በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በአደይ አበባ ቅርጽ እየተገነባ የሚገኘው ብሔራዊ ስታድየም ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ከተጀመረ ከሰባት መቶ ቀናት በላይ ተቆጥረዋል።
የስታድየሙ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ሲጀመር በዘጠኝ መቶ ቀናት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱ የሚታወቅ ሲሆን የግንባታው ሂደትና አፈጻጸም በየጊዜው በመንግስት ክትትልና ግምገማ እየተደረገበት ይገኛል። የስታድየሙን ግንባታ በቅርበት እየተከታተለ የሚገኘው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የግንባታው አማካሪ ድርጅት እንዲሁም ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው የቻይናው ስቴት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ አመራሮች የስታድየሙን የግንባታ ሂደት በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸውን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ፣ ሚኒስትር ዲኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታዲየም አማካሪ ድርጅት፣ የስፖርት ዘርፍ አመራሮች፣ የቻይናው ስቴት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ የብሔራዊ ስታድየሙ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታን ለማጠናቀቅ ዘጠኝ መቶ ቀናት መቀመጡን በማስታወስ ከግንባታ ውል ስምምነቱ ቀን ጀምሮ ውይይቱ እስከተካሄደበት እለት ድረስ ከሰባት መቶ ቀናት በላይ እንደወሰደ ተጠቁሞ፣ በቀሪ ቀናት የግንባታ ስራው መጠናቀቅ መቻል እንዳለበት ተገልጿል።
የስታድየሙ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ሲጀመር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት የጨመረበት ወቅት በመሆኑ ከውል ስምምነቱ በኋላ የቻይና ባለሙያዎች ወዲያው ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ስራውን እንዳልጀመሩ የብሔራዊ ስታድየሙ ግንባታ አማካሪ ዶክተር ኢንጂነር መሠለ ኃይሌ አብራርተዋል።
በቻይና ስቴት ኢንጂነሪግ ኩባንያው በኩል ባለሙያዎቹ ከመጡ በኋላም ግንባታውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ከውጪ የሚገቡ የግንባታ መሳሪያዎችን ግዢ ለመፈፀም የውጪ ምንዛሪ ጥያቄ ቶሎ ምላሽ ያለማግኘት ችግር እንደነበር ተጠቁሟል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታድየም ግንባታ መንግስት ከፍተኛ ትኩረትና ከፍተኛ በጀት መድቦ ለማስገንባት በቁርጠኝነት ወደ ስራ የገባ መሆኑን ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል።
በተቋራጩ አመራሮች በኩል የቀረቡት የውጪ ምንዛሪ ክፍያ መዘግየትና የግንባታ መሳሪያዎች ወቅታዊ ገበያ መናር ጋር ተያይዘው የሚነሱት ጥያቄዎችን በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከንግድ ባንክ አመራሮች ጋር የጀመረውን የስራ ግንኙነት በማጠናከር በጉዳዩ ዙሪያ በመነጋገር የውጪ ምንዛሪ ችግርን ለመፍታተት በጥብቅ ክትትል እንደሚሠራ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ከገበያ ዋጋ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ችግር መሆኑን በመጥቀስም የቻይና መንግስት ኢንጂነሪንግ ኩባንያም የራሱን ጥረት በማሳደግ ስታድየሙ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለበት ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።
በመንግስት በኩል የተመደበው የዶላር ክፍያ የተፈቀደ ቢሆንም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በዳሽን ባንክ መካከል በተከሰተው ያለመግባባት ክፍያውን መፈጸም እንዳልተቻለ በውይይቱ ተገልጿል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ፍሰሐ ብርሃኑ የዳሸን ባንክ የዉጪ ምኒዛሪ ኃላፊ በሰጡት ማብራሪያ፣ አሳሪ ህጎች በአሰቸኳይ ተሻሽለው ጥያቀው ከቀረበ ባንኩ ክፍያውን ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስትሩም በሁለቱ ባንኮች መካከል የተከሰተውን ችግር በጋራ በፍጥነት ለመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በውይይቱ ላይም ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመፍታት እንደሚሠራ የመፍትኤ አቅጣጫ ተቀምጧል። ከውይይቱ በኋላም የአዲስ አበባ ስታድየም የጥገና ሂደትን በተመለከተ ገንቢ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ አጠቃላይ የእድሳት ግንባታው ስልሳ ስምንት በመቶ መጠናቀቁን ማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታዲየም በ2008 ዓም ተጀምሮ በ2012 ዓም የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቅቆ ሁለተኛ ምዕራፍ መጀመሩ ይታወቃል። አጠቃላይ የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ 900 ቀናት እንደሚፈጅ ሲጠበቅ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከ 5ነጥብ5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስወጣ ይጠበቃል ።
የአደይ አበባ ስታዲየም ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ 62,000 በላይ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዳለው ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 /2014