ሌላው በዚህ ሳምንት የምናስታውሰው ክስተት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቅን ነው። አቶ ኃይለማርያም ስልጣናቸውን በቃኝ ብለው መልቀቂያ ያስገቡት በዚህ ሳምንት የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር።
ከምርጫ 97 በኋላ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ሕወሓት መር በሆነው ኢህአዴግ ላይ ይነሳ የነበረው ሕዝባዊ ቁጣ 2008 ዓ.ም ላይ ጠነከረ። በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ሕዝባዊ አመጾች ተቀጣጠሉ። መስከረም 2009 ዓ.ም ቢሾፍቱ ላይ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይትና አስለቃሽ ጭስ ብዙዎች ተገደሉ፤ ቆሰሉ። ሕዝባዊ ቁጣው እየጨመረ መጣ። ኢህአዴግ ማጣፊያው ሲያጥረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ። መፍትሔ ሊሆን ግን አልቻለም፡፡
በመጨረሻም የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመፍትሔው አካል ለመሆን ሲሉ የሥራ መልቀቂያ አስገቡ። አቶ ኃይለማርያም ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እና ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመነሳት መጠየቃቸውን የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ. ም መግለጫ ሰጥተው በይፋ ለሕዝብ አሳወቁ። የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውንም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገብተዋል።
በወቅቱ በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት፤ ከኃላፊነታቸው የሚነሱትም በአገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት እና የፖለቲካ ችግር ለማስወገድ የሚወሰደው መፍትሄ አካል ለመሆን በማሰብ መሆኑን ነበር። ለወቅታዊዎቹ የአገሪቱ ችግሮች መፍትሄ ፍለጋ ህዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ሊቀመንበርነት ለመነሳት ለግንባሩ ምክር ቤት የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውንም የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም፤ የኢህአዴግ ምክር ቤት በሚያካሂደው ስብሰባ ለጥያቄአቸው የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
አቶ ኃይለማርያም ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ዴኢህዴን) ሊቀመንበርነት ለመነሳት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ጥያቄዬን ይቀበላል ብዬ አምናለሁ ብለው እንደነበር ይታወሳል። ያስገቧቸው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤዎች ውሳኔ እስከሚያገኙ በኃላፊነታቸው እንደሚቆዩም ተናግረዋል።
የወቅቱ የ52 (አሁን 56) ዓመቱ አቶ ኃይለማርያም የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜና በሞት መለየትን ተከትሎ መስከረም 2005 ዓ.ም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደመጡ ይታወቃል። ለአምስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።
የአቶ ኃይለማርያም በራሳቸው ፈቃድ ሥልጣን መልቀቃቸውም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ተብሏል። ስልጣን መልቀቅ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ያልተለመደ ስለሆነ በወቅቱ ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበርም ይታወሳል። የመረጃ ምንጮቻችን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2014