
ዩን ሲውክ ዬኦል አዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ።
የእስያ አህጉር አራተኛው ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን አስተናግዳለች።
በዚህ ምርጫ ላይ ሁለት እጩዎች ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩ ሲሆን የ61 ዓመቱ የፒፕል ፓወር ፓርቲ እጩ የሆኑት ዩን ሲውክ ዬኦል አዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
በጥብቅና ሥራ ይተዳደሩ የነበሩት ዩን የገዢው ፓርቲ እጩ የሆኑትን ሊ ጃኢ ሚዩንግን በጠባብ ውጤት አሸንፈዋል ሲል የደቡብ ኮሪያ ዜና አገልግሎት ዮናፕ ዘግቧል።
አዲስ የተመረጡት ፕሬዚዳንት ዩን በፈረንጆቹ 2017 በስልጣን ላይ የነበሩት ፓርክ ጆንግ ሄ በሙስና እንዲከሰሱ እና በፍርድ ቤት እንዲቀጡ ምርመራውን በመምራት ትልቁን ኃላፊነት መወጣታቸው በደቡብ ኮሪያውያን ዘንድ እንዲመረጡ አድርጓቸዋልም ተብሏል።
በምርጫው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት መራጮች መካከል 98 በመቶዎቹ ድምጽ የሰጡ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 48 ነጥብ 6 በመቶዎቹ ለዩን ሲውክ ዬኦልን መርጠዋል።
አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት በሁለት ወራት ውስጥ ዘጠኝ ጊዜ ሚሳኤል ያስወነጨፈችው ጎረቤት አገር ሰሜን ኮሪያ ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል እንደሚጠበቅበት የአገሪቱ ዜጎች ተስፋ አድርገዋል ተብሏል።
52 ሚሊዮን የህዝብ ብዛት ያላት ደቡብ ኮሪያ ኦሚክሮን በተሰኘው አዲስ ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ናት።
አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንትም በኮሮና ቫይረስ የተጎዳውን የአገሪቱ ኢኮኖሚን የሚያሻሽሉ እርምጃዎች እና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መቀነስና መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን መስራትም ይጠበቅባቸዋል፡፡
አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሙን ጃኢን ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉ ሲሆን በወራት ውስጥ ለአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዩን ሲውክ ዬኦል ስልጣን እንደሚያስረክቡ ይጠበቃል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2014