“ቁመትሽ ሎጋ ነው ሰንደቅ ያሰቅላል …” ከሚለው ዘመን ተሻጋሪ ጥኡም ዜማ አንሰቶ “ጠይም ዘለግ ያለ …” እስከሚለው ድረስ ቁመት የውበት መገለጫ ሆኖ በሃገራችን ዘፈኖች መካከል ብቅ ብቅ ሲል ይደመጣል። መቼም ረዘም ያለው የመወደዱን ያህል ቁመት በዛ ሲል ደግሞ “ብቅል አውራጅ”፤ “ዛፉ” እና ሌሎች ቅፅል ስሞች እየተሰጡት ሲጠራም እንሰማለን። ለዛሬ የሕይወት እንግዳችን የሆኑት አቶ ብርሄ ጋሹም ቁመታቸው ከመርዘሙም በላይ እንደ ሰማይ ስባሪ የሚታዩ ቅፅል ስማቸውም “ዛፉ” እንደሆነ ነግረውናል።
ደማቅ ፈገግታ ፈታቸው ላይ የሚነበበው እኚህ ዘንካታ ሰው በፍጹም ቤተሰባዊ ስሜት ለቃለ መጠይቅ ወደ ተቋማችን በመጡበት ወቅት ለከበባቸው ሰው ሁሉ ሰላምታ ይሰጣሉ። በግርምት ከሚመለከታቸው ሰው ባሻገር አብሬ ፎቶ ልነሳ ላለው ሰው በሙሉ ፈቃደኝነት እየቆሙ በመነሳት ወደ ውስጥ ዘልቀናል። ትህትና አክብሮት በሚታይበት ፊት ተወልደው ባደጉበት በጎጃም አካባቢ የንግግር ዘዬ እንዲህ ተጨዋውተናል፤ መልካም ንባብ።
አቶ ብርሄ ጋሹ ትውልድና እድገታቸው በጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ ዞን፣ ፋግታ ለኮማ ወረዳ፣ ድማማ አንገረፍ ቀበሌ፤ አንገረፍ ጊዮርጊስ በምትባል ልዩ አካባቢ ውስጥ ነው። ልጅ ሆነው እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የገጠር ሕጻን በተለመደ የአስተዳደግ ዘዬ ማደጋቸውን የሚናገሩት ልጅ እያሉ ከጓደኞቻቸው የተለየ ቁመት እንዳልነበራቸው ያስታውሳሉ። አቶ ብርሄ ቁመታቸው እየተመዘዘ መሆኑን ያወቁት እድሜያቸው ወደ ጉርምስናው እየተጠጋ ባለበት ጊዜ እንደነበር አይረሱም።
“ልክ ቁመቴ እየተመዘዘ ሲሄድ ማን በስሜ ይጥራኝ። ሁሉም ሰው ብርሄ የሚለውን ስሜን ረስቶ ዛፉ፣ ዝግባው . . . ሆነ መጠሪያዬ። እኔም ብሆን ካለሁበት አካባቢ ሰው የተለየሁ መሆኔን ሳስበው ከገበያውም ከአካባቢው ሰው ልዩ መሆኔ ይሰማኝ ጀመር።” የሚሉት አቶ ብርሄ “ሰው በታች እያለ እኔ በፈረስ ላይ ሆ ኜ እንደምሄድ ነው የምታየው” ይላሉ።
“አቶ ብርሄ መች ተወለዱ?” ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ “እኔ ማንበብም መፃፍም አላውቅም፤ የትውልድ ዘመኔ ይህ ነው ብዬ ባልናገርም አሁን እድሜዬ 38 ደርሷል።” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ ብርሄ አሁን በመገናኛ ብዙኃን ከታዩ በኋላ ለጋስ ኢትዮጵያውያን በርካታ ጫማዎችን ሳያበረክቱላቸው በፊት በሕይወታቸው አንድም ቀን ጫማ ተጫምተው አያውቁም ነበር።
ቁመታቸው 2 ነጥብ 50 ሜትር የሆነው አቶ ብርሄ ምስላቸው ሕዝብ ዘንድ የደረሰበትን አጋጣሚ እንዲህ ይተርካሉ። “በአካባቢያችን በበጋ መስኖ እርሻ የተዘራን ስንዴ ለመጎብኘት የአካባቢው የሥራ ኃላፊዎች ወደ ወረዳው በመጡበት ወቅት አብራ የመጣች ጋዜጠኛ ቁመታቸውን በመመልከት በጣም ተገርማ አንድ ፎቶግራፍ በማንሳት ካስተዋወቀች በኋላ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ወደ’ነ አቶ ብርሄ ቀዬ መጉረፍ መጀመራቸውን ይናገራሉ። በወቅቱ የልማት ሥራውን ለመጎብኘት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ወደ አንገረፍ አቅንተውም ነበር። ብዙ እንግዶችም አብረዋቸው ነበሩ። አቶ ብርሄም ተጠርተው ርዕሰ መስተዳደሩን በአካል ከማግኘታቸውም ባሻገር አብረውም ፎቶ መነሳታቸውን ያስረዳሉ።
“ቁመትዎ አስቸጋሪ ሆነብዎት ያውቃል?” በማለት ላነሳንላቸው ምላሽ የሰጡት አቶ በርሄ “ረጅም መሆኔን እግዜር አንዴ ከሰጠኝ ምን አደርጋለሁ ብዬ ብኖርም እየዋለ እያደረ ደግሞ ችግር አመጣብኝ። ሥራ መሥራት አልቻልኩም። ማረስ ፈተና ሆኖብኛል። ለበሬዎቹ የሚስማማው ሞፈር እና ቀንበር ሳዘጋጅ እኔን አስጎንብሶ ወገቤን ሊሰብረው ይደርሳል። ለምን በቁመቴ የሚስማማ አላደርግም ሲል ደግሞ በሮቹ አልተመቻቸውም፤ ለገሙ። አልንቀሳቀስ አሉ። ስለዚህ አርሶ መብላት ለኔ ፈተና ነው።” ይላሉ።
በቁመታቸው የተነሳ የሚገጥማቸው ፈተናው በዚህ ብቻ አያበቃም። የሚበቃቸውን ልብስ ስለማያገኙ በልካቸው ለማሰፋት ለሁለት ሰው በሚበቃ ዋጋ ጨርቅ ይገዛሉ። “ልብስማ ያው ወጪ ይጠይቀኛል እንጂ ሁለት ሰው የሚለብሰውን ባለሙያዎች ይሰሩልኛል። ልብስ ሳሰፋ እንደ ጨርቁ ሁኔታ ለሁለቱ ሰው የሚሆነው ለእኔ ይበቃኛል። ለአንድ ጊዜ 1500 ብር እንደዛ አካባቢ እከፍላለሁ። የሁለት ሰው ሂሳብ ነው የምከፍለው” ሲሉ ያስረዳሉ።
ወደ መገናኛ ብዙሃን ብቅ ካሉ በኋላ በለጋሶች እንዲህ ጫማ በጫማ ሳይሆኑ በፊት እግራቸውም ጫማ አይቶ አለማወቁን እንዲያውም የጫማ ቁጥራቸውንም እንደማያውቁት ይናገራሉ። “እሰካሁን ጫማ የማልለብስብት ምክንያት እግሬም እንደ ቁመቴ አብሮ ስላደገ ገበያ ላይ ያለው ጫማ ስለማይበቃኝ ነበር” የሚሉት አቶ በርሄ “አሁንማ እድሜ ለሃገሬ ሰው አንዱ ቀዩን፤ አንዱ ጥቁሩን ባይነት ባይነት እያመጣልኝ ባለ እልፍ ጫማ ሆኛለሁ” ይላሉ።
“ቀድሞ ጫማ ቁጥሬን አላውቅም፤ ጫማም አድርጌ አላውቅም። ጫማ የሚባል ከእግሬ ገብቶ አያውቅም። ከተወለድኩኝ ጫማ አድርጌ አላውቅም። እኔ እግሬ ትልቅ ስለሆነ ነው። ሁሌም ጫማ ስለ ማላደርግ እግሬ ተሰነጣጥቋል። አሁን ግን ካልሲው አይቀር፤ ጫማው አይቀር ባይነት ባይነት እየቀያየርኩ ነው እግዜር ይስጥልኝ” ሲሉም ባለ ውለታዎቻቸውን ያመሰግናሉ።
የአቶ ብርሄ የቁመታቸውን ልክ ሲጠየቁ ማንበብም መጻፍም ስለማይችሉ ልኩ ስንት እንደሆነ ባያውቁትም፤ በተደጋጋሚ የለኳቸው ሰዎች ቁመታቸው 2 ነጥብ 50 ሜትር መድረሱን አረጋግጠውላቸዋል። ከቤተሰቦቻቸው መካከል እንደሳቸው አይነት ቁመት ያለው ሰው አለመኖሩን የሚናገሩት አቶ ብርሄ ቤተሰቦቻቸው “ቁመትህ እንደ ጓደኞችህ ቢሆን ዓይን ውስጥ አትገባም ነበር” እንደሚሏቸው ደጋግመው ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ ቁመታቸው ልዩ በመሆኑ ካልሆነም ተወዳድሮ ‘ልዩ ነገር’ ማግኘት እንደነበረበት ሁሌም ያነሳሉ። በዚህ ምክንያትም ‘ከሁለት አንድ ያጣህ ጎመን ሆንክ ይሉኛል’ ብለዋል።
አቶ ብርሄ ጋሹ የትምህርት ቤትን ደጅ ረግጠው አያውቁም፤ የፊደል ዘር አልቆጠሩም። “ምክንያት?” ሲባሉ “ወላጆቼ ምስኪን ነበሩ” ሲሉ ይመልሳሉ። ከዘጠኝ ዓመት እድሜያቸው ጀምሮ ሰው ቤት ነው ያደጉት። ”
ሕጻን ስለሆንኩኝ እናት አባቴን አገለግላለሁ በሚል እንጂ እንደዚህ እጉላላለሁ ብዬ አላሰብኩም። አሁን ግን አዝናለሁ፤ ብማር ኖሮ ራሴም አልጉላላም፤ ቤተሰቦቼንም እረዳ ነበር።” ይላሉ።
በቁመታቸው የተነሳ ካገኙት ነገር ይልቅ የተጎዱትን ማስታወስ ይወዳሉ። ከትዝታዎቻቸውም መካከል” ሁለት ጊዜ ወድቄ በተሰበርኩ ጊዜ፣ ቁመቴ ረዥም ባልሆን ብወድቅም እንኳን እነሳ ነበር። ብዙዎች አጠገቤ እየወደቁ ሳይሰበሩ ምንም ሳይሆኑ ይነሳሉ፤ አያቸዋለሁ። እኔ ግን ስወድቅ ሁለቱም ጊዜ አንዴ ቀኝ እጄን ሌላ ጊዜ ደግሞ ግራ ጫንቃዬን ተሰበርኩ። በዚህ በዚህ ቁመቴን አማርራለሁ። ሁለተኛው መሥራት ስችል ያለው ኅብረተሰብ እንዳሻው ሲያርስ እና ሲያጭድ ሳየው እና እኔ እንደዛ መሆን ሲያቅተኝ ስሜታዊ እሆንና እናደዳለሁ።” የሚሉት አቶ ብርሄ “ወይ ተምሬ እንደ ሰው ለቤተሰቦቼም ሆነ ለኔ ቀን አላወጣሁ፤ ወይም እንደ ሰው በጉልበቴ ሰርቼ አላድር ሁሉ ነገር ችግር ነው” ብለዋል።
“ረዥም በመሆንዎት ከሰው በተለየ የሚያገኙት ጥቅም ምንድነው?” ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ብርሄ ሲመልሱ “አንዳንዴ ከላይ ያሉትን ነገሮች ሳወርድ ጥቅም ነው፤ ሌላው የማያወርደውን ሳወርድ ደስ ይላል። ከታች ያለውን ለማንሳት ነው እንጂ፤ ከላይ ያለውን ለማውረድ ለእኔ የላይኛው ስለሚቀርበኝ ለእኔ ደስ ይላል። አሁን ደግሞ ቀረጻ እና ቃለ መጠይቅ ሲደረግልኝ ተስፋ አለው መሰል ከሌላው ኅብረተሰብ ቁመቴ ስላደገ አይደል እላለሁ።” በማለት ነገ ብሩህ ተስፋ እንደሚታያቸው፤ ለእሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው የተሻለን ነገን የማግኘት ተስፋን ሰንቀው ያወጋሉ።
አቶ ብርሄ ባለትዳር ናቸው። የመጀመሪያ ልጃቸውን የወለደችላቸው ሚስታቸው አልፈልግም ብላ ጥላቸው ሄደች። ያኔ የመጀመሪያ ሚስታቸው ጋር እንደተለያዩ ብቸኝነት ሲያስከፋቸው ሥራ ፍለጋ ብለው ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንደነበረ ያስታውሳሉ። ያኔ ሰው ምን ተዓምር መጣ ብለው ብርሄ ያረፈበትን ቤት ሰው ከቦት ነበር። ሊመለከታቸው ከየአቅጣጫው በርካታ ሰው ተሰበሰበ። በኋላ ፖሊስ ጋር ስልክ ተደውሎ በፖሊስ ሰው መበተኑን ያስታውሳሉ። የመጡበትን ዓላማ ሳይዘነጉ ሥራ አግኝተው ቢጀምሩም እንደ ልዩ ፍጥረት በመታየታቸው ከቀናት በላይ መቆየት ተስኗቸው ወደ ትውልድ ቀያቸው መመለሳቸውን ያስታውሳሉ።
ከዚህ በኋላም በድጋሚ ሚስት ለማግባት ፈልገው ያጫሉ። ያጯትም በርዝመታቸው የተነሳ አልፈልግም በማለት ወደ ኋላ ትላለች። በኋላም ተስፋ ባለመቁረጥ ውሀ አጣጫቸውን የፈለጉት አቶ በርሄ አሁን አብራቸው ያለችውን ሚስታቸውን አጩ፤ ይህች ሴት ላለማግባት ብታንገራግርም ቤተሰቦቿ አሳምነዋት በትዳር ለመጣመር በቁ። አሁን ካገቧት ሚስታቸው ጋር ሦስት ወንድ ልጆች አፍርተዋል። አቶ ብርሄ የአንድ ሴት እና የሶሰት ወንዶች በድምሩ የአራት ልጆች አባት ለመሆን በቅቷል።
እንደ አቶ ብርሄ ገለፃ “ማረስ፣ ማጨድ እና ማረም አልችም። የሚያስቸግረኝ በጣም ዝቅ ስል ወገቤ እና አንገቴ ይወጣና ስሜታዊ ያደረግኛል” ይላሉ። እንዲህም ቢሆን መተዳደሪያቸው እርሻ ነው። ለዚህም ባለቤታቸውን ያመሰግናሉ።” ባለቤቴ ሁሉንም ትሠራለች። ጎረቤቶቼም በእርሻ ሥራ ከጎኔ አልተለዩም። አንዳንዴ ግን ሥራ በዝቶባት እንደ ሌሎቹ ባሎች ረዳት ልሆናት ሳልችል ስቀር ቢከፋትም ሁሉን እሷ ይዛ ነው የምንኖር።” “አሁን ያለችው ሚስቴ በአጨዳው በምኑ ሥራ ሲበዛባት አንዳንዴ እንዲህ ሆነህ [ቁመትህ ረዝሞ] ተቸግረህ እኔም ተቸግሬ ብላ ይሰማታል እንጂ ከዛ ውጭ ፍቅረኛ ነን።” በማለት ያመሰግናሉ።
“ማኅበረሰቡ በሙሉ እንደዚህ ሆንክ በሚል ለእኔ መንግሥት ድጋፍ ቢያደርግልህ እያለ የሚቆረቆር ነው። በአጨዳም ሆነ በእርሻ ያግዘኛል። በልማት እና በጥበቃም አያዘኝም። የኔን ኮታ ኅብረተሰቡ ነው የሚሸፍነው።” በማለት አቶ ብርሄ የአካባቢያቸውን ማኅበረሰብ ያመሰግናሉ።
“መኖሪያ ቤትዎት የተለየ ነው ወይ? አልጋዎትስ ምን ይመስላል?” ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ብርሄ ምላሽ ሲሰጡ “እኔ የምኖርበት ቤት እንደ ኅብረተሰቡ ነው የተሠራው። በሩም ተመሳሳይ ነው። ስገባ እና ስወጣ እያጎነበስኩኝ ነው።” ይላሉ። “የምተኛበት አልጋ ግን ከሌሎች ረዘም ተደርጎ ተሠርቶልኛል፤ እንዲያ ባይሆን እግሬ መሬት ሲጠርግ ነበር የሚያድር።” ብለዋል። “ሌላ አልጋ ላይ ስተኛ በአንድ በኩል በጣም ይተርፋል።”
ፈራ ተባ እያልኩኝ “ፆታዊ ግንኙነትስ እንዴት ነው? አልኩኝ። መጀመሪያ ረዘም ያለ ሳቅን አስቀድመው “በዛ ጉዳይ ላይ ደግሞ ወገል እና ማረሻ ከተገጣጠመ ችግር የለውም።” የሚል በፈገግታ የታጀበ ምላሽ አግኝቻለሁ።
“ግን ሴቶቹ አላገባህም የሚሉት ለምን ይመስልዎታል?” “እምቢ የሚሉት ረዥም ነው ሠርቶ አያበላንም። አንዳንዱ ደግሞ ይኼን ሰውዬ አያችሁት እያለ ስለሚስቅ ስለሚሳቅባቸው ነውር ይመስላቸዋል። ለዛም ነው እንጂ ከሰው የተለየ ምን ፍጥረት ሆኜ ነው?” በማለት ጥያቄዬን በጥያቄ ይመልሳሉ።
በዘራቸው ውስጥ እንደሳቸው ረዥም ቁመት ያለው በቤተሰቡ ውስጥ አለመኖሩን የሚናገሩት አቶ ብርሄ “የኔ ፍጥረት የተለየ በመሆኑ ቆሜ ሌሎች የማያዩትን ነገር አያለሁ። ፈቀቅ ያለ ከማዶ ወደ ተራራ አካባቢ ሌሎች የማያዩትን እኔ ማየት እችላለሁ” በማለት ያስረዳሉ።
“ከልጆችዎትስ መሐል በእርስዎ የወጣ ይኖር ይሆን?” ስንል ለሰነዘርነው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ብርሄ ሴቷ ልጃቸው ረዥም እንደምትሆን እንደሚገምቱ ይናገራሉ። “የመጀመሪያ ሴት ልጄ አገዳዋን ሳየው እንደኔ ባትሆንም ረዥም ነው። 10 ዓመቷ ነው፤ ሳየው አገዳዋ፣ ጣቷ፣ አንጓዋንና እጇን . . . ሁኔታዋን ሳየው ረዥም ትመስለኛለች። ሌላው ወገኔን ሳየው አጭር ነው። እንደ እኔ ቀርቶ የኔን ግማሽ አይሆንም” ብለዋል።
“ልጆቼ ጨቅላ ናቸው፤ ጨቅላ ስለሆኑ፣ ገና ትንሽ ስለሆኑ ረዥም ይሁኑ አጭር ብዙም ገንዘብ ብለን ለማወቅ ይቸግረናል። ያው ብቻ በጣም ይወዱኛል። ለትንሽ ደቂቃ ተለይቻቸው ስመጣ ብርቀኛ ሆነው መጣ መጣ እያሉ ይደሰታሉ።” በማለት ለልጆቻቸው ያላቸው ፍቅር ኃያል መሆኑን ይናገራሉ።
“አቶ ብርሄ እንደው በዚህ ቁመቱ ምክንያት ምን ገጥሞት ይሆን?” በማለት ላቀረብንላቸው ጥያቄ እንዲህ በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። “አንዲቱ ገበያ እያለሁ ከታች እግሬን ቆነጠጠችኝ። ዞር ብዬ ሳያት ‘ለካ ይሄ ሰውዬ ይሰማል’ ብላኛለች። በዚህ በዚህ ይሰማኛል።” “ፀባዩ ጥሩ ነው። በዚህ ቁመቱ ክፉ ቢሆን ሰው ይረብሽ ነበር ” በማለት ሰዎች እንደልዩ ፍጥረት መመልከታቸው ቅሬታ የሚፈጥርባቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።
የአቶ ብርሄ ሌላው ፈተና ትራንስፖርት ነው። “መኪና ላይ ወንበሩ እግሬን ስለማይመቸኝ ዳር ላይ ሆኜ እንጂ እንዳሻኝ አልሆንም። ሾፌሮች እና ረዳቶች የሁለት ሰው ቦታ ስለምትይዝ የሁለት ሰው መክፈል ነበረብህ ይሉኛል።” “ሁለት ሰው ይዘን ነበር የምንሄደው እያሉ ገበያም ስንሄድ ሞተረኞች የሁለት ሰው ይቀበሉኛል” ።
አቶ ብርሄ ጋሹ እድሜያቸው ሰላሳ ስምንት በመድረሱ ከዚህ በኋላ ቁመቴ ይጨምራል ብለው እንደማያስቡ ይናገራሉ። ለወደ ፊት የቁመት ውድድር መወዳደር ይፈልጋሉ። “የወደፊት ዕቅዴ ተወዳድሮ ማሸነፍ ነው። ተወዳድሬ ከኢትዮጵያ አንደኛ መውጣት አለብኝ። አሁንም አንደኛ ነኝ። ተወዳድሬ ማሸነፍ አለብኝ ነው እቅዴ።” በማለት በቁመታቸው መታወቅ የሚፈልጉ መሆኑን ያስረዳሉ።
ቁመታቸው በመርዘሙ ከሰው የተለየ ምግብ ብዙም እንደማይበሉ የሚናገሩት አቶ ብርሄ “መጠጥ ግን በደንብ ነው የምጠጣው። እኛ ሃገር የሚጠጣው ጠላ ነው። ምንም በጠጣ ሽንቱ እስካላስቸገረኝ ድረስ አይበግረኝም።” ብለዋል።
አቶ ብርሄ በሰዎች አይንና ልብ ከገቡ በኋላ በርካቶች እሳቸውን ማነጋገር፤ ፕሮግራም መሥራትና ሌሎችም ጉዳዮች እየተከናወኑ በመሆኑ ብዙዎቹ በገንዘብ፣ በአልባሳት … ድጋፍ እያደረጉላቸው ይገኛል። የሁል ጊዜም ህልማቸው የሆነውን ገንዘብ አግኝተው ልጆቻቸውን በአግባቡ ማልበስ ጥያቄም በደጋግ እጆች እየተመለሰ መሆኑን ይናገራሉ።
“ለወደፊት በቁመት ውድድር ተወዳድሬ ገንዘብ ባገኝ ልጆቼን በወግ ባስተምር ደስ ይለኛል፤ ገጠርም ያው ሥራውን እኔ ስላልቻልኩት ከተማ አካባቢ ቦታ ተሰጥቶኝ ብኖር” የሚል ጥያቄ አላቸው።
“ሰው ካወቆት በኋላ በአኗኗርዎት ላይ ምን ተቀየረ?” ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ “መጀመሪያ የወገኔን ደግነት ተመልክቼበታለሁ፤ ሁሉም ሰው ለሰው ፍቅር እንዳለው አይቻለሁ፤ የከተማ ሰው በሩን ዘግቶ ነው የሚበላው ሲባል እውነት ይመስለኝ ነበር። ግን ሁሉም ሰው ደግ ነው” የሚል ምላሽ የሰጡት አቶ ብርሄ በተለያዩ አካላት የገንዘብም፣ የቁሳቁስም ድጋፍ እንደተደረገላቸው ይናገራሉ።” በተለያየ ጊዜ ቀረፃ እያደረጉ ለሰው ላስተዋወቁኝ፤ ፕሮግራሞችንም ተመልክተው እጃቸውን ለዘረጉልኝ በሙሉ አመሰግናለሁ።” በማለት የነበረንን ቆይታ አጠናቀናል።
ተፈጥሮ በለገሰቻቸው ቁመት ከመቸገር አልፈው እውቅና ያገኙት አቶ ብርሄን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በመመልከት ከሃገረ አሜሪካ ወደ ሃገሯ ኢትዮጵያ ለመምጣት ዝግጅት ስታደርግ የነበረችው ወይዘሮ ፍሬዘውድ ዮሐንስ ለወዳጅ ዘመድ ከሚሰጠው ስጦታ መካከል ለአቶ ብርሄም በልካቸው የሚሆን ጫማ ገዝታ ወደ ዝግጅት ክፍላችን ጎራ በማለት አበርክታላቸዋለች።
ወይዘሮ ፍሬዘውድ ለመጀመሪያ ጊዜ እኚህን ሰው ስትመለከት “አሜሪካ ቢሆኑ እንዴት ያሉ ባስኬት ቦል (ቅርጫት ኳስ) ተጫዋች ይወጣቸው ነበር” ብላ ማሰቧን ትናገራለች። በሃገሯ በዚህ ልክ ረጅም ሰው መኖሩ ቢያስደንቃትም ባዶ እግራቸውን መሆናቸው አሳዝኗት ስጦታውን ለመግዛት ማሰቧን ትናገራለች። እሳቸውም ክብረት ይስጥልኝ በሚል ምርቃት ስጦታቸውን ተቀብለዋል።
እኛም ሀሳባቸው ይሙላ፤ ያሰቡት ይሳካላቸው። በማለት ከመለሎው አቶ ብርሄ ጋሹ ጋር የነበረንን ለዛ ያለው ጨዋታ አብቀተናል።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም