
በፍሎሪዳ የሚገኙ አንድ የፌደራል ዳኛ የባይደን አስተዳደር አውሮፕላኖች እና ሌሎች የሕዝብ ማጓጓዣዎች ላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲደረግ ያወጣውን ሕግ ” ሕጋዊ አይደለም” ሲሉ ውድቅ አደረጉ።
ዳኛ ካትሪን ኪምቦል ሚዜል የብሔራዊ ሕብረተሰብ ጤና ኤጀንሲ ሕጉን በማውጣት ሕጋዊ ሥልጣኑን ተላልፏል ብለዋል። የአሜሪካ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከአሁን በኋላ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንደማያስገድድ አስታውቋል።
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ባለፈው ሳምንት ሕጉን እስከ አውሮፓውያኑ ግንቦት ሦስት ድረስ አራዝሞት ነበር። ተቀማጭነታቸውን ፍሎሪዳ ያደረጉት ዳኛ ሚዜል የፌደራል ዳኞች በአገር አቀፍ ደረጃ የመንግሥት ፖሊሲዎችን የሚያግዱ ውሳኔዎችን ሊሰጡ ይችላሉ ብለዋል።
ዳኛዋ ሰኞ ዕለት ያስተላለፉት ውሳኔ በሁሉም አየር ማረፊያዎች፣ ባቡሮች፣ ታክሲዎች እና መተላለፊያ ቦታዎች ማስክ ማድረግ የሚለውን ግዴታ እንደሚሽር ቢቢሲ ዘግቧል።
የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ፕሳኪ ውሳኔውን “የሚያሳዝን” ያሉት ሲሆን ሲዲሲ አሁንም መንገደኞች አፍና አፍንጫቸውን እንዲሸፍኑ እንደሚመክር ተናግረዋል። ሲዲሲ ሰኞ ዕለት በተሰጠው ብይን ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የኅብረተሰብ ጤና ባለሥልጣን ሰርጂን ጀነራል ቪቬክ ሙርቲ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እስከ ግንቦት ድረስ መራዘሙን አስታውቀው ነበር።
ክሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት ያመራው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በወግ አጥባቂው ቡድን የጤና ነጻነት መከላከያ ፈንድ (ኤችኤፍዲኤፍ) እና ሁለት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ጭንቀታቸውን እና ድንገተኛ ድንጋጤን ይጨምራል ባሉ ሁለት የፍሎሪዳ ነዋሪዎች ነው።
ከሳሾቹ የሲዲሲ ሕግ ልክ ከሁለት ዓመት በታች እንዳሉ ህጻናት ሁሉ ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነጻነትን የሰጠ በመሆኑ “ዘፈቀዳዊ እና ወጥ ያልሆነ” ሲሉ ተከራክረዋል።
በቀድሞው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የተሾሙት ዳኛ ሚዜል በውሳኔው ላይ “ሥርዓታችን ፍላጎቶችን ለማስተናገድ ኤጄንሲዎች በሕገ ወጥ መንገድ እንዲሰሩ አይፈቅድም” ብለዋል።
በመሆኑም “ፍርድ ቤቱ ሕጉ ሕገ ወጥ መሆኑን በማወጅ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን የሚያስገድደው ትዕዛዝ እንዲነሳ አድርጓል” ሲሉ ተናግረዋል።
ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ የአሜሪካ አየር ማረፊያን ደህንነት የሚመራው የትራንስፖርት ደህንነት አስተዳደር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ትዕዛዝን እንደማይፈፅም አረጋግጧል።
ዩናይትድ ኤርላይንስ፣ ዴልታ አየር መንገድ፣ የአላስካ አየር መንገድ እና አሜሪካን ኤርላይንስ በበኩላቸው በአገር ውስጥ በሚደረጉ በረራዎች እና በተወሰኑ የውጭ በረራዎች ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንደማያስገድድ አስታውቀዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2014