
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች ሲባል፤ መልክዓ ምድሩ፣ ወንዙ ሸንተረሩ፣ ጋራና ጫካው፣ በድምሩ ኢትዮጵያ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የተካለለው የመሬት ክፍል ወደ ፈጣሪው እጁን ይዘረጋል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ብሂሉ ኢትዮጵያ የአማኞችና የሃይማኖተኞች አገርና ምድር እንደመሆኗ እነዚህ ኃይማኖተኛ ሕዝቦች በደስታቸው ለምስጋና፣ በፈተናቸው ለጥያቄ፣ በችግርና መከራቸው ለልመናና ጸሎት ወደ ፈጣሪያቸው ይመለከታሉ፤ ፈጣሪያቸውን ይማጸናሉ ለማለት ነው። 99 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ ሃይማኖተኛ ወይም አማኝ ነው ሲባልም፤ ይሄ ሁሉ ሕዝብ የሚያመልከው ፈጣሪ ያለው፤ ለምስጋናም ሆነ ለተማጽኖ እጁን ከፍ አድርጎ የሚያናግረው የታመነ አምላክ ባለቤት መሆኑን ያስረዳል።
ኢትዮጵያ ደግሞ ክርስትናን እና እስልምናን የመሳሰሉ ታላላቅ እምነቶች በጉያዋ አቅፋ የያዘች፤ ፈሪሃ ፈጣሪ ያላቸው ሕዝቦች አገር ናት። ክርስትናን በአራተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በምድሯ ያስፋፋችው ኢትዮጵያ፤ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎቹ ዓመታት ነብዩ መሐመድ እስልምናን ማስተማር በጀመሩበት ወቅት የመካ ሕዝቦች ያሰቃዩአቸው ስለነበር መጠጊያ ያልነበራቸው ተከታዮቻቸውን “ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ፤ እዛም ማንንም የማይበድል መንግሥት ታገኛላችሁ፤ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስም እዛ ቆዩ” በማለት የላኳቸውን የእስልምና እምነት ተከታይ መልዕክተኞችን በመቀበል እስልምናን አንድ ብላ ጀምራለች።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ ብዝሃነት፣ አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ ፍቅርና መተሳሰብን ከፍ ያለ እሴታቸው አድርገው መኖር፤ ሰው መሆን ከሁሉም በላይ ከፍ ያለ ቦታ እንዳለው፣ ይልቁንም ሰውነት ከፈጣሪ መልክና አምሳል ጋር በእጅጉ የተጎዳኘ ክቡር የመሆን ምስጢር እንደሆነ ለዓለም ማሳየት የጀመሩበት ወቅት ነበር። ይህ ብቻም ሳይሆን ክርስትናም ሆነ እስልምና በኢትዮጵያ አንዱ አንዱን የሚገፉበት ሳይሆን፤ አንዱ ለአንዱ አጋዥና አለኝታ ሆነው የዘለቁበት፤ በየዘመናቱ የሚፈጠሩ ጥቃቅን ክፍተቶችንም በኃይማኖታዊ ዶግማዎቻቸው ታግዘው እየገሩ ሕልውናቸውን ጠብቀው የኖሩባት፤ እየኖሩም ያሉባትና ወደፊትም የሚኖሩባት ናት።
በዚህ መልኩ የሃይማኖቶች ጥላ ሆና የምትገለጸው ኢትዮጵያ፤ ዛሬም ድረስ የተለያዩ እምነቶች እየተቀበለች በነጻነት እንዲስፋፉና እንዲፋፉ እድል የሰጠች መሆኗን ጠልቆ ለተመለከተ፤ እውነትም ኢትዮጵያውያን ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ፣ ዘወትር በፈጣሪያቸው መስመር ተጉዘው መልካም ሰብዕናን የተላበሱ፤ አብሮነት፣ ፍቅርና መተሳሰብን ያነገሱ ስለመሆናቸው ለመመስከር የሚያጎላድፈው ነገር አይኖርም። ለዚህ ደግሞ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖቶች፣ አስተምህሮቶች፣ አማኞችና ቤተ እምነቶች ጭምር ያሉ የመተሳሰብና የወንድማማችነት እሴት እንደ ማጣቀሻ ቢጠቀም የበዛ ማሳያ አለው።
ይሁን እንጂ ከሰው ልጆች እሴት ያፈነገጡ፣ ከሃይማኖቶች አስተምህሮ የወጡ፣ በእኩይ ፍላጎትና ተልዕኮ የተመረዙ ጥቂቶች ይሄንን የሃይማኖቶች አብሮነት፣ የአማኞች ወንድማማችነት በእጅጉ ይጠየፉታል። ተጠይፈውም አይቆሙም ቤተ እምነቶችን የግጭት፣ የኹከትና የደም ቅጥር ለማድረግ ሲታትሩ ይታያሉ። እንደ አሸባሪው ሕወሓትና ጀሌዎቹ ጽንፈኛ/አክራሪ ኃይማኖተኛ ነን ባዮች የዚህ አብይ ማሳያዎች ናቸው። ከሰሞኑ እዚህም እዚያም ሃይማኖትን ታክከው፣ የእምነት ጭምብል ደርበው በቤተ እምነቶች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መስተዋላቸውም የነዚሁ እኩያን ሴራና ፍላጎት መሆኑ እሙን ነው።
ምክንያቱም፣ የየትኛውም ኃይማኖትና እምነት ፀብን ሳይሆን ሰላምን፤ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን፤ መለያየትና መገፋፋትን ሳይሆን በኅብረት መቆምን፤ ጠላትነትን ሳይሆን ወንድማማችነትን፤የሚያስተምር ነውና። የየትኛውንም ኃይማኖትና እምነት አስተምህሮ በወጉ የተገነዘበ አማኝ ደግሞ በምንም መልኩ ለጽብ አይነሳሳም፣ ለጥላቻ ልቡ አይገዛም፣ በውሸት አይታበይም፣ በወንድሙ ላይ እጁን አያነሳም፣ ለጥፋትና ክፋት የሚሆን ሰብዕና አይኖረውም። ለዚህም ነው ዛሬ ላይ እዚህም እዚያም የሚታዩ ሃይማኖትን የታከኩ፣ እምነትን የተጠጉ እኩይ ተግባራት ደግሞ ከየትኛውም ሃይማኖትና እምነት የተፋቱ፤ የእምነቶች አስተምህሮ መሠረት የሌላቸው ናቸው የሚባለው።
እነዚህ አካላት ዓላማቸውን ስለ እምነቱ በመቆርቆር ራስን መስጠት ሳይሆን፤ ለእኩይ ተልዕኳቸው መሳካት ሃይማኖቱን፣ ቤተ እምነቱንና አማኙን ተከልሎ የጥፋት ጉዳያቸውን ማስፈጸም ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ በታሪኳ የኃይማኖቶች ጥላ እንጂ የሃይማኖቶች መፋጃ ሆና አልተገለጠችም። ይልቁንም ክርስቲያንና ሙስሊሙ ጡት ተጣብተው፣ በዓል አብረው አክብረው፣ አብረው አፍጥረው፣ ከፍ ሲልም ተጋብተውና ተዋልደው የኖሩባት የሃይማኖቶች መናኸሪያ ነች። በመሆኑም ኅብረተሰቡ እነዚህን ኃይሎች ነቅሶ ሊጠብቅና ሊከላከላቸው፣ ከውስጡ ነጥሎ በማውጣትም አሳልፎ ሊሰጣቸው፤ ለጥፋት ተግባራቸው ያጠለቁትን የሃይማኖት ጭምብል በማስወለቅም የኢትዮጵያን የሃይማኖት ጥላነት ከፍታ ማረጋገጥ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም