መቼም ሆነ መቼ በአገር ሉዓላዊነትና በሕዝብ መከፋፈል የተቃጣ ጥቃት የመመከት ኃላፊነት የሚጣልበት የዚያው ዘመን ትውልድ ወጣት ነው። የካቲት 12 የፋሽስት ኢጣሊያ ጭፍጨፋንም የመመከት ኃላፊነቱ በወጣቱ ተጥሎ የነበረ መሆኑን ከአራት አሥርት አመታት በላይ አሻግሮ የሚያሳየን ጥሩ መነጽር ነው።
በወረራው በመቆጣትና እምቢኝ ለአገሬ በማለት በመሀል አዲስ አበባ ላይ ሰፍሮ ሲቀማጠል በነበረው በፋሽስት ኢጣሊያ የጦር አዛዥ በጄኔራል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ የካቲት 12፣ 1929 ዓ.ም ቦንብ በመወርወር ያቆሰሉት ሁለቱ ወጣቶች አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስግዶም የከፈሉት መስዋዕትነት ጋር በእጅጉ ይሰናሰላል። ብዙ ወጣቶች እንደሚናገሩት ታሪኩ ለአሁኑ ትውልድ ወጣቶች አስተማሪ፤ ለአገር ሉዓላዊነት ደግሞ መሠረት ጥሎ ያለፈ ነው።
ለዛሬም የኢትዮጵያ ወጣቶች ይሄን ዕለት በመዘከሩ፣ የአገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቁና የሕዝብን አንድነት በማጎልበቱ እንዲሁም በየትኛውም ወቅት ይሄን ማድረግ የሚያስችላቸውን ዝግጅት በመሰነቁ በኩል ዕለቱን በማስመልከት እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ ልናስቃኛችሁ ወድደናል። ቅኝታችን የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ እና የአማራ ወጣቶች ማህበርን የተንተራሰ ነው።
ወጣት ብርሃኑ በቀለ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ ፕሬዚዳንት እንደሚናገረው ከ84 ዓመታት በፊት በነበረው በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበረው ወጣቱ ትውልድ የአገር ሉዓላዊነትን የሚዳፈር ወራሪን ለመመከት ታላቅ ተጋድሎ አድርጎ አልፏል። የዚህ ወጣት ታላቅ ተምሳሌቶች ከእዚያ ዘመን ትውልድ የወጡት ሁለት ወጣቶች ናቸው – ሞገስ አስግዶምና አብርሃም ደቦጭ።
እነዚህ ወጣቶች በፋሽስት ወረራ በመቆጨትና በአገራቸው እና በወገናቸው ላይ እያደረሰ ባለው በደል በመቆርቆር ለሕይወታቸው ሳይሳሱ በፋሽስት ኢጣሊያ የጦር አዛዥ በጄኔራል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ አደጋ ጥለዋል። ምንም እንኳን የቦምብ አደጋው ግራዚያኒን ባይገድለውም አቁስሎታል። ወጣቶቹ ግራዚያኒን ማቁሰላቸውም ሆነ አደጋውን በዚሁ የወቅቱና የፋሽስት ታላቅ የጦር መሪ ላይ መጣላቸው በፋሽስት ዘንድ ታላቅ ቁጣ ቀስቅሶ ለ30 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ጭፍጨፋ ምክንያት ቢሆነውም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ደግሞ ታላቅ የአገር ሉዓላዊነትን የማስከበርና ቅኝ መገዛትን የመጠየፍ መነሳሳትና ቁጭትን ፈጥሮ ማለፍ ችሏል።
በየትኛውም ዘመን የነበረ ኢትዮጵያዊ ወጣት እንዲህ እንደ እነ ወጣት ሞገስና አብርሃም ያለ ስሜት ነው ያለው። ሞቱን ይመርጣል እንጂ በፍፁም በባዕድ ተረግጦና ተገፍቶ መገዛትን አይሻም። ምን አልባትም ፋሽስት ወረራው ተሳክቶለት ቢሆን መቼም መቼም አሜን ብሎ እንደማይገዛለት ከጭፍጨፋው በኋላ የያኔዎቹ ወጣቶችና የዛሬዎቹ አባቶቻችንና እናቶቻችን እምቢኝ ለአገሬ ብለው በቁርጠኝነት በመነሳት በዱር በገደሉ ብርቱና ታላቅ ተጋድሎ አድርገው ዛሬ ለሚዘከረው ድል ያበቁን መሆኑ ምስክር መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ወጣት ብርሃኑ በቀለ ወደ ኋላ መለስ በማለት የፊቱን ዘመን የወጣቶች ተጋድሎ ገድል ያወሳል።
‹‹ከዛሬ 84 ዓ.ም በፊት ፋሽስት በበቀል ተነሳስቶ በግፍ ከጨፈጨፋቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሕዝቦች አብዛኞቹ ወጣቶች ነበሩ›› ያለው ወጣቱ ሆኖም በፋሽስት እንደተወረረች ሳትቀር ደምና አጥንታቸውን ገብረው ነፃነቷንና ክብሯን ማስጠበቃቸውንና ለእስከ ዛሬው ህልውናዋም መሠረት ጥለው ማለፋቸውን ይገልፃል ወጣት ብርሃኑ።
እንደ ወጣቱ ፕሬዚዳንት በዚያን ዘመን አገርን ለመውረርና ለማስወረር የሚሠሩ አካላት ነበሩ። ፋሽስት አገራችንን ለመውረር የበቃው በነዚህ ዓይነቶቹ ከሃዲያኖች ታግዞና ተገፋፍቶ ነው። እኛ በወቅቱ ከነበሩ አንዳንድ እናትና አባቶች እንደሰማነውም አብዛኞቹ ምስጢር አውጥታችኋል በሚል ከ30ሺዎቹ ባላነሰ ጭፍጨፋ ደርሶባቸዋል። በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱን የአገር ክህደትና ወረራ ሥራ የሚሠሩ የዛሬው ዘመን ትውልድ አንዳንድ ወጣቶች እንዲሁም ጠላቶቻችን እኛም ሆንን ፕሬዚዳንቱ እንደሚለው ከየካቲት 12ቱ ሦስት ትምህርቶችን መውሰድ አለባቸው። አንዱ ወረራንና ቅኝ ግዛትን በመጠየፍ አሻፈረኝ ብሎ ራስን እስከ መስዋዕት የሚያደርስ ትግል ማድረግ ነው። ሁለተኛው አገራችን በሰላማዊ መንገድ በምትለማበት ሁኔታ በማገዝ ርብርብ ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑና በአገር ውስጥም ሆነ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ወጣቶችም ኢትዮጵያ በምንም መልኩ የማትደፈር የተመሠረተችው አገር በሚወዱና በጀግኖች ወጣቶች መሆኑን መረዳት አለባቸው። ‹‹ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚፈልጉ ራሳቸው ይፈርሳሉ ተብሏልና የትኛውም ኃይል የጀግና አገር የሆነችውን ኢትዮጵያን ማፍረስ አይችልም›› ብሏል።
ወጣት ብርሃኑ እንደሚናገረው ከዚህ አኳያ አሁን ያሉት ወጣቶች ለአገራቸው ዘብ ይቆማሉ። አሁን ያሉት የኢትዮጵያ ወጣቶች ዘብ ለመቆም የሚያስችልም ቁመና አላቸው። ምክንያቱም አገራቸው ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ፣ የአገራቸውን ታሪክ፣ የአገራቸውን አቅም፣ የአገራቸውን ባህል በሚገባ የሚያውቁ ናቸው።
ወጣቶቹ በአሁኑ ወቅትም በአገራቸው ሰላም ጉዳይ እየሠሩ ነው። ‹‹ለምሳሌ ሊጉ ከተደራጀበት አንዱ ዓላማ የሰላም ግንባታ ስልጠና መስጠት ነው›› የሚለው ፕሬዚዳንቱ ሰላም የሚያመጡ ምንድን ናቸው የሚለውንም እንደሚያካትት በአፅዕኖት ይናገራል። ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር እንደመሆኗ ከሚያካትታቸው ውስጥ ሰላምን የሚያመጡት መቻቻልና መከባበር በዋነኝነት እንደሚጠቀሱም ይገልፃል። ወጣቶች ይሄን መሠረት አድርገው የአንዱ ባህል ለሌላው ወግ መሆኑንና ምንም ዓይነት የሚበላለጥ ባህልም ሆነ ታሪክ እንደሌላቸውና የካቲት 12ን ጨምሮ ሁሉም የጋራቸው እንደሆነ መረዳት አለባቸው ሲል የሰጠንን ሀሳብ ቋጭቷል።
‹‹የየካቲት 12 ድሉም ሆነ ሁሉም የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት ነው›› ሲል በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙት የአማራ ወጣቶች ከዚሁ አንፃር በዓሉን ዘክረው ለመዋል የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ እንደሚገኙ በመግለጽ ጀምሮ ሀሳቡን ያካፈለን ወጣት አባይነህ ጌጡ የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ነው። ወጣት አባይነህ እንደሚናገረው የዚያን ዘመን ወጣቶች ዛሬ ዘመን በዘመን ላይ ሲደራረብ አባቶቻችን የምንላቸው የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል የሆነችውን ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት ነፃ አውጥተው ህልውናዋን ለዛሬው ትውልድ በማሸጋገር ሉዓላዊነቷን ማስቀጠል ችለዋል። የየካቲት 12 የሁለቱ ወጣቶች የጀግንነት ገድል ዕለት ለአገር ሉዓላዊነት ታላቅ አበርክቶ አድርጎ አልፏል። ጭፍጨፋው ፋሽስት የፈፀመው ግፍና በደል ከመሆን ባሻገር ለአብነት የሚወሳም ነገር አለው። ፋሽስት በ30 ሺህ ንፁሃን የነበሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ የፈፀመው አንድም በወጣቶቹ የጀግንነት ገድል ተደናግጦ መሆኑ፤ ሁለትም ከህልውናው ዘለቄታ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ስጋት ስለገባው እንደሆነም ጥርጥር የለውም።
ታሪክ እንደሚያወሳው ፋሽስት በንፁሃን ዜጎች ላይ አካፋን ጨምሮ ሌሎች መሣሪያዎችን በመጠቀም የበቀልና የፈሪ ዱላውን ያሳረፈው ወጣቶቹ የጀግንነት ገድል በፈፀሙበት የካቲት 12 ዕለት ብቻ አይደለም። በዚህ ዕለት የፈፀመው ጭፍጨፋ ስላላረካው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ወጣቶች አስደናቂ ተጋድሎ ስለሰጋም ማግስቱን ሙሉ ጨምሮም ነበር። በወቅቱ በዚህ ጭፍጨፋ በመቆጣት የአማራ ወጣቶችም ከሌሎች አካባቢ ተወላጅ ወጣቶች ጋር እኩል ተጋድሎ ያደረጉበት ሁኔታ አለ። የአማራ ወጣቶች ማህበር ይሄን ትግል በየካቲት 12 ቀን 2014 ዓ.ም እንደአገር ዘክሮ ለመዋል የተለያዩ ዝግጅቶች አድርጓል። ከዝግጅቶቹ መካከል የስነጽሑፍ ሥራዎች እንዲሁም ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡባቸው መድረኮች ይጠቀሳሉ። በወቅቱ ምን ምን ጀግንነቶች እንደተፈጸሙ ይወሳል።
‹‹እንዲሁም በእነዚህም ሆነ በሌሎች ዝግጅቶች ወጣቶች ከዚህ በፊት የነበረው የአገራቸው ታሪክ ምን እንደነበረ እንዲያውቁ ይደረጋል›› የሚለው ወጣት አባይነህ ሁለተኛው ከፊቶቹ በተሻለ መንገድ የአሁኖቹ ወጣቶች አገር እንዲያስቀጥሉ መሥራት ነው። አገር ማስቀጠል የሚቻለው በቀላሉ እንዳልሆነና አሁን ያለችውን አገር ለማስቀጠል የያኔዎቹ ወጣቶች አባቶቻችን የዛሬ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ብዙ ዋጋ ከፍለው እንደሆነ እንዲረዱ የማድረግ ሥራ ይሰራል። በዚህ ረገድ በዓሉ ታስቦ ሲውል ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ጀግኖች አርበኞች አባቶች እንደሚሳተፉም ነው ወጣቱ ሊቀመንበር ያወጋን።
ዝግጅቱ የዚህ ዘመን ቀጣይ ወጣት ያለፈውን ታሪክ እንደመነሻ በመውሰድ አገሩን እንዴት መጠበቅ እንደሚገባው ተሞክሮ የሚወስድበት መሆኑንም ወጣት አባይነህ ያስረዳል። የአማራ ወጣት አገራችን ሳትፈልግ ሕግ ለማስከበርና ሕልውናዋን ለማስጠበቅ በገባችበት ጦርነት የወጣቱ ሚና የጎላ ነበር። ወራሪውና ተስፋፊው የሕ.ወ.ሓ.ት ቡድን የአፋርና የአማራን ሕዝቦች አያሌ መሠረተ ልማቶችን አውድሟል። የመብት ጥሰቶች አድርሷል። ብዙ በደሎችን በአማራ ላይ ፈፅሟል።
በተለይ በሕግ ማስከበርና በሕልውና ዘመቻው ወቅት እያንዳንዱ ወጣት በሚችለው አቅም አስተዋጽኦ ማድረጉንም ሊቀመንበሩ ያወሳል። ወጣቱ ይሄን አስተዋጽኦ ያደረገው በተለይ ባለበት አካባቢ የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር ተደራጅቶ አካባቢውን በመጠበቅ እንደሆነም ያሰምርበታል። ከዚሁ ጎን ለጎን ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለሚሊሺያዎች፣ ለልዩ ኃይሎች ካለው ከዕለት ጉርሱ እየቀነሰ ድጋፍ ሲያደርግም ቆይቷል።
‹‹ወጣቱ ራሱ የትግሉ አካል ሆኖ የአካልና የሕይወት መስዕዋትነት ከፍሏል›› የሚለው የወጣት ማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት አባይነህ በመከላከያ ሠራዊትም ሆነ በሚሊሺያና በልዩ ኃይል የገባው ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል መሆኑን አበክሮ ይናገራል። ከዚህ በመነሳት በዚህ አሁን ባለንበት ዘመን ያለ ወጣት አገር የማስቀጠል ፍላጎቱ ራሱን አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ የዘለቀ ነው ማለት ይቻላል ብሏል ወጣት አባይነህ ጌጡ። እኛም እንዲህ ዓይነቱ ተሞክሮ ይደግ ይመንደግ! ከዛሬ 84 ዓመታት በፊት በሁለቱ ወጣቶች ሞገስ አስገዶምና አብርሃም ደቦጭ በተሰኙት ሁለት አገር ወዳድ ወጣቶች ከተፈፀመው አኩሪ ፍፁም የአገር ፍቅር የተላበሰ የጀግንነት ገድል የአሁኑ ወጣት ትውልድ ትምህርት ይውሰድ! የየካቲት 12ቱን የድል በዓልም ይዘክር፣ ታሪኩንም ያጉላና ያስታውስ በማለት ተሰናበትን፡፡
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2014