
-ህጻናቱ የተራቡት በአገሪቱ በተከሰቱት ጦርነቶች ምክንያት መሆኑን ተመድ ገልጿል።
ተመድ ጨምሮ በሰባት አገራት ለረሃብ የተጋለጡ ህጻናትን ለመርዳት 100 ሚሊዮን ዶላር መበጀቱን ገለጸ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ናይጀሪያ፣ ኬንያ እና የመን የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ለረሃብ ተጋልጠዋል።
በመሆኑን በነዚህ አገራት ለረሃብ የተጋለጡ ህጻናትን ለመታደግ 100 ሚሊዮን ዶላር በጀት መልቀቁን አስታውቋል።
የተመድ ማዕከላዊ አስቸኳይ ምላሽ ፈንድ እንዳሳወቀው በሰባቱ አገራት ባለው ጦርነት ምክንያት ለረሃብ የተጋለጡ ህጻናትን መታደግ ያስፈልጋል ብሏል።
ከጦርነቱ በተጨማሪም በሰባቱ አገራት በተከሰተ ድርቅ እና የኢኮኖሚ ምስቅልቅል ሚሊዮኖች ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን መመገብ እንዳልቻሉ ድርጅቱ በሪፖርቱ ገልጿል።
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ተጨማሪ ዜጎችን ለረሃብ እንደሚያጋልጥ ተመድ አስጠንቅቋል።
ሁለት ቢሊየን የዓለም ሕዝብ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ይኖራል- ተመድ በየመን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ያለው የረሃብ ሁኔታ ደረጃ አምስት ላይ የሚቀመጥ ነው ያለው ድርጅቱ በታሪክ አስከፊው የህጻናት ሞት ሳይከሰት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ገልጿል።
በናይጀሪያ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በአንጻራዊነት የተሻለ ቢሆንም በጊዜው ለረሃብ ለተጋለጡት ከወዲሁ ድጋፍ ካላደረግን ተመሳሳይ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ተመድ አስታውቋል።
የዓለም የዳቦ ቅርጫት የሚባሉት ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ መሆናቸው የዓለምን ሲሶ ምግብ አቅርቦት አደጋ ላይ ጥሏል። ለረሃብ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር መጨመሩንም ነው ድርጅቱ የገለጸው።
ተመድ ከአንድ ወር በፊት አሁን ላይ የረሃብ አደጋ ያጋጠማቸው ሰባቱን አገራት ጨምሮ ሌሎች አገራት ላሉ ተረጂዎች 43 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው መግለጹ ይታወሳል።
ይሁንና እንዲደጎም ካቀረበው የ43 ቢሊዮን ዶላር በጀት ውስጥ እስካሁን የተገኘው 6 ነጥብ 5 በመቶ ያህሉ ብቻ ከለጋሽ አገራት እና ድርጅቶች መገኘቱን አስታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 /2014