እነሆ ዓባይ ኃይል ማመንጨት ጀመረ። ባለፈው እሁድ የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም የመጀመሪያው ኃይል የማመንጨት ሥራውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በይፋ አስጀምረውታል። ከ13ቱ ኃይል ማመንጫ ዩኒቶች አንዱ ስራ ጀምሯል። በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ለደረሰው የህዳሴው ግድብ፤ ያሰቡትንም፣ የጀመሩትንም፣ ያስፈጸሙትንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመስግነዋል።
ዓባይ የኃይል ምንጭ ከመሆኑ በፊት የጥበብ ምንጭ ሆኖ ኖሯል። ለዘመናት እንጉርጉሮው፣ ቅኔው፣ አባባሉ፣ ወዘተ… ስለአባይ ብዙ ብሏል። በአጠቃላይ የጥበብ ምንጭ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል። እነዚያ ጥበባት ቁጭት የወለዳቸው ስለነበሩ ነው ለዛሬ ስኬት ያበቁት። እነዚያ የሕዝብ የስነ-ቃል ጥበባት በውስጣቸው ቅኔ የያዙ ነበሩ። የዓባይን አይደፈሬነትና አስቸጋሪነት የሚናገሩ ነበሩ። እነሆ ዛሬ የሚደፍረው ትውልድ ተፈጠረና ለዚህ በቃ።
ዓባይ ወዲያ ማዶ ማሽላ ዘርቼ
ወፎች ጠረጠሩት መሻገሪያ አጥቼ
በድሮው ጊዜ ዓባይን መሻገር የሚሞከረው በበጋ ወቅት ውሃው መጠኑ ሲቀንስ ብቻ ነበር። እንደ ዛሬው ድልድይ በሽበሽ አልነበረም። አንድ ከዓባይ ወዲህ ማዶ ያለ ሰው ከዓባይ ወዲያ ማዶ ያለች ጉብል ካፈቀረ መገናኘቱ ከባድ ነበር። ፍቅሩ ሲጠናበት ነው እንዲህ በማሽላ የመሰላት። ያቺን ያፈቀራትን ቆንጆ እዚያው አጠገቧ ያለ ሊያፈቅራት ስለሚችል ‹‹ወፎች ጠረጠሩት መሻገሪያ አጥቼ›› ብሎ ተቀኘ። ፍቅሩ በጣም ባስ ሲልበት ደግሞ ፈጣሪንም መማጸን በሚመስል መልኩ እንዲህ አለ።
አንቺ ወዲያ ማዶ እኔ ወዲህ ማዶ
አንገናኝም ወይ ተራራው ተንዶ?
ይላታል። ‹‹ተራራው›› ተብሎ የገለጸው ራሱ ውሃው ነው። ተራራ በአስቸጋሪ ነገር ይመሰላል። እናም ተራራው ተንዶ ሲል ውሃው የሚጎልበትን መንገድ እየተመኘ ነው።
እነሆ የዚያ ዘመን እንጉርጉሮዎች የተናገሩት ትንቢት ደረሰ። ወዲያ ማዶ እና ወዲህ ማዶ ያለ ሰው መገናኘት ብቻ ሳይሆን ‹‹ተራራው›› የተባለውን ዓባይ መናድ ተቻለ። ዓባይ በሰው ልጅ ቁጥጥር ሥር ዋለ። ዓባይ ተገደበ፤ ጥበብ ብቻ ሳይሆን ኃይል አመነጨ፤ ራት መሆን ጀመረ።
ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በታኅሣሥ
የማን ሆድ ይችላል እስከዚያ ድረስ?
ታኅሣሥ የበጋ ወቅት መጀመሪያ ነው። የያኔው ዘመን ሰው ዓባይን እንዲህ በምናብ ያወራው ነበር። ‹‹መቼ ነው ጎደል የምትል›› ሲለው በበጋ ወቅት ብሎታል ማለት ነው። እነሆ በትውልድ ቅብብሎሽ የዚህኛው ዘመን ሰው ደግሞ ዓባይን በምናብ ሳይሆን በእውን አናገረው።
ዓባይ ውሃው ብቻ አልነበረም አስፈሪ። ወደ ወንዙ የሚያስገቡ መንገዶች ሁሉ ዳገትና ቁልቁለት ናቸው። ስለዚህ ከአንዱ ወደ አንዱ ስንሄድ ቁልቁለት ወርደንና አቀበት(ዳገት) ወጥተን ነው። ይህም ድካሙ ቀላል አይደለም። ዓባይን ተሻግረን ለምናገኘው ነገር ሁሉ ዳገት እንወጣለን፤ ቁልቁለት እንወርዳለን። ላሰበው ነገር ቆራጥ የሆነ ሰው ይሄ ሁሉ አይበግረውም። የያኔው ዘመን ሰው ቁጭቱን እንዲህ ይገልጽ ነበር።
ዓባይ ቁልቁለቱን እምባዬ እያነቀኝ
ዓባይ አቀበቱን ላብ እያጠመቀኝ
መቅረትስ አልቀርም እስከዚያው ጨነቀኝ።
የያኔው ዘመን ሰው የተናገረበት ዓውድ ምን እንደሆነ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በፍቅር አስመስለው ነው የሚናገሩት። ለምንም ይናገሩት ለምን የዚህ ስንኝ መልዕክት ግን ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ የደረሰባትን ውጣ ውረድ ይገልጻል። መሪዎቻችን ልክ እንደ አፍቃሪው በዓባይ ዳገትና ቁልቁለት ተጨንቀዋል፤ በላብ ተጠምቀዋል። የዓባይ ዳገትና ቁልቁለት አሸንፎኝ አልቀርም እንዳለው አፍቃሪ፤ የአገራት ሴራና ተንኮል ሳይበግራቸው በፍጹም አንተወውም ብለው እንሆ ለስኬት አብቅተውታል።
ዓባይ ሞላ አሉ ሞላ አሉ
እንደ ዕድሌ ሁሉ
የሚባል የአገር ቤት የባህል ዘፈንም አለ። ይህ ዘፈን ትክክለኛ መልዕክቱን አግኝቷል። የያኔው አንጎራጓሪ ለግድቡ አልነበረም፤ የዓባይ ወንዝ ሲሞላ ዝም ብሎ ውስጡ ሀሴት ያደርጋል። ዓባይ ሲሞላ የጥጋብ ዘመን ነው ይሉታል። የአዝመራው ማማር ያስደሰተው ገበሬ ነው ‹‹ዓባይ ሞላ አሉ እንደ ዕድሌ ሁሉ›› የሚለው። እነሆ ዛሬ በኃይል ማመንጨቱም ሞልቶለታል።
ዓባይ ቢሞላ ቢሞላ
አለው አሉ መላ
የሚባል የባህል ዘፈንም አለ። የሚገርመው ግን እነዚህን የባህል ዘፈኖች የመረመራቸው አልነበረም። ለዚህ አንጎራጓሪ የታየው መላ ምን ይሆን? ይህን የገጠመው ሰው ግን ነብይ መሆን አለበት። ምናልባት ከዘመናት በኋላ የተሰራው ድልድይ ታይቶት ይሆን? ዓባይ በሰው ልጅ እጅ እንደሚገደብ ታይቶት ይሆን? ኧረ እንዲያውም አንዳንዱ የቃል ግጥም ዓባይ እንደሚገደብ እርግጠኛ የሆነ ይመስላል። ዓባይ ተደላድሎ ይቀመጣል የሚል ትንቢት የነበራቸው ይመስላል።
ዓባይ ቢሞላ ቢጎድል
አለው መደላድል
ይሄ ማለት እኮ ቢሞላም ቢጎድልም አያሳስበንም፤ አንድ ቦታ አደላድለን ነው የምናስቀምጠው ለማለት የታሰበ ይመስላል።
አያት ቅድመ አያቶቻችን ስለ ዓባይ ያልተቀኙት የለም። እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ይሆናል፤ ዓባይ የብዙ ነገር መነሻቸው ነበር ማለት ነው። እንግዲህ አስቡት! ያኔ ዓባይ ሳይገደብ ማለት ነው፤ ዓባይ ሰውን እየጠለፈ ከመግደል በስተቀር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መስጠት ባልጀመረበት ዘመን ማለት ነው።
ዛሬስ?
ዛሬ ዓባይ በኢትዮጵያውያን ቁጥጥር ሥር ነው። ወንዙ ላይ በተለያዩ ስፍራዎች ብዙ ድልድዮች ተሰርተው ለመሻገር የነበረው ችግር እንደተወገደ ሁሉ፣ ማደሪያ የለውም የተባለው አባይ ጉባ ላይ ማደሪያ፣ ማረፊያ ተበጀለት። ‹‹አለው አሉ መላ›› እያለ ሲተነብይ የነበረው ሰው እነሆ ትንቢቱ ደርሶለት ዓባይ መላ ተገኝቶለት ተገደበ፤ ብርሃንና ራትም መሆን ጀመረ።
እነዚህን የቃል ግጥሞች ማስታወስ የፈለግንበት ምክንያት ለመዝናኛነት አይደለም። ይልቁንም ዓባይ ከጥንት ጀምሮ ለኢትዮጵያ ‹‹ምን ነበር?›› የሚለውን ስለሚያስታውሱን ነው። ግብጾች ‹‹ሁሉ ነገራችን ነው›› የሚሉት አባይ ለኢትዮጵያውያንም ምን ያህል ሁሉ ነገራቸው እንደሆነ ስለሚጠቁም ነው።
በሌላ በኩል፤ ያኔ ምንም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማይሰጥበት ጊዜ ይህን ያህል ከተዘመረለት ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ 24 ሰዓት ቢዘመርለት ይበዛበታል ወይ? ለማለትም ነው። እንዲያውም የሚገባውን ያህል እንዳልዘመርንለት አመላካች ነው። ከእነዚህ የሀገረ ሰብ ጥበባት የዓባይ ጉዳይ የመሪዎችና የፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን የሕዝብ መሆኑን እንረዳለን። ከአባይ ገና ብዙ ይጠበቃል፤ ኃይል ማመንጨት ጀመረ እንጂ ግንባታው ገና አልተጠናቀቀም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ የዓባይ ልማት ጉዳይ የትውልድ ቅብብሎሽ ነው። የቀደሙት ሀሳቡን አመነጩ፣ ቀጣዩ ትውልድ ይገነባዋል ብለው አስጠንተው አስቀመጡ። እነሆ ያ ቀጣይ ትውልድ ደግሞ ግንባታውን አስጀመረ፣ ሌላው የተለያዩ ምዕራፎችን እንዲያልፍ አድርጎ ብርሃን ማመንጨት እንዲጀምር አደረገ።
ስለዚህ ሁላችንም የዚህ ትውልድ ሰዎች የዓባይን ምንነት ለትውልድ ማሳወቅና የኔነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግ ይገባናል። ኢትዮጵያውያን ከቁጭት ወደ ብርሃን ማመንጨት እንዲሁም እራትነት አሸጋገረውታል። ኪነ-ጥበብ ያን ዘመን ሁሉ የተጠበበችበት ዓባይ ሰሞኑን ብርሃንና እራት መሆን መጀመሩን ስትሰማና ስታይ ደግሞ ምን ትል ይሆን? ብዙ እንጠብቃለን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2014