በግንባታ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም ከአገሪቷ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ1980ዓ.ም ኢትዮጵያ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) አሸናፊ መሆኗን ተከትሎ በወቅቱ በነበሩት የአገሪቷ መሪ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽልማት›› በሚል ነበር የግንባታ ሃሳቡ የተጠነሰሰው፡፡ ይሁንና ሦስት አስርት ዓመታትን ለሚጠጋ ጊዜ ዘግይቶ፤ በ2008 ዓ.ም ወደ መጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ተገባ፡፡
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ባለቤትነት እየተገነባ ያለው ይህ ግዙፍና ዘመናዊ ስታዲየም ሲጠናቀቅም የዓለም ዋንጫን እና ኦሊምፒክን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡ አሁን በሁለተኛው ዙር የግንባታ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ስታዲየሙ ከተያዘለት ጊዜ አንጻር የዘገየ ቢሆንም፤ የስፖርት ቤተሰቡ መጠናቀቁን በጉጉት ይጠብቀዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ግንባታውን እየተከታተለ ይገኛል፡፡
ከሰሞኑም በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ አፈጻጸምን በተመለከተ በስፍራው ተገኝተው የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በተሰጠው የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የኦዲት ግኝት ሪፖርት የመመርመር ተግባር መሠረት የ2012 በጀት ዓመት ክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡ በዚህም ሁለተኛ ዙር ግንባታው ከተጀመረ ሁለት ዓመት ያስቆጠረውን ስታዲየምና በዙሪያው እየተገነቡ የሚገኙ ተጓዳኝ ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ከኦዲት በኋላ ማስተካከያ የተደረገባቸውንና ያልተደረገባቸው ጉዳዮች ላይም ከሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሚኒስቴሩ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ የሚመሩበት የአፈጻጸም መመሪያ እስካሁን ያለመዘጋጀቱን ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡
ሚኒስቴሩም ከዚህ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የነበረውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አዋጅ መነሻ በማድረግ የስታዲየሞችን ደረጃ ለመለየት ሰነድ በማዘጋጀት መመሪያውን ለማውጣት እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ከደረጃዎች ጋር በተያያዘ ሚኒስቴሩ በራሱ የመወሰን ኃላፊነት የሌለው መሆኑና የሚመለከተው ደረጃዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤትን ቢሆንም በጉዳዩ ላይ የሚወስን ቦርድ ያልተቋቋመለት በመሆኑ እስካሁን መዘግየቱ ተመልክቷል፡፡
ከግንባታው ጋር በተያያዘ አስቀድሞ ሊሠራባቸው የሚገባቸው የቅድመ አዋጭነት ጥናትና ሊያሟላ የሚገባቸው ነገሮችም በዝርዝር አለመቅረባቸውና ወቅታዊ አለመደረጋቸውንም ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡ ነገር ግን ሚኒስቴሩ በአዲስ መልክ በቅርቡ በመዋቀሩ እንዲሁም አመራሮቹ አዳዲስ በመሆናቸው በኦዲት ግኝቱ ዙሪያ የተጠናቀረ ዝግጅት በማድረግ በቀጣይ እንዲያቀርብ በቋሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
ከቋሚ ኮሚቴው ጋር በነበረው ውይይትም ሚኒስቴሩ የስታዲየሙ ግንባታ እንዳይፋጠንና በተያዘለት የጊዜ ገደብ መሠረት እንዳይካሄድ መሰናክል የሆኑበትን ጉዳዮች አመላክቷል፡፡ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ በዚህ ወቅት በአገሪቷ ደረጃቸውን የሚያሟሉ ስታዲየሞች አለመኖር ከፍተኛ ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግንባታው እስካሁን ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ ይህም ከታላቁ የህዳሴ ግድብ በመቀጠል ከፍተኛ ወጪ የሚደረግበት ግዙፍ ፕሮጀክት ያደርገዋል፡፡ ይሁንና ከክፍያና የውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር እንደገጠመው ጠቁመዋል፡፡
ለግንባታው የሚውሉ ቁሳቁሶችን ከውጭ ማስገባት የግድ ሲሆን፤ ለዚህም የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ተቋራጭ ክፍያ የሚፈጸመው በብር እና በዶላር ሲሆን፤ እስካሁን የውጭ ምንዛሬ ክፍያው አልተከናወነም፡፡ ይህ በዚህ እንዳለም ተቋራጩ ተጨማሪ የዋጋ ማሻሻያ ጥያቄ አንስቷል፡፡ በመሆኑም ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት የፖለቲካ ውሳኔ ማግኘት የግድ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን የስታዲየም ግንባታው በሚከናወንበት ስፍራ ላይ ከነበሩት ነዋሪዎች ጋር በተያያዘ እስካሁንም መፍትሄ ያላገኘ ችግር መኖሩ ተመላክቷል፡፡ ይኸውም በስፍራው ላይ የሚገኘው የእምነት ስፍራ ተለዋጭ ቦታዎችን በመስጠት እንዲነሳ ቢደረግም ተግባራዊ ሊደረግ አልቻለም፡፡ በዚህም ላይ ከቦሌ ክፍለ ከተማ አልፎ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በተለያዩ ጊዜያት ንግግር ቢደረግም አሁንም ድረስ ለውጥ ባለመኖሩ ቋሚ ኮሚቴው በቀረቡት ጉዳዮች ላይ እገዛ እንዲያደርግ ሚኒስትሩ ሃሳቡን አንጸባርቀዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 /2014