
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እስልምናን ከተቀበሉ አገራት ቀዳሚዋ ስለመሆኗ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን የሚገልጹት እውነታ ነው፡፡ ይህንን እውነታም ነብዩ መሃመድ(ሰ.ዐ.ወ) ገልፀውታል፡፡ ሙስሊሞች መካን ይገዙ በነበሩ ቁረሾች ችግር በገጠማቸው ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሂጅራ የተካሄደባት አገር ስለመሆኗም የእምነቱ አባቶች ይገልጻሉ፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የሁሉም እምነቶች ቤት ስለመሆኗ በገሃድ የሚያሳይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ እስልምናና ክርስትና ከሺህ ዓመታት በላይ በአንድ ላይ ኖረዋል፡፡ በነዚህ ዓመታትም በሌሎች ዓለማት የምንሰማቸው ግጭቶች አልተሰሙም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው በመከባበርና አንዱ የሌላውን እምነት እና ብሔር እንዲሁም ማንነቱን በማክበር መኖርን የተለማመዱ ናቸውና፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ እምነቶችም የሚታወቁት አንዱ ከሌላው ጋር ባለው የጠበቀ ግንኙነት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ አንዱ የሌላውን ቤተእምነት በመገንባት፣ በበዓል ወቅትም በመጠራራትና አብሮ በመብላት፣ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት በመረዳዳት፣ ከዚያም አልፎ የጋራ እሴቶችን በጋራ በመጠበቅ ነው፡፡
በአገራችን የዘመናት የአብሮነት ታሪክ ውስጥ መቻቻል፣ መተዛዘን እና መረዳዳት ያለውን ፋይዳ በውል የሚረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብም በሰው ልጅ የዘመናት ጥረትና ድካም የዘረጋቸውን መልካም እሴቶች ኃላፊነት የማይሰማቸው አካላት በአንድ ጀንበር ሊንዱት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አንዴ በሃይማኖት ስም ሌላ ጊዜ በብሔር ስም ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት የሚደረጉ ጥረቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡
ሰሞኑን በጎንደር ከተማ በተለይ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮችን በማጋጨትና ይህንንም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማስፋት በኢትዮጵያ ውስጥ የማይበርድ እሳት ለመለኮስ ሙከራ ተደርጓል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም ሴራውን በውል ያልተገነዘቡ ጥቂት የተለያዩ እምነት ተከታዮች ጉዳዩን ለማራገብና አገራችንን ወደለየለት ብጥብጥ ለማስገባት የሞከሩ ሲሆን፣ አብዛኛው የአገራችን ሕዝብ ግን ችግሩን በመገንዘቡ የታለመው ሴራ ሊከሽፍ ችሏል፡፡
በርግጥ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ የጥፋት ተግባራት በተለያየ መልኩ ሲካሄዱ የሰነበቱ ናቸው፡፡ በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመበታተን የውስጥና የውጭ ኃይሎች ያልሞከሩት ጥረት የለም፡፡ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ለማጋጨት በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡
በተጨማሪም የአማራና የትግራይ፣ የኦሮሞና የሶማሌ፤ የአፋርና ኢሳ፣ ሲዳማና ኦሮሞ ወዘተ ልዩነቶችን በማስፋት እርስ በርስ ለማጋጨት ያልተፈነቀለ ድንጋይ፣ ያልተማሰ ጉድጓድ የለም፡፡ ይሁን አንጂ እነዚህ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ላለፉት በርካታ ሺህ ዓመታት አብረው የኖሩና እርስ በርስ የተዋለዱ ጭምር በመሆናቸው መለያየት እንደማይቻል በተግባር አሳይተዋል፡፡
ባለፈው ዓርብም በአገራችን ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የአገራችንን ገጽታ በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግ እና የእስልምና ሃይማኖትን ሰላም መሠረትነት የሚያረጋግጥ የአደባባይ የአፍጥር ሥነሥርዓት ተካሂዷል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለመበታተን ለሚፈልጉ የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡
ይህ ሥነሥርዓት በአንድ በኩል የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለሰላም ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጡና በተራ ፕሮፓጋንዳ ተነድተው ወደግጭት የማያመሩ መሆናቸውን በግልጽ ከማሳየቱም በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የሌለ ለማስመሰል የሚጥሩ የውጭ ኃይሎች የውሸት ፕሮፓጋንዳቸውን ለዓለም አደባባይ ያሳጣ መልዕክት ያስተላለፈ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን ጥቂት የሚባሉ በሰላማዊ ሕዝብ ውስጥ ተሰግስገው በየማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ እየተሽከረከሩ ሰላምን ለማደፍረስና አገርን ለማበጣበጥ የሚጥሩ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች በተለይ በእምነት ሽፋን የተለያዩ የግጭትና የልዩነት ስብከቶችን ሲያሰራጩና ኅብረተሰቡንም ለብጥብጥ ሲጋብዙ ይታያል፡፡ ዋነኛ ዓላማቸው ደግሞ በብጥብጥ ውስጥ የራሳቸውን ጥቅም ማካበት ነው፡፡ ነገር ግን ጥፋትን በሕግ እንጂ በጥፋት ማረም ሌላ አደጋን መጋበዝ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዓይነት ክፉዎችን በምንም መልኩ እንዲሰለጥኑብን የማንመች ሕዝቦች መሆናችንን ደግመን ደጋግመን ማሳየት አለብን፡፡ መላው ሙስሊም ማኅበረሰብም በኢድ ወራት ያሳየውን እርስ በርስ የመረዳዳት እና ሰላሙን የመጠበቅ የቆየ ታሪኩን በአብሮነቱ ሊያስቀጥል ይገባል፡፡
ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የእምነት አባቶችም ሥርዓት አልበኝነት እንዳይሰለጥን ማኅበረሰቡን በሞራልና በሥነምግባር ማነጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ክፉውን ጊዜ እንደ ዒድ ሶላት ሰብሰብ ብለን ልንጋፈጠው፣ በኅብረታችን የሚገጥሙንን ፈተናዎች እንደ ምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን ዕድል በእኛው እንጂ በሌላ በማንም እጅ እንዳልሆነ ለዓለም ማሳየት ይኖርብናል፡፡
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ለግላችን ሳይሆን ለጋራ ህልውናችን እንድናስብ የሚያስገድደን፣ ከግል ምቾታችን በላይ ለጋራ ደኅንነታችን እንድንተጋ በእጅጉ ግድ የሚልበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ምሕረት፣ ስለ ይቅርታ እና ስለ ፍቅር እንጂ፣ ስለ ጠብና ጥላቻ ማሰብ አይቻልም፡፡ ቀጣይ ጊዜያትም ስለ አንድነት እንጂ፣ ስለ መለያየት የምንዘምርባቸው ጊዜያት ሊሆኑ አይገባም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም