ይህ ቀን የተለያዩ ስያሜዎች አሉት:: የላብ አደሮች ቀን፣ የወዝ አደሮች ቀን፣ የሠራተኞች ቀን እየተባለም ሲገልጽ ኖሯል:: የሁሉም ቃላት ትርጉሞች ተመሳሳይና የኢንዱስትሪ ሠራተኛውን የሚመለከቱ ናቸው:: በብዛት የላብ አደሮች ቀን በመባል የሚታወቅ ቢሆንም፣ በተለይ በሃገራችን የሠራተኞች ቀን በሚል ሲከበር ቆይቷል:: በውጪዎቹ ሃገሮች ደግሞ ደግሞ May day እና Labor day በመባል ይታወቃል:: እነዚህም የኢንዱስትሪ ሠራተኛውን የሚመለከቱ ናቸው::
ቀኑ በኢትዮጵያ በስፋት መከበር ከጀመረበት ከየካቲት 1966 ዓ.ም አብዮት ወዲህ በተለያየ ስያሜዎች ሲጠራ ቢቆይም ከዚያው ከደርግ ዘመን አንስቶ የሠራተኞች ቀን እየተባለ ይጠራል:: የኢንዱስትሪ ሠራተኞች ማኅበራትን ይዞ ከተመሠረተው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን በመነሳት ስንመለከተውም ቀኑ የሠራተኞች ቀን መሆኑን እንረዳለን::
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ይህን የሠራተኞች ቀን እናስታውሳለን:: አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ቀኑ ዛሬ ሆነና ዕለቱን በታሪክም አስመስሎታል:: እነሆ ስለዚህ ቀን ዓለም አቀፋዊና አገር አቀፋዊ ሁኔታዎች ከተለያዩ ሰነዶች ያገኘናቸውን መረጃዎች በማሰባሰብ ምን እንደነበርና አሁን ምን ላይ እንዳለ እናስታውሳለን:: በዚህ አጋጣሚ በዚህ ዓመት የሚከበረው በአገራችን ለ47ኛ ጊዜ ነው:: በዓለም ደግሞ ለ133 ጊዜ ነው:: የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የዓለም የኢንዱስትሪ ሰራተኞች (Industrial Workers of the World) የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድረ ገጽ እና የሐበሻ ጊዜ የአማርኛ ጦማር ሰነዶችን ያገኘንባቸው ናቸው::
የላብ አደሮች ወይም የሠራተኞች ቀን ሲባል ወደብዙዎች አዕምሮ የሚመጣው የሶሻሊስት ሥርዓት ነው:: የሚገርመው ግን ይህ ንቅናቄ የተጀመረው በካፒታሊስት አገሮች መሆኑ ነው:: በኋላ ላይ ግን የሶሻሊስት ሥርዓት አቀንቃኞች አጠናክረው አስቀጠሉት:: ለሶሻሊስት ሥርዓት መጠናከርም ፈር ቀዳጅ ሆነ:: በኢትዮጵያም ብዙ ሰው ቀኑን የሚያስታውሰው የሶሻሊስት ሥርዓት አራማጅ ከነበረው በ1966ቱ አብዮት ወደ ስልጣን ከመጣው ከደርግ መንግሥት ጋር በማያያዝ ነው::
የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ፤ ሠራተኛው መደብ በቀን የሚሠራበት ሰዓት ከስምንት ሰዓት እንዳይበልጥ ከፍተኛ ትግል ማድረግ የጀመረበት ወቅት ነበር:: በዘመኑ በቀን ከ10 እስከ 16 ሰዓት ለሥራ ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች ለአደጋ ተጋልጦ መሥራት የተለመደ ነበር:: በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ሕይወትን ማጣት፣ አካል መጉደል፣ ለዘላቂ የጤና ችግር መዳረግም የተለመዱ ሁኔታዎች እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ::
በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1860ዎቹ ሠራተኞች የሥራ ሰዓት በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ ሆኖ የሙሉ ቀን ደመወዝ እንዲከፈላቸው ባልተደራጀ መልኩ መጠየቅ ጀመሩ:: ነገር ግን የዘመኑ ከበርቴዎች ለጥያቄው ምላሽ መስጠት አልፈለጉም:: ይህም ሠራተኞች እንዲደራጁና ከፍተኛ ትግልና ተጋድሎ እንዲያደርጉ በር ከፈተ:: ቀጣሪዎች በቀን ለረዥም ሰዓታት በማሠራት ከፍተኛ ትርፍ ማግኘትን ብቻ የለመዱ በመሆናቸው የሠራተኞችን ጥያቄ ለመመለስ ፈቃደኞች አልሆኑም:: ጥያቄው ግን የበለጠ እየተጠናከረ መጣ::
ጥያቄው እየተጠናከረ ሲመጣ በወቅቱ ከከበርቴዎች ከፍተኛ ነቀፌታ አጋጠመው:: ሠራተኞችም ብዙ መስዋዕት ከፍለዋል:: ‹‹አድማ አስነስታችኋል፤ ምርታማነታችን ቀንሷል፤ እኛ ቀጣሪዎች በምንፈልገው መጠን ካልሠራችሁ አንፈልጋችሁም›› እየተባሉ ከሥራ ተሰናብተዋል:: ከ20 ዓመታት መራር ተጋድሎ በኋላ ግን የሠራተኛው መደብ የድል ጮራን ማሳየት ጀመረ::
ሠራተኞች ይህን እንቅስቃሴ ሲጀምሩ፤ ዘመኑ ሶሻሊዝም እንደ አዲስ ያቆጠቆጠበት፣ ለሠራተኛው መደብ እጅግ ምቹ የሆነ ርዕዮተ ዓለም የሰፈነበት ነበር:: ሶሻሊዝም ደግሞ ከግል ይልቅ ለጋራ ሀብት ትኩረት የሚሰጥ፣ መብቶችን በጋራ ለማስከበር የሚሞክር፣ በአብዛኛው በሩሲያ፣ ኩባና ሰሜን ኮርያ በሰፊው ሲቀነቀን የኖረ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ነው::
አብዛኞቹ ሠራተኞች የምርቱ ተቆጣጣሪ፣ አከፋፋይና ተጠቃሚ መሆን አለባቸው›› የሚል አስተሳሰብ ውስጥ የገቡበት ጊዜ ነበር:: በብዙዎች ላብ ጥቂቶች የሚጠቀሙበት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች እየሞቱና እየቆሰሉ ጥቂቶች ትርፍ የሚያጋብሱበት ካፒታሊዝም አያስፈልገንም የሚሉት ሠራተኞች ናቸው ሶሻሊዝምን እንደ አዲስ አማራጭ ማቀንቀን የጀመሩት::
ካፒታሊዝም ደግሞ ግለኝነትን የሚያበረታታና ሀብት በጥቂቶች እጅ እንዲሆን የሚያቀነቅን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ነው:: በአሜሪካና አብዛኞቹ የአውሮፓ ሃገሮች /ምዕራባውያን ሃገሮች/ የሚተገበር የፖለቲካ አመለካከት ነው::
የሠራተኛውን መደብ ሐሳብ የሚጋሩ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እንደ አሸን መፍላት ጀመሩ:: ይሁን እንጂ ቡድኖቹ የፈረጠመ ሀብት በፈጠሩት ካፒታሊስቶችና ከበርቴዎች እየተደቆሱ ውጤታማ መሆን አልቻሉም:: እንዲያውም አንዳንዶቹ ቡድኖችና የሠራተኛ ማኅበራት እየተገለበጡ የባለሀብቱ በትር ሆነው ሠራተኛውን መደብ መምታት ጀመሩ:: በዚህ የተቆጣው ሠራተኛው መደብ ከሶሻሊዝም ወደ ሥርዓት አልበኝነት (አናርኪዝም) ማጋደል ጀመረ:: ሥርዓት አልበኝነቱ ደግሞ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችን በኃይል አስወግዶ ኢንዱስትሪውን እስከ መቆጣጠርና መንግሥታትን እስከማስወገድ ድረስ የሚዘልቅ እንዲሆን የሠራተኛው መደብ ፈለገ:: በዚህም ፖለቲካዊ አካሄዶችን በኃይል በመገርሰስ ላይ ተጠመዱ፤ የሠራተኛ ማኅበራትና የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞችም የሠራተኛውን መደብ ተጠግተው ነገሮችን ማቀጣጠል ጀመሩ:: በዚህም የሠራተኛው መደብ ጥያቄ ፖለቲካ እንዲያዝል ተደረገ::
ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ ነው እንግዲህ ሚያዝያ 23 ቀን 1878 ዓ.ም የተደራጁ ነጋዴዎችና ሠራተኞች ‹‹ፌዴሬሽን›› የተሰኘ ድርጅት አንድ ሠራተኛ መሥራት ያለበት በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሆን አወጀ:: ይሁን እንጂ አሠሪዎች ይህንን ውሳኔ በፀጋ መቀበል አልፈለጉም::
ሠራተኞቹ ደግሞ በሥራ ማቆም አድማና በሰላማዊ ሰልፎች መብታቸውን ለማስከበር ጥረታቸውን ቀጠሉ:: በመጀመሪያ ተራማጆችና ሥርዓት አልበኝነትን አቀንቃኞች አመጽ ለማካሄድም ሆነ አሠሪዎችን ለማስገደድ ተቸገሩ:: ይሄኔ ሳሙኤል ፊልድማን የተባለ ግለሰብ ሥርዓት አልበኝነትን በሚያቀነቅኑት ቡድኖች ጋዜጣ ላይ ‹‹በቀን ስምንት ሰዓትም ሠራ አስር ሰዓት ባሪያ ባሪያ ነው›› ሲል አንድ ጽሑፍ አሳተመ:: ይህን ተከትሎ ሩብ ሚሊዮን የሚሆኑ ሠራተኞችና ነውጠኞች የሥራ ሰዓት በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሆን በመጠየቅ በአሜሪካ ችካጎ ከፍተኛ ተቃውሞ ማካሄድ ጀመሩ::
በዚህም ተቃውሞ ነጋዴዎች፣ የሠራተኞች ማኅበራት፣ የሶሻሊስት ሌበር ፓርቲ እና የሠራተኛው መደብ ተሟጋቾች ንቁ ተሳታፊዎች ሆኑ::: አመጹን ለመቀልበስ ክንዳቸው የዛለባቸው ከበርቴዎች እጅ ሰጡ፤ የሠራተኞች የሥራ ግዴታ በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሆን ወስነናል አሉ:: በትግሉ ውስጥ ከሠራተኛው መደብ ጎን የነበሩት ነውጠኛ ተራማጆች ድሉን ከሥራ ሰዓት ማስቀነስ በላይም ስኬታማ እንዲሆን አደረጉት:: በምጣኔ ሀብታዊ መዋቅሩ ውስጥም ለውጥ እንዲደረግ በመሻት ከሚያዝያ 23 ቀን 1878 ዓ.ም ቀጥሎ ያሉትን እንቅስቃሴዎች የሚመለከቱ ሰነዶችን ለሕትመት አበቁ::
ይህን የሠራተኞች ቀን ለማስከበር፤ ሠራተኛው ታገል፤ ጦርነት በገዥዎች ላይ፣ ሠላም በሠራተኛው መደብ ዘንድ ይስፈን፤ ሞት ለቅንጡዎችና ቦዘኔዎች፤ የደመወዝ አከፋፈል ሥርዓቱ ዓለምን ኢ-ፍትሐዊ አድርጓታል፤ አሠሪዎች በትንሽ ደመወዝ ጉልበት አይበዝብዙ፤ ወይም እነሱም ሠርተው እኩል ይከፈላቸው፤ መሥራት ወይም መሞት ምርጫቸው ይሁን፤ ፈንጅዎች ከምርጫ ኮሮጆ በተሻለ መብትን ያስከብራሉ፤ ፍላጎታችሁ ስምንት ሰዓት ማሠራት ይሁን፤ ካልሆነ የከበርቴዎችን ፖሊስና ሚሊሻ ጭምር ልክ እናስገባለን… የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ አመጾች ተቀጣጠሉ::
ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ ሚያዝያ 23 ቀን 1878 ዓ.ም በመላው የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች በ13 ሺህ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ከ300 ሺህ በላይ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ:: በችካጎ ብቻ 40ሺህ ያህል ሠራተኞች ከፖሊስ ጋር የተፋጠጡ ነውጠኞችን ተቀላቀሉ:: ነውጠኞቹ የሠራተኞችን መብት ለማስከበር ከበርቴዎችንና ገዥዎችን እስከወዲያኛው ለመፋለም እየተነሱ መደስኮር ቀጠሉ:: ሠራተኞች እንደ ከበርቴዎች ክቡር ሰው መሆናቸውን ‹‹እናውጃለን›› አሉ::
ይህን በተመለከተ በወቅቱ አልበርት ፓርሰንስ፣ ጆን ሞስት፣ ኦገስት ስፒስ እና ሉዌስ ሊንግ የተባሉ የመደቡ መብት አቀንቃኞች ስማቸው በሰፊው ይነሳ ነበር:: በእነዚህ ሰዎች አርዓያነትም በችካጎና በመላው የተባበሩት አሜሪካ ግዛቶች ሰልፎች የሥራ ማቆም አድማዎች አቀጣጠሉ:: መልካሙ ነገር ግን በሰልፎቹና አድማዎቹ እንደተፈራው የሰው ሕይወት አልተነጠቀም:: ባለስልጣናትና ከበርቴዎች በሰልፎቹ የሠራተኛውን መደብ ጥንካሬና የነውጠኞችን ከሠራተኛው መደብ መሰለፍ በቅጡ ተረዱት:: ሠራተኞችም አመጹን እየተቀላቀሉ ሄዱ፤ የሰልፈኞች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመቶ ሺዎች መሆን ጀመረ::
ሚያዝያ 25 ቀን 1878 ዓ.ም ግን በሰልፈኞችና አመጸኞች መካከል ግጭት ተፈጠረ:: ከዚያን ጊዜ አንስቶ ለስድስት ወራት ያህል ፖሊስ ሠራተኞችን በየጉራንጉሩ እያፈነ ወስዶ ማሰቃየትና ማሰር ጀመረ:: አብዛኞቹ እስረኞች የነውጠኞቹ ደጋፊዎች የሆኑ የብረታ ብረት ሠራተኞች ማኅበር አባላት ነበሩ::
ይሁን እንጂ ይህም አካሄድ አመጹን መግታት አልቻለም፤ የብረታ ብረት ሠራተኞች በታሠሩበት አካባቢ በተደረገ አንድ የቅስቀሳ ንግግር ወደ 200 መቶ የሚጠጉ ሠራተኞች በአንድ ጊዜ ከፖሊስ ጋር ገጠሙ:: ሁለት ሠራተኞች ሲሞቱ በርካቶች ቆሰሉ:: ነውጠኞቹ ሕዝቡን ከጎናቸው አሰልፈው ከፖሊስ ጋር ለመፋለም በችካጎው ሀይማርኬት አደባባይ ስብሰባ ጠሩ:: ነገር ግን በዕለቱ በነበረው የአየር ሁኔታ ምቹ አለመሆንና በማስታወቂያ ጊዜው ማጠር የተነሳ አስር ሺዎች ይካፈላሉ ተብለው ሲጠበቁ ሦስት ሺህ ሰዎች ብቻ ተገኙ:: ከተገኙት ሰልፈኞች መካከል የችካጎ ከተማ ከንቲባ እስከ ቤተሰባቸው ተጠቃሽ ናቸው:: በሰልፉ ላይ ንግግር ያደረገው ኦገስት ስፒስ ‹‹በማንም ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ አይገባም›› በማለትም ከንቲባው ጥቃት እንዳይደርስባቸውና ከሠራተኛው ወገን መሰለፋቸውንም ተናገሩ::
ይሁን እንጂ ስፒስ ንግግሩን እየቀጠለ ሲሄድ ስሜት ቀስቃሽ ቃላትን መጠቀም ጀመረ:: ይሄኔ ድንገት ሁለት ሠራተኞች ወደ ፖሊስ ተንደርድረው ሄዱ፤ ፖሊስም በአጸፋ ወደ ሰልፈኞቹ ተጠጋ::
ወዲያውኑ በፖሊስ ላይ ከማን እንደሆነ ያልታወቀ ቦንብ ተወረወረ:: ነውጠኞች እንደተናገሩት ግን ቦንቡን የወረወረው የፖሊስ ደጋፊ የሆነ ሰው ነበር፤ ፖሊስ የኃይል እርምጃ ለመውሰድና ሠልፈኞችን እንዲመታ በር ለመክፈት:: የሆነው ሆኖ ፖሊስ በወሰደው የአጸፋ ተኩስ ቢያንስ ስምንት ሰልፈኞች ሞቱ፣ አርባ ያህል ደግሞ ቆሰሉ:: በተወረወረው ቦንብ የሞተው ግን አንድ ፖሊስ ብቻ ነበር::
በእርግጥ ቦንብ የወረወረው ሰው ማንነት በቅጡ አልተለየም ነበር፤ ነገር ግን የነውጠኞች መሪዎች የተባሉ ሰዎች ማለትም አልበርት ፓርሰን፣ ኦገስት ስፒስ፣ ሚካኤል ሺዋብ፣ ጆርጅ ኢንግል፣ አዶልፍ ፊሸር እና ሉይስ ሊንግ ታሠሩ:: ለግድያውም ኃላፊነት አለባቸው ተባሉ:: ከእስረኞቹ ሦስቱ ቦንብ በተወረወረበት ሰልፍ እንኳ ያልነበሩ ናቸው:: ይህም ዓለም የእነዚህን ሰዎች መታሠር በተለየ ሁኔታ እንዲመለከተው አስገደደ፤ የታሠሩት በፖለቲካዊ አመለካታቸውና ማኅበራዊ ኢ-ፍትሐዊነትን በመታገላቸው ነው የሚል ዕይታ ተፈጠረ::
መስከረም 1 ቀን 1880 ዓ.ም ከእስረኞቹ መካከል ፓርሰን፣ ስፒስ፣ ኢንግል እና ፊሸር የተባሉት የሠራተኛው መደብ አቀንቃኞች በስቅላት ተቀጡ:: ሊዊስ ሊንግ የተባለው ተሟጋች ደግሞ በመጨረሻ በባለስልጣናት እንደሚገደል ሲያውቅ ራሱን አጠፋ:: ቀሪዎቹ የመብት ተሟጋቾች መሪዎች ፊልደን ኒቤ እና ሽዋብ ነበሩ፤ እነሱም ከስድስት ዓመታት እሥር በኋላ ነበር የተፈቱት::
በዚህ መልኩ በአሜሪካ የተቀጣጠለው ትግል ሚያዝያ 23 ቀን 1880 ዓ.ም የመጨረሻ ምዕራፍ አገኘ:: በመንግሥትና በአሠሪ ከበርቴዎች ሰዎች በቀን ለስምንት ሰዓታት ብቻ መሥራት እንዳለባቸው ታመነ፤ ተወሰነ:: ቅዳሜም እንደ እሑድ ሁሉ የሳምንቱ የእረፍት ቀን ሆነ:: በዚህ የተነሳ ሚያዝያ 23 ቀን በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ደግሞ ግንቦት አንድ ቀን የዓለም የሠራተኞች ቀን እየተባለ ለሠራተኞች መብት ሕይወት የከፈሉ ሰዎች የሚታሰቡበት ሆነ::
በዓሉ በዚህ ዘመን በዓለም በብዙ ሃገራት እየተከበረ ይገኛል:: በዓለማችን ከ66 ሃገራት በላይ ብሔራዊ በዓል አድርገው ያከብሩታል፤ ሌሎች ደግሞ ብሔራዊ በዓል ባያደርጉትም አስበውት ይውላሉ:: ከፍተኛ የሠራተኞች ተጋድሎ የተካሄደባት አሜሪካ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ከታሪክ እንዲፋቅ ጥረት ታደርግ ነበር፤ በኋላ ግን አልቻለችምና እንዲሁ አስባው ትውላለች::
በኢትዮጵያ ደግሞ በተለይም በሶሻሊስቱ የደርግ መንግሥት ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠው ነበር፤ ምክንያቱም ደርግ ፊውዳላዊ ሥርዓትን ገርስሶ የሶሻሊስት ሥርዓት ስለሚከተል የሠራተኛው መደብ አክባሪ ነበር:: ይህ ሠራተኞች ቀን በሃገራችን ሥራ ዝግ ተደርጎ ዛሬም ይከበራል::
በደርግ ዘመን ታላላቅ ሰልፎችና የተለያዩ መድረኮችን በማካሄድ ሲከበር የነበረ ሲሆን፣ እሱን አስወግዶ ወደ መንግሥታዊ ስልጣን ከመጣው የኢሕአዴግ መንግስት ወዲህ በአዳራሽ ውይይቶች፣ በኢንዱስትሪ ሠራተኞች መካከል በሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች እየተከበረ ይገኛል::
በሃገራችን ቀኑ በብሔራዊ ደረጃ ዝግ ተደርጓል:: ከሃገራዊ ለውጡ ወዲህም በተለያዩ የሠራተኞች ጥያቄዎች ላይ ምክክር በማድረግ ሠራተኞችና ማኅበሮቻቸው ድምፃቸውን በማሰማት ያከብሩታል፤ ዛሬም የሠራተኞች የደሞዝ ጉዳይ፣በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ያሉ አለመግባባቶች፣ የሥራ ደህንነት የሠራተኛውን የማኅበሮቹ አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደመሆናቸው በእዚህ ላይ የመወያያ ሰነዶች እየቀረቡ ውይይት በማድረግ ሲከበር ቆይቷል:: የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን የሚያካሂዳቸው የሠራተኛው ስፖርታዊ ውድድሮችም ሌሎች የበዓሉ ድምቀት ሆነው ቀጥለዋል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም