ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየካቲት 12 ቀን መታሰቢያ ሐውልት ሥር አበባ አኖሩ
አዲስ አበባ (ኢ/ዜ/አ/)፴፯ኛው የኢትዮጵያ ሰማዕታት መታሰቢያ ቀን በዓል ባለፈው ማክሰኞ በመላው ኢትዮጵያ በጥልቅ ስሜት ተከበረ። ክቡር ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚሁ ዕለት በየካቲት ፲፪ ቀን አደባባይ ተገኝተው በሰማዕታቱ መታሰቢያ ሐውልት ሥር የአበባ አክሊል አስቀምጠዋል።
እንደዚሁም ክቡር ዶክተር ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ስም የተዘጋጀውን አበባ ሲያኖሩ፤ የግርማዊት እቴጌ መነን ት/ቤት ተማሪዎች የቀይ መስቀልና የየካቲት ፲፪ መታሰቢያ ትምህርት ቤት ልጃገረዶችም በሰማዕታቱ መታሰቢያ ሐውልት ሥር የአበባ አክሊል አስቀምጠዋል።
የታክሲ ማኅበር የድርቅ ርዳታ ስብሰባ ይጀምራል
የአዲስ አበባ መናገሻ ከተማ ታክሲዎች ማኅበር ለድርቅ ቀበሌዎች ርዳታ ለማሰባሰብ በማኅበሩ ስም የገንዘብ ደረሰኝ ካርኒ ያሳተመ መሆኑን የማኅበሩ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ጣፋ ገለጡ።
ማኅበሩ የርዳታ አሰባሰቡን ሥራ የሚጀምረው የፊታችን እሁድ ወ.ወ.ክ..ማ. ፊት ለፊት በሚገኘውየማኅበሩ ጽህፈት ቤት በሚያደርገው የአባ ማኅበርተኞች ስብሰባ መሆኑን አቶ ስንታየሁ አስታውቀዋል። የአዲስ አበባ ታክሲ ማኅበር በድርቅ ለተጎዱት ኢትዮጵያውያን መርጃ የሚሆነውን ገንዘብ የሚሰበስበው ከማኅበሩ አባሎች ብቻ ሳይሆን የማኅበሩ አባል ካልሆኑት ታክሲ ነጂዎችና የታክሲ ባለንብረቶች ጭምር ስለሆነ፤ እነዚህ ሰዎች የርዳታ እጃቸውን በመዘርጋት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።
ማህበሩ ቀደም ሲል ባደረጋቸው ስብሰባዎች ስለ ጉዳዩ በሠፊው ከተወያየ በኋላ፤ የርዳታ መሰባሰቡን ዘመቻ ለመጀመር በመወሰን የገንዘብ ደረሰኝ ካርኒ ማሳተሙን የማኅበሩ ኃላፊ አስረድተዋል። (ሚያዝያ ፳፬ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ.ም )
አርጀንቲና ለድርቅ ቀበሌ 15ሺ ኲንታል እህል ረዳች
አዲስ አበባ (ኢ.ዜ.አ.) በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ቀበሌዎች ችግር ማቃለያ እንዲሆን የአርጀንቲና መንግሥት 15ሺ ኲንታል እህል ትናንት በርዳታ ሰጠ።
በእርሻ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ተገኝተው ርዳታውን ለክቡር ደጃዝማች ካሣ ወልደማርያም የእርሻ ሚኒስትር በድርቅ ለተጎዱ ቀበሌዎች የመቋቋሚያ ዕቅዶች አስፈጻሚ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ያስረከቡት ክቡር ሚስተር ካርሎስ አውግስቶስ ማሣ በኢትዮጵያ የአርጀንቲና መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ናቸው።
ክቡር አምባሳደሩ ስጦታውን ባስረከቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ አገራቸው በኢንዱስትሪና በእርሻ ሥራ ያላትን የረጅም ጊዜ ልምድ ጠቅሰው፤ ይህንኑ ልምዷን ለኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ለማስተዋወቅ መንግሥታቸው በእርሻ ሚኒስቴር አማካይነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ሰፊ ዕቅድ ያለው መሆኑን ገልጠዋል።
በዚሁ የርዳታ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ ክቡር ደጃዝማች ካሣ ወልደማርያም ጉዳት ለደረሰባቸው ቀበሌዎች ሕዝብ ችግር ማቃለያ እንዲሆን የአርጀንቲና መንግሥት ለልማት የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን በመስጠት ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ባለው ዕቅድ መሠረት፤ በነፋስ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ለእርሻ ሥራ የሚውሉ መሣሪያዎች በማቅረብና በማስተዋወቅ ለኢትዮጵያ ርዳታ እንደሚሰጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል። (ጥር 18 ቀን 1966 አ.ም)
የመብል ዘይት ዋጋ አስበልጠው የሸጡ ሁለት ሰዎች 300 ተቀጡ
አዲስ አበባ፤(ኢ.ዜ.አ.) የንግድ፤ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያወጣውን የንግድ መመሪያ በመተላለፍ በአዲስ ከተማ ሁለት ነጋዴዎች የመብል ዘይት ዋጋ አስበልጠው ሲሸጡ በመገኘታቸው እያንዳንዳቸው ሦስት መቶ ብር ትናንት ተቀጡ።
አቶ ተስፋዬ ምትኩ የተባሉት ነጋዴ አዲስ ከተማ ገበያ አዳራሽ ጎን ከሚገኘው የሸቀጣ ሸቀጥ መደብራቸው ውስጥ አንደኛ ደረጃ የሆነውን አንድ ሊትር የመብል ዘይት ፩ ብር ከ፹፭ ሳንቲም መሸጥ ሲገባቸው ዋጋ በመጨመር ፪ ብር በመሸጣቸው ፤እንዲሁም አቶ አሊ ሐሰን የተባሉት አዲስ ከተማ ከዱሮ በርበሬ ተራ አጠገብ ከሚገኘው የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ የሆነውን አንድ ሊትር ፩ ብርከ፷፭ ሳንቲም ሂሳብ መሸጥ ሲገባቸው ዋጋ በመጨመር ፩ ብር ከ፺ ሳንቲም ሲሸጡ በመገኘታቸው በሁለቱም ተከሳሾች ላይ በዐቃቤ ሕጉ አማካይነት የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ትናንት በዋለው ችሎት አንደኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ለተደረገባቸው የእምነት ክህደት ጥያቄ ተከሳሾቹ አድራጎታቸውን ሳይሸሽጉ በማመናቸው እያንዳንዳቸው ፫፻ (ሦስት መቶ ብር)መቀጣታቸውን ከፍርድ ቤቱ የደረሰን ዜና አረጋግጧል። (የካቲት 20 ቀን 1966 አ.ም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 15 /2014