ምዕራባውያን ድፍን አፍሪካን እንደቅርጫ ሥጋ ተከፋፍለው የተፈጥሮ ሃብቷን ሲመዘብሩ፣ ሕዝቦቿን እንደ እቃ ሲሸጡና ሲለውጡ ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋዕትነት ክብሯን አላስደፈረችም ነበር። ውቅያኖስ አቋርጦ ድንበር ተሻግሮ የገባውን የኢጣሊያን ወራሪ አባቶቻችን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ነጻነት ያረጋገጡት እዚህ ግባ የሚባል ወታደራዊ ትጥቅና የሰለጠነ ሠራዊት ሳይኖራቸው ነው። የመጣባቸውን ጠላት ለመመከት አንድ ልብ ሆነው ሆ ብለው በመነሳታቸው ለድል በቅተዋል። በዚህ አንድነታቸው ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀን የአውሮፓ ሠራዊት በማሸነፍ ዓለምን አስደምምዋል፤ ጥቁር ነጭን ማሸነፍ እንደሚችል በተግባር በማሳየት ለመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራት ሆነዋል። ነጮችንም አንገት አስደፍተዋል።
‹‹አንድነት ኃይል ነው›› እንዲሉ አባቶቻችንን ለድል ያበቃቸው ምስጢር አገር ወዳድነታቸውና አንድነታቸው ነው። ትናንት አንድ ላይ ቆመው ዋጋ ባይከፍሉ ኖሮ ዛሬ ነጻነታችንን አረጋግጠን የምንኖርባት ኢትዮጵያ ላትኖረን ትችል ይሆናል፤ ቋንቋችን፣ ማንነታችንና ባህላችንም ሊዋጥ ይችላል። ኢትዮጵያ በትውልዶች ቅብብል ሉዓላዊነቷን እያስከበረች እዚህ ደርሳለች። የአሁኑም ትውልድ የራሱን ታሪክ እየሠራ ኢትዮጵያን ከነሙሉ ከብሯ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ አደራውን እየተወጣ ነው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ 126ኛው የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው በዚህ ልዩ እትም የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማኅበር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ተከስተ አያሌውን እንግዳ አድርጓል።
ወጣቱ ትውልድ አባቶቹ በአብሮነት ያስመዘገቡትን ድል እንዴት ማስቀጠል እንዳለበትና እንዴት የራሱን ታሪክ ማስመዝገብ እንደሚገባው ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።
የዓድዋ ድል በዓል በአባቶቻችን አኩሪ ተጋድሎ የተገኘ ነው። ድሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል ነው። ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ሲመጡባቸው እሺ ብሎ ከመቀበል ይልቅ ሞትን የሚመርጡ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩበትና ጣፋጭ ድል ያስመዘገቡበት ነው። የአፍሪካ አገራት በሙሉ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር ወድቀው የባሪያ ፍንገላና የተፈጥሮ ሀብት ዝርፊያ ሲፈጸምባቸው በነበርበት በዚያ ወቅት ጀግኖች አባቶቻችን ወራሪውን የኢጣሊያ ሠራዊት አሸንፈው ነጻነታቸውን ያረጋገጡበት ትልቅ ድል ነው። ድሉ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ብርሃን የፈነጠቀ ነው።
ኢትዮጵያውያን የዚህ ድል ባለቤት እንዲሆኑ ያስቻላቸው ምንድን ነው? እንዴት ዘመናዊ መሣሪያ ከታጠቀና ከሰለጠነ የአውሮፓ ወታደር ጋር ገጥመው ሊያሸንፉ ቻሉ? ሌሎች የአፍሪካ አገራት እንዴት ይህንን ማድረግ ተስኗቸው በግዞት ኖሩ? የሚሉትን ጥያቄዎች ስንመለከት የተለያዩ መልሶችን ልናገኝ እንችላለን ይላል ወጣት ተከስተ። የመጀመሪያው ኢትዮጵያውያን በሉዓላዊነታቸው ሲመጡባቸው የማይወዱ መሆናቸው ነው ይላል። የውስጥ ጉዳያቸውን ተወት በማድረግ አንድነታቸውን አጠናክረው ጠላታቸውን የመመከት ልምድ ያላቸው ሕዝቦች በመሆናቸው ነው።
የዓድዋ ድል እንዲህ አይነት ስነልቦና ባላቸው ሕዝቦች ተጋድሎ የተገኘ ነው። ስለአገራቸው ክብርና ስለወገናቸው ሲሉ ብዙዎች ተሰውተው በደማቸው የጻፉት ደማቅ ታሪክ ነው። የዓድዋ ዘመን ትውልዶች ለመላው አፍሪካ የተረፈ ታሪክ ይሥሩ እንጂ በየዘመኑ ያሉ ኢትዮጵያውያን የየራሳቸውን ታሪክ የሠሩ ናቸው።
ከዓድዋ ድል በፊት ኢትዮጵያ በስልጣኔ ገናን ስም እንዲኖራት ያደረጉ በአክሱም፣ በላሊበላ፣ በፋሲለደስ፣ በጀጎል ግንብ ወዘተ አሻራቸውን ያስቀመጡ ትውልዶች ነበሩ። የዚያድባሬን ወረራ ለመቀልበስ በተደረገው ትግል ስለአገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት ሲሉ በርካቶች ተሰውተውና ቆስለው በደማቸው ጠብታ ኢትዮጵያን አስከብረዋታል። ኢትዮጵያውያን በአገር ጉዳይ አንድ የመሆናቸው ጉዳይ ሁልጊዜም አሸናፊ እንዲሆኑ ሲያደርጋቸው ተመልክተናል።
እያንዳንዱ ትውልድ በየጊዜው የራሱን ታሪክ እየጻፈ አልፏል የሚለው ተከስተ አሁን ያለውም ትውልድ የአገሩን ሉዓላዊነት በማስጠበቅም ሆነ የልማት ሥራዎችን በመሥራት አዳዲስ ታሪኮችን እያስመዘገበ ነው ይላል። የአባቶችን ታሪክ መዘከር እንደተጠበቀ ሆኖ እነርሱ ባጎናጸፉን ነጻነት ውስጥ ሆነን አዳዲስ ታሪክ በመሥራት ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ይላል።
በትውልድ ቅብብሎሽ ሁልጊዜም የአገርን ሉዓላዊነት መጠበቅም ሆነ አዳዲስ ታሪኮችን ማስመዝገብ ቀጣይነት ያለው እንደሆነ የተናገረው ተከስተ አሁን ያለው ትውልድም አንድነቱን ጠብቆ ታሪክ የማይረሳቸውን ድሎችን እያስመዘገበ ነው ብሏል።
በተለይም ዋናውን የአገር ጠላት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በተያዘው የመንግሥት አቅጣጫ ትውልዱ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ያደረገው ርብርብ አንድ ማሳያ ነው።
ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ የሚሳድሩትን ጫና በመቃወም በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ሲያካሂዱት የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ታሪክ የማይረሳው ነው። ታሪክ መሥራት ማለት ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ገድል መፈጸም ነው።
ወጣቱ ከዓድዋ ድል የሚማረው የጦርነትን አሸናፊነት ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም አስቸጋሪ ጉዳይ ተረዳድቶና ተባብሮ ድል ማድረግ እንደሚቻል ጭምር ነው። ያኔ አባቶቻችንን የመጣብንን ወራሪ ጠላት ተባብረው በመጣል አሸናፊ እንድንሆን አስችለውናል የሚለው ተከስተ የዛሬውም ትውልድ በሁሉም ዘርፍ አሸንፎ ለመገኘት አንድነቱን ማጠናከር እንደሚገባው ከዓድዋ ድል መማር አለበት ይላል። እያንዳንዱ ወጣት አቅሙን፣ የሥራ ልምዱንና እውቀቱን በማስተባበር አገሩን ከድህነት የሚያወጣበትን መንገድ ማሰብ ሲችልና ወደ ሥራ ገብቶ እራሱንም አገሩንም ሲለውጥ ታሪክ ሠራ ማለት ነው። በህዳሴ ግድቡ ላይ ያኖረውን አሻራውን በሌላም ላይ መድገም ይኖርበታል።
ጀግኖች አባቶቻችን የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ያስረከቡንን አገር ጠንክረን በመሥራት ከድህነት አውጥተን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው። ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ሕዝብ ብዛት ከስልሳ እስከ ሰባ በመቶ የሚገመተው ሕዝቧ ወጣት እንደሆነ አንዳንድ ጥናቶች ያመላክታሉ ያለው ተከስተ ይህ ትኩስ ኃይል ፊቱን ወደ ልማት ቢያዞር በአጭር ጊዜ አገሩን መለወጥ የሚያስችል አቅም አለው ብሏል።
ኢትዮጵያ ካላት የወጣት ኃይልና ተፈጥሮ ከለገሳት ጸጋ አንጻር ማደግ በሚገባት ደረጃ ላይ አልደረሰችም የሚለው ተከስተ ወጣቱ ጠንክሮ በመሥራት መጪው ትውልድ ከድህነት ባርነት ነጻ እንዲወጣ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግሯል።
አባቶቻችን ከቅኝ ግዛት ነጻ ባያወጡት የአሁን ትውልድ በራሱ አቅም ዓባይን በመገንባት ታሪክ አይሠራም ነበር። መጪው ጊዜ ከህዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጨት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ በርካታ የሥራ እድሎችን ለመጠቀም የሚያስችል እንደመሆኑ ወጣቱ ዓባይን በመገደብ ብቻ ሳይሆን ፈጣን እድገት በማስመዝገብ አዲስ ታሪክ የሚሠራበት እድል ተፈጥሯል ብሏል። በዓድዋ ጦርነት አባቶቻችንን ለድል ያበቃቸውን አገር ወዳድነት እና አንድነት ተጠቅመን ከድህነት መውጣት እንደምንችል ተናግሯል።
ኢትዮጵያ ረዥም እድሜና ቀደምት ስልጣኔ ያላት አገር ብትሆንም በሚመጥናት የእድገት ደረጃ ላይ አትገኝም ያለው ተከስተ ዛሬም ድረስ በበሬ የሚያርስ፣ እንጨትን ለማገዶነት የሚጠቀም፣ በኩራዝ የሚኖር፣ ማኅበረሰብ ያላት ነች። ሰፊ የእርሻ መሬት ይዛ በምግብ ራሷን መቻል አቅቷት ምርት ከውጭ የምታስገባ መሆኑ የሚስቆጭ ነው ይላል።
ኢትዮጵያን ማሻገር የሚቻለው ጦርነትን ድል በማድረግ ብቻ ሳይሆን አገርን የሚያኮራና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባርን ማከናወን ሲቻል ነው። በአገሩ ሉዓላዊነት ጉዳይ እንደ አባቶቹ ነፍሱን ለመስጠት የሚሰስት ወጣት እንደሌለ ታይቷል ያለው ተከስተ ወጣቱ በዚሁ ግለት ፊቱን ወደ ልማት ቢመልስና ኢትዮጵያን ከድህነት ቢያላቅቅ ሌላ ታሪክ ማስመዝገብ ይችላል ብሏል።
በቅርቡ አገራችን ተገዳ የገባችበት ጦርነት በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ቀውሶችን አስከትሏል ብሏል።
አገራቸውን ለማዳን ሆ ብለው የተነሱ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ፤ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ይዘው አገር ለማፍረስ ከተነሱ ጸረ ሰላም ኃይሎች ጎን የተሰለፉ ጥቂት ወጣቶችንም አይተናል። በዚህ ዘመን ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የተሻለ ግንዛቤ አለው የሚባለውና አደራ የተረከበው ወጣት አባቶቹ በደምና በአጥንታቸው አስከብረው ያስተላለፉለትን አገር በጥቂት ጥቅመኞች ተታሎ የጥፋት እጁን በእናት አገሩ ላይ ማሳረፉ የሚሳፍር ተግባር ነው ብሏል።
ዘመኑ የስልጣኔ ነው፤ ለስልጣኔ ቅርብ ነው የሚባለው ደግሞ ወጣቱ ማኅበረሰብ ነው፤ ከስልጣኔ መገለጫዎች አንዱ ችግሮችን በውይይት መፍታት ነው። ወጣቱ በውይይት በክርክርና በሀሳብ ልዕልና ችግሮችን መፍታት እየቻለ የሴረኞችን ከንቱ ሀሳብና ምኞት እየሰማ አላስፈላጊ መስዋዕትነት መክፈል የለበትም። በራሱ ወገንና ሕዝብ ላይ የጭካኔ እጁን የሚሰነዝርና የራሱን ሀብት የሚያወድም ወጣት ለስልጣኔ ቅርብ ነው የሚባለውን የዚህ ዘመን ትውልድ የማይወክል ነው።
ወጣትነታችንን ለመልካም ነገር የምናውልባቸው በርካታ ጉዳዮች እያሉን አባቶቻችን እንደዓድዋና ካራማራን በመሳሰሉት ጦርነቶች ደማችውን አፍስሰው ያስረከቡንን አገር የሌሎች ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን የምናፈርስ መሆን የለብንም። መሆን ካለብን እንደ ህዳሴው ግድብ ያሉ የልማት ሥራዎችን ደጋግመን በመሥራት እንደዓድዋ ድል አድራጊዎቹ አባቶቻችን ስማችንን የሚያስጠራ አሻራ ማስቀመጥ ነው።
አንዳንድ ነፍጥ ያነገቱ ተቃዋሚዎች ወጣቶችን እያታለሉና በጥቅም እየደለሉ አገራቸውን እንዲክዱና ለሞትና ለከፋ ችግር እንዲዳረጉ አድርገዋቸዋል። ከዚህ አንጻር አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከትግራይ እናቶች ጉያ እየነጠቀ በርካታ ወጣቶችን አስገድሏል። ይህ ታሪክ የማይረሳው ጥፋት ነው ይላል ተከስተ።
አባቶቻችን የዛሬ 126 ዓመት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እና የሰለጠነ ሠራዊት ሳይኖ ራቸው ከጣሊያን ወራሪ ጋር በዓድዋ ተራሮች ላይ የተዋደቁት ኢትዮጵያ ተደፈረች ብለው ነው። የዓድዋ ተራሮች አባቶቻችን ደማቸውን ያፈሰ ሱባቸው አጥንታቸውን የከሰ ከሱባቸው ታሪካዊ የድል አምባዎቻችን ናቸው። ዛሬ ጥቅማችን ተነካብን ብለው ያኮረፉ ቡድኖች ዓለም የሚያውቀውን የዓድዋን ድል ሳይቀር የእኛ እንጂ የሌላው ኢትዮጵያዊ አይደለም ሊሉ ይቃጣቸዋል።
ባለፉት የሕወሓት የበላይነት ዘመን ትውልዱ ስለዓድዋ ድልና ስለአባቶቻችን የጋራ ተጋድሎና አንድነት እምብዛም ስላልተነገረው፤ አንድነቱን አስጠብቆ ለመቀጠል ፈተና ውስጥ ገብቶ እንደነበር የሚታወስ ነው የሚለው ተከስተ ትውልዱ ስለአገሩ ሕዝቦች የቀደመ ፍቅር፣ ትብብርና አንድነት፤ ስለጋራ ታሪካቸውና ስላስመዘገቡት ውጤት እንዲያውቅ ከማድረግ ይልቅ ከፋፋይ አስተሳሰቦችን እንዲለማመድ ተደርጓል። ዛሬ እየታጨደ ያለውም በዚያን ወቅት የተዘራው መርዝ ነው። የዓድዋን ታሪክ የሚያወሱ የትምህርት ይዘቶች በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የመካተታቸው ነገር አናሳ ነበር። አብዛኛው ወጣት ዓለም የሚያውቀውን የዓድዋ ድል ታሪክ አያውቀውም።
ወጣቶች ራሳቸውን ከመጥፎ ድርጊት በማቀብ የአባቶቻቸውን ታሪክ መድገም ይጠበቅባቸዋል። ባለንበት ዘመን የተለያዩ ጥያቄዎች ያላቸው ወጣቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ጥያቄዎችን በመመካከርና በመወያየት የመፍታት ባህል ሊያዳብሩ ይገባል።
መንግሥት ሊያካሂደው ባሰበው አገራዊ ምክክርና ውይይት ውስጥ ወጣቶችም እርስ በእርስ የመነጋገርና የመተራረም መድረክ ሊፈጠርላቸው ይገባል። ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶች በአገራዊ ምክክሩ ላይ የመሳተፍ እድል ቢሰጣቸው ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት የጋራ መፍትሔ ሊያመጡ ይችላሉ። ወጣቱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብና አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ከዘመኑ ጋር መራመድ ይጠበቅበታል። የዓድዋ ድል በአብሮነት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያስተማረን በመሆኑ ወጣቱ የዓድዋን ድል በልማቱ ዘርፍም በመድገም የራሱ ታሪክ መሥራት ይጠበቅበታል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014