ዘንድሮ ኢትዮጵያውያንና ፆም በልዩ ሁኔታ ተሳስረዋል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ የዐቢይ ፆምን፣ ሕዝበ ሙስሊሙ ደግሞ የረመዳን ፆምን በተመሳሳይ ወቅት ስለፆሙ ወደ ፊት ኢትዮጵያውያን የዘንድሮውን ፆም ሲያስታውሱ ትልቅ ትዝታ ይኖራቸዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ ዐበይት የፆም ጊዜያት በአማኞች ዘንድ ልዩ ስፍራና ክብር የሚሰጣቸው መንፈሳዊ ተግባራት ናቸው፡፡ አማኞች የሥጋ ምቾታቸውን ቀንሰው ስለትናንት፣ ስለዛሬና ነገ በፆም፣ በፀሎትና በስግደት ፈጣሪያቸውን ይማፀናሉ፡፡ በሃይማኖቶቹ አስተምህሮዎች የሚታዘዙ ሌሎች ተግባራትንም ይፈፅማሉ፡፡
የሃይማኖት አባቶችም ሕዝቡ የፆም ጊዜያቱን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እንዲሁም ለአገር ሰላምና እድገት የሚጠቅሙ መልካም ተግባራትን በማከናወን ማሳለፍ እንደሚገባው ቀደም ብለው አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የዘንድሮውን ዐቢይ ፆም ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ተግተን ካልፀለይን በስተቀር ፈተናው ይፀናብናል፡፡ በፈተና ውስጥ ብንሆንም ፈጣሪን በመለመን ፈተናውን መቋቋም እንችላለን፡፡ የፆሙን ወራት ስለሕዝባችን ዘላቂ ሰላምና ስምምነት አጥብቀን በመፀለይ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማሰብና በመርዳት ማሳለፍ ይገባናል፡፡ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እንፀልይ›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በበኩላቸው የረመዳን ፆም መጀመርን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በታላቁ የረመዳን ወር መደጋገፍና መረዳዳት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ‹‹የረመዳን ወር ሙስሊሞች ራሳቸውን ከአላህ ጋር የሚያቀራርቡበት፣ የግል ስሜታቸውንና ራስ ወዳድነታቸውን የሚያርቁበት እና ይቅር የሚባባሉበት ወር በመሆኑ በዚህ የተቀደሰ ወር ተጠቃሚ ለመሆን ራሳችንን ማስተካከል ይጠበቅብናል›› ብለዋል፡፡ የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዑስማን አደም በበኩላቸው በጦርነትና በድርቅ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በእርግጥ በእነዚህ የፆም ወራት የሚታየው የሕዝቡ የመደጋገፍ ባህል ልዩና አስደናቂ ነው፡፡ ክርስቲያኑ ለክርስቲያኑ፣ሙስሊሙ ለሙስሊም ወገኖቹ ከሚያደርገው እገዛ ባሻገር ክርስቲያኑ ለሙስሊሙ፣ ሙስሊሙም ለክርስቲያን ወገኑ የሚያደርገው ድጋፍ፣ የሚያሳየው ፍቅርና አክብሮት የተለየ ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ ሙስሊሙ ክርስቲያኑ በፀሎት የሚያሳልፍባቸውን ስፍራዎች በማፅዳትና በማስተካከል ሲሳተፍ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ክርስቲያኖችም ሙስሊም ወገኖቻቸው የሚሰግዱባቸውን ቦታዎች በማፅዳት መሳተፋቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆነን ዘንድ እስኪ ወደ ኋላ መለስ ብለን እናስታውስ፡፡
ከባለፈው ዓመት (1442ኛው) የኢድ አል-ፈጥር በዓል ቀደም ብሎ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከናወኑ በርካታ የጎዳና ላይ የአፍጥር መርሐ ግብሮች የሚዘነጉ አይደሉም፡፡ የአፍጥር ዝግጅቶቹ ሕዝበ ሙስሊሙ በጋራ ዱአ (ጸሎት) ያደረገባቸውና ማዕድ የተጋራባቸው አስደናቂ መርሐ ግብሮች ከመሆናቸው ባሻገር ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድሞቹ/እህቶቹ ጋር ያለውን ፍቅርና ትስስር ይበልጥ ያጠናከረባቸው መድረኮች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የአፍጥር መርሐ ግብሮች ተጀምረው እስከሚጠናቀቁ ድረስ የክርስትና እምነት ተከታዮች ተሳትፎና ሚና እንደነበርና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን መርሐ ግብሮቹ የሚከናወኑባቸውን ስፍራዎች ከማጽዳት ጀምሮ ዝግጅቶቹን በማስተባበርና ጥበቃ በማድረግ አኩሪ የፍቅርና የአንድነት ተግባራትን እንዳከናወኑም አይዘነጋም፡፡
በተለይ ደግሞ ከጎዳና ላይ የአፍጥር መርሐ ግብሮቹ መካከል የብዙዎችን ቀልብ የሳበውና ማክሰኞ ዕለት፣ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍጥር ሥነ ሥርዓት የሚዘነጋ አልነበረም፡፡ በረመዳን ፆም ማጠናቀቂያ እና በኢድ አል-ፈጥር በዓል ዋዜማ ላይ የተከናወነው ይህ የአፍጥር መርሐ ግብር፤ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና በተሳታፊው ቁጥር አዲስ ክብረ ወሰን (ከ15ሺ በላይ ሕዝብ የተሳተፈበት) የተመዘገበበት ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ መርሐ ግብር ላይ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ዝግጅቱ ያማረና የተሳካ እንዲሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ የአደባባይ ላይ የአፍጥር ሥነ ሥርዓት እንዲያከናውን ከመጀመሪያው ጀምሮ አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያውያን ትብብር ወዳጅን አስደስቷል፤ ጠላትንም አስከፍቷል፡፡ በተለይም ‹‹ኢትዮጵያውያንን በሃይማኖት ከፋፍለን የህዳሴውን ግድብ ስኬት እናደናቅፋለን›› ብለው ያሰቡ አካላት እጅግ ደንግጠዋል፡፡
መሰል ተግባራት የሕዝቡን ትስስር ከማጎልበት ባሻገር በአሁኑ ወቅት ከውስጥም ከውጭም ብዙ ፈተናዎች ለተደቀኑባት ኢትዮጵያ እጅግ ትልቅ አወንታዊ ትርጉም አላቸው፡፡ የውስጥ ኃይሎችን ተጠቅመው አገሪቱን እረፍት የነሷት የውጭ ኃይሎች የእኩይ ድርጊታቸው ዋነኛ ምክንያት/ስሌት የኢትዮጵያውያንን ልዩነት መጠቀም ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን የተለያዩ፣ የማይስማሙና የተከፋፈሉ ናቸው›› በሚል ስሁት ግምት የዓላማቸው ተጋሪ የሆኑ የውስጥ ኃይሎችን በማሰለፍ አገሪቱን መበጥበጥን እንደዋነኛ አማራጭ አድርገው የሚጠቀሙበት እነዚህ ኃይሎች መሰል የአንድነት መርሐ ግብሮች (የጎዳና ላይ ኢፍጣር) ምቾት ይነሳቸዋል፡፡ እነዚህ መርሐ ግብሮች ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ለሙስሊም ወገኖቻቸው ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር የሚያሳዩባቸው ስለሆኑ ይህ የኢትዮጵያውያን ትብብርና መከባበር ጠላቶች ያሰቡትን እኩይ ተግባር ለማስፈፀም አቅም እንዲያንሳቸው ያደርጋል፡፡
በወቅቱ የአዲስ አበባውን ጨምሮ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የተከናወኑ የጎዳና ላይ የአፍጥር መርሐ ግብሮችና የኢድ አልፈጥር በዓል የሶላት ስግደቶች በሰላም መጠናቀቃቸው የእስልምና እምነትና የእምነቱ ተከታዮች ሰላምን የሚሹ መሆናቸውንና የሌሎች እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ትብብርና ሚና ምን ያህል ወሳኝ እንደነበር አሳይተዋል፡፡
ዘንድሮም በተለያዩ አካባቢዎች የአፍጥር መርሐ ግብሮች እየተከናወኑ ነው፡፡ መደጋገፉና መተባበሩም እንደትናንቱ ቀጥሏል፡፡ ይህ አስደሳችና አኩሪ ተግባር በመተጋገዝና በመከባበር መኖር መለያው ለሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተጨማሪ ደስታና የኩራት ምንጭ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል የኖረውን የቆየና ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስርም ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
የዐቢይ ፆም ወራት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ላቅ ያለ ስፍራ አላቸው፡፡ በጎ ተግባራትን በማከናወን ግለሰባዊም ሆኑ አገራዊ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ በፆም፣ በፀሎትና በስግደት ለፈጣሪ ምልጃና ተማፅኖ የሚቀርብባቸው ጊዜያት ናቸው፡፡ ታላቁ የረመዳን ፆም ደግሞ ሕዝበ ሙስሊሙ ከፈጣሪው የሚታረቅበት፤ ፍቅር፣ ወንድማማችነቱንና አንድነቱን የሚያጎለብትበት እንዲሁም ከየትኛውም መጥፎ እሳቤ የሚርቅበት ታላቅ የፆም ወቅት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በብዙ መከራዎች ተተብትባ የምትገኝ ሲሆን፤ የዐቢይና የረመዳን ፆም ወራት መልካም ተግባራት በጦርነት፣ በድርቅ፣ በበሽታ፣ በምጣኔ ሀብታዊ ቀውስና በሌሎች ፈተናዎች ውስጥ ለምትገኘው አገር ፈውስ የመሆን አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም የእነዚህን ዐበይት የፆም ጊዜያት መልካም ተግባራትን በማጠናከር የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ትስስር ማጠንከር ይገባል፡፡
ሌላው በአሁኑ ወቅት ከረመዳን ፆም ጋር በተያያዘ ለማኅበራዊ እሴቶቻችን ማጎልበቻነት እንደመልካም አጋጣሚ ልንጠቀምበት የሚገባው ‹‹ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት›› የተሰኘው ታላቅ መርሐ ግብር ነው፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከኢድ አልፈጥር እስከ ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓላት ድረስ ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ ገብተው እንዲያሳልፉ ታስቦ የተዘጋጀው ይህ ኹነት የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ብዝኃነት ለማሳየትና የመደጋገፍ ባህላቸውን ለማጠንከር የሚያስችል ይሆናል፡፡ የዝግጅቱ አስተባባሪ ብሔራዊ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበክር አሕመድ ‹‹ዝግጅቱ ኢትዮጵያ የብዝኃነትና የእኩልነት አገር መሆኗን እንዲሁም የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያጎሉና መልካም እሴቶቻችንን የምናሳይበት ነው›› ብለዋል፡፡ ኹነቱ የተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚከወኑበት ይፋ የተደረገ ሲሆን እነዚህን መርሐ ግብሮች ለማኅበራዊ መስተጋብራችን መጎልበት በመጠቀም እንደ አገር የገጠሙንን ፈተናዎች ለማለፍ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2014