ቢቂላ ዮሐንስ እና አባስ ሲራጅ የተወለዱት ኦሮሚያ ክልል፣ ወለጋ ዞን ሲሆን የተዋወቁት ሁለቱም በብየዳ ሥራ ላይ ተሰማርተው እያለ ቡራዩ ከተማ ነው። ቢቂላ በትምህርት አባስ በልምድ ያገኙትን የብየዳ እውቀት አቀናጅተው ወርቅን ከኮረት አንጠርጥረውና ከደለል አጥበው የሚያወጡ አራት ማሽኖችን ሠርተው ጥቅም ላይ አውለዋል። በዛሬው ዝግጅታችንም የጓደኛሞቹን የሥራ ትጋት፣ ፈጠራና ስኬት የምናስቃናችሁ ይሆናል።
ቢቂላ በነቀምቴ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ ጀነራል ሜካኒክስ ዲፓርትመንት በሌቭል ሦስት የሜታል ትምህርቱን ተከታትሎ በመመረቅ በሜቴክ ብረታብረትና ኮርፖሬሽን በመቀጠር በብየዳ፣ በፕላስማ ኦፕሬተርነትና በፋብሪኬቲንግ ሙያዎች ሠርቷል። ጎን ለጎንም በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ትምህርቱን እስከ ሌቭል አምስት ተምሯል።
ሜቴክ ለህዳሴው ግድብና ለስኳር ፕሮጀክቶች የሚውሉ ግብአቶችን ለማምረት ሠራተኞች ሙያዊ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ሲያደርግ ቢቂላም በኤሮፒያን ዌልዲንግ ሶሳይቲ /EWS/ የተለያዩ የብየዳ ዓይነቶችን እንዲማር ይደረጋል፤ በዚሁ መሠረት መገናኛ አካባቢ በሚገኘው ጀርመን ስልጠና ማዕከል ገብቶ የኢንተርናሽናል ብየዳ ስልጠናውን ይወስዳል። ከዚያም በሜቴክ ስር ሆኖ በበለስ አንድ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት፣ በኢሉ አባቦራ ዋዮ የማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲሠራ ይደረጋል። ከዚያም በኮካ ፋብሪካና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥሮ የመሥራት ዕድል ያገኛል። ባህርዳር ከተማ በመሄድ በነበረው የብየዳ ሙያ በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ጀልባዎችን ሠርቷል። ቢቂላ በዩሮፒያን ብየዳ ማዕከል የተለያዩ የብየዳ ዓይነቶችን መማሩና ዓለምአቀፍ ሰርተፊኬት መያዙ በዘርፉ ተፈላጊ እንዳደረገው ይናገራል።
እዚህ አገር በአመዛኙ የሚታወቀው በኤሌክትሮድ የሚበየደው ዓይነት እንደሆነ የሚናገረው ቢቂላ ከአንድ መቶ በላይ የብየዳ ዓይነቶች አሉ ይላል። ለምሳሌ አልሙኒየም የሚበየድበት ማሽን እራሱ ሽቦ እየተፋ የሚያጣብቅ ነው። የማይቀልጥ ኤሌክትሮድ እየተጠቀመ ብረትን በሙቀት እያቀለጠ እርስ በርሱ እንዲጣበቅ የሚያደርግም ሌላ ዓይነት የብየዳ ጥበብ እንዳለም ይገልጻል። ቢቂላ በየሮፒያን የብየደ ማዕከል ሲማር እነዚህንና ሌሎች በርካታ የብየዳ ዓይነቶችን ተምሯል። በዚህም ስድስተኛና የመጨረሻውን የበያጅነት ደረጃ አግኝቷል።
ቢቂላ በተለያዩ ድርጅቶች እየተቀጠረ መሥራት ከጀመረ በኋላ በሚያገኘው የወር ደመወዝ ብቻ መኖር እርካታ አልሰጠው ይላል። ያካበተውን ሙያ ጥቅም ላይ ቢያውለው የተሻለ ነገር ማድረግ እንደሚችል አስቦ ፊቱን ወደ ግል ሥራ ያዞራል።
የትምህርት ሰርተፊኬቱን በማሳየት ከሚኖርበት ቡራዩ ከተማ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ፈቃድ ያወጣል። ከቤተሰብና ከሚያውቃቸው ሰዎች ላይ ገንዘብ ተብድሮ የተወሰኑ ማሽኖችን ከገዛ በኋላ በቤተሰብ ቦታ ላይ የግል ሥራውን “ሀ” ብሎ ይጀምራል። የራሱን ዲዛይን እያወጣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ትንንሽ ማሺኖችንና የመኪና ስፖንዳዎችን የመሥራት ሙከራ ውስጥ ይገባል።
በዚህ አጋጣሚ ከአባስ ጋር ይተዋወቃል። አባስ የልምድ ሙያተኛ ነው። በቡራዩ ከተማ በተወሰነች ቦታ ላይ መስኮትና በሮችን እየበየደ የሚተዳደር ወጣት ነው። ወጣቶቹ ልምድና እውቀታቸውን አቀናጅተው ቢሠሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ይነጋገራሉ። በጋራ ሠርተው ውጤት ለማምጣት አስበው ቢንቀሳቀሱም ሥራው እነርሱ እንዳሰቡት አልሄድ ይላቸዋል። በእነርሱ ተማምኖ የመኪና ስፖንዳ የሚያሠራ ሰው ይቅርና ትንንሽ ሥራዎችን እንኳ እንደልብ እያገኙ መሥራት ሳይችሉ ይቀራሉ።
ግን ተስፋ አልቆረጡም። ቢቂላ ዲዛይኖችን እያወጣ የሻማ ማቅለጪያና መሥሪያ ማሽኖችን ለመሥራት ሞከሩ፤ የሚገዟቸውም ይሁኑ ማሺኑ እንዲሠራላቸው የሚያዙ ሰዎች ግን አልነበሩም። ያም ቢሆን በኪሳራ ውስጥ የራሳቸውን ፈጠራ ከመሥራት አልታቀቡም። አንድ ቀን አንድ አዲስ ነገር ሠርተው ተፈላጊ እንደሚሆኑ በማሰብ ሁሌም ተግተው ይሠሩ ነበር።
ዛሬ እንደ ምኞታቸው ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ተፈላጊ ሆነዋል። ቢቂላ የስኬታቸውን ሂደት እንዲህ ያስረዳል።
‹‹በአንድ ወቅት እዚሁ ቡራዩ ከተማ ጫላ ከሚባል ሰው ጋር ተዋወቅን፤ ጫላ የቤኒሻንጉል አካባቢ ነዋሪ ነው፤ ከጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ በወርቅ ቁፈራ ሥራ ላይ ተሰማርቷል። አፈር ማጠቢያ ማሽን ቢያገኝ ውጤታማ ሥራ እንደሚሠራ አጫወተኝ። የቁሳቁስ መግዣውን አግዘንና ማሽኑን እኛ እንሥራልህ አልኩት። በብየዳ ሙያ ጥሩ እውቀት እንዳለኝ ቢያውቅም ሊያምነኝ አልቻለም። በጣም እየተቀራረብን ስንመጣና አንዳንድ ሥራዎቻችንንም ሲመለከት እያቅማማም ቢሆን እንድንሠራለት ተስማማን።
ወደ ሥራ ከመግባታችን በፊት የወርቅ ማጠቢያ ማሽኖችን ከኢንተርኔት ላይ እያወረድኩ ቪዲዮውን በመመልከት አጠቃላይ የሚሠሩበትን ቁሳቁስና እንዴት እንደሚሠሩ አጠናሁ። ያንን መነሻ በማድረግ አስፈላጊ ቁሳቁስ ካሟላን በኋላ እኔ ዲዛይን እያወጣሁ አባስም በብየዳ እየረዳኝና ተጨማሪ ሀሳቦችን እየሰጠኝ ‹‹ፕሮሚል›› የሚባል አነስተኛ መጠን ያለው ማሽን ሠራን። ማሽኑ ኳርትዝ /የድንጋይ ኮረት/ ውስጥ የሚገኝ ወርቅን በውሃ እያጠበና እያንጠረጠረ ወርቁን በአንድ በኩል የሚለይ ነው። ጫላ ማሽኑ ተሠርቶ ሥራ እስኪጀመር ድረስ እምነት አልነበረውም። ማሽኑን ወርቅ ወደ’ሚቆፈርበት ቦታ ወስደን ሙከራ ስናደርግ እንዳሰብነው ሀሳባችን ተሳካልን። ጫላም ደስተኛ ሆነ። የእርሱን ውጤታማነት የተመለከቱ ሌሎች ወርቅ ቆፋሪዎችም ተመሳሳይ ትእዛዝ ማቅረብ ጀመሩ። ሌላም ተመሳሳይ ማሺን ሠርተን ሸጥን። ሰዎች በሥራችን መተማመን ጀመሩ።
በቀጣይ ደግሞ ከኮረት ወይም ከኳርትዝ ሳይሆን ከደለል ወርቅን እያጠበ የሚያወጣ ማሽን እንድንሠራላቸው ጥያቄ አቀረቡልን። ከወርቅ አምራች ማህበሩ ጋር በጋራ የሚሠራ አንድ ባለ ሀብት አስፈላጊውን ቁሳቁስ ገዛልንና ማሽኑን ሠራን። ስሙንም «ቢኤስዲ አንድ መቶ አልነው» ይላል ቢቂላ።
ከቀደመው ሥራቸው በመማር ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርታቸውን እያሻሻሉ መሆናቸውን ይናገራል። ቢቂላና አባስ ሙሉ ጊዜያቸው የወርቅ አፈር ማጠቢያ ማሽን በማምረት ማሳለፍ ከጀመሩ ወዲህ በሥራና በሃሳብ እየተረዳዱ የተሻለ አቅምና ፍጥነት ያላቸውን ማሺኖች እያመረቱ ነው። በተለይም ከወርቅ አምራች ማህበር ጋር ተዳብለው የሚሠሩት ባለሀብት ዛሬ ላገኙት እውቅና አስተዋጽኦ ስላበረከቱላቸው ያመሰግኗቸዋል።
ሦስተኛው ማሽን ተሠርቶ ውጤታማ ከሆነ በኋላ ሌሎች ወርቅ አምራች ማህበራት ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበውላቸው አራተኛውን ማሽን ለመሥራት ይበቃሉ። ማሽኑ በሰዓት ከሰባ እስከ መቶ ቶን አፈር ማጠብ ይችላል። ይህም በቀን አምስት መቶ ሰው ማጠብ የሚችለውን አፈር የሚያጥብ ነው። በኤሌክትሪክ ወይም በጀኔሬተር መሥራት ይችላል።
የደለል ወርቅ የሚገኘው አብዛኛውን ጊዜ ወንዝ አካባቢ በመሆኑ ማሽኑ ወንዝ ዳር ተተክሎ በተገጠመለት ፖምፕ ውሃ እየሳበ ያጥባል። ምንም ዓይነት ኬሚካል ስለማይጠቀም ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር የሚያሳድረው ተጽእኖ የለም። አራተኛው ማሽን እስከ 200ሺ ዶላር ግምት ያለው ነው።
እነ ቢቂላ እስከ አሁን ድረስ ለሠሯቸው ማሺኖች የባለቤትነት እውቅና (ፓተንነት ራይት) ለማግኘት እንቅስቃሴ አለመጀመራቸውን ይናገራሉ። ለዚህ ዋና ምክንያታቸው የጊዜ እጥረት ነው። የሠሩትን ሥራ በየባዛሩና በየተቋሙ እያስተዋወቁ እውቅና ለማግኘት ከመሯሯጥ ይልቅ ቅድሚያ መስጠት የፈለጉት ለደንበኞቻቸው ፍላጎት መልስ መስጠት ነው። በርከት ያሉ ማሽኖችን በመሥራት ከውጭ የሚገባውን ማሽን መተካትና የብዙዎችን ጥያቄ መመለስ ጊዜ የሚሠጠው ጉዳይ አይደለም ይላሉ።
የምርቶቻቸውን አቅምና ቴክኖሎጂ በማሳደግ የአገር ውስጥ ፍላጎትን አሟልተው ወደ ሌሎች አፍሪካ አገራት የማሰራጨት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል። በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ የወርቅ አፈርን ለማጠብ የሚያስችሉ ማሽኖችን የሚያመርት አንድ ካምፓኒ የመፍጠር ህልም አላቸው። ስለሆነም ሁልጊዜ ራሳቸውን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተዋወቅና በመሥራት አቅማቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋል።
በመጀመሪያው ሥራቸው ኪሳራ እንጂ ጥቅም እንዳላገኙ የተናገረው ቢቂላ ከሦስተኛ እና አራተኛ ሥራቸው ግን ጠቀም ያለ ትርፍ አግኝተው ለሥራው የሚስፈልጓቸውን መበየጃ ማሽኖችና የተለያዩ ቁሳቁሶች በመግዛት እራሳቸውን እንዳጠናከሩበት ይገልጻል። የማሽኑ ፈላጊዎች ቁጥር እየበዛ መጥቷል ያለው ቢቂላ ከሰሞኑ ከጋምቤላና ጉጂ አካባቢ የመጡ ወርቅ አምራች ማህበራት ማሽኑን ለማሠራት አነጋግረውናል ብሏል። የሚድሮክ ካምፓኒ ሠራተኞች ነን ያሉ ሰዎችም ደውለውላቸው ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንደተሰጣቸውና ከውጭ እያስመጡ የሚጠቀሙትን ማሽን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸውልናል ብሏል።
ይሁንና የብረት ዋጋ መጨመርን ተከትሎ ማሽኑን ሠርቶ ለማጠናቀቅ የሚፈጀው ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ በሥራቸው ላይ እንቅፋት መሆኑን ተናግሯል።
ጓደኛሞቹ የፈጠራ ሰዎች የድንጋይ ከሰል ለማምረት የሚያስችሉ ማሽኖችንም የመሥራት ፍላጎት አላቸው። በአገር ውስጥ እየተመረተ ያለው የድንጋይ ከሰል ስለማይታጠብ ከውጭ ከሚመጣው ምርት ጋር እየተቀላቀለ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎችና ለአንዳንድ የሴራሚክ ፋብሪካዎች ኃይል የመስጠት አገልግሎት እንዳለው የተናገረው ቢቂላ በቀጣይ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽን በመሥራት ከውጭ በከፍተኛ ወጪ የሚገባውን ምርት ለማስቀረት እቅድ እንዳላቸው ገልጿል። አገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ሲመረት ደቃቁን ክፍል አጥቦ የሚያስወግድ ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ የድንጋይ ከሰል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ለጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸውን ከባለሙያዎች ተገልጾልናል የሚለው ቢቂላ ደቃቁን ክፍል አጥቦ ማስወገድ የሚያስችል ማሽን ለመሥራት መዘጋጀታቸውንም ይናገራል።
የድንጋይ ከሰል ማሽን ከውጭ ለማስገባት እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ጠቅሶ አንድ ባለሀብት ለጊዜው ከውጭ የማስገባት ፍላጎታቸውን ገትተው እነርሱ ለመሥራት ያሰቡትን ማሽን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ተናግሯል።
ቢቂላ ሥራቸውን እያስፋፉ ሲሄዱ በዚያው ልክ ሰፊ ቦታና ተጨማሪ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው፤ አሁን ተከራይተው ለሚሠሩበት ሙሉ ግቢ በወር አርባ ሺህ ብር እየከፈሉ መሆናቸውን የሚናገረው ቢቂላ የሚመለከተው አካል የቦታ ድጋፍ በማድረግ በሥራና በሥራ ዕድል ፈጠራው ዘርፍ የሚያደርጉትን ጥረት ቢያግዛቸው የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑ ይገልፃል።
መቁረጫ፣ ማጠፊያና መጠቅለያ ማሸኖች ስለሌሏቸው ሌላ ቦታ እየሄዱ በክፍያ እንደሚያሠሩ ተናግሯል። ብድር ቢመቻችላቸው እነዚህን ማሽኖች በእጃቸው በማድረግ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠርና የእውቀት ሽግግር ማድረግ እንደሚችሉም ቢቂላ ይናገራል።
ማሽን ሲሠራም ይሁን ተተክሎ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የሰለጠኑ ሙያተኞች ያስፈልጉታል የሚለው ቢቂላ ማሽኑ ላይ ለሚሠሩትም ይሁን ሲበላሽ ለሚጠግኑት ሙያተኞች ስልጠና በመስጠት በሥራው ሰንሰለት ውስጥ ለሚያልፉ በርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል ብሏል።
እኛም እንዲህ ዓይነቱ ፈጠራ ቢበረታታ በቴክኖሎጂ እውቀት የበለጸገ ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ከማፋጠን አኳያ ጉልህ ድርሻ የሚኖረው መሆኑን በመመስከር አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር ቢደረግላቸው ተገቢ ነው እንላለን። ሌሎች ወጣቶችም የቢቂላ ዮሐንስን እና አባስ ሲራጅ አርአያነት ይከተሉ ዘንድም አደራ እንላለን። ሰላም!!!
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2014 ዓ.ም