ሴትነት በበርካታ ውጣውረዶች የተሞላ ነው። በተለይ ብዙም የትምሕርት ጥቅም ባልገባውና ባለተስፋፋበት ገጠር አካባቢ ተወልዶ አድጎ ለትዳር እንጂ ለትምሕርት እምብዛም ትኩረት አይሰጥም።
እንደው ቢሳካ እንኳን በትምህርት ከፍ ያለ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍና የግል ጥረትን የሚጠይቅ ነው። የዛሬዋ እንግዳችን ወይዘሮ አየለች እሸቴም በራሳቸው ጥረት ራሳቸውን አስተምረው ከመምሕርነት ተነስተው ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ላይ ደርሰዋል።
ፓርላማ ገብተው ለዓመታት የነቃ ተሳትፎ በማድረግም ከራሳቸው አልፈው ለሕብረተሰቡ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ወይዘሮ አየለች እሸቴ ውልደታቸውና አድገታቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም አጣዬ ከተማ በር ጊቢ ቀበሌ ነው።
ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምሕርታቸውን ያጠናቀቁትም እዚሁ አጣዬ ከተማ ነው። ከሰባተኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ያለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ደግሞ በአጣዬ ከተማ አጣዬ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንት ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት በሥራ ዓለም ከተሰማሩ በኋላ ሲሆን የፓርላማ አባል ከሆኑ በኋላ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሕዝብ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል።
ሥራ የጀመሩት ለሙያው የሚያበቃ የተወሰኑ ኮርሶችን በመውሰድ ሰባት ዓመት ባገለገሉበት መምሕርነት ሲሆን የፖለቲካ ተሳትፏቸው ለአምስት ዓመታት በኤፍራታና ግድም እስከ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪነት ከሰሩበት ኃላፊነት ይነሳል።
‹‹ፖለቲካ ውስጥ እገባለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም የሚሉት ወይዘሮ አየለች፤ የመጀመሪያ ደረጃም ሆነ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ በውሳኔ ሰጪነት የተጫወትኩት ሚና የለም›› ሲሉ ይናገራሉ። ሆኖም ተማሪ ቤት እያሉ ከሰፈር ጓደኞቻቸው ጋር አብረው ሲሆኑ የመምራትና በነገሮች ላይ ቁርጠኛ ውሳኔዎችን የማሳለፍ ልምምድ እንደነበራቸው ይናገራሉ።
ወይዘሮ አየለች ቀድመው በቀጠሮ ሰዓት በመገኘትና በዚህ በኩል አርአያ የሚሆን መመሪያ በማስተላለፍ ያደርጓቸው የነበሩ ልምምዶች ቢኖርም በፍፁም ወደ ፖለቲካው ያመጧቸዋል ብለው አልጠበቁም።
ከዚህ ይልቅ ወደ ፖለቲካው መግባት ያስቻላቸው ከመምሕርነት ሙያ ወደ ወረዳ አመራርነት መምጣታቸው እንደሆነ ይጠቁማሉ። በወረዳ አመራርነት በሰሩባቸው ጊዜያቶች አብዛኛዎቹ ሥራዎች በባሕርያቸው ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ነበሩ።
የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙም ይፈልጉ ነበር። ሕብረተሰቡን የመጥቀም ዓላማም ነበራቸው። ይሄን ማድረግ አጠቃላይ በአገር ደረጃ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተገንዝበዋል።
‹‹በመጨረሻ እነዚህ ሁሉ አስተዋጽኦዎች ተደማምረው ወደ ፖለቲካው መስክ ሊያስገቡኝ ችለዋል›› የሚሉት ወይዘሮ አየለች፤ በዚህ መልኩ ወደ ፖለቲካው ገብቶ ሕዝብን ከማገልገል በላይ የሚያስደስት ነገር እንደሌለ ይጠቅሳሉ። ወደ ፖለቲካው ጎራ ከተቀላቀሉ በኋላ በኃላፊነት ከሰሩባቸው ቦታዎች መካከል በተለይ ዓመት ከመንፈቅ ያገለገሉበት የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪነት ለከፍተኛ ኃላፊነት በር ከፍቶላቸዋል።
በወቅቱ የዞኑ ካቢኔና የክልል ምክር ቤት አባልነት እድል አግኝተውበታል። በ1998 ዓ.ም ኤፌሶን ምርጫ ክልልን በመወከል ፓርላማ ለመግባትም አስችሏቸዋል። በፓርላማ ቆይታቸው የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም ከ2003 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ሰርተዋል። ከ2009 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ደግሞ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው አገልግለዋል።
በኋላም ወደ ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር በሚኒስትር ዴኤታነት መጥተዋል። ከአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ምስረታ ጀምሮም አሁን የማሕበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው እያገለገሉ ወዳሉበት ሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመድበዋል።
ወይዘሮ አየለች የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው በሰሩበትም ሆነ በፓርላማ ቆይታቸው የሴቶች ጉዳይ ከምክር አልፎ በሁሉም መስክ ተደማጭነት አግኝቶ እስከ ታች መሬት ላይ በመውረድ እንዲተገበር በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን ያስረዳሉ።
ለዚህም ከሕግ አንፃር ለትግበራው አስፈላጊ የነበሩት ጉዳዮች በሁሉም በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲነሱ በማድረግ፣ አጠቃላይ ሂደቶችን በመከታተል፣ በመስክ ምልከታ በመሳተፍ፣ ክፍተቶችን በመለየት፣ ግብረ መልስ በመስጠት፣ ሲያደርጓቸው የቆዩ ጥረቶች ይዘረዝራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት በወቅቱ በምክር ቤቱ የነበሩ ሴቶች ጉዳያቸው ትኩረት እንዲያገኝ በማድረጉ የነበራቸው የእርስ በእርስ መስተጋብር የተሻለ ነበር። እሳቸውም ሆኑ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሴት መሆን ሴቶች ወደ አመራር እንዲመጡ አስችሏል።
የእሳቸው አበርክቶም ቢሆን በተናጠል ባደረጉት ሳይሆን በዚህ መልኩ በጋራ ከተደረገ ርብርብ ጋር ተሰናስሎ ይነሳል። የእርሳቸው ርብርብ ጉዳያቸውን በአፈ ጉባኤ በኩል በማቅረብ በሰለጠነና በተደራጀ አግባብ አመራር እንዲሰጥበት ሲያደርግ ቆይቷል። ሴቶች በማሕበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረጉ ረገድም ትልቅ አበርክቶ ነበረው።
በአሁኑ ወቅት በሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማሕበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ወይዘሮ አየለች ‹‹ፓርላማ ለኔ ትምሕርት ቤቴ ነው። አገራዊ ሁኔታን ለማየት ዕድል ሰጥቶኛል ፤ እይታዬንም አስፍቶታል›› ይላሉ።
እሳቸው የፓርላማ አባል በነበሩበት ዘመን ፓርላማ ውስጥ መሻሻሎችን ቶሎ አለማየት፣ ከውሳኔ ሰጪነት አኳያ፣ ተጠቃሚነትን በውጤት አስደግፎ ከማምጣት አንፃር ብዙ ጉድለቶች ይታዩ እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ ከአስፈፃሚ አካላቶች ጋር የነበረው የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ዝቅ ያለና ፈታኝ የነበረ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ከአቅም ግንባታ ጋር ተያይዞ ክፍተቶች የነበሩ መሆኑንም ተናግረው፤ ሆኖም አቅም እየተገነባ የሚሄድ አንፃራዊ በመሆኑ በሂደት ማሻሻል መቻሉንና የሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በቁጥርም በተግባርም መጨመሩን ይጠቁማሉ።
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን በሚመለከት ዓለም ትልቅ ትምሕርት የወሰደበት ስለመሆኑ ወይዘሮ አየለች ያብራራሉ። ወደ ፓርላማው ለውጡን የሚመጥኑ ሴቶች መግባታቸውንም በአወንታነት ያነሳሉ። ለዚህ ታዲያ የእሳቸውና የሌሎች ሴት የፓርላማ አባላት ትልቅ መሰረት እንደጣለም ያመለክታሉ።
በፓርላማ ቆይታቸው የሚያስደስታቸውና አሁንም ሆነ ወደፊት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለው የሚያስቡት የሴቶችን ደሕንነት፣ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያደናቅፍ፣ ማሕበራዊ እሴቶቻቸውን የሚጎዳ ሕጎችን አስፈፃሚው አካላት እንዲያያቸው ማድረጉ እንደሆነም ወይዘሮ አየለች ያብራራሉ።
ሴቶች ጉዳያቸው በዕቅድ ውስጥ እንዲካተት በማድረጉ በተለይም የአምስት ዓመቱ ስትራቴጂ ዕቅድ ሲታቀድ የላቀ ሚና መጫወታቸውንም ይናገራሉ። ዕቅዱ ሴቶች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በየመስኩ የሚጠቀሙበትንና ተሳታፊ የሚሆኑበትን ታሳቢ ማድረጉንም ይጠቅሳሉ። ይሄ በመሆኑም በምክር ቤቱ በመጀመሪያው ዘመን የነበረው የሴት አባላት ቁጥር በየጊዜው በተለይ በአራተኛውና በአምስተኛው ዘመን ላይ መሻሻሎች ማሳየቱን ይገልፃሉ።
‹‹ፓርቲዎች የነበሩት በሶስተኛው የምክር ቤት ዘመን ነው›› የሚሉት ወይዘሮ አየለች በተለይ በ1997 ዓ.ም በነበረው ምርጫ ብዙ ተሳታፊዎች ወደ ምክር ቤቱ የገቡበት ሁኔታ እንደነበር ያስታውሳሉ። ፓርላማው የሴት አመራሮች ቡድንን (ኮከስ) አደረጃጀት ይፈቅድ ስለነበረ በዚህ ውስጥም ሴቶች በስብሰባና በሌሎች ይሳተፉ እንደነበርም ይጠቁማሉ።
ሆኖም አሁን ላይ ሆነው ሲያስቡት የሴቶች ተሳትፎ እንደሚፈለገው አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ያስታውሳሉ። ‹‹ከአመራሩ ጋር በቅርበት በመሥራት በፓርላማው ሴቶች በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ አድርገናል›› ሲሉም የሚናገሩት ወይዘሮ አየለች፤ ሴቶች በዚህ መንገድ መሳተፋቸው በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳይሆኑ መሰናክል የሆኑ ሕጎችም ሆኑ ተግዳሮቶች በሌላ እንዲቀየሩና እንዲሻሻሉ በማድረጉ በኩል ፋይዳው የላቀ እንደነበርም ያስረዳሉ።
ሴቶች በፓርላማ ባገኙት የተመራጭነት ዕድል በፓርላማውም ሆነ ከፓርላማው ውጪ ያላቸው አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣም ይጠቅሳሉ። እርሳቸው ፓርላማ ለመግባት በትምሕርት ራሳቸውን ያበቁ እንደነበርም ገልፀው፤ ፓርላማውን ለመቀላቀል የበቁትም በዚህ መልኩ የትምህርት ዝግጅት ሰንቀው ራሳቸውን በማብቃት መሆኑንም ያስረዳሉ።
ብዙ ሴቶች ወደ ምክር ቤቱ ከገቡ በኋላ በትምህርት ዝግጅት በኩል ራሳቸውን ማሻሻላቸውንና ከወቅቱ ጋር አብረው በመሄድ ወቅቱ የሚጠይቀውን የትምህርት ዝግጅት ለማሟላት ብዙ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ያነሳሉ።
በምክር ቤቱ የተጣለባቸውን ኃላፊነትና የተሰጣቸውን የሥራ ድርሻ በአግባቡ ከመወጣት ጎን ለጎን በተረፋቸው ጊዜ ለትምህርት በማዋል ዘመኑ በሚጠይቀው በትምህርት ዝግጅት ሲበቁ ቆይተዋል።
በዚህ ምክንያት ከትምህርት ዝግጅት አንፃር ሴቶች በፓርላማው መጀመሪያና እሳቸው በነበሩበት ዘመን የነበራቸው ሲነፃፀር ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱንም ይናገራሉ። ከአንደኛው ምርጫ ዘመን በሌላኛው ምርጫ ዘመን ዝቅተኛ የነበረው መወዳደሪያ የትምህርት ዝግጅት እያደገ የመጣበት ሁኔታ መፈጠሩንም ያወሳሉ።
በተለይ እሳቸው በነበሩበት ምርጫ ዘመን በፓርላማ ይሳተፉ የነበሩ ሴቶች የትምህርት ዝግጅት በየትኛውም ምርጫ ክልል ከትምህርት ዝግጅት አንፃር ፓርቲዎች የሚያስቀምጡትን መመዘኛ መስፈርት መሰረት ያደረገ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ወደ አባልነት የሚመጡት ሴቶች ዝቅተኛ መስፈርት ተብሎ የተቀመጠውን መመዘኛ አሟልተው የሚገኙ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ። ይህን አሟልተው የተገኙ ሴቶች በፓርቲ ውስጥ እንደሚወዳደሩና ለውድድሩ የትምህርት ዝግጅት ብቻ ሳይሆን የሥራ ልምድንና ሌሎች መስፈርቶች ይጠየቅ እንደነበርም ያወሳሉ።
በጊዜው በሴቶች ዘንድ በነበረው የፓርላማ ልምምድ እሳቸውን ጨምሮ ሕግ በማውጣት፣ አስፈፃሚውን አካል በመከታተልና በመቆጣጠር እንዲሁም በሌሎች ተግባራት ዙሪያ የሚጣልባቸውን ኃላፊነት በሙሉ መወጣት የሚችሉበት ወቅት እንደነበርም ይጠቅሳሉ።
ወይዘሮ አየለች እንደሚሉት ፓርላማው በቋሚነት የሚንቀሳቀስ የራሱ ሰራተኞች ያሉትና ጽሕፈት ቤቱም በባለሙያ የተደራጀ በመሆኑ፤ በተጨማሪም ሴቶች ወደ ፓርላማ ሲገቡ የአቅም መገንቢያ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። በተለይ ከአቅም ጋር ተያይዞ ያሉ ሂደቶችን ሁሉ እንዲረዱና ከዚህ በመነሳትና በመታገዝም ሥራቸውን በመሥራት የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ይደረጋል። የምክር ቤት አባላት በየዘመኑ ሊቀያየሩ ቢችሉም የፓርላማው ጽሕፈት ቤት በቋሚነት ይሰራል።
በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፓርላማም ተመሳሳይ ሥራ ይሰራራል። ወደ ፓርላማው የገቡት ሴቶችም በዚሁ መልኩ አቅማቸውን ገንብተው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይደረጋል። ‹‹ሴቶችን በዚህ መልኩ ለማብቃት ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እየጎለበተ እንዲሄድ ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አየለች፤ በዚህ በኩል እሳቸው በምክር ቤቱም ሆነ በኃላፊነት በቆዩባቸው ጊዜያት የተሰሩ ሥራዎች መኖራቸው የማይካድ እንደሆነ ይናገራሉ።
ለውጡን ማምጣት የቻሉት በየምርጫ ዘመኑ የነበሩት ሴቶች የሴቶችን አቅም በመገንባትና ከኮሚቴው ጋር በቅንጅት በመሥራት መሆኑንም ያስረዳሉ። በእሳቸውና በሌሎች እህቶቻቸው በተሰራው ሥራ ለውጥ የመጣ ቢሆንም ታዲያ ለውጡ ግን በቂ እንዳልሆነና ገና ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠይቅ ይጠቁማሉ።
በዚህ በኩል በአዲስ የተደራጀውና ለሁሉም ነገር መሰረት ለሆኑት ሴቶች ትኩረት የሚሰጠው ማሕበራዊ ዘርፉ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያምናሉ። ዘርፉ አካል ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንን፣ አጠቃላይ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚያካትት መሆኑንም ይጠቁማሉ።
እንደ አገርም የማሕበራዊ ሥርዓት እንዲዘረጋ የሚያደርግ ሃሳብ መሰነቁንም ይጠቅሳሉ። አሁን እስከ ጦርነት በመዝለቅ የላላውን የማሕበራዊ መስተጋብር እሴቶችን የሚያጠናክር እንደሆነም ይገልፃሉ።
በተለይ ቤተሰብ ለማሕበረሰብ መሰረት በመሆኑ በቤተሰብ ጉዳይ ላይ መሥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ተናግረው፤ ዘርፉ በአዲሱ አዋጅ ከተሰጠው ኃላፊነቶች ውስጥም ይህ አንዱ መሆኑንም ይጠቁማሉ። የሴቶችና ወጣቶች ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲሁም የሕፃናት መብትና ደሕንነት ጥበቃንም ያካተታል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአዲሱ መንግስት ምስረታ በፊት እነዚህ ሥራዎች በሁለት ተቋም ሲሰሩ መቆየታቸውንም ያመለክታሉ።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 15 /2014