በዛሬው ሳምንታዊው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1962 ዓ.ም ከወንጀልና ፀጥታ ጋር በተያያዘ የተሠሩ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል፡፡ ዘገባዎቹ እንዲህም ይደረግ ነበር እንዴ የሚያሰኙና በአቀራረባቸውም ወጣ ያሉ በመሆናቸው አንባቢን ይስባሉ ብለን ነው ይዘናቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
በሲዳሞ ተገደለች የተባለች ሴት በሕይወት ተገኘች፤ በዚህ ምክንያት 33 ሰዎች ታስረው ነበር
አዋሳ (ኢ/ዜ/አ/) ተገድላለች በመባል ፴፫ ሰላማውያን ሰዎች ያስከሰሰችው ሒዶ ጉራሮ የተባለችው ሴት በሕይወት ተገኘች::
ሒዶ ጉራሮ በሰው እጅ ሕይወቷ አልፏል የተባለው በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ጦሎ ቦቶ ቀበሌ ግንቦት ፲፯ ቀን ፷ ዓ/ም/ ሲሆን ፤ጉዳዩን በመመርመር ላይ ለሚገኘው አዋሳ ከተማ ያስቻለው ከፍተኛው ፍ/ቤት ፪ኛ ወንጀል ችሎት በሕይወት መኖሯን በማረጋገጥ የጽሑፍ ማመልከቻ ያቀረበችው ታኅሳስ ፳፬ ቀን ፷፪ ዓ/ም ነው::
አቶ ሶሬ ቦጮ የተባለው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር ፴፮/ ፭፻፳፫ መሠረት ፴፫ ሰዎች በመተባበር ባለቤቱን ሒዶ ጉራሮን በጦር መሣሪያ በማስፈራራት ደብድበው ከገደሉ በኋላ ፮ሺህ ፪፻፷ ብር ግምት ያላቸው የቀንድ ከብትና ሌላም ንብረት ፤እንዲሁም በቤቱ ውስጥ የነበረውን ፪ሺህ ፭፻ ብር ጥሬ ገንዘብ በመውሰድ የሰው መግደልና የዘረፋ ወንጀል መፈጸማቸውን ያመለክታል::
፴፫ ሰዎች የዝርፊያና የሰው መግደል ወንጀል ለመፈጸማቸው በሐሰት ማስረጃ ከተረጋገጠ በኋላ ፤ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀዳሚ ምርመራ ጉዳዩ እንዲጣራ ስለታዘዘ፤በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር ፹ መሠረት ክሱ ተከፍቶ ከተከሰሱት ፴፫
ሰዎች መካከል ፱ ሰዎች ተይዘው በወህኒ ቤት እንዲቆዩ ተደረገ:: የቀሩት ፳፬ ሰዎች በመፈለግ ላይ እንዳሉ ሞተች የተባለችው ሴት ‹‹ በተባለው ቀን ጨርሶ በዚያ አገር የለሁም ::በፈቃድ ወደ ዘመዶቼ ሔጄ ነበር ›› በማለት ማመልከቻዋን ይዛ አዋሳ ከተማ ያስቻለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፪ኛ ወንጀል ችሎት ታኅሳስ ፳፬ ቀን፲፱፻፷፪ ዓ/ም ቀርባ አመለከተች::
ከአሁን በፊት በቀዳሚ ምርመራ በሐሰት ከመሰከሩት ሰዎች መካከል አቶ ሻርጃ ሾራ ቀርቦ በሰጠው ቃል ‹‹ከዚህ በፊት ሞታለች ብዬ የመሰከርኩት ሴት ይህቺ ናት:: አስቀድሜም አውቃታለሁ አብረንም በጉርብትና ብዙ ኖረናል:: ነገር ግን ከሳሹ ጠጅ ጋብዞ በሐሰት እንድመሰክርለት ስለጠየቀኝ መሰከርኩ እንጂ ስትገደል አላየሁም ›› በማለቱ የፍርድ ውሳኔ እስኪሰጥ በወህኒ ቤት እንዲቆይ ተደርጓል:: የቀሩት ፪ ምስክሮች አቶ ጊጋ ፉላስና አቶ እሬቦ ኖቲ የተባሉት ጠፍተው በመፈለግ ላይ ይገኛሉ:: እንዲሁም በ፴፫ ሰዎች ላይ በሐሰት ክስ ያቀረበው አቶ ሶሬ ቦጮ በመጥፋቱ በመፈለግ ላይ መሆኑን አንድ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ገለጠ::
(ጥር 6 ቀን 1962 ዓ.ም)
ፈቃድ የሌላቸው የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ተቀጡ
አርባ ምንጭ (ኢ/ዜ/አ/)፡- ያለፈቃድ የጦር መሣሪያ ሲነግዱ የተገኙት አራት ሰዎች እያንዳንዳቸው ፬፻ ብር ተቀጡ ::
ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የጦር መሣሪያ ሲነግዱ የተገኙት ቢርመጫ ኢላላ፣አስጨናቂ ወንድሙ ፣ደመቀ አድነውና ዓለሙ ዘነበ የተባሉት ተከሳሾቹ ሁለት ረጃጅም አልቤንና አንድ ምንሽር ጠብመንጃ ለሰዎች ለመሸጥ ሲያስማሙ፤በፖሊስ መከታተል የተያዙት ጥቅምት ፱ ቀን ፷፪ ዓ.ም ነው:: እነ ቢርመጫ በዚህ አፈጻጸማቸው አርባ ምንጭ ሒያ ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሰው ከቀረቡ በኋላ ፤አድራጐታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠ እያንዳንዳቸው ፬፻ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ተበይኖባቸዋል::
እንዲሁም በእጃቸው የተገኙት ጠብመንጃዎች በውርስ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆኑ ፤በተጨማሪ መወሰኑን ሻምበል ባሳድነው ባማው የአርባ ምንጭ ምድብ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ገልጠዋል:: በተከሳሾቹ ላይ ይኸው ቅጣት የተወሰነው ከትናንት በስቲያ ነው::
(ጥር 6 ቀን 1962 ዓ.ም)
564 ልዩ ልዩ ጥይቶች ይዞ የተገኘው 50 ብር ተቀጣ
ባህርዳር (ኢ-ዜ-አ)፡- 564 ልዩ ልዩ ጥይቶች ይዞ የተገኘው ሰው 50 ብር ተቀጣ :: ዓለሙ ደስታ የተባለው ይኸው ሰው ፩፻፺፪ የካርባን ፫፻፸፪ የወጨፎ ጥይቶችን ይዞ ከአዲስ አበባ ወደ ባህርዳር ሲጓዝ የተያዘው ባለፈው ታኅሳስ ፳፫ ቀን ፷፪ ዓ.ም/ በመራዊ ከተማ ነው::
ዓለሙ በዚህ አድራጎቱ ተከስሶ መየጣ ወረዳ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍል ተበይኖበታል :: በእጁ የተገኙትም ጥይቶች ለመንግሥት ገቢ እንዲሆኑ መወሰኑን ሕግ አስከባሪው ወታደር ብርሃኑ ተገኝ ገልጠዋል::
(ጥር 22 ቀን 1962 ዓ.ም)
ጨለማን ተገን እያደረጉ ድብደባና ዘረፋ የሚፈጽሙ አርባ ሰዎች ተያዙ
አዲስ አበባ (ኢ-ዜ-አ-) የአዲስ አበባ ፖሊስ ረዳት ዋና አዛዥ ኰሎኔል አድማሱ ሀብተማርያም፤ ትናንት ከጧቱ ፬ ሰዓት ላይ ፤ሰሞኑን ጨለማን ተገን እያደረጉ በሰላማዊ ሰው ላይ ድብደባና የንብረት ዘረፋ አድርገዋል፤በመባል በፖሊስ መከታተል ስለተያዙት ፵ ሰዎች መግለጫ ሰጡ::
ስለነዚሁ ሰዎች ገለጣ ባደረጉበት ጊዜም ፤የአዲስ አበባ የወንጀል ምርመራ ዋና ሹም ሌተናል ኰሎኔል ሥዩም ጨፍቄ ተገኝተው፤ፖሊሶቹ ወስላቶች ናቸው የተባሉትን በእንዴት ያለ ታክቲክና ዘዴ ደርሰው እንደያዙዋቸው አስረድተዋል::
ከተያዙት ፵ ወስላቶች መካከል ፳፰ቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ ፍርዳቸውን የሚጠባበቁ ሲሆን ፤ወንጀል የፈጸሙበትን ሥፍራና ቀበሌ በመምራት ማሳየታቸውንም ጭምር ሌተናል ኰሎኔል ሥዩም ጨፍቄ የአዲስ አበባ ወንጀል ምርመራ ዋና ሹም ገልጠዋል::
ኰሎኔል አድማሱ ሀብተማርያም የአዲስ አበባ ፖሊስ ረዳት ዋና አዛዥ ስለተፈጸመው የወንጀል ሥራ በዝርዝር ሲያስረዱ፤‹‹የወንጀሉ አፈጻጸም በዝቶ የተገኘው በቂርቆስ ቀበሌና የጎጃም በረንዳ በተባለው አካባቢ ሲሆን እስካሁን በተደረገው ጥብቅ ቁጥጥርና መከታተል ወንጀለኞቹ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ሁሉንም በመሰብሰብ ለማዕከላዊ የወንጀል አሻራ ክፍል አስረክበናል›› ብለዋል::
ጉዳያቸው ተጣርቶ ለፍርድ ይቀርባሉ ከተባሉት ሰዎች መካከል ፲፭ቱ የተያዙት በአዲስ ከተማ ሲሆን ፲፫ቱ ደግሞ በቂርቆስ ቀበሌ መሆኑ ተረጋግጧል:: በመጨረሻም የወንጀል ምርመራ ክፍል ዋና ሹም ሲገልጡ ፤ወንጀል የተፈጸመባቸው ሥፍራዎች ከዱሮ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልና ከልዑል መኰንን ት/ቤት ፊት ለፊት ያለው ቦታ ቁጭራ አቶ ሁሴን በረንዳ አጠገብ ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን በረንዳ አጠገብ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አዲሱ ከተማ ቁጭራ ሠፈርና እህል ተራ ‹‹ጎጃም በረንዳ›› የሚባለው ሠፈር፤ አባኮራን ሠፈር መሆናቸውን ገልጠዋል::
እንዲሁም አርበኞች መንገድ ዮሐንስ ቤ/ክ ፊት ለፊት የድሮ አባዲና ፖሊስ ማቋረጫ ራስ ደስታ ሆስፒታል ‹‹ሐምሌ 16 አጠገብ›› እሪ በከንቱ ድልድይ ናዝሬት መኪና ተራ ደብረ ዘይት መንገድ መስከረም ቡና ቤት ኦርማ ጋራዥ አካባቢዎች ይገኙበታል::
ወንጀሉን ፈጽመዋል በመባል ወጣቶች ቢያዙም ንብረት የጠፋባቸው ንብረታቸውን ለመውሰድ ቀርበው ባለመጠየቃቸው ኰሎኔል መገረማቸውንና ወደፊት እየቀረቡ እንዲወስዱ አሳስበዋል::
(የካቲት 21 ቀን 1962 ዓ.ም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4 /2014