
የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ጉባኤውን በዛምቢያ ሉሳካ ሊያካሂድ ነው።
የስራ አስፈጻሚ ጉባኤው የፊታችን ሐምሌ 7 ቀን እስከ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በዛምቢያ መዲና ሉሳካ እንደሚያካሄድ ህብረቱ አስታውቋል።
የስራ አስፈጻሚ ጉባኤው ከህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ቀድሞ የሚካሄድ ነው።
በጉባዔው የወቅቱን የህብረቱን ሊቀመንበር የሴኔጋሉን ፕሬዝዳንት ማኪ ሳልን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የህብረቱ አመራሮች እንደሚገኙ የህብረቱ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቋል።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔውን በዓመት ሁለት ጊዜ ይካሄዳል። ዋናውና በቋሚነት በወርሃ ጥር የሚካሄደው የመሪዎቹ ጉባዔ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ሁለተኛው ደግሞ በተመረጡ የህብረቱ አባል አገራት በዙር ይካሄዳል።
የህብረቱ ስራ አስፈጻሚዎች ጉባዔም ከመሪዎቹ ቀደም ብሎ ነው የሚካሄደው። በመሆኑም 41ኛው መደበኛ የስራ አስፈጻሚዎች ጉባኤ በሉሳካ እንደሚካሄድ ህብረቱ አስታውቋል።
የአፍሪካ ህብረት ልዑክ እና የጉባኤው አዘጋጅ ዛምቢያ በሉሳካ ተገናኝተው የጉባኤውን ቅድመ ዝግጅት ስራ እንደጀመሩም ነው የገለጸው።
በጉባኤው ላይ የሕብረቱ የ2023 በጀት ጉዳይ፣ የድህረ ኮሮና ቫይረስ ስራዎች፣ የህብረቱ አባል አገራት ፈተና በሆኑ ጉዳዮች እና በሌሎች ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአካል ጉባኤውን ሳይካሄድ የቆየው የአፍሪካ ህብረት ከሁለት ዓመት በኋላ ባሳለፍነው የካቲት 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ የመሪዎች ጉባኤውን ማካሄዱ አይዘነጋም።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም