በአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጁ አልባሳትና ጫማ መሸጫ መደብሮች ውስጥ ስዘዋወር አይኔ አዳዲስ በገቡ፣ የዘመኑ ዲዛይነሮች በተጠበቡባቸው ጫማዎች ላይ አረፈ። በተለይ በወጣቶች ዘንድ ተመራጭ የሆኑ ዘመናዊ ጫማዎች በየሱቆቹ ውስጥ ተደርድረዋል።
ልክ እንደ አልባሳት ሁሉ ጫማዎችም ወቅትን ጠብቀው የሚለበሱ በጋና ክረምትን ታሳቢ ተደርጎው የሚዘጋጁ የመኖራቸውን ያህል ለተለያየ ዝግጅቶች በሚሆን መልኩም የተመረቱ ጫማዎች በመደብሮቹ ይታያሉ።
አራት ኪሎ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ፊት ለፊት ካሉ የአልባሳትና ጫማ መሸጫ ሱቆች ወደ አንዱ ገባሁ። የጊዜውን ፋሽን ልኬትን ያሟሉና ገበያው ላይ ተፈላጊ የሆኑ ጫማዎች በሱቁ ይታያሉ።
በሱቋ ውስጥ ከብር 450 እስከ 2500 ብር ድረስ ዋጋ ወጥቶላቸው ለሽያጭ የተዘጋጁ ጫማዎች በየረድፉ ተደርድረው ይታያሉ። እንደየጥራት ሁኔታቸው ዋጋቸው መጨመርና መቀነስ ይታይበታል ፤ አይነታቸው በርካታ የሆኑ ጫማዎች በተለያየ ብራንድ ተሰርተው ቀርበዋል፤ የቆዳና የስኒከር በሚል በየምድባቸው ተከፍለው ተደርድረዋል። ከብራንድ ጫማዎች የሚበዙቱ አዲዳስ፣ ፑማ፣ ስኬቸርስ፣ ጆርዳንና ናይክ የተሰኙ ጫማዎች በቁጥር ከፍ ይላሉ።
አስተናጋጆቹ ለደንበኞቻቸው እያቀረቡ ሲያስተናግዱ ተመልክቼ እኔም በተራዬ መጠያየቅ ውስጥ ገባሁ። ሀና አያሌው የሱቁ የሽያጭ ሰራተኛ ነች። ከ3 ዓመት በላይ በዚህ ሙያ ውስጥ ቆይታለች። በምትሰራበት ሱቅ ውስጥ በአብዛኛው ከቱርክና ከዱባይ የመጡ ዘመናዊ ጫማዎች ይገኛሉ። በደንበኞቿ በአብዛኛው የሚፈለጉት የውጪ ጫማዎች መሆናቸውን የምትናገረው ሀና፣ የአገር ውስጥ ስሪት ጫማዎች እንደሌሉ ታስረዳለች።
ሀና እንደምትለው ፤ የጫማ ገበያው እንደ ልብስ ገበያው ፈጣንና የመቀያየር ባህሪ ባይኖረውም ጫማዎች በየወቅቱ በአዲስ መልክ ወደ ገበያው በዲዛይነሮች ተሰርተው ይቀርባሉ፤ ተጠቃሚዎችም አዳዲስና በሌሎች ያልተለበሱ ጫማዎች ገዝተው ማድረግን ይመርጣሉ። ደንበኞቿ በአብዛኛው በወጣት እድሜ ላይ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። አልፎ አልፎ ከፍ ባለ እድሜ ላይ የሚገኙት ደግሞ የጫማ ፋሽን ተከትለው መግዛትን ይመርጣሉ።
ከወጣቶቹ በስተቀር በአብዛኛው ወደ ሱቅ የሚመጡት ደንበኞቿ ፋሽንን የሚከተሉ ሳይሆኑ፣ ትኩረታቸው በጫማው ጥንካሬና ውበት ላይ የሆነ ናቸው።
አካባቢው ላይ ባሉ የጫማ መሸጫ ቤቶች የአገር ውስጥ ስሪት የሆኑ ጫማዎች ማግኘት አልቻልኩም ነበርና ይህ ለምን ሆነ ስል ሀናን ጠየቅሁዋት። የአገር ውስጥ ጫማዎች እንደማታቀርብ የተናገረችው ሀና፣ የእዚህ ምክንያቱ ደግሞ ደንበኞቿ በአብዛኛው የሚመርጡት የውጭ ጫማዎች መሆኑ ነው። የአገር ውስጥ ጫማዎች በአብዛኛው በደንበኞቿ የማይመረጡበት ምክንያት የዲዛይን ችግር መሆኑን ጠቅሳ፣ ከውጪ የሚመጡት የተሻለ ውበትና ዲዛይን የተላበሱ መሆናቸውን ታስረዳለች።
መዓዛ ሙሉነህ እዚያው አራት ኪሎ በሚገኝ ሱቋ በጫማና ልብስ ሽያጭ ተሰማርታለች ። እሷም ሱቅ ውስጥ የአገር ውስጥ ጫማዎች የሉም። መዓዛም ለእዚህም ምክንያት ብላ የምትጠቅሰው የአገር ውስጥ ጫማዎች በብዙዎች የማይመረጡ መሆናቸውን ነው። የወቅቱን ፋሽን በተከተለ መልኩ ተመርተው ለገበያ እየቀረቡ አለመሆኑን ትጠቅሳለች።
አገራዊ ኢኮኖሚን በማጠናከር ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆኑ ወቅትን ታሳቢ ያደረጉ ጫማዎችን በአገር ውስጥ በማምረት ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን መቀነስ ለግዥው የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት እንደ አገር አቅጣጫ ተይዞበት ሊሠራበት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ገበያው አሁንም በውጭ ምንዛሪ በገቡ የውጭ ጫማዎች ተይዟል።
የአገር ውስጥ ጫማዎች በስፋት ገበያው ላይ አለመገኘት በጅምር ደረጃ ያሉት የዘርፉ አምራቾች የተሻለ ገቢ እንዳያገኙ እንቅፋት ይፈጥራል። ለአገር ውስጥ ጫማ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ገበያው ላይ ያሉ ምርቶች አብዛኞቹ ከውጪ የሚገቡ መሆናቸው በራሱ መልዕክት ያስተላልፋል።
የአገር ውስጥ ጫማ አምራቾች በተለይም የቆዳ ውጤት አምራች ኢንዱስትሪዎች ገበያው ላይ የተሻለ ምርት አምርተውና አቅርበው ከሌላው ጋር ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ መሥራት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን ያስገነዝባሉ። በገበያው ንቁ ተሳታፊ ያላደረጋቸው የሚያመርቱበት ማሽንና ቴክኖሎጂ የተሻለ አለመሆኑ መሆኑን ያስረዳሉ።
ገበያው ላይ ያሉ የአገር ውስጥ ጫማ አምራቾችም ምርቶቻቸው የዲዛይን ችግር እንዳለባቸው ያምናሉ። የኤኤ የቆዳ ውጤቶች ምርት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ኪዳኔን ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊት ለፊት እየተካሄደ ባለው ኤግዚቢሽን ላይ ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚ አቅርበዋል።
በገበያው ላይ የሚገኙት ጫማዎች በአብዛኛው ከውጭ አገር የመጡ መሆናቸው ዋንኛ ምክንያት አገር ውስጥ የሚሰሩት በውበትና በዲዛይን ተወዳዳሪ መሆን ባለመቻላቸው ነው ይላሉ። የጫማ ማምረቻ ማሽኖቹ እንደ ውጪዎቹ የተሻሉና ዘመናዊ አለመሆናቸውም ሌላው ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ። በሚሠራባቸው እቃዎች ጥራት ደረጃ ግን የአገር ውስጥ ጫማዎች በአብዛኛው የተሻሉ መሆናቸውን አቶ አለማየሁ ይገልጻሉ።
በየጊዜው የዲዛይን ለውጥ በማድረግ ለገበያ ለማቅረብ ጥረት የሚያደርጉ መሆናቸውን የሚገልፁት አምራቹ አቶ አለማየሁ፤ የተሻለ ለመሥራት ግን በዘርፉ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ማሳደግና የዲዛይን ሙያን ማስፋፋትን እንደሚጠይቅ ያስረዳሉ። በእሳቸው ኢንዱስትሪ ውስጥም በየጊዜው መሻሻል በሚያመጡ ዲዛይኖች ለመሥራት ቢሞከርም የአቅም ውስንነትና የቴክኖሎጂ አቅም በማነሱ ምክንያት የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ይናገራሉ።
በእርግጥም ከበፊቱ በተሻለ መልኩ ዲዛይነሮቻችን አዳዲስ የጫማ ሞዴሎችን በማምረትና ዲዛይናቸውን በማሻሻል ሰርተው የሚያቀርቧቸው ጫማዎች ስለመኖራቸው ከኤግዚቢሽኑ መረዳት ችለናል። ዊንታ ሁናቸው በዚያው በኤግዚቢሽኑ ላይ ተሳታፊ ከሆነች ጓደኛዋ ጋር የቆዳ ጫማ ማምረቻ ከፍታ በማምረት ላይ ትገኛለች። ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ኤግዚቢሽኑ ላይ መገኘታቸውን ታስረዳለች።
ዊንታ በአገር ውስጥ ጫማዎች ላይ የተለየ እይታ ነው ያላት። በቀደመው ጊዜ በተወሰኑ ግለሰቦች ይዘወተሩ የነበሩ የአገር ውስጥ ጫማዎች ዛሬ ላይ ተሽለውና በብዙዎች ተመርጠው ይደረጉ ዘንድ ዲዛይነሮቻችን ልዩ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ናቸው ትላለች። የአገር ውስጥ ጫማዎች የሚፈልግ ደንበኛ ቁጥር ለውጥ እያሳየ መሆኑንም ትናገራለች። ዲዛይነሮች አገራዊ ምርት ማሳደግና ገበያው ላይ የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ታነሳለች።
በአልባሳት በተለይ በባሕላዊ አልባሳት ዘርፍ ላይ በዲዛይነሮች በኩል እየመጣ ያለው ለውጥ የጫማውንም ዘርፍ ቢጎበኘው በአገር ውስጥ ጫማዎች ላይ የሚታየውን ለውጥ በማስቀጠል ዘርፉ ከውጪ የሚመጡ ጫማዎችን የሚወዳደርበትን በር ይበልጥ ክፍት ማድረግ ይቻላል። የዘርፉ ባለሙያዎች የሚጠይቁትን የቴክኖሎጂ ችግርንም የሚመለከተው የመንግሥት አካል ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በመሆን ለመፍታት መሥራት ይኖርበታል። ምክረ ሀሳባችን ነው።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም