችላቸውን አጀንዳ ቀርጸውን ሃብት መድበው በተላላኪ ቅጥረኞች አማካኝነት ቀን ከሌት እየተጉ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡
በቅርቡም በጎንደር፣ በወራቤ እና ሌሎችም አካባቢዎች የተገለጠው የእነዚሁ ኃይሎች እኩይ ሴራ እንጂ የአብሮ ኗሪው ሕዝብ (ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ) አለመሆኑ የታወቀ ነው። ይሄን ተከትሎ የሚራገቡ ወሬዎች፤ የሚሰራጩ የጥፋት ቀስቃሽ መልዕክቶችና ሌሎችም የውጭም ሆነ የውስጥ ጉዳይ አስፈጻሚ የጥፋት ኃይሎች እና ግብራበሮቻቸው እንጂ የብዙሃኑን አማኝ ስሜትና ፍላጎት የተሸከሙ አልነበሩም። ከኢድ እስከ ኢድ ታላቅ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪን ተከትሎም ሁነቱ እንዳይሳካ ለማድረግ እነዚሁ ኃይሎች በብርቱ ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ከኢድ አፍጥር እንዲሁም ከኢድ ታላቁ ሶላት መርሐ ግብር ጋር በተያያዘም በብዙ መልኩ መርዛማ መልዕክቶቻቸውንና አስተሳሰቦቻቸውን በብዙሃኑ ለማስረጽ ተግተው ቀስቅሰዋል። የአፍጥር መርሐ ግብሩ ላይ ያልተሳካላቸውን በሶላት መርሐ ግብሩ ለማስፈጸምም በብርቱ ለፍተዋል። የሚፈልጉት ባይሰምርላቸውም በጥቂቱም ቢሆን ግርግር ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም ትልቁ የብዙሃኑ ፍላጎት እንጂ የጥቂቶች ፍላጎት መቼም ቢሆን የሚሳካ አይደለምና ሕልማቸው በአጭር ተቀጭቶ ሴራቸው ከሽፏል። የእስልምናን የሰላም ገጽ ለማጠልሸት የሸረቡት እኩይ ዓላማ እንደ ጉም ተኖ ጠፍቶባቸዋል፡፡
በእለተ ኢድ በአዲስ አበባ የተፈጸመውን ይሄን የእኩያን የሴራ ተግባር ተከትሎ “በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራና በውስጣዊ ባንዳዎች ተባባሪነት ኢትዮጵያን የማተራመስ እኩይ ውጥን በፍፁም አይሳካም!” ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተውም፤ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የ1443ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል ሶላት በደማቅ ሁኔታ በመካሄድ በሰላም ተጠናቋል። አብዛኛው ሰላም ወዳድ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ እንዲካሄድ ያደረጉት ተሳትፎና ከፀጥታ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት ያሳዩት ተነሳሽነት በእጅጉ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው፡፡
ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለማተራማስና ለማፍረስ እንደ መሳሪያ ከሚጠቀሙባቸው ጉዳዮች ውስጥ የለውጥ ሂደቱ ፈተና ሆነው የቀጠሉት የሃይማኖት ፅንፈኝነት፣ አክራሪነትና መንደርተኝነት ዋነኞቹ እንደመሆናቸው፤ የውስጥ ባንዳዎች በሃይማኖት ሽፋን ከውጭ ኃይሎችና ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተቀናጅተው ማህበራዊ ትስስሮቻችንን ለመበጣጠስ፤ በሀገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን ለማድረግ እንዲሁም ከአንድነት ይልቅ መበታተንና መከፋፈል እንዲፈጠር አልመው እየሰሩ ይገኛሉ። በተለይም በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ካጋጠመው ረብሻ ጋር ተያይዞ ግጭቱን ወደ ደቡብ ክልል ወራቤ ከተማና ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋፋት ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ሙከራ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰሞኑን የፀረ-ኢትዮጵያ አቋሞቻቸውን በመግለፅ ቀጣይ ሊፈጥሩት ስላሰቡት ሁከት በአደባባይ ሲገልፁ ሰንብተዋል። ይህንኑ እኩይ ዓላማቸውን ትናንት በአዲስ አበባ የታላቁ ዒድ ሶላት ላይ ለመተግበር ሙከራ አድርገዋል። በሰማዕታት ሐውልትና በመስቀል አደባባይ በንብረት እና በፀጥታ ኃይሎች ላይ ከደረሰ መለስተኛ ጉዳትውጭ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ወዳድ አማኞችና በፀጥታ ኃይሎች ቅንጅት የትርምስ ፍላጎቱና ዕቅዱ ከሽፏል። በመሆኑም መላው ህዝባችን የታሪካዊ ጠላቶቻችን በውስጣችን የሚገኙ የተላላኪዎቻቸውን እኩይ ሴራዎች ተገንዝቦ ፅንፈኝነትንና መገፋፋትን በቁርጠኝነት በመታገል ህብረ ብሄራዊ አንድነቱን ማረጋገጥ አለበት፤ ያሳሰበው መግለጫው፤ መንግሥትም በፅንፈኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሲል አረጋግቷል፡፡
ይሄን አይነት የሕዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት በመሸርሸር እኩይ ፍላጎትን ለማሳካት በጥቂቶች የሚደረግ ጥረት በምንም መልኩ ቢሆን ብዙሃኑን ሊወክል አይችልም። በመሆኑም እኩይ ተልዕኮ ተሸካሚ ጥቂቶች በዝተው እንዲያውኩ እድል መስጠት ስለማይገባም፤ ዘመን የማይሽረውን የህዝቦች አንድነትና መተባበርን በማጎልበት ያለ ልዩነት ሃይማኖትን፣ ብሄርንና መንደርተኝነትን ማእከል ያደረገውን አክራሪነትና ፅንፈኝነትን መዋጋት ይኖርበታል። ይሄን ሲያደርግ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ ፈተናዎቹን በድል መሻገር ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም