በኢትዮጵያ አምራች ኃይል በብዛት፤ ለጨርቃ ጨርቅ ደግሞ ግብአት የሚሆን ጥጥ አላት። ሀገሪቱ ለጥጥ ምርት የተመቸችና ለዚህ ምርት ግብዓት የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ስፍራዎችም አሏት። የጨርቃጨርቅ በተለይም የተዘጋጁ ልብሶችን ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ዝግጁ መደረጋቸውን ተከትሎም በርካታ የውጭ ኩባንያዎች አልባሳት እያመረቱ ለውጭ ገበያ እየላኩ ናቸው።
ለውጭ ገበያ የሚመረቱት አልባሳት የወቅቱን ፋሽን የተከተሉ እንደመሆናቸው ዘርፉ የፋሽን ኢንዱስትሪ በሀገሪቱ ይበልጥ እግሩን እንዲተክል የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ማለትም ያስችላል። በኢንዱስትሪው ሰራተኞች ፣ አመራር አካላትና ሌሎች ከኢንዱስትሪው ጋር ትስስር ላላቸው አካላት በመንግሥት በኩል የሚሰጡ ስልጠናዎች ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው።
አቶ ባንቲሁን ገሰሰ ቀድሞ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሚባለው ተቋም የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል፤ ተቋሙ አሁን በአዲስ አወቃቀር የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ልማትና ምርምር ማእከል በሚል እንዲጠራ ተደርጓል።
ከፋሽን ጋር በተያያዘ ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ባንቲሁን እስከ አዲሱ አወቃቀር ድረስ ያለውን መረጃም ሰጥተውናል። እሳቸው እንዳሉት፤ የተቋሙ ተልዕኮ የሰው ኃይል ማብቃት ነው። ዘርፉን የሚደግፉ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ለማፍራት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ሲሰራ ቆይቷል። በእዚህም ፋብሪካዎቹ በቂ ገበያ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል።
እንደሳቸው ገለጻ፤ በአጠቃላይ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ሲታይ በባህላዊ መንገድ ረጅም ጊዜ የቆየ የሥራ ልምድ አለ፤አሁን ባህላዊውን ወደ ዘመናዊ በመቀየር እንዲሁም ፋሽን ተኮር በማድረግ በገበያው ተወዳዳሪ ከመሆን አኳያ ብዙ እየተሠራበት ነው።
ከዘመን ዘመን ተሻግሮ ግዙፍ ገንዘብ ከሚንቀሳቀስበት ዘርፍ አንዱ የአልባሳት ፋሽን መሆኑን ጠቅሰው፣ በአልባሳት ፋሽን በኩል ሠፊ አቅም እንዳለ ይናገራሉ። ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አብዛኛው በጉልበት የሚሠራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያለውን ጉልበት በመጠቀም በጨርቃ ጨርቅ ሠፊ ሥራ ለመሥራት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ያስረዳሉ።
ከኢትዮጵያ ህዝብ 70 በመቶው ወጣት ነው ፤ ይህ ሀይል ለገበያውም ሆነ ለሥራው ትልቅ አስተዋፅኦ አለው የሚሉት አቶ ባንቲሁን፣ የተማረ ጉልበት ለመጠቀም ነው ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀገር ውስጥ እንዲቋቋሙ የተደረገው ይላሉ። ይህም ዘርፉ በከፍተኛ፣ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች በዘርፉ ተሰማርተው የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪው እንዲያድግ በማድረግ እና ዘርፉ ከባህላዊ አሠራር ጎን ለጎን ወደ ዘመናዊ አሠራር ስፌት ቅድና ፋሽን እንዲሸጋገር አድርጎታል ሲሉ ጠቅሰው፣ ኢንዲስትሪዎቹ ከ100ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም አስታውቀዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በነበሩት ባህላዊ አሠራሮች ለረጅም ጊዜ ጨርቃ ጨርቅን ተጠቅመን ቆይተናል። አሁን ግን ገበያውን ለማሸነፍና የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ፋሽን ተኮር አሠራሮች መከተል ሚና አለው። አልባሳት በፋሽን ከተሠሩ ገበያው የሚረባረብባቸውና ሰው በብዛት ለብሶ የሚታይባቸው ናቸው። የህንድ፣ የቻይና፣ የአሜሪካ እና የተለያዩ ሀገሮች ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እየገቡ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ በተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እያደረጉ ነው። በዚህም ወጣቶች የሥራ ዕድል እያገኙ፣ በዘርፉ እየተሰማሩ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ እንዲሳለጥና አሠራሩ እንዲዘምን አድርገውታል።
በዚህም ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተናግረው፣ በጣም የዘመኑ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ወደ ገበያው እየገቡ ነው። ኢንዱስትሪዎቹ በዘመናዊ መንገድ ልምዱን እንዲወስዱ እና የፋሽን አልባሳቱ እንዲዘምኑ ለማድረግ ከውጭ ረጅም ልምድ ያላቸው የተለያዩ ኩባንያዎች ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲያመርቱ እየተደረገ ነው፤ በዚህም ቴክኖሎጂዎችን ወደ እኛ ሀገር የማሸጋገር እና ፋሽን ተኮር ፣ውድ ዲዛይን፣ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶች እንዲመረቱ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ያብራራሉ።
አቶ ባንቲሁን እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች በጣም ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው። ኢንዱስትሪዎች የጨርቃ ጨርቅና አልባሳቱ በጣም የዘመኑና ገበያውን የሚስቡ ሆነው እንዲመረቱ እንዲሁም ፋሽን ተኮር ሆነው እየዘመኑ በሀገር ውስጥም በውጭም ገበያ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው፤ ከባህላዊ መንገድ ወደ ዘመናዊ መንገድ ማሸጋገሩ በራሱ ለገበያ ያላቸውን አስተዋፅኦ የሚያጎላ ነው።
አሁን ወደ ማእከል የተቀየረው ተቋም በግዙፍ እና በጣም ፋሽን ተኮር የሆኑ አልባሳትን ለማምረት በሚያስችሉ መሣሪያዎች የተደራጀ መሆኑን አስታውሰው፣ ቢዚህም ለኢንዱስትሪ ሰራተኞችና መሪዎች ስልጠናዎች ይሰጣሉ፤ ሠልጣኞች ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ግብረ መልስ ይሰበስባል፤ በተሰጠው ሥልጠና መሠረት ደግሞ ፤ጥናትና ምርምር ይደረጋል፤ ግብአት ይሰበስባል ሲሉ ያብራራሉ። በግብአቱ መሠረት ደግሞ እንደገና የገበያ ክፍተቱ እየተለየ በቂ ዕውቀት ያልያዙ በደንብ ሥልጠና እንዲያገኙና ዕውቀትና ክህሎት የሌላቸው እየተለዩ ፤ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ እንደሚደረግ ይገልጻሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ተቋሙ የተለያዩ አልባሳት የሚያመርቱ ለወጣቶች፣ ለወይዛዝርት ለኮረዶች ለጉብሎች የሚያገለግሉ መሣሪያዎች አሉት። ከፋሽን ጋር የሚሄዱ አልባሳት እንዲያመረቱ ከማድረግ አኳያ አጫጭር ሥልጠናዎች ይዘጋጃሉ። ሱፐርቫይዘሮችን ከፋብሪካዎቹ ባለሙያዎችን ፣አመራሮችን እያስመጣ በየጊዜው አጫጭር ሥልጠናዎችን አዘጋጅቶ ሥልጠና ይሰጣል። ባሉት የፕሮጀክት ፈንዶችም በኩል ሥልጠናዎች ይሰጣሉ።
ይህን ሁሉ ተከትሎም ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ሰዎች ፋሽን ተኮር አልባሳት የሚሠሩና የሚያዘጋጁ ወጣቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። በፊት በሙያው በቂ ክህሎት ያለው ሰው አልነበረም። በባህላዊ መንገድ ብቻ ሲሄዱበት ነበር። በዓለም ገበያ ውስጥ ገብቶ ማምረትና መወዳደር የሚችል ዕውቀትና ክህሎት የነበረው ሰው አልነበረም ይላሉ።
ይህ ሁኔታ ተቀይሯል፤ ከፋብሪካዎች ጋራ ቁርኝት በመፍጠር በየጊዜው ለባለሙያው ፣ ለኦፕሬተሩ ለሠራተኛው ለሱፐርቫይዘሩ ሥራ እየተሰጠ የሰዎችን አቅምና አጠቃላይ ክህሎታቸውንና አመለካከታቸውን የማሳደግ ሥራ በተከታታይ እየተሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት። በገበያ ትስስሩም ፋብሪካዎች ምርታቸውን ወደ ውጭ ሀገሮች መውሰድና መወዳደር እንዲችሉ ለማድረግ የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ተወዳዳሪ ሆነው በአነስተኛ ዋጋ አቅርበው ብዙ ምርት በመሸጥ ከፍተኛ ትርፍ የሚያገኙበት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ይጠቁማሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ተቋሙ አጠቃላይ የማማከር አገልግሎት በመሥጠት፤በጨርቃ ጨርቅ አልባሳት በጥጥ ዘርፉ ዙርያ የተሰማሩ ፋብሪካዎቹንም እርሻዎቹንም ሁሉ በማካተት ለባለሀብቶቹና ለፋብሪካዎቹ ሙሉ ድጋፍ ይሠጣል። ድጋፎቹ ቴክኒካል እንዲሁም የኢንዱስትሪ ባህሉንና አመራሩን ለማሳደግ የሚያስችሉ ረጅምና የአጭር ጊዜ የአመራር ሥልጠናዎች ናቸው የሚሰጡት።
በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው የሚሰማሩ ኦፕሬተሮች ባለሙያዎች ሱፐርቫይዘሮች ሁሉ እንዴት ተቀናጅተው ፋብሪካውን መምራት እንዳለባቸው ዕውቀትና ክህሎት የማስጨበጡ ሥራዎች ናቸው የሚሰሩት። ባለሙያዎቹም ሙሉ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው አጫጭር ሥልጠናዎች እያዘጋጁ ይሰጣሉ።
የስፌት፤ የሽመና አሠራር፤ የፊኒሺንግ ሥራዎች ቴክኖሎጂዎች፤ የምርመራና ላቦራቶሪ ሥራዎች እና የልብስ ስፌት የተለያዩ ዘመናዊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች መሣሪያዎቹን ተጠቅሞ በየጊዜው የዲዛይንና የፋሽን ሥራዎቹ ዘመናዊ እየሆኑ ከወቅቱ ጋር አብረው እንዲሄዱ የሚያደርጉ ሥልጠናዎች እየተዘጋጁ ለኢንዱስትሪ አመራሮች ባለሙያዎችና ለኦፕሬተሮችም በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ይዘጋጃል። በፋብሪካዎቹም ሄዶ ክፍተታቸውን በማጥናትና ክፍተታቸውን ለመሙላት የሚያስችሉ ሥልጠናዎችም ይሰጣሉ።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 /2014