
በአደገኛ እጽ ዝውውር እና በሕገ-ወጥ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብ በሚሉ ወንጀሎች ክስ የቀረበባቸው የቀድሞ የሆንዱራስ ፕሬዝደንት ለአሜሪካ ተላልፈው ተሰጡ።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሆንዱራስን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ሁአን ኦርላንዶ ህርናንዴዝ በአሜሪካ አውሮፕላን ወደ ኒው ዮርክ ተወስደዋል።
የቀድሞ ፕሬዝደንት ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው ከጀመሩ ከሳምንታት በኋላ ነበር ከሁለት ወራት በፊት ከመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
ህርናንዴዝ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል አደንዛዥ እጽ ወደ አሜሪካ እንዲገባ ማሴር፣ ጦር መሳሪያ መጠቀም እና መያዝ እንዲሁም ጦር መሳሪያ ለመጠቀም እና ለመያዝ ማሴር የሚሉት ይገኙባቸዋል።
በቀድሞ ፕሬዝደንት ባለቤት የትዊተር ገጽ ላይ በተለጠፈ ተንቀሳቃሽ ምስል፤ ህርናንዴዝ የቀረቡባቸውን ክሶች አጣጥለዋል።
የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ ህርናንዴዝ ዛሬ ሚያዚያ 14/2014 ኒውዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብሏል።
ዐቃቤ ሕግ ዳሚአን ዊሊያምስ የቀድሞ ፕሬዝደንት ከፍተኛ መጠን ያለው ኮኪዬን ለማዘዋወር ከእጽ አዘዋዋሪዎች ጋር ተጣምረዋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የህርናንዴዝ ታናሽ ወንድም ከእጽ ዝውውር ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው በአሜሪካ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
የህርናንዴዝ ታናሽ ወንድም ቶኒ ህርናንዴዝ ለታላቅ ወንድሙ ፕሬዝደንታዊ የምርጫ ቅስቀሳ እንዲውል ከታዋቂው የእጽ አዘዋዋሪ ዮአኪን ‘ኤል ቻፖ’ ጉዝማን 1 ሚሊዮን ዶላር ተቀብሏል ይላሉ የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ።
ጆአን ኦርናልዶ ህርናንዴዝ ላለፉት 8 ዓመታት የሆንዱራስ ፕሬዝደንት በሆኑበት ወቅት አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች ምርመራ እንዳይከፈትባቸው፣ በቁጥጥር ሥር እንዳይውሉ እና ለአሜሪካ ተላልፈው እንዳይሰጡ በመከላከል በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በጉቦ መልክ ይቀበሉ ነበር ተብሏል።
የቀድሞ ፕሬዝደንት ግን በተቻለኝ አቅም ሁሉ የእጽ ዝውውርን ስከላከል ቆይቻለሁ ይላሉ።
እአአ 2014 ላይ ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት ህርናንዴዝ፤ በርካታ እጽ አዘዋዋሪዎችን ለአሜሪካ አሳልፌ በመስጠቴ የተበሳጩ እጽ አዘዋዋሪዎች በቂም በቀል ተነሳስተው መሠረተ ቢስ የሆኑ ማስረጃዎችን እያቀረቡብኝ ነው ይላሉ።
ህርናንዴዝ ባለፉት ሁለት ወራት በሆንዱራስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቆይተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014