ደግነት እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች በማድረግ መርካት፣ ሕይወትን ለማሸነፍ መፍጨርጨር፣ ይነጋል ላሉት ቀን ጨለማው እስኪገፍ የኑሮ ጎህ እስኪቀድ ድረስ ለማንጋት መሯሯጥ መለያው ነው።
በዚያ ላይ ወጣት ነው፤ ሮጦ በማምለጫ ነግዶ በማትረፍያ ለጋ እድሜው ላይ ያለ፤ ነስረዲን ጀማል መጠርያ ስሙ ነው። እትብቱ የተቀበረው በስልጤ ዞን ሌራ አካባቢ በአያቱ ቤት ነው።
ሕይወት የነገርና የክፋት ድሪንቶዋን ብትደራርትበትም፣ አንዴ ሳቅ እያለች አብዛኛውን ጊዜዋን ገለማምጣ የፈገግታ ፊቷን ብትነሳውም ከገፋችው ትላንት ከበረታበት ማታ በላይ በመጠንከር ዛሬን እያየ ይገኛል።
ፈገግታ ከፊቱ ጠፍቶ የማያውቀው ወጣት ነስረዲን፤ አሁን በሚሰራው ሥራ ውስጥ ከመሰማራቱ በፊት ብዙ ክፉ ቀናት ነበሩ። ለብቻው አዝኖና ተክዞ ያሳለፋቸው እልፍ መአልትም እንዲሁ አሉ።
በዘመድ መገፋትና ሰው በማጣት ውስጥ ሆኖ የብቸኝነት ጊዜን በብዛት አሳልፏል። ይህ ደግሞ በጦር ጭምር በተደጋጋሚ እንዲወጋ አድርጎታል። ለመኖር ያልገባበት ጉድጓድ ያልወጣው ተራራ የለም፤ አንድና ብቸኛ ነፍሱን በሕይወት ለማኖር ብዙ ዋጋ ከፍሎ በብዙ መገፋት ውስጥ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል።
በማይቆጠሩ የእምባ ቀናት ውስጥ አልፎም በሕይወቱ ውስጥ ብዙ አይነት ነገር ተመላልሷል፤ የሕይወትን ሁሉንም የሚባል መልኮቿን አይቷል፤ ማንም ሰው ስለ ሕይወት ሊናገር ከሚችለው በላይ መናገር በሚያስደፍረው መልኩ ላይም ይገኛል።
ለመኖር መተናነስን፣ ያልፋል በሚባል እንጉርጉሮ ክፉ ቀንን በፊት ፈገግታ ረትቷል። የገፉትን ክፉዎች በፍቅር ማሸነፍ የቻለም ነው። የጎደለውን ለመሙላት በመሯሯጥ የሕይወቱን ብዙ ወራት ያሳለፈባቸው መክሊቶችም ባለቤት ነው።
አራት ኪሎ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መዝናኛ ክበብ በር ላይ ተቀምጦ ላየው ብዙ ፈተናን ተጋፍጦ ያደገና የኖረ አይመስልም። ነገር ግን እርሱ ሕይወቱን የሚገፋው በእጆቹ ጥበብ ጫማዎችን በማሳመር ወይም ብዙዎች በሚያውቁት ስያሜ ሊስትሮ በመስራት ነው።
በእጆቹ ለብዙ ሰዎች ጫማ ውበት ሰጥቷል። ኑሮ በአዲስ አበባ በ2001 ዓ.ም ለነስረዲን ሕይወቱ ሌላ መስመር የያዘበት ዓመት ነውና ከልቡ የሚጠፋ ጊዜ አይደለም። ምክንያቱም ይሄ ዓመት ከገራገሮቹ እንዲሁም ከሥራ ወዳዶቹ መኖሪያ ነስረዲንም እትብቱን ካስቀበረበት ከስልጤ ዞን ሌራ አካባቢ ከአያቱ ቀዬ ወጥቶ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የገባበት ጊዜ ነበር። እሱ ከኖረባት ከጠባቧ ሌራ አካባቢ አንፃር ሲታይ አዲስ አበባ ለነስረዲን በዋና የማታልቅ ትልቅና ሰፊ ውቂያኖስ ሆነችበት።
ወጪ ሂያጁ፣ ሯጭ ተራማጁ፣ ቋሚ ተቀማጩ፣ በልፋቱ አዳሪው፣ ኪስ አውላቂው፣ አማኝ ኢ-አማኙ፣ ደጋሽ ቀዳሹ ሁሉም በሚተራመስባት ትልቋ ከተማ ውስጥ ከትሟልና ብዙ ነገር ተመሰቃቅሎበታል፤ የማያውቀው ነገርም ገጥሞታል።
እናም ነስረዲን በሰፊዋ አዲስ አበባ ውስጥ መንገዱን የሚመራው ኮምፓስ ይሻ ነበር። ነስረዲን አዲስ አበባ ሲገባ የአራተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ነበር፤ ሁሉን ትቶ ከሌማትሽ እንጀራ አብልተሸ ከማድጋሽ ውሃ አጠጪኝ ብሎ አምኗት የመጣው እንግዳ ተቀባይና ደጓ አዲስ አበባ ቤት ለእንግዳ ብላ አባብላ አልተቀበለችውም። የደስታ ምድር አድርገው የሳሉለት አዲስ አበባ ለነስረዲን ተቃራኒ ነበረች። እንደውም ከገነቷ ፍሬ ልታቀምሰው አልፈቀደችለትም። አዲስ አበባ ለምስኪኑ ነስረዲን እናትነቷን ትታ እንጀራ እናት ነበር የሆነችበት።
የመሸበት እንግዳዋን ተንጎዳጉዳ ያላትን አቅምሳ አልተቀበለችውም፤ ከፋችበት እንጂ። እሱ ግን የሕይወትን ክፉ ቡጢ በትዕግስት በበረታው ጫንቃው ተሸክሞ ታትሮ የማለፍን ድንቅ ጥበብ ገና በሕፃንነት ልቡ ነበር የተሸከመውም።
ይህ ደግሞ አዲስ አበባም ገብቶ እንዳይወድቅ አድርጎታል። አራት ኪሎ አካባቢ 12 ቀበሌ ጫት መሸጥን መተዳደሪያቸው ባደረጉ አጎቱ ቤት ለጥቂት ጊዜያት ጎኑን አሳርፏል። ሥራቸውን ባይፈልገውም አብሯቸው መስራት ግን ጀምሮ ነበር። ይህ ሲሆንም ጉልበቱን ሳይሰስትና ሳይለግም ልክ እንደ ልጅ ሆኖ በማገልገል ነው።
ነስረዲን በአጎቱ ቤት እያለ በጭንቅላቱ እየተመላለሰ ያስጨነቀውን ነገር መፍትሄ ለመስጠት ሲያመነታ ከርሟል። ይህም ጫት እየሸጡ ከመኖርና ከጫት ጋር ከሚነካኩት ነገሮች ራሱን ማራቅ ነው።
በአራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አካባቢ የሊስትሮ ዕቃዎችን ገዝቶ ጫማ መጥረግ የጀመረውም ይህንን ከመጥላቱ አንጻር እንደሆነ ይናገራል። የወጣትነት ጉልበቱን የለመዱት አጎቱ ግን በሥራ ወጥረው ያዙት፤ ሕይወቱ ውስጥም የሚሰራባቸውን እቃዎች እስከማሰረቅ የደረሰ ብዙ አይነት ድራማ ፈጠሩበት። ግን ያም ሆኖ ሥራውን ከመከወን አልተቆጠበም። በዚህ የተናደዱት አጎትም ቤታቸው ተመልሶ መምጣት እንደማይችል ነገሩት።
ከዚያ በኋላ የእርሳቸው በር ለነስረዲን ዝግ መሆኑን አስረድተው ከቤታቸው አባረሩት። እርሱ ግን ለጊዜው በአጎቱ ድርጊት ሳይጨናነቅ የጫማ ጠራጊነትን ሥራውን ቀጠለ። ከአጎቱ ቤት ሲባረር ከጫትና በዙሪያው ካሉ መጥፎ ነገሮች መራቁን አስተዋለ እንጂ የት አርፋለሁ፣ እንዴት እሆናለሁ የሚለውን ሳያገናዝብ ነበር።
በዚህም በሊስትሮ አቅሙ ለማረፍያ የምትሆነውን ደሳሳ ጎጆ እንኳን ለመከራየት አልቻለም። ለሰው አዛኙ ጥሩና መልካሙ ነስረዲን በረንዳ ከማደር የሚሻል ነገር በማጣቱ አጎቱን ከነ ክፉ ትዝታቸው ከሕይወቱ አስወጥቶ ሕይወቱን በተለየ መስመር ላይ አስምሮ ጎዳና ተዳዳሪ በመሆን ጎዞውን ቀጠለ። ጎዳና ለነስረዲን ቤቱ፣ ራቱ፣ አልጋው ፣ መጠለያው፣ ወዳጁ ሆነችለት። እዛው በጎዳና እየኖረ መልካም አሳቢ ጥሩ ሰዎችን ተጎዳኘ።
በትህትናው እንዲሁም ፈገግታ በማይለየው ፊቱ በሥራ አካባቢው ያለ ብቻ ሳይሆን ባላፊ አግዳሚው ዘንድ ተወዳጅ ሆነም። የገዛ ስጋው በሆኑት አጎቱ ቢገፋም የአካባቢው ሰዎች ይደግፉት ገቡ። ጫማ በማሳመር የእለት ቁርሱን የቀን ኪሱን እየሞላ ኑሮውን ቀጠለ።
መልካም ሰዎችን ጓደኛ አድርጎ ሰጥቶታልና በረንዳ ላይ እያደረ ትምህርቱን በአፄ ናኦድ ትምህርት ቤት ከአንደኛ ክፍል እስከ አራተኛ ክፍል ተማረ። እየሩሳሌም አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ደግሞ እስከ ሰባተኛ ክፍል ተከታተለ። አሁንም በዚያው ትምህርቱን ቀጥሏል።
ነስረዲን ከጫማ መጥረግ ቀጥሎ ሕይወቱን የገፋው ወዳጆቹ ባዘጋጁለት አነስተኛ የላሜራ መደርደሪያ ጋዜጣ በመሸጥ ነው። ዛሬ ላይ ነስረዲን ጫማ መጥረጉን ትቶ ጋዜጣ እየገዛ እና ወረቀት እየሰበሰበ ከጓደኛው ጋር እየተጫረተ በመሸጥ ጫማ ከሚጠርግበት ዘመን የተሻለ ኑሮ ይኖራል። የነስረዲን ዛሬ ዛሬ ላይ ያጎነበሰው የነስረዲን አንገት ቀና ለማለት ቀን እየወጣለት ነው።
እሱ ሊስትሮ በሚሰራበት ወቅት አንድ ነገር ቢጎድለው የሚሟላለት እንዳልነበረው አስታውሶ ዛሬ የሱ ቀን ሲቀና ደግሞ ሥራ አጥ የሆኑ ልጆችን በአቅሙ ለመደገፍ የተቻለውን ለማድረግ መሥራት ጀመረ።
የሕይወትን አቀበት ቁልቁለት ለብቻው መጓዝን የሚያውቀው ነስረዲን ቢያንስ እሱ እየቻለ ሌሎች ሰዎች እንዲቸገሩ አይፈልግም። ስለዚህም መልካም ማድረግን አስቦ ብቻ ቁጭ አላለም፤ ለመነሻነት ኑሯቸውን በበረንዳ ላደረጉና የሱን ትናንት ዛሬ ላይ ለሚኖሩ ለአስር ሰዎች የሊስትሮ እቃዎች ማለትም፤ ቡርሽ ቀለምና መቀመጫዎች እንዲሁም ጀብሎ መስራት ፍላጎት ላላቸው ደግሞ እቃ ማስቀመጫና የሚሸጡትን እቃ ለመግዛት የሚረዳቸውን ትንሽ ብትሆንም የአቅሙን ብር ሰጥቷቸዋል።
ወጣት ነስረዲን ሌላም የተቀደሰ ሃሳብ ይዞም ብቅ ብሏል። በቀን ቢያንስ ለአንድ ሰው የአንድ ጊዜ ምግብ ይችላል። ‹‹እኔ ዛሬ በቀን ሶስት ጊዜ እየበላሁ ነው፤ ይሄን ማድረግ የማይችሉ ግን ብዙ ሰዎች አሉ፤ ካለኝ እጋብዛቸዋለሁ የሌለኝ ቀን ደግሞ የኔን ምግብ አጋራቸዋለሁ›› ሲልም የየእለት እንቅስቃሴውንና የቸርነት ተግባሩ ነግሮናል።
የምስጋና ችሮታ እንደ መከፋት እንደ መገፋቱ ቢሆንና በሕይወቱ ያላሰባቸው ጥሩዎች ከቁብ ያልቆጠራቸው መልካሞች ባይኖሩ ኖሮ ዛሬ ከጎዳናው ብርድ፤ ከገፊዎች ክፋት በሕይወትም መቆየት እንደማይችልም አውግቶናል። እናም ወጣቱ ነስረዲን ሕይወት ፈገግታዋን ባላሳየችው ወቅት ከጎኑ ለነበሩ፤ በቀን ወረት ላልተያዙ፤ ከከፋበት ቀን ጋር አብረው ላልጨለሙበት፣ መልካም አሳቢ ደግ ሰዎች በሙሉ ምስጋናውን ለግሷል።
አብረውት የሊስትሮ ስራ ሲሰሩ ለነበሩ ደግ አሳቢዎች የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሰራተኞችና አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞችና አመራሮች፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላትም ምስጋናው ላቅ ያለ ነው። ምክንያቱም ትናንቱን አብርተውለታል፤ ዛሬውን ገንብተውለታል።
የነስረዲን መልእክት ወጣት ነስረዲን አሁንም የሕይወት ጉዞው ጅማሬ ላይ ቢሆንም፣ ብዙ አይነት የድልና የማሸነፍ ቀናቶችን እንደሚያሳልፍ ያምናል። ከትንሿ እድሜው የቀሰማትን ልምድ ሌሎች ሰዎችም ቢካፈሉት ይመኛልም።
ይህም ነገ ይነጋል የሚለው ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ መልእክቱን አስተላልፏል። ማንኛውም የሕይወት ትግል ላይ ያለ ሰው ከምንም በፊት ጠንክሮ በመታገልና ተስፋ ባለ መቁረጥ መንፈስ ሊመላለስ እንደሚገባው ይናገራል። በተለይም ወጣቶች የመስሪያና የማመስገኛ እድሜያቸውን ሊጠቀሙበት እንደሚገባቸውም ገልጿል። ማንኛውም ሰው ለነስረዲን ከልቡ ኖሯል የሚባለው የራሱን ብቻ ሕይወት ለመቀየር መፍጨርጨር ብቻ ሳይሆን አብሮ ከመብላት በተጨማሪ ትንሽም ብትሆን ያለችውን ነገር ለሰዎች በማጋራትና ተረዳድቶ በመኖር ሲያደርግ ብቻ ነው።
ጠንክረው መስራትንም ብቻ ሳይሆን ጥቂት ናት ሳይሉና ሳይሰስቱ ለሌሎች መስጠትን ተችረዋልና የነስረዲን እጆች ከብዙ ሰው እጆች ይለያሉ። ወጣት ነስረዲን መልካም ለመሆን የሚያስፈልገው ጥሩ ህሊና እንጂ የኪስ በገንዘብ መሞላት እንዳልሆነ ይናገራል። ባለን መጠን የመቻላችንን ልክ ለሌሎች ልናጋራ ይገባል ሲልም ይመክራል።
ሁሉም ሰው የተራበን ማብላት፣ ለተቸገሩ መድረስን፤ የሰዎችን ችግር እንደ ራስ ማሰብን በተግባር ኖሮ ጣዕሙን ሊያውቅ እንደሚገባ የተናገረው ወጣቱ፤ በእርሱ እሳቤ ሰዎችን የመርዳት አቅምና እድሉ ኖሯቸው ሰውን ያልረዱ ሰዎች ለሰው በማድረግ ውስጥ የሚገኘውን ደስታ ማግኘት አይችሉም ይላል።
የመስራት እድል ኖሯቸው ዝቅ ብለው መስራት ለማያስቡ ሰዎችም ወጣት ነስረዲን መልእክት አለው፤ መጀመሪያ ዝቅ ብሎ መስራትና ሥራ መፈለግ የሕይወትን ክፉ ቀን ማየትና ችግሮች በምን መልኩ እንደሚፈጠሩና መፍትሄዎቹ ምን መምሰል እንዳለባቸው መረዳት ነው። የመስራት ባህልን ማዳበርም ነው።
ስለሆነም ሁሉም ሰው ዝቅ የማለትን ጥቅም መረዳት እንዳለበት ያስገነዝባል። ብዙ ሰዎች እውቅና ካላቸው የትምህርት ተቋማት ወረቀት ይይዙና በተማሩበት ሥራ እስከሚያገኙ ቁጭ ሲሉ ሲመለከት በልቡ ይታዘባቸዋል። ምክንያቱም የጊዜንና የመስራትን ጥቅም ከእርሱ በላይ የሚረዳው የለም። በመሥራት ውስጥ ያለውን ጥቅምና እርካታም ጠንቅቆ ያውቀዋል።
በዚህም ይህንን የሚያደርጉ ሰዎች አሁኑኑ መንቃት አለባቸው ይላል። በአጠቃላይ ወጣት ነስረዲን በመርዳት ውስጥ የምታልፍ ሕይወት ታብባለች፤ ሥራ የማትሰራ ጉልበትም ትደክማለች ብሎ የሚያምን ነው።
ስለዚህም ከሰው ጥገኝነት ለመውጣት መስራት ግድ ነው። በዚያ ላይ መልካም አሳቢነት ሲታከልበት ለጭንቅላት ነጻነት ፣ ለህሊና እረፍት ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለኑሮም ምቾትን መስጠት እንደሆነ ያስባል። ሰዎችም ይህንን ገንዘብ እንዲያደርጉ ይመክራል። ምክሩ ለሕይወታችን ስንቅ ይሁነን እያል ለዛሬ አበቃን። ሰላም!!
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 /2014