ዛሬ በዚህ አምድ የምንዘክራቸው ባለውለታችን ብዙ መልካም ተግባራትን አከናውነው ሳለ ታሪካቸውና አበርክቷቸው በሥራቸው ልክ ካልተነገረላቸው ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆኑትን ደራሲ፣ የታሪክ ተመራማሪ፣ የግብርና ሳይንስ ሊቅ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያና ፖለቲከኛ የነበሩትን ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ ወልደመስቀልን ነው፡፡
ወደ ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ ወልደመስቀል ታሪክ ከመግባታችን በፊት አባታቸው ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደመስቀል ታሪኩን በአጭሩ እንተዋወቃቸው፡፡
ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደመስቀል ገና ሕፃን ሳሉ አባታቸው በሞት ስለተለዩዋቸውና አቶ ተክለወልድ የሚባሉት አጎታቸው የራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ አሽከር ስለነበሩ በራስ ዳርጌ ቤት አደጉ፡፡ በኋላም አጎታቸው ሲሞቱ የራስ ዳርጌ አገልጋይ ሆኑ፡፡ የቤተ ክህነት ትምህርት ተምረው ስለነበር የእልፍኝ ጸሐፊ ሆነው እንዲሠሩ ተሾሙ፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ሳሉም የዋና ጸሐፊነቱን ቦታ በመያዝ ፀሐፌ ትዕዛዝ ተባሉ፡፡ በ1888 ዓ.ም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለዓድዋ ጦርነት ሲዘምቱ ራስ ዳርጌ አዲስ አበባ ሆነው አገር እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት በተሰጣቸው ጊዜ ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደመስቀል የራስ ዳርጌ የቅርብ ረዳት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዓድዋ ድልና ከራስ ዳርጌ ሞት በኋላም በንጉሰ ነገሥቱ ልዩ ጽሕፈት ቤትና በእቴጌ ጣይቱ እልፍኝ ውስጥ ሰርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጽሕፈት ሚኒስትር፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዘዳንትና የእርሻ ሚኒስትር ሆነው እንዳገለገሉም ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ላይ በተጣለው የቦምብ አደጋ ተጠርጥረው ወደ አዚናራ ደሴት ተወስደው ታስረው ነበር፡፡ የፋሺስት ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላም በልዩ ልዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ ቆይተው ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በ1947 ዓ.ም አርፈዋል፡፡
ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደመስቀል ታሪኩ እና ወይዘሮ ደስታ አየለ በትዳር ተጣምረው ከመሰረቱት ቤተሰብ በ1897 ዓ.ም የተወለደው ልጅ ማኅተመሥላሴ ተባለ፡፡ ማኅተመሥላሴ ሰባት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ያደገው ቡልጋ ውስጥ ወይን አምባ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ ነው፡፡ የአማርኛ ትምህርት መማር የጀመረውም እዚያው ነው፡፡ ሰባት ዓመት ሲሞላው ደግሞ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቤቱ ውስጥ መምህር ተቀጥሮለት የአማርኛ ትምህርቱን መማር ቀጠለ፡፡ የአማርኛ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም ከ1907 እስከ 1913 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተማረ፡፡ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ያጠናውም በዚህ ወቅት ነበር፡፡
ከ1914 እስከ 1916 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጥሮ ሠርቷል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጥሮ ይሠራ በነበረበት ወቅት፣ በኅዳር ወር 1915 ዓ.ም፣ ከወይዘሮ አምሳለወርቅ ክፈተው ጋር ትዳር መሰረተ፡፡ በ1916 ዓ.ም ለትምህርት ወደ ግብፅ ሄዶ አንድ አመት ከቆየ በኋላ ወደ ፈረንሳይ አቀና፡፡ በዚያም ፓሪስ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ብሔራዊ የግብርና ሳይንስ ከፍተኛ ተቋም ተምሮ በማጠናቀቅ በዲግሪ ተመርቆ በ1921 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡
እንደተመለሰም ስለትምህርቱም የዳግማዊ ምኒልክን የወርቅ ሜዳይ ተሸለመ፡፡ ከውጭ አገር የቀሰመውን የእርሻ ትምህርት በሥራ ላይ እንዲያውል በአምቦ አካባቢ የእርሻ ልማት ሥራዎችን እንዲያከናውን ስለታዘዘ፣ በአካባቢው የሚገኙ የእርሻ መሬቶች በዘመናዊ መልኩ እንዲለሙና የሕዝቡም ኑሮ መሻሻል እንዲያሳይ አድርጎ አጠናቀቀ፡፡ የአምቦ ከተማ ፕላንም በዘመናዊ አሠራር እንዲቀየስና ሕዝቡም ቦታ እየተመራ ቤት እንዲሠራ አደረገ፡፡ ለዚህ ሥራውም ባለአምበሉን ‹‹የሥላሴ ኒሻን›› ሽልማት ተሸለመ፡፡
በ1926 ዓ.ም በ‹‹ባላምባራስ›› ማዕረግ የልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ የጽሕፈት ሹም ሆኖ ተሾመ፡፡ በዚህ ኃላፊነት ላይ በማገልገል ላይ ሳለ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ላይ በተጣለው የቦምብ አደጋ ባላምባራስ ማኅተመሥላሴ ተጠርጣሪ ሆኖ ከአባቱ ከፀሐፌትዕዛዝ ወልደመስቀል ታሪኩ ጋር ወደ አዚናራ ደሴት ተወስደው ታስረው ነበር፡፡ ከዓመት ከስድስት ወራት እስራት በኋላ ከአዚናራ ደሴት ተፈትቶ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር የኢትዮጵያን ጥንታዊ መዛግብትን በማውደም ያደረሰው በደል ቀላል አልነበረም፡፡ የአገሪቱ ቅርሶች በከንቱ ባክነውና ወድመው መቅረታቸው ያንገበገበው ባላምባራስ ማኅተመሥላሴ፣ መዛግብቱን ሰብስቦ ማስቀመጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ከመዝገብ ቤት የሚያገኛቸውን የጽሑፍ ማስረጃዎች በቻለው መጠን ገልብጦ ለማስቀረት ሞክሯል፡፡
ባላምባራስ ማኅተመሥላሴ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ምድር ከተባረረ በኋላ ኢትዮጵያን ለመገንባት በተደረገው ጥረት ከግንቦት 1933 እስከ 1938 ዓ.ም ድረስ የወሎ፣ የበጌምድርና የትግራይ ጠቅላይ ግዛቶች ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሹም ሆነው አገልግለዋል፡፡ ‹‹የክፍለ ሀገራት አመዳደብ መስታወት›› የሚል እቅድ አዘጋጅተው ለአገር ግዛት አስተዳደር ሚኒስቴር በማቅረብ ተግባር ላይ እንዲውልም አድርገዋል፡፡
እስከ 1946 ዓ.ም በእርሻ ሚኒስቴር እንዲሁም በእርሻና ከብት እርባታ ልዩ መስሪያ ቤት እስከ ሚኒስትርነት ማዕረግ ድረስ በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ በእርሻ ሚኒስትርነታቸው ዘመን የአምቦ የእርሻ ምርምር፣ የሾላ የከብት በረት፣ የሆለታ የወይን ልማት፣ የእንጦጦና የደብረብርሃን የበግ እርባታ ማዕከላትንና ሌሎች የግብርና ተቋማትን አቋቁመዋል፡፡ አምቦ ውሃን አዲስ አበባ ድረስ በማስመጣት የውሃውን ጠቃሚነት ለቤተ-መንግሥቱ ያስተዋወቁት ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ ወልደመስቀል እንደሆኑ በታሪካቸው መዝገብ ላይ ሰፍሯል፡፡ በዚህ ጊዜም ለልዩ ልዩ ተግባራት ወደ ውጭ አገራት ተልከው ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጧቸውን ተልኮዎች ፈፅመዋል፤ የአዲስ አበባ ከተማ ተጠባባቂ ከንቲባም ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከ1948 እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ተጠባባቂ ሚኒስትር፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ እንዲሁም የሥራና መገናኛ ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው በሠሩበት ጊዜም ከጠንቀቃነታቸው የተነሳ በእቅድ ላልተያዙና አዋጭነታቸው ላልተመዘኑ ሥራዎች የመንግሥት ገንዘብ ወጪ እንዳይደረግ ጠንካራ አቋም ነበራቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ምክንያት ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር ጭምር አለመግባባት ውስጥ ይገቡ እንደነበር በታሪክ ተጽፏል፡፡
ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ ለረጅም ዓመታት በልዩ ልዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ያገለገሉበት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ ከነበሯቸው መደበኛ የሥራ ኃላፊነቶች በተጨማሪ የንጉሰ ነገሥቱን መልዕክት በመያዝ፤ ልዩ ልዩ ስምምነቶችን ለመፈራረም ወደ በርካታ አገራት ተጉዘው የተሰጧቸውን ተልኮዎች ፈፅመዋል፡፡ በመጨረሻዎቹ ዓመታት የዘውድ አማካሪ እንዲሁም የብሔራዊ መርሐ ልሳን ፕሬዘዳንት ሆነውም ሠርተዋል፡፡
ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ ወልደመስቀል በተለያዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይ ሆነው ለረጅም ዓመታት ከማገልገላቸውና ለአገር እድገት አስተዋፅዖ ከማበርከታቸው በተጨማሪ ጎላ ብሎ የሚጠቀስላቸው አበርክቶ በሥነ-ጽሑፉ ዘርፍ ያከናወኑት ተግባር ነው፡፡ እኚህ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው በታሪክና ባህል፣ በትምህርተ ጥበባት እና በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ከአሥራ አምስት በላይ (ያልታተሙትን ሳይጨምር) መጻሕፍትን አበርክተዋል። በተለይ ‹‹ዝክረ ነገር›› የተባለው መጽሐፋቸው በብዙ ጸሐፍትና አንባቢያን አንደበት ተደጋግመው ከሚጠቀሱት ሥራዎቻቸው መካከል ዋነኛው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በታሪክ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውና አጠቃላዩን የኢትዮጵያን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚዘክር/የሚዳስስ ነው። መጽሐፉ በርካታ መረጃዎች የታጨቁበት መዝገብ በመሆኑ ታሪካዊ ማስረጃዎችን ለማመሳከር የተፃፈ ነው፡፡ ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ ይህን መጽሐፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳቸውን ዋነኛ ምክንያት ሲገልፁ፡-‹‹… ጊዜ ያሻሻለው አዲስና ጠቃሚ የሆነ የሥልጣኔ ሥራ እንዲስፋፋ የዘመኑንም እርምጃ መከተል የሚገባ ቢሆንም ስርና መሰረቱን፣ ያለውን ያገርን ልምድና ጠባይ በጭራሽ መተውና መልቀቅ የዝክረ ነገሩን መርሳት ለሰው ልጅ የተገባ ተግባሩ ሆኖ ዐይታይም፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን ማንኛውም ነገር ከታየና ከታወቀ በኋላ ሰዓት ሲያልፍ ‹ነበር› ከመባል አይቀርም፡፡ ነገር ግን የታሪክ ሰንሰለት በመሆኑ ማንም ሰው ያለበትን ዘመንና ያለፈውን ሁኔታ ለማስተያየት ብልጫና ጉድለቱንም ለማመዛዘን ‹ነበር›ን ማወቅ አለበት፡፡ ስለዚህም ለአገር አስተዳደር በየጊዜው የሚሠራው ሕግና ደንብ ትዕዛዝና ማንኛውም ይህን የመሰለው ሁሉ እየተጠራቀመና እየተዘጋጀ ለመጪው ትውልድ መተላለፍ ይገባዋል፡፡ እንዲህ ሳይሆን ቀርቶ ያለፈው እየተረሳ ሳይሰበሰብና ሳይከማች የጊዜውን ብቻ በመከተል ወደ ፊት ለመራመድ የተፈለገ እንደሆን ግን ማስረጃው መሰረት ያልያዘ፣ አንድነት ያጣና የተበተነ ከመሆን ይደርሳል …››
‹‹ጥበበ ገራህት›› እና ‹‹ብዕለ ገራህት›› የተሰኙት መጽሐፎቻቸው ደግሞ በእርሻ ሥራ ላይ ያተኮሩና ለሥራውም መማሪያ እንዲሆኑ አስበው ያዘጋጇቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ መጻሕፍት (ያልታተሙትን ጨምሮ) መካከል፡-
ሀ). ታሪክና ባህል
1. ዝክረ ነገር
2. የአባቶች ቅርስ
3. እንቅልፍ ለምኔ
4. አማርኛ ቅኔ ነጠላ
5. አማርኛ ቅኔ ከነመፍቻው
6. ስለ ኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት አስተዳደርና ግብር
7. ያገር ባህል (ቡልጋ)
8. ባለን እንወቅበት
9. የቀድሞው ዘመን ጨዋ ኢትዮጵያዊ ጠባይና ባህል
10. ቼ በለው
11. ኁልቁ ትውልድ ዘንጉሥ ሳህለሥላሴ
12. የኛም አሉ እንወቃቸው
ለ). ትምህርተ ጥበባት
1. ጥበበ ገራህት
2. ብዕለ ገራህት
ሐ). መንፈሳዊ
- ዕፁብ ድንቅ
2. ስም ከመቃብር በላይ
3. ሰዋስወ ሰማይ … ይጠቀሳሉ፡፡
ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ አስተማሪ የሆኑ መጻሕፍትን ከመጻፍ ባሻገር ቅርሶችን (በተለይ የጽሑፍ) ሰብስቦ በመንከባከብ ረገድ በገንዘብ የማይተመን ትልቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ለዚህ አስተዋፅዖዋቸውና አርዓያነታቸውም በ1958 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ሥነ-ጽሑፍ ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ የ‹‹ብላቴን ጌታ›› ማዕረግም ተሰጥቷቸዋል፡፡ በወቅቱ ታትሞ የነበረው የሽልማት ድርጅቱ መጽሔትም እንዲህ ሲል አትቶ ነበር፡-
‹‹… ክቡርነታቸው የሰበሰቡዋቸውን ቅኔዎች በዓይነቱና በአግባቡ በማስቀመጥ በቃል በአጭሩ የሚነገሩትን ተረቶች ሲወርድ ሲዋረድ የቆየውን የቤተ-ክህነትና የቤተ-መንግሥት ስርዓት ለዛ ባለው የአማርኛ ድርሰት በማቅረብ ቋሚ ሥራ በመሥራታቸው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ሰባት ሺህ ብር ከወርቅ ሜዳሊያና ዲፕሎማ ጋር ይሰጣቸዋል …››
ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ በሽልማት ሥነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹… አዲሱ ትውልድ የውጭ አገር ሥልጣኔና ቋንቋ በሰፊው በሚከታተልበት ጊዜ ከጥንታዊ አባቶች የተላለፈውና የሚነገረው ሁሉ በጽሑፍ ሆኖ ካልቆየ ከአገሩ መሰረታዊ ባሕል ተለያይቶ የሚቀር መሆኑን ማሰቡ መንፈስን ከብርቱ ጭንቀት ላይ የሚጥል ነበር … በጥናት በኩልም አገራችን ግራና ቀኝ ቢሄዱ የማያደናቅፍ ሰፊ መስክ ስላለ በማንኛውም ረገድ ጥልቅ ምርመራ እያደረጉ ቅርሶቻችንና ባሕሎቻችንን ለእኛም ሆነ ለዓለም ማስተዋወቁ ጠቃሚ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቶች ‹እኛም አለን እወቁልን› የሚለውን ዓላማ በመከተል ተግተው መሥራት ይኖርባቸዋል …››
ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ የኢትዮጵያ ታሪክ በጥልቀት እንዲመረመርና እንዲጠና ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፡፡ የታሪክ መጻሕፍትን ከመጻፍ ባሻገር ራሱን የቻለ የታሪክ ጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲቋቋም በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ከፍትኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ወጣቶች የአገራቸውን ታሪክ አውቀው ነገን የተሻለ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተደጋጋሚ ምክሮችን ለግሰዋል፡፡ በአንድ ወቅትም «እኛ ኢትዮጵያውያን አገራችን ጥንታዊት መሆኗን ሥልጣኔም በመሻት አዋቂዎችና አስተዋዮች አባቶቻችን በብዙ የደከሙ መሆናቸውን በመገንዘብ ላገራችን ወጣቶችም ሆነ ወይም ለውጭ አገር ሰዎች እውነተኛውንና ምስክርም ሊሆን የሚገባውን ሁሉ እየሰበሰብን ማዘጋጀትና ለመጭውም ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ አለብን» በማለት ተናግረው ነበር፡፡
ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ ወልደመስቀል በተለያዩ መስኮች ላበረከቷቸው ዘመን አይሽሬ አስተዋጽዖዎቻቸው ብዙ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በርካታ የታሪክ ባለሙያዎችና የሕትመት ውጤቶችም ምስጋናና ውዳሴ ቸረዋቸዋል፡፡ በአገር ውስጥ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ሥነ-ጽሑፍ ሽልማትንና የኢትዮጵያን የክብር የኮከብ ኒሻንን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ የዩጎዝላቪያን፣ የግሪክን፣ የጀርመንንና የቺኮዝሎቫኪያን የክብር ኒሻን ሽልማቶችንም ተቀብለዋል፡፡ ከመደበኛ መንግሥታዊ ኃላፊነቶቻቸው በተጓዳኝ ከ40 በላይ ለሚሆኑ ተቋማት የቦርድ አባልና ፕሬዘዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ዘመናቸውን ያለ ምንም ዕረፍትና የጊዜ ብክነት በጥንቃቄ የተጠቀሙ ሰው ናቸው፡፡ የሠሩትን ያህል ያልተዘመረላቸው መሆናቸው ግን አይካድም፡፡
በ1967 ዓ.ም መንበረ መንግሥቱን የጨበጠው ቡድን (ደርግ) የንጉሰ ነገሥቱን መንግሥት ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር ሲያውል ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ ወልደመስቀልም ታሰሩ፡፡ በእስር ላይ ሳሉ ባጋጠማቸው ሕመም በ1971 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም በአዲስ አበባ የካ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡ ብላቴን ጌታ ማኅተመሥላሴ ወልደመስቀል በ1915 ዓ.ም በሕግ ካገቧቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ አምሳለወርቅ ክፈተው 11 ልጆችን አፍርተዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 /2014