የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋ እ.ኤ.አ ከ2001 ጀምሮ የዓለም ከ19 ዓመት በታች ሴቶች ቻምፒዮናን ሲመራ ቢቆይም፤ ወጣት ሴቶችን ማዕከል ያደረገ ተጨማሪ ውድድር አስፈለገው። በመሆኑም የእድሜ እርከኑን በመጨመርና በመቀነስ ሁለት የዓለም ዋንጫ ውድድሮችን ለማድረግ ወሰነ።
በዚህም መሰረት ከ17 ዓመት በታች እና ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫን በየሁለት ዓመት ልዩነት ማካሄድ ጀመረ። በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች የዓለም ዋንጫን ማካሄዱም ብዙም ትኩረት ላልተሰጣቸው የሴቶች እግር ኳስ ማነቃቂያ እንዲሁም ታዳጊና ተተኪ የሆኑ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማፍራት የሚያስችል ሆኗል።
ሁለቱ ውድድሮች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መካሄድ ቢኖርባቸውም፤ የመላው ዓለም ስጋት በነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ተያዘው ዓመት ሊዘዋወር ችሏል። በዚህም መሰረት ሁለቱም የዓለም ዋንጫዎች ከወራት በኋላ ይካሄዳሉ። ኢትዮጵያም በእነዚህ ውድድሮች አፍሪካን ወክላ ተሳታፊ ለመሆን ዝግጅት በማድረግ ላይ ናት።
ለዚህም አስቀድሞ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ኮስታሪካ የምታዘጋጀውን ዓለም ዋንጫ ለመቀላቀል እጅግ የተቃረቡት የኢትዮጵያ ከ20ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሶስት ሳምንት በኋላ የመጨረሻውን ዙር መጀመሪያ ጨዋታ ያደርጋሉ። አምስት ዙሮች በነበረው ማጣሪያ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈው ቡድኑ ከጋና ጋር በደርሶ መልስ ለሚያደርገው ጨዋታም ዝግጅቱን ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም አንስቶ አጠናክሮ ቀጥሏል።
በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው ቡድኑ ታንዛኒያን በድምር ውጤት ከረታ በኋላ እረፍት ለማድረግ የቻለው ለጥቂት ቀናት ብቻ ነበር። ከእረፍት መልስ ተጨማሪ ተጫዋቾችን በመጥራት 27 አባላትን በመያዝ ነበር የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨምሮ በተለያዩ ሜዳዎች መደበኛ ልምምዱን የጀመረው። በማጣሪያው በተደረጉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ሊበቃ የሚችል ብቃቱን አሳይቷል።
በእስካሁኑ ጨዋታዎች 18 ግቦችን ሲያስቆጥር፤ 3 ግቦችን ማስተናገዱ ጠንካራ ቡድን ያሰኘዋል። ከቡድን ባለፈም በተናጥል የተጫዋቾች ክብረወሰን 7 ግቦችን በማስቆጠር ረድኤት አስረሳኸኝ ቀዳሚው ስፍራ ላይ ተቀምጣለች። አረጋሽ ካልሳ ሶስት ግቦች ሲኖሯት፤ ቱሪስት ለማ፣ አራያት ኦዶንግ እና መሳይ ተመስገን ደግሞ በሁለት ግቦች ይከተላሉ።
ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዓለም ዋንጫ ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን፤ ህንድ ደግሞ አዘጋጅ አገር ናት። በውድድሩ ላይ ከስድስት አህጉር አቀፍ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽኖች የተወጣጡ 16 ቡድኖች ተሳታፊ ናቸው። በአንድ አገር ከምትወከለው ኦሺንያ በቀር ሁሉም አህጉራት ሶስት ሶስት አገራትን ሲያሳትፉ፤ ኢትዮጵያም ከእነዚህ መካከል ለመሆን ወደ ዝግጅት ገብታለች።
በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ በወጣው የማጣሪያ መርሃ ግብር መሰረትም ከቅድመ ማጣሪያው በኋላ በሶስት ዙሮችን የደርሶ መልስ ጨዋታ ጥለው ማለፍ የቻሉ ሶስት ቡድኖች የዓለም ዋንጫው ተሳታፊ ይሆናሉ። ኢትዮጵያም የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዋን ከዩጋንዳ ጋር እንደምታደርግ የምድብ ድልድሉ ያሳያል።
በአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድንም ከየካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም አንስቶ ለ44 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ አስቀድሞ ነበር ወደ ዝግጅት የገባው።
በሂደትም 19 ተጨዋቾችን ተቀንሰው 25 ተጫዋቾችን በመያዝ በቀን ሁለት ጊዜ (ጠዋት እና አመሻሽ ላይ) በካፍ ልህቀት ማዕከል ዝግጅታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በቀጣይም በልምምድ እንዲሁም እርስ በእርስ በሚያደርጉት ግጥሚያ ከቡድኑ ጋር የሚቀጥሉ ተጫዋቾች የሚለዩ ይሆናል።
ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውንም የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም በዩጋንዳ ካምፖላ ሲያደርግ የመልስ ጨዋታውን ደግሞ መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ያካሂዳል። በዚህ የደርሶ መልስ ጨዋታ አሸናፊ የሚሆነው ቡድንም ከኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ አሸናፊ ከሚሆነው ቡድን ጋር የሚፋለም ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 18 /2014