አብዛኞቻችን ወጣቶች ተምረን እራሳችንን እስከምንችል ድረስ እያንዳንዱ መሠረታዊ ወጪያችን በወላጆቻችን ይሸፈናል።ከምግብ እስከ አልባሳት ከትምህርት ቤት እስከ ሕክምና ያለው ወጪያችን በሙሉ የወላጆቻችን ዕዳ ነው።
አንዳንድ ብልሆች ግን ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በምትኖራቸው ትርፍ ጊዜ የተለያዩ ሥራዎችን እየከወኑ የራሳቸውን ወጪ በመሸፈን ወላጆቻቸውን ያግዛሉ። አለፍ ሲልም ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለወላጆቻቸውም ይተርፋሉ። በከተሞች አካባቢ ግማሽ ቀን ጫማ በማሳመር እየሠሩ ወይም ታክሲ ላይ ‹‹እየወየሉ›› የሚማሩ በርካቶች ናቸው። በገጠር አካባቢ መስኖ እያለሙ፣ ዶሮ እያረቡ፣ የሸክላ፣ የስንደዶ፣ የእንጨት፣ የበርኖስ፣ የጭራ ወዘተ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን እያመረቱ በመሸጥ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተምሩ በርካቶች ናቸው።
የዛሬዎቹ የወጣቶች አምድ እንግዶቻችን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለምዶ አጠራር ‹‹ምኒልክ መስኮት›› ተብሎ በሚጠራ ቦታ የአካባቢያቸውን ፀጋ ተጠቅመው ቀዝቃዛማውን የአየር ንብረት መቋቋም የሚያስችሉ እንደ ኮፊያ፣ ስካርቭ (የአንገት ልብስ)፣ ቦርሳ፣ ፎጣ ወዘተ እየሠሩ የሚሸጡ ናቸው። በዚህም የራሳቸውን ወጪ ሸፍነው መኖር ችለዋል፤ ከዚያ የሚተርፋቸውንም ባንክ መቆጠብ ጀምረዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣው የኑሮ ውድነት ወላጆች የሚይዙትን የሚጨብጡትን ባሳጣበት በዚህ ወቅት ራሳቸውን ችለው የሚማሩ ወጣቶች ለቤተሰቦቻቸው የሚሰጡት እፎይታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። እኛም ለሥራ በወጣንበት አጋጣሚ የተመለከትነው የወጣቶቹ የሥራ እንቅስቃሴ አስደምሞን ተሞክሯቸውን ለሌሎች ማሳየት ስላስፈለገን የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርጋቸው ወደድን።
ደረሰ ለማ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምኒልክ መስኮት በሚባለው ቦታ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን እየሠሩ ሲሸጡ ካገኘናቸው ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። ደረሰ ሙያውን ከቤተሰቦቹና ከታላላቆቹ እንደተማረው ይገልጻል። ልጅ እያለ ሰዎች የሚሠሩትን ሥራ በትኩረት የመመልክት ልምድ ነበረው። ቀስ በቀስ ሙያውን ከቀሰመ በኋላ እርሱም እንደሌሎቹ እየሠራ በመሸጥ ገቢ ማግኘት ይጀምራል። የራሱን ገቢ ማግኘት ከጀመረ ወዲህ የደብተር የእስክሪፕቶ እና ሌሎች ወጪዎቹንም ጭምር እየሸፈነ መማር ይጀምራል።
ደረሰ አሁን የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እራሱን በራሱ እየረዳ እዚያው ተወልዶ ባደገበት አካባቢ አጠናቆ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመማር ወደ ደብረ ሲና ካቀና አራት ዓመታትን አስቆጥሯል።
ደብረ ሲና ከትውልድ መንደሩ 25 ኪሎ ሜትር የምትርቅ በመሆኑ በየቀኑ እየተመላለሱ መማር ስለማይችል እዚያው ቤት ተከራይቶ መቀመጥ ግዴታ ሆኖበታል።
20 ከሚሆኑ ባልደረባዎቹ ጋር ተደራጅቶ ይሠራ ስለነበር ለትምህርት ወደ ደብረ ሲና በሄደ ጊዜ ጓደኞቹ የሥራ ጫና እንዳይበዛበት ይተባበሩት እንደነበር ይገልጻል። ይሁንና የሚሠራውን ቁሳቁስ እዚያው ይዞ በመሄድ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በሚኖረው ትርፍ ጊዜ ብቻ እየሠራ የድርሻውን ያበረክታል። በየሳምንቱ ዓርብ ማታ ወደ ትውልድ መንደሩ እየሄደ ቅዳሜና እሁድን በመሥራት ከሰኞ እስከ ዓርብ የእርሱን ሥራ የሚሸፍኑለትን ጓደኞቹን ያግዛቸዋል።
በዚህ መልክ እየሠራ የትራንስፖርት የምግብና የቤት ኪራይ ወጪውን ይሸፍናል። በየወሩ ለቤት ኪራይ 400 ብር ይከፍላል። የትራንስፖርትና የሚቋጥረውን ስንቅ ጨምሮ እስከ 600 ብር ያወጣል። አንዳንድ ጊዜ ከትምህርት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚያወጣቸውን ወጪዎች በሙሉ ሸፍኖ በአጠቃላይ በወር ከ1000 ብር በላይ እያወጣ ይማራል። ይህን ሁሉ ወጪውን የሚሸፍነው ከጓደኞቹ ጋር ሆነው የሚሠሯቸውን የዕደ ጥበብ ውጤቶች እየሸጡ በሚያገኘው ገቢ ነው።
ደረሰ በየሳምንቱ ዓርብ ወደ ትውልድ አካባቢው በመሄድ ማህበሩ በትምህርት ምክንያት የሰጠውን ጊዜ ተግቶ በመሥራት ያካክሳል። የትውልድ መንደሩ ከመሸጫው ስፍራ እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ቢርቅም ማልዶ እየተነሳ ቦታው ላይ በመድረስ የሚቀድመው የለም። ገበያ ላይ ሆኖም እጆቹ ሥራ አይፈቱም የሚሸጣቸውን ዕቃዎች እየሠራ ይተካል። ቀኑን ሙሉ እየሸጠም እየሠራም አምሽቶ ማታ ወደ ቤቱ ይገባል።
ደረሰ እንደሚለው ‹‹የመሸጫ ቦታው የተመረጠበት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። ቦታው ‹‹የምኒልክ መስኮት›› ወይም ‹‹ገማሳ ገደል›› ይባላል። አጼ ምኒልክ አንኮበር ቤተመንግሥታቸው በነበሩ ጊዜ አያታቸው ንጉሥ ሳህለሥላሴ ሰላ ድንጋይ ነበሩ። ወደ አያታቸው ቤት ሲመጡ አካባቢውን የሚቆጣጠሩትና ዙሪያ ገባውን የሚቃኙት በዚህ ከፍተኛ ቦታ ላይ ሆነው ስለነበር ስፍራው ‹‹የምኒልክ መስኮት›› የሚል ስያሜን አገኘ። ከዚህ ታሪክ አንጻር ይህ ቦታ በአገር ውስጥና በውጭ ዜጎች የመጎብኘት ዕድል አለው።
በተጨማሪም ጣሊያኖች ዳግም ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ወደ መሀል ሲስፋፉ ከነበረበት ቦታ አንዱ ይህ ስፍራ ነው። ይህን ከፍተኛ ቦታ በመቆጣጠር በወጊያ መሃል የሚያገኟቸውን ቁስለኞችና አቅመ ደካሞች ከዚህ ገደል ላይ እየወረወሯቸው ይገድሏቸው እንደነበር ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። በዚህ የተነሳ ቦታው ስለሚጎበኝ እኛም ከበርኖስ እና ከበግ ጸጉር የተሠሩና የአካባቢውን ባህል የሚገልጹ አልባሳትን እየሠራን እንሸጣለን። በዚህ ቦታ ከእኛ በፊት የነበሩ በርካታ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን እየሠሩ እራሳቸውን አስተምረው ለቁም ነገር ደርሰዋል። እኛም የእነርሱን ፈለግ ተከትልን እየሠራን ነው›› ይላል ደረሰ።
ከሁለት ዓመት ወዲህ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የቱሪስቶች ፍሰት ስለተቋረጠ ገቢያቸው በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሎ እንደነበር ይገልጻል። በአካባቢው የተከሰተው የጸጥታ ችግርም ሌላ ተግዳሮት ሆኖባቸው ከርሟል። ሰርቶ ለመሸጥ ይቅርና ተረጋግቶ ለመኖር እንኳ ተቸግረው እንደነበር ይናገራል። በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ አንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ሥራቸው ተስተጓጉሏል። አሁን ግን እንደበፊቱ ባይሆንም የተሻለ የገበያ እንቅስቃሴ እንዳላቸው ነግሮናል። ለጊዜው የውጭ አገር ቱሪስቶች ፍሰት ወደ ነበረበት ባይመለስም ውስን ምርቶቻቸውን ለአገሬው ሰው የመሸጥ ዕድል በማግኘታቸው ሥራቸውን በትኩረት እየሠሩ ናቸው።
ደረሰ ደንበኞቹን ለመያዝና ምርቱን ለማስተዋወቅ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ምርቱን መግዛት ፈልገው እንደአጋጣሚ ገንዘብ ሳይዙ የመጡ ደንበኞች ሲገጥሙት በባንክ እንዲልኩለት በአመኔታ ይሰጣቸዋል። በተለያዩ ጊዜያት እንዲህ ዓይነት ክስተት ገጥሞት ሰጥቷቸው ልከውለታል።
ቀደም ሲል ነጋዴዎች ከአዲስ አበባ እየመጡ በርከት ያለ ምርት ይገዘዋቸው እንደነበር የሚገልጸው ደረሰ አሁን አሁን ደግሞ እዚህ ድረስ መምጣት ሳያስፈልጋቸው በኢሞ እና በቴሌግራም ምርቶቹን እያዩ የሚፈልጉትን ዓይነትና መጠን በመግለጽ ግብይት እንደሚፈጽሙ ተናግሯል።
እነርሱ ምርቱን እንደላኩላቸው ሸማቾቹም ገንዘቡን በባንክ ይልኩላቸዋል። ይህም ዘመኑ ወደሚፈልገው የግብይት ሥርዓት /ቴሌብር/ ለመግባት መንደርደሪያ እየሆናቸው ነው። ምኒልክ መስኮት የሚባል የማህበራዊ ገጽ በመክፈት ምርታቸውንና የአካባቢውን ታሪካዊ ዳራ የሚያስተዋውቁበት የቴሌግራም ግሩፕ እንዳላቸውና ይህም አስፈላጊውን መረጃ ለመለዋወጥ እንደረዳቸው ደረሰ ገልጾልናል። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ባዛሮች ላይ እየተገኙ ምርቶቻቸውን የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራሉ።
ቦታው በቱሪስቶች እንዲታወቅ ከማድረግ አንጻር የእነርሱ የዕደ ጥበብ ውጤቶች አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይናገራል። ቱሪስቶች ዕቃ ለመግዛት በሚቆሙ ሰዓት ስለቦታው ታሪካዊ ዳራ የሚያስረዱ የአካባቢው አስጎብኚዎችም ተፈጥረዋል ይላል። ቦታውን አጥሮ መንክባከብና የበለጠ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ከማድረግ አንጻር የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት ጠቁሟል። ቦታው ለቱሪስት መዳረሻ ሆኖ ቢለማና ማረፊያ ሪዞርቶች ቢኖሩት ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ነው ይላል።
ሌላው በተመሳሳይ ሥራ ላይ ሆኖ ያገኘነው ወጣት ኃይልዬ ላቀው ይባላል። እርሱም እንደ ደረሰ ከልጅነቱ ጀምሮ ሙያውን ከአካባቢው ሰዎች እየተማረ ማደጉን ይናገራል። አዘውትሮ ይሠራ የነበረው ኮፊያ ነበር። አሁን ግን ቦርሳ፣ ዘንቢል እና ሾፌሮች መቀመጫ ላይ የሚዘረጉት ሙቀት መከላከያ ምንጣፍ መሥራት እንደተለማመደ ይገልፃል። በየጊዜው ምርቶቻቸው የተሻለ ፈጠራ እየታከለባቸው የተሻለ ዋጋ እያወጡላቸው መሆኑን ነግሮናል።
በማህበር ተደራጅተው መሥራታቸውም የዕውቀትና የፈጠራ ሽግግር ለማድረግ እንደረዳቸው ገልጿል። የማህበሩ አባላት ሁልጊዜ አዳዲስ ሐሳቦችንና አሠራሮችን በማምጣት አቅማቸውን ለማሳደግ ይጥራሉ። ለምሳሌ ቦርሳ ለመሥራት የበቁት ባዛር ላይ ከጨርቅ የተሠራ የቦርሳ ምርት ከተመለከቱ በኋላ ነው። ከኢንተርኔት የሚያዩትን አዳዲስ ነገር ለመሥረት ሙከራ ያደርጋሉ።
ኃይልዬ እንደሚለው፤ ማህበራዊ ሚዲያውን መረጃዎችን ለመለዋወጥና አዳዲስ ዲዛይኖችን ለመመልከት ይጠቀሙበታል። በማህበር መደራጀታቸው በተለይም እንደ እርሱ ያሉና በትምህርት ምክንያት ከአካባቢው ርቀው ለሄዱ ተማሪዎች እገዛ እንዳደረገላቸው አጫውቶናል።ኃይልዬ ልክ እንደጓደኛው ደረሰ ሁሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደብረ-ሲና ተቀምጦ የሚማር ቢሆንም ባለው ትርፍ ጊዜ እየሠራ ማህበሩን ያግዛል።
ወጣቶቹ በተመሳሳይ ዕድሜና ደረጃ ስለሚገኙ ተግባብተው መሥራት የሚችሉ ናቸው። እራሳቸውን ከመርዳት አልፈው ለቤተሰቦቻቸውም የገንዘብ ዕገዛ ያደርጋሉ። በአካባቢው የሚገኘው አርሶ አደር የበጎችን ፀጉር እየሸለተ በመሸጥ ጥቅም እንዲያገኝ አድርገዋል።
እንደወጣቶቹ አባባል ከበጎች የሚገኘውን ፀጉር በዚህ መልክ ጥቅም ላይ ማዋል ባይቻል ምናልባትም የአካባቢን ገጽታ የሚያበላሽ ቆሻሻ ይሆን ነበር። ዓለም በቴክኖሎጂ እየታገዘ ከበግ ፀጉር ውድ አልባሳትን እያመረተ በመሸጥ የገቢ ምንጩን እንደሚያሳድግ የገለጸው ወጣቱ የእነርሱም ሥራ በቴክኖሎጂ ቢታገዝ ለአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል። ታዲያ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ የሚያደርጉ ከሆነ እነዚህ ወጣቶች ዛሬ በጥቂቱ የጀመሩትን ሥራ ነገ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግሩት ልብ ይሏል።
ኢያሱ መለሰ እና ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2014