
የኤምሬትስ አየር መንገድ ኃላፊ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት ክልከላ ካልጣለ በስተቀር አየር መንገዱ ወደ ሩሲያ የሚያደርገውን በረራ እንደሚቀጥል አስታወቁ።
“አቁሙ ከተባልን እናቆማለን ካልሆነ በየጊዜው የምናደርገውን በረራ እንቀጥላለን” ሲሉ ኃላፊው ሰር ቲም ክላርክ ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ምዕራባውያን ሃገራት በርካታ ማዕቀቦችን ጥለዋል እንዲሁም ዋና ዋና የሚባሉ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችም ሩሲያን ለቀው ወጥተዋል።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የኤምሬትስ አየር መንገድ ወደ ሩሲያዎቹ ሞስኮና ሴንት ፒተርስበርግ ከተሞች በረራዎችን ከሚያደርጉ ጥቂቶቹ አንዱ በመሆን ቀጥሏል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አየር መንገዱ ይህንን አቋም እንደገና ያጤነው እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄም የአየር መንገዱ ኃላፊ የእሳቸው ውሳኔ ሳይሆን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ መንገደኞችን ከማጓጓዝ በተጨማሪ በማዕቀቡ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ የሰብአዊ ቁሳቁሶችን የምግብና የህክምና አቅርቦቶችን ጨምሮ ሌሎች ጭነቶችን ያጓጉዛል። የሩሲያ ህዝብ በዩክሬን ውስጥ ያለው ጦርነት አካል ላይሆን እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
እናም በሞስኮ ውስጥ ተልእኮ ያላቸው ሌሎች አገራት ዲፕሎማሲያዊ ስራቸውን ወደ አገር ውስጥ በመግባት እና በመውጣት መስራት መቻል አለባቸው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“በምናደርጋቸው በረራዎች በዋናነት ህዝብን እያገለገልን ነው፤ ምናልባትም የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ መንግሥት የሚመለከተው በዚህ መንገድ ነው” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የነዳጅ ጭማሪ ቢኖርም በረራዎችም በዚሁ መጠን መጨመራቸውን ይናገራሉ።
አየር መንገዱ የነዳጅ ጭማሬውም ጋር በተያያዘ በአውሮፕላን ታሪፎች ላይ ተጨማሪ ዋጋ ቢጥልም ይህ ሁኔታ በመንገደኞችም ላይ ሆነ በጭነት አጓጓዦች ላይ ያመጣው ለውጥ የለም ይላሉ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2014