
በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን የተነሱት የቀድሞ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በጠና ታመው በሆስፒታል ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል(ቪዲዮ) መውጣቱ በበርካታ ሱዳናውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
ፕሬዚዳንቱ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት በእስርቤት ሳሉ በመታመማቸው ነው።
በሱዳን በፈረንጆቹ 1989 የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት በመምራት ወደ ስልጣን በመምጣት እና በሙስና ክስ ምክንያት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከሶስት አመት በፊት ከስልጣን የተነሱት በሽር ለእስር ተዳርገዋል።
ሮይተርስ የተንቀሳቃሽ ምስሉን ምንጭ እና እውነተኛነት ማረጋገጥ እንደማይችል በዘገባው ጠቅሷል። ነገርግን የፕሬዚዳንቱ ጠበቃ ፕሬዚዳንት በሽር በእስር ላይ መሆናቸውን አረጋግጧል።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ፕሬዚዳንቱ በሆስፒታል ክፍላቸው ውስጥ ሆነው ሊጠይቋቸው የመጡትን ሰዎች ሰላም ሲሉ፣ የተለመደ ልብስ ለብሰው እና ሰአት አድርገው በሆስፒታሉ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ ብሏል ዘገባው።
ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ከፍርድ ቤት ውጭ የታየ የመጀመሪያው ተንቀሳቃሽ ምስል ነው ተብሏል። በሌላ ተንቀሳቃሽ ምስል ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ሌሎች በሆስፒታሉ ያሉ ታማማሚዎች ሲጠይቁ ታይተዋል።
የፕሬዚዳንቱ ጠበቃ አብዱልራህማን አል ከሊፋ ፕሬዚዳንቱ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ መሆኑን ገልጸዋል።
የተወሰኑ ሱዳናውያን ፕሬዚዳንቱ እንዲድኑ ሲለምኑ፣ ሌሎች ለፕሬዚዳንቱ በተደረገው እንክብካቤ ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። አንድ የማህራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ይህን ለፕሬዚዳንቱ ተደረገ ያለውን እንክብካቤ ካየ በኋላ የአብዮቱ ሰማእታት ሞት ትርጉም የለውም ሲል ብስጭቱን ገልጿል።
ሱዳን አሁን ላይ አልበሽርን ከስልጣን ባነሱት የጦር ጀነራሎች እየተዳደረች ትገኛለች። በሱዳን ስልጣን የያዙት ጀነራሎች ስልጣናቸውን ወደ ሲቪል አስተዳደር እንዲቀይሩ የሚፈልጉ ተቃውሞዎች ሱዳን እስካሁን ድረስ እንዳትረጋጋ አድርገዋታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም