ይህ ጊዜ ሰው መሆን የተፈተነበት ወቅት እንደሆነ በብዙ መልኩ አይተናል። በተለይም በሰሜኑ ጦርነት እጅግ ዘግናኝና አስነዋሪ ተግባራት ወንድምና እህት በምንላቸው በራሳችን ዜጎች ሲፈጸምም ታዝበናል፤ ሆኖብን ያየነውንም ቤት ይቁጠረው።
በዚህ ደግሞ ብዙዎች የሥነልቦና እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ማንም ሳይነግረን እናውቀዋለን። የጦርቱ ጠባሳ ጥሎት የሄደው ጭንቀት በራሱ ሕመም በመሆኑ በመንፈስ ለመረጋጋት አያስችልም። እናም እንደ አገር ይህ ጊዜ መተካከሚያ መሆን ያለበት እንደሆነ እሙን ነው። በተለይም የሥነልቦና ባለሙያዎች ለዚህ ጊዜ እጅግ አስፈላጊና ቋሚ መድኃኒት ከታቢ መሆን ይኖርባቸዋል።
በአዕምሮ ጤና ችግር ምክንያት ብዙ ውስብስብ ችግሮች በአገር ላይ ተፈጥረው አይተናል፤ ወደፊትም የምናጣው ነገር ይኖረናል። ስለሆነም ቢያንስ የአሁኑን አክሞ ለወደፊቱ መዘጋጀት እንዲገባ ሐኪሙ ታማሚው ጋር ሊደርስ ይገባል።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ የሥነልቦና ባለሙያዎች የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛሉ። በዚህም 12 የሥነልቦናና የአካል ሕክምና የሚያደርጉ ሴቶች ተሰባስበው የአደረጉት ድጋፍ ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ሳናነሳ አናልፍም። እነዚህ ሐኪሞች በአዲስ አምባ የተቀናጀ በጎ አድራጎት ድርጅት አስተባባሪነትና በአማራ የአደጋ ጊዜ መሰባሰብ እና የወንፈል ተራድኦ የገንዘብ ድጋፍ አማካይነት ባለሙያዎች በምስራቅ አማራ ተንቀሳቅሰው የሥነልቦና ሕክምና እና የተለያዩ እገዛዎች በመስጠት ችግሮችን ለማቅለል የሞከሩ ሲሆን፤ ይህ የመጀመሪያችን ነው ብለውናል።
እኛም ተግባራቸው ምን እንደሚመስልና በቀጣይ ምን ለመሥራት እንዳሰቡ እንዲነግሩን ከመካከላቸው አንዷ የሆኑትን የአዲስ አምባ የተቀናጀ በጎአድራጎት ድርጅት መስራች፤ የሥነልቦና ባለሙያና የምክር ቤት አባል ዶክተር ማስተዋል መኮንንን አነጋግረናል።
ያሉንንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል። እርሳቸው እንዳሉን፤ በምስራቅ አማራ ክልል ባሉ ከተሞች ላይ በወራሪው ኃይል አስገድዶ መድፈር ለደረሰባቸው ከ650 በላይ ሴቶችና ሕጻናት የሥነልቦና ሕክምና እና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ለዚህ ደግሞ የአማራ የአደጋ ጊዜ መሰባሰብ ድጋፍ ሰጪ ድርጅትና ወንፈል ተራድኦ ድርጅት በገንዘብ በኩል በብዙ መልኩ አግዟቸዋል።
እነርሱም የተለያዩ ወጪዎቻቸውን ሸፍነው ነጻ አገልግሎት ሰጥተዋል። የነጻ አገልግሎቱ በገንዘብ ሲተመን ከ300ሺህ ብር በላይ ይሆናል። ነገር ግን ባለሙያዎች ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ እርካታ እንዳገኙበት ያምናሉ።
ምክንያቱም ዋጋ የማይታመንለትን የሰው ሕይወትን ታድገዋል።
ከነበረባቸው የሥነልቦና እና የኢኮኖሚ ችግርም ይላቀቁ ዘንድ የቻሉትን አድርገዋል። በዚያ ጉዳት ውስጥ ያሉትን ለማከምም አሁንም ቁርጠኛ ናቸው። ይህ ደግሞ ለአዕምሮ እረፍት ከመስጠቱም በላይ አገርን በማረጋጋቱ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። ይህን ተግባር የፈጸሙት በድንገት በተፈጠረ አጋጣሚ እንደነበር የሚያነሱት ዶክተር ማስተዋል፤ ለሌላ ሥራ ወደ ደሴ በአቀኑበት ወቅት የእነዚህን የሴቶችና ሕጻናት እሮሮና ስቃይ አይተው ማለፍ አልሆነላቸውም።
እናም ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሰቡ። ዝም ብለው ከመመለስ ይልቅ የሆነ እርምጃ መራመድ እንዳለባቸው ወሰኑና ለ10 ሴቶችና ሕጻናት አጭር የሥነልቦና ሕክምና ሰጡ። ለአንዳንድ ነገር ይሆናቸዋል በማለትም አሜሪካ ከሚኖሩ አንዲት ግለሰብ ጋር ተነጋግረው ባገኙት ድጋፍ ለእያንዳንዳቸው አምስት ሺህ ብር ሰጥተው ለጊዜው ተለይዋቸው።
ሁነቱ እንቅልፍ የነሳቸው፤ መተኛትም ያቃታቸው ዶክተር ማስተዋል፤ በቀጥታ አገር ውስጥ ካሉ ጓደኞቻቸው ጋር ተመካከሩ። ወደ ውጪ ማኅበረሰቡም በማማተር ከሆስፒታሉ ውጪ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ አስበው አሜሪካ ካሉ አጋሮቻቸው ጋር ተነጋገሩም።
ይህ ደግሞ ውጤት ያመጣ እገዛ እንዲያደርጉ አስቻላቸው። ከ10 አልፈው ከ650 በላይ ሴቶችና ሕጻነትን ለማገዝ የበቁትም ለዚህ ነው። በዚያ ላይ እነዚህ አካላት የሥነልቦና ሕክምና ብቻ ሳይሆን የአካልም ሕክምና ያስፈልጋቸዋልና በብዙ መልኩ አግዘዋቸዋል። ቀጣይ እድላቸውም ቢሆን ብዙ መሥራትን ስለሚጠይቅ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።
ገንዘቡ ከሳምንት በኋላ የሚለቀቅ ሲሆን፤ ከ10 እስከ 20 ሺህ ብር እንደሚደርስም ነግረውናል። አብዛኞቹ ጥቃት የደረሰባቸው አካላት ከእድሜ በላይና ከእድሜ በታች ናቸው። በዚህም ብዙ ሕክምናን ይፈልጋሉ።
በተለይ የተደፈሩበት አግባብ ያልተለመደ ወይም መደበኛ ያልሆነ በመሆኑ ብዙ እገዛን ካላገኙ ብዙ እህቶች በሕይወት መኖራቸው ጭምር አጠያያቂ ይሆናል። በብዙ ወንዶችም ከመደፈራቸው ባለፈ አካላዊ ጉዳታቸውም እንዲሁ ከባድ ነው። ስለዚህም በጥቃቱ ከሥነልቦናም በላይ አካላዊ ጉዳቱ የጠነከረ አድርጎታል። በመሆኑ በቀላሉ ለማከም ያስቸግራል።
በዚህም አራቱ በጎ ፈቃደኛ የሕክምና ዶክተሮች የጉዳቱ ሰለባዎችን ማከምና ከሆስፒታሎች ጋር ማገናኘት ዋነኛ ሥራቸው አድርገው ሲሰሩ ቆይተዋልም ብለውናል። እንዲያውም ለአብነት ደሴ ላይ ከ100 በላይ፤ ወልዲያም እንዲሁ ከ100 በላይ ሴቶችና ሕጻናት ተለይተው በሆስፒታል እገዛ እያገኙ መሆኑን አጫውተውናል። ማንም ሰው በዚህ ጥቃት ውስጥ ወዶ ሊሳተፍ አይችልም። ለብቀላና እነርሱን ለመጉዳት ታስቦ የተደረገ ነው።
የሕዝብንም ሥነልቦና ለመስበር የተፈጸመ እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን ወደውት እንደሆነ እየተደረገ ብዙ በደል እየደረሰባቸው ነው የሚሉት ዶክተር ማስተዋል፤ በጫናው ምክንያት ራሳቸውን ከማግለል አልፈው ማጥፋትም ይመኛሉ። ማኅበረሰቡም ቢሆን “የጁንታ ትራፊ” እያለ ያሳምማቸዋል፤ ያገላቸዋልም።
ከማኅበራዊ ሕይወትም አስወጥቷቸዋል። በሚደርስባቸው ዘለፋ እና ማግለል ገበያም ሆነ የእምነት ቦታዎች እንኳን ለመሄድ ይሳቀቃሉ። በመሆኑም ማኅበረሰቡን ማስተማር ላይ መንግሥት መሥራት አለበት። የሃይማኖት አባቶችም እንዲሁ ሊያግዟቸው እንደሚገባ አስረድተዋል።
ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች ስናገኛቸው እጅግ በሥነልቦናም በአካልም ቆስለው ነበር። ነፍሰጡሮችም አሉበት። ገና ምርመራ እየተደረገላቸው ያሉም ይገኛሉ። እናም ይህንን ማከም ጊዜ የሚሰጠው አይደለም። ምክንያቱም በልየታ ነብሰጡሮችን እፎይታ መስጠት ይገባልና። አሁን ያሉበትን የጤና ሁኔታ በማረጋገጥ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ የተለያዩ የሕክምና ቅድመ ክንውኖች ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ትልቁን ድርሻ መውሰድ አለበት። መተንበይ እንደሚቻለው ከጥቂት ወራት በኋላ በየመንገዱ የሚጣሉ ሕጻናት ሊኖሩ ስለሚችሉ የሕጻናት ማሳደጊያ ተቋማትን ከአሁኑ ማዘጋጀት ይገባል።
የተለያዩ ባለሙያዎችና ባለሀብቶችም በመተባበርና የመንግሥትን ሥራ ማገዝ እንደሚኖርባቸው ነግረውናል። ብዙ እህቶች የመጀመሪያ ደረጃ የሥነልቦና እገዛ ካገኙ በኋላ አዎንታዊ ለውጦች እንዳሳዩ የሚገልጹት ዶክተር ማስተዋል፤ ፍጹም ጤነኛና ለሌሎች አርኣያ የሚሆኑ ሴቶችን ብዙ አግተናል ብለዋል። “የደረሰባቸውን ነገር ሲገልጹም ሌሎች እንዲናገሩና እንዲበረታቱ ሲያደርጉም አይተናል።
ከጎናቸው ሰው እንዳላቸውም በብዙ መልኩ መረዳታቸውን ተገንዝበናል። ስለዚህም በትንሽ እገዛ የቀደመ ጭንቀታቸውን መቀየር ከቻሉ ብዙዎችን በተለያየ ድጋፍ ማገዝ ብንችል ምን ያህል በአገሪቱ ላይ መረጋጋትና ሰላም እንደምንፈጥር መገመት አያዳግትም” ብለዋልም። ማኅበረሰቡ እንዳያገላቸውና ወደ ኅብረተሰቡ የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ ማመቻቸትም እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል። በዚያው ልክ የሃይማኖት አባቶች እንዲያግዟቸውም ጥሪ አቅርበዋል። አስገድዶ መደፈሩ ቀጣይ እጣ ፋንታቸውን ጭምር ሊያጨልምባቸው የመጣ ነው።
በመደፈራቸው ምክንያት ሴቶች መኖራቸውን ጠልተዋል፤ ነብሰጡር የሆኑ ሴቶች ደግሞ ጽንሱን ለማጨናገፍ የባህል መድኃኒት ይወስዳሉ፤ ካልቻሉም ራሳቸውን ለማጥፋት ብዙ ሙከራዎች አድርገዋል። እናም በየቦታው ያለው ሕዝብ ይህንን አውቆ አለሁላችሁ ማለት አለበት። ዛሬን ሊያተርፋቸው ይገባል። ችግራቸው ስር የሰደደና በቀላሉ የማይታከም ነው።
ስለዚህም ይህንን መወጣት የእያንዳንዱ ኃላፊነት ነውና ልብ ይበለውም ይላሉ። ጥቃቱ የደረሰባቸው ሴቶችና ሕጻናት ከ10 እስከ 70 ዓመት እድሜ ላይ ያሉ ናቸው። ይህ ደግሞ የአካል ስብራቱ ከነበረበት በላይ እንደሚያደርገው መማር ሳይጠበቅ ማወቅ ይቻላል። እናም ሁሉም ሰው ድርሻ አለውና የበኩሉን ማበርከት ይገባዋል። ሁላችንም ሠራዊት ሆነን ግንባር ላይ ልንዋጋ ባንችልም የተለያየ መክሊት እና አገራዊ ግዴታ ስላለብን ሁላችንም በምንችለው መንገድ የድርሻችንን መወጣት አለብን።
አገር ስትደማ ዝምታን ካልመረጥን በስተቀር አገራችንን የምንፈውስበት የተለያየ ስጦታ አለንና። ስለሆነም የተሰጠንንና ያለብንን ኃላፊነት አይተን ልናገለግል ይገባልም ብለዋል። ከዚህም በኋላ ማናችንም መተኛት እንደሌለብን ማመን አለብን። የቻልነውን ለማበርከት እየተጋን ጉዳትን መፈወስ ላይ እንረባረብም ሲሉ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
የአገራችን ችግር አካሚ ስንሆን መተኪያ የሌለው ደስታን፣ ዋጋ የማይተመንለትን የአዕምሮ እርካታ እናገኛለን የሚሉት ዶክተር ማስተዋል፤ ብዙ ጥቃቱ የደረሰባቸው ሴቶች ራሳቸውን በመሳታቸው ምክንያት ዛሬ ድረስ አልነቁም፤ አባትና ወንድማቸው አለያም ሌላ ቤተሰብ ነው ሆስፒታል ያመጣቸው። ነገር ግን ይህ ጉዳይ የሥነልቦና ቀውስ እንደሆነ ማንም አይረዳውም። ምክንያቱም የሥነልቦና ችግር የማይታይ፣ የማይዳሰስና የማይጨበጥ ነው። እናም ሰው ቀለል አድርጎ ይመለከተዋልና ከአካል ጉዳቱ በበለጠ በሰዎች ጤናማ ሕይወት ላይ ቀውስ ያስከትላል።
እኛ ባለሙያዎች መጥተን የስነልቦና እገዛ በማድረጋችን ብዙ የመንፈስ እርካታ አግኝተናል ብዙ እህቶችንም ጠቅመናልም ሲሉ ከገጠመኛቸው በመነሳት አጫውተውናል። በዚህች አገር ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ውስብስብ የሆኑ ማኅበራዊ ችግሮች መነሻቸው የአዕምሮ ጤና መዛባት እንደሆነ የሚያነሱት ዶክተሯ፤ የሥነልቦና ሕክምና ብዙ ነገሮችን ይለውጣል፤ አገርንም ወደ መረጋጋቱ ውስጥ ያስገባል፤ ልማትም እንዲፋጠን ያደርጋል።
እናም ዛሬ ላይ በሁሉም መስክ አገር የሚያስፈልጋት የሥነልቦና ጽንሰ ሃሳብን መሠረት ያደረገ ውይይት ላይ አበክሮ መሥራት ነው። የሥነልቦና ቀውስ ውስጥ ካሉ አካላት ጀምሮ ማኅበረሰቡን በሥነልቦናዊ ማከም እንዲሁም መንገዱን እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም መንግሥት፣ ግለሰቦችና ባለሙያዎች እንዲሁም ድርጅቶች ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ።
የሥነልቦና እገዛውን ሰሜን ሸዋ፣ ከምቦልቻና ደሴ እንዲሁም ወልድያን ማዕከል በማድረግ እንደሠሩ ያጫወቱን ዶክተር ማስተዋል፤ የመጀመሪያ ደረጃ የሥነልቦና እገዛ ካደረጉ ለሁሉም ሰልጣኝ ሴቶች የባንክ አካውንት በመክፈት ለሶስቱ ማዕከላት ሰልጣኝ እህቶች ሦስት ሺህ ብር በአካውንታቸው እንዲደርሳቸው አድርገዋል። ወልድያ ላይ ያሉት ደግሞ በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት ውስጥ በአካውንታቸው የሚቀበሉ ይሆናሉ ብለውናል።
በተጨማሪ እነዚህ ሰልጣኝ እህቶች እርስ በእርሳቸው እንዲደጋገፉ እና እንዲረዳዱ በማሰብ በየአካባቢያቸው ማኅበር መሥርተው ቢያንስ በየወሩ እንዲገናኙ እና እንዲወያዩ የሚያደርግ አሠራር መፍጠራቸውንም ገልጸውልናል። በተመሳሳይም በወቅቱ ከገቡበት የሥነልቦና ቁዘማ በመውጣት የግል ሥራቸውን ለመሥራት የሚያስችላቸውን መነቃቃት ለመፍጠር እንዲያስችል ወደፊት የሚሠሩት ሥራ በፍላጎታቸው ልየታ እንደተደረገበትም ነግረውናል። ይህ ውስብስብ ማኅበራዊ እና ሥነልቦናዊ ቀውስ ያስከተለው የእህቶቻችን አስገድዶ መደፈር ችግር ከአገር ውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን የገንዘብ እርዳታ ብቻ የሚሸፈን እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶክተር ማስተዋል፤ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ እርዳታ ነው።
መንግሥት የራሱ ጉዳይ አድርጎት ጉዳት የደረሰባቸውን እህቶች ማቋቋም ላይ እንዲሠራ መንገድ የመጥረግ እና በኅብረተሰቡ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ተግባርም ነው። ምክንያቱም በተንቀሳቀስንበት ወቅት በእህቶቻችን ላይ አስገድዶ የመደፈር ነገር እንዳለ እንኳን የማያውቅ የኅብረተሰብ ክፍል ገጥሞናል።
በዚህም የጥቃቱ ሰለባዎች ተገቢ የሆነ ማኅበራዊ፤ ሥነልቦናዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እገዛ ሳያገኙ እንዲቀሩ ከፍተኛ ክፍተት ይፈጥራል። ስለዚህ የእኛ ቀጣይ ዓላማ ይህንን የያዘ ነውም ብለውናል። ኅብረተሰቡን በማስተማር በቀጣይ ለተደፈሩ እህቶቻችን ማንኛውንም እገዛ ይዞ እስከ መድረስ ያሉ ሥራዎችን ለማከናወን ተዘጋጅተናል የሚሉት ዶክተር ማስተዋል፤ በተለይ በሚዲያዎች ላይ ለመሥራት እቅድ እንዳላቸውና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የመጀመሪያ ጉዟቸውን እንዳደረጉ ገልጸውልናል።
በአሁኑ ወቅት ያለውን ውስብስብ ሁኔታ መንግሥትም ሆነ ማኀበረሰቡ እንዲያውቀው እና በአንክሮ በመመልከት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው እንፈልጋለን ብለዋል። ድርጅታቸው አዲስ አምባ የተቀናጀ በጎ አድራጎት ድርጅት እስከ አሁን በጦርነቱ ለተጎዱ አካላት እገዛ የሚሆን ከ110 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሰባስቧል።
ከዚህ በኋላም እስከ 200 ሺህ ዶላር ሊላክ እንደሚችል የተናገሩት የድርጅቱ መስራች፤ ይህም የተደፈሩ እህቶችን ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ መስመር ተዘርግቷል። በእስካሁኑ ጉዞም ማለትም ሦስት ሺህ ብር የተሰጣቸውን ብንጠቅስ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል። በነጻ አገልግሎትም ብዙ ሥራዎችን አከናውኗል፤ ወደፊትም ይህንን ነገሩን ያስቀጥላል። ምክንያቱም ዋና ዓላማው አገሩን ማገዝ እንደሆነም አስረድተዋል።
በምስራቅ አማራ በነበረው የሥነልቦና እገዛ እና የሕክምና አገልግሎት ከድርጅቱና በአማራ የአደጋ ጊዜ መሰባሰብ ድጋፍ ሰጪ ድርጅት እንዲሁም ወንፈል ተራድኦ ጎን በመሆን ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ በርካታ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት እንደነበሩ የሚያነሱት ዶክተር ማስተዋል፤ የአማራ ክልል የሴቶችና ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፤ የአማራ ክልል ሴቶችና ወጣቶች ቢሮ፤ የሁሉም ዞኖች የሴቶችና ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፤ የሁሉም ወረዳዎች የሴቶችና ወጣቶች ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች፤ በዞኖቹ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችና ደብረ ብርሃን መምህራን ኮሌጅ እንዲሁም ለሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ምስጋና ከሚገባቸው ውስጥ እንደሆኑ ይናገራሉ።
በተመሳሳይ ስማቸውን ያላስታወሱት የደሴ ባለሀብትም እንዲሁ ወሎ ዩኒቨርስቲ ስለወደመ ምግብ በማቅረብ ሲንከባከቧቸው ስለቆዩ ምስጋናቸውን ይቸራሉ። እኛም ይህንን ሀሳብ ጠንስሰው ወደ ተግባር ቀይረው ወገኖችን ሲደግፉ ለቆዩት አካላት ምስጋና ሳናቀርብ አናልፍምና በርቱ ማለት እንፈልጋለን። ሌሎችም አርኣያነታቸውን ተከትላችሁ ለወገኖቻችን ድረሱላቸው ስንል መልዕክታችንን በማስተላለፍ ለዛሬ አበቃን። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 22 /2014