
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እንዳስታወቀው የአውሮፓ ነዳጅ ሻጭ ኩባያዎች ከሩሲያ ነዳጅን በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ በሆነው ሩብል መግዛት ይችላሉ ብሏል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ኩባንያዎቹ ነዳጅ ከሩሲያ በሩብል መግዛት የሚችሉት የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ በማይጋፋ መንገድ እንዲሆንም ኮሚሽኑ አሳስቧል።
ይሁንና እነዚህ የአውሮፓ ነዳጅ ሻጭ ኩባንያዎች ህብረቱ በሩሲያ ነዳጅ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዴት ማክበር እንዳለባቸው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን አላብራራም።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋ ይፋዊ ጦርነት ከጀመረች ሁለት ወራት ሞልቷታል።
በዚህም ምክንያት በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት አስተባባሪነት በሩሲያ ላይ ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦች በሩሲያ ላይ ተጥለዋል።
ሩሲያ በበኩሏ ጠላቴ ናቸው ያለቻቸው የአውሮፓ ህብረት አገራት እና አሜሪካ ከሩሲያ ነዳጅ በሩብል እንዲገዙ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለም ሩሲያ የዩክሬን ቁልፍ የወደብ ከተማ የሆነችው ማሪዮፖል ከተማን ተቆጣጥሬያለሁ ያለችው ሩሲያ ደቡብ እና ምስራቅ ዩክሬን ለመቆጣጠር አዲስ ዘመቻ መጀመሯን ገልጻለች።
ዩክሬን በበኩሏ ማሪዮፖል ከተማ እስካሁን በሩሲያ ጦር በቁጥጥር ስር አለመዋሏን ገልጻ በደቡባዊ ዩክሬን ከተሞች ላይ አዲስ ጥቃት እንደተከፈተባት አስታውቃለች።
በሩሲያ ላይ ከአሜሪካ እና አውሮፓ አገራት እኩል በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ለማድረግ ወደ ህንድ ያቀኑት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁለት ወር በፊት የዘጉት እና በዩክሬን መዲና ኬቭ የሚገኘውን ኢምባሲ ሊከፍቱ መሆናቸውን ከዴልሂ ተናግረዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም