ወረቀትና ጋዜጦች ሲበታተኑና ሲከማቹ ምን ዓይነት ድብርትን እንደሚፈጥሩ በቤታችን ብቻ መረዳት እንችላለን፡፡ ቢሮ ሲሆን ደግሞ ክብደቱን የቢሮ ሠራተኛው ይናገረው፡፡ ከድብርቱ ባለፈ በጤናችን ላይ ብዙ ዓይነት ችግር ይፈጥራል፡፡ የመጀመሪያው በጠረኑ ብቻ ለብዙ በሽታ ማጋለጡ ሲሆን፤ በተለይ ቀደም ሲል እንደ አስምና ሳይነስ ያለበት ሰው ይህንን ጠረን መቋቋም ይከብደዋል። በዚህም ዓይነት ተጋላጭ የሚሆነው እርሱ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርበት ሥራው ላይ የሚሰማሩ የጽዳት ሠራተኞች ምስክር ናቸው፡፡ ስንቶች ታመው እንደተኙም በየመሥሪያቤታችን እናውቀዋለን፡፡ እኛም ብንሆን መረጃ ፈልገን በማገላበጣችን ብቻ ምን ያህል እንደምንታመም ነጋሪ አያሻንም፡፡
ሌላው የወረቀት ችግር ሲቃጠልና ሲቀበር የሚያመጣው ነው፡፡ ብዙ ኬሚካልን በውስጡ ስለሚይዝ ሲቃጠል አየር ይበከላል፡፡ ሲቀበር ደግሞ የአፈር ለምነትን ይቀንሳል፡፡ ታዲያ ለዚህ መፍትሄ አለን የሚል ድርጅት ስንሰማ እንዴት ማለታችን አልቀረም፡፡ በእርግጥ ድርጅቱ ለዚህ ብቻ ሳይሆን መፍትሄን የቸረው በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ላሉ እናቶችም ጭምር ነው፡፡ እናም ለዛሬ መፍትሄ ሰጪውን አካልና ተጠቃሚዎቹን እናቶች በማነጋገር ልናወጋችሁ ወደናል፡፡ መልካም ንባብ ተመኘን፡፡
መፍትሄ አለን ሲሉ የተነሱት አምስት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ አንዴ ማማ ማኒፋክቸሪንግ ፒ.ኤል.ሲ በሚል ስም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ፕሮጀክታቸው ደግሞ የእናት ፍቅር የሚል ነው፡፡ እናም ወረቀትን ሰብስቦ እናቶችን ወደ ሥራ በማስገባት መደገፍን አልመው ይሠራሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የአየር ንብረት ብክለትንና የመሬት ለምነትን ያስጠብቃሉ፡፡ ስለዚህም ሦስት ነገሮችን በማገናኘት መፍትሄ የመስጠት ተልዕኮን አንግቧል፡፡ እነርሱም ተቋማት፣ እናቶችና የአየር ንብረት ጥበቃ የሚሉ ናቸው፡፡
በተቋማት ያሉ ሠራተኞች በተለይ ከወረቀት ጋር በስፋት ግንኙነት ያላቸው ሠራተኞች አወጋገዳቸው የጸዳና ጤናማ የሚያደርጋቸውን ሁኔታ የሚፈጥር ሲሆን፤ እናቶች ደግሞ በዚህ ወረቀት የእጅ ሙያቸውን ተጠቅመው የገቢ ምንጫቸውን እንዲያገኙ ያደርጋሉ። በዚህም የሚቃጠል፣ የሚቀበርና የሚከማች ወረቀት አይኖርም፡፡ የአየር ንብረቱም በዚህ ሁኔታ ነው የሚጠበቀው፡፡
ከመስራቾቹ አንዱ የሆነችው መቅደስ ተሾመ ስለዚህ ድርጅት አላማና የቀጣይ እቅድ እንደነገረችን፤ ይህ መፍትሄ ሰጪ ፕሮጀክት ‹‹የእናት ፍቅር›› ይሰኛል። ሥራውን የጀመረው ከዓመት በፊት ነው፡፡ ከስያሜው እንደምንመለከተው ዋና ህልሙ በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ያለችን እማማ ብለን የምናቆላምጣትን እናት ቀና ማድረግ ነው፡፡ እናት ከነበረችበት ደረጃ አንዴ እንኳን ከፍ ካለች ብዙ ነገሮችን ትለውጣለች የሚል እምነት ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡ ስለዚህም ምሳሌነቷን ማስፋት ላይ አተኩሮ ይሠራል፡፡
እናት የሁሉም ናት፡፡ በዚህም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ለሁሉም ትደክማለች፡፡ ስለዚህም ሁሉንም ያሳተፈ ሥራ ለመከወን የቀን ገቢያቸው ከ80 ብር በታች የሆኑ እናቶችን መርጠው ወደ ሥራ እንዲገቡ ሆነዋል፡፡ ይህ ሲሆን ጎን ለጎን የአየር ንብረቱንና የመሬት ለምነቱን እያስጠበቁ እንደሆነ የምታስረዳው መቅደስ፤ ተግባሩ እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ ጭምር የሚቀጥል መሆኑን ነግራናለች፡፡
ሥራውን አሀዱ ያሉት መፍትሄ በመስጠት ብቻ ሳይሆን የሥራ እድልም በመፍጠር ጭምር እንደሆነ የምትገልጸው መቅደስ፤ ፕሮጀክቱ 20 ሺህ ቶን ወረቀትና ጋዜጣ መሰብሰብ ላይ ሲደርስ 1050 እናቶችን ይይዛል። በተጨማሪ 500 ወጣት ሥራ አጦችንና 100 የሚሆኑ የጽዳት ሠራተኞች ለወረቀት ስብሰባ ሥራው እንዲያግዙ የሚካተቱበት ይሆናል፡፡ አሁን ላይ መሰብሰብ የተቻለው አነስተኛ በመሆኑ 63 እናቶችን በማሳተፍ ተግባሩ ተጀምሯል፡፡ ከሥራ አጥ ወጣቶች ደግሞ 25 የሚሆኑት ሥራ እንዲጀምሩ ተደርገዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አጋር የሚሆኑ 52 ተቋማት እንደተሳተፉበትና ይህ በቂ እንዳልሆነ ታስረዳለች፡፡
ይህ ቁጥር እንደ መጀመሪያ እቅድ የተያዘ መሆኑን የምታነሳው መቅደስ ተቋማት በራቸውን ከከፈቱ ብዙ እናቶችን አቅፎ መሥራት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሥራው አዋጭነት እጅግ የሚያግዝ ነው፡፡ ምክንያቱም የእጅ ጥበብ ውጤቶቹ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ጭምር የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ተፈላጊነታቸውም አሁን ባለው ሁኔታ እንኳን እጅግ ሰፊ ነው፡፡ እናም ለእናቶች ድጋፍ ሲሉ ተቋማት እየተጨናነቁበት ያለውንና ለጤናቸው ጠንቅ የሆነውን ወረቀት በማስረከብ ብቻ አጋዥነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ ታቀርባለች፡፡
በእናት ፍቅር ፕሮጀክት ውስጥ እናቶች የገበያው አምባሳደር ሆነው በመሄዳቸው ብዙ ተቋማት ፈቃደኝነታቸውን እየቸሩ እንደሚገኙ የምትገልጸው መቅደስ፤ ለእናቶች የሚፈጠረው የሥራ እድል በእጅ ሥራው ብቻ ሳይሆን በወረቀት መሰብሰቡም ስለሆነ ጉዳዩን ተቋማቱ በሚገባ ተገንዝበው በራቸውን ሊከፍቱ እንደሚገባም ታሳስባለች፡፡
የአንዴ ማማ ድርጅት እናቶችን ሲያግዝ በተለያየ መልኩ ሲሆን፤ የሥራ እድሉን በመፍጠርና መሥራት የማይችሉ እናቶችን ደግሞ ዝም ብሎ በማገዝ ነው።በእርግጥ እነዚህ እናቶችም ሆኑ መሥራት የሚችሉት በድርጅቱ አማካኝነት ሳይሆን የተመረጡት ወረዳዎችና ተቋማት ነው፡፡ የተሰጧቸውን እናቶች ነውም እነርሱ በዘየዱት መልኩ እገዛን እንዲያገኙ የሚያደርጉት።ስለዚህም የእናት ፍቅር ፕሮጀክት ለሁሉም እንደሆነ በዚህ ተግባር ታይቷልም ትላለች፡፡
ብዙዎች በቅርብ ያለ ሀብታቸውን አያዩትም፡፡ ይህ ፕሮጀክት ግን እናቶችን ቀና አድርጎ፣ አየር ንብረትን ጠብቆ ፣ ጤናችንን ተንከባክቦ ውጤት ያስገኛል የምትለው መቅደስ፤ እንዲህ መተሳሰራችንን በሌላም መድገም ይቻላልና ዓይናችን የቅርባችን ላይ ያማትር፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለች ብዙ ሀብት ያላት አገር ብዙ እናቶችንና ወጣቶችን ማትረፍ ትችላለችና ሀብታችን ሳይባክን እንጠቀምበትም ስትል ትመክራለች፡፡
ሌላው በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጠን የማህበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት እንዲሁም የቴክኖሎጂና ዲዛይን ባለሙያው ኤፍራተስ አዳነ በበኩሉ እንደሚለው፤ ይህ ፕሮጀክት እናቶች የገቢ ምንጫቸውን ከቤታቸው ሳይወጡ በትርፍ ሰዓታቸው የሚያሳድጉበት ነው። ከድብርት ተላቀውና አቅማቸውን አጎልብተው የሚሠሩበትም ነው፡፡ በወር 1200 ብር እያገኙ በትንሹም ቢሆን ጎዶሏቸውን ይሞላሉ፡፡
ከዚያ በተጨማሪ የእናት ፍቅር 17 ዘላቂ የልማት ግቦችን አልሞ የሚሠራና አገሪቱን ወደ እድገት ጎዳና የሚያራምድ ፕሮጀክት ነው።ምክንያቱም ብዙዎቹ በትንሹም ቢሆን በውስጡ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የእድገት ጥቋሜውን ከ0 ነጥብ 8 በላይ ማድረግ ፤ ድህነትን መቀነስ፤ የሥራ እድል መፍጠር፤ አህጉራዊ ትስስርን ማስፋትና የጾታ እኩልነትን ማምጣት የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ቀጣይነት ያለው ከተማ መፍጠርም አንዱ የልማት ግቡ አላማ ነው። ስለሆነም እነዚህን ተግባራት እየከወነ በመሆኑ ጠጠር ወርዋሪ ያደርገዋል፡፡
ወደ እድሉ ተጠቃሚዎች ስንገባ ደግሞ መጀመሪያ ያነጋገርናት ወይዘሮ የሻረግ ፍትጉ ስትሆን፤ ተመርጣ የመጣችው ከቂርቆስ ክፍለከተማ የድሃ ድሃ በሚል ነው፡፡ ለዚህ ያበቃት ደግሞ ብዙ ምክንያት እንደነበረ ታነሳለች። የመጀመሪያው የነበረችበት ሕይወት ብዙ ልፋትንና ዱላ ቀረሽ ትግልን የሚጠይቅ መሆኑ ነበር።ሁለት ልጆቿን ለማሳደግ ብዙ ጊዜ በደንቦች ንብረቷ ተወስዷል። በዱላም ተደብድባ የምታውቅበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። በዚያ ላይ የመንገድ ላይ የልብስ ንግዱ ብዙ ፈተና የበዛበት ቢሆንም በቂ ገንዘብም አያስገኛትም፡፡ በዚህም እርሷ ሳትበላ ልጆቿን በመመገብ ዓመታትን አሳልፋለች። እንዲያውም ባለቤቷ ኖሮ ባያግዛት ይህም ጊዜ እንደማይታለፍ ታነሳለች፡፡
የኮሮና ጊዜ እጅግ የተሰቃየችበትና በጣም የማይረሱ ፈተናዎችን ያለፈችበት እንደነበር የምታወሳው የሻረግ፤ የልጆቿን ጉሮሮ ለመሙላት በጽዳት ሠራተኝነት በሰው ቤት ተቀጥራ ታገለግል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሁሉ ነገር ቦታ ቦታ ይዞላታል፡፡ ምክንያቱም ያንን ሕይወት ስታሳልፍ የሚያውቃት ክፍለከተማ በዚህ እድል ተጠቃሚ እንድትሆን መርጦ ልኳታል፡፡ በዚህም አንዴ ማማ ድርጅት ውስጥ በቤቷ ሆና በእረፍት ጊዜዋ የምትሠራውን ሥራ አግኝታለች፡፡ ሥራው ወረቀት መጠቅለል ሲሆን፤ ተገቢውን ስልጠና አግኝታ የምትከውነው ነው፡፡ ደስተኛም ሆና እንደምታደርገው አጫውታናለች፡፡
ሌላዋ ያነጋገርናት ሴት ወይዘሮ ብርቱካን አድማሱ የምትባል ሲሆን፤ እንደ የሺሀረግ ሁሉ በክፍለከተማ ተመልምላ የገባች ነች፡፡ ከአረብ አገር ተመላሽ ስትሆን በሕገወጥ መንገድ ሄዳ ታስራ በመመለሷ ከስህተቷ ለመማርና በአገሯ ሠርታ ለመለወጥ እየተጋች ባለችበት ሁኔታ ነው ይህንን እድል ያገኘችው፡፡ በእርግጥ እዚህ ከመግባቷ በፊት ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ገጥመዋታል፡፡ አንዱ ኑሮ ጠብ አለማለቱ ሲሆን፤ ዳግም መመለስንም አሳስቧት ነበር፡፡ ነገር ግን በአንዴ ማማ ድርጅት ውስጥ መካተቷ ይህንን ሀሳቧን እንድትቀይር አድርጓታል፡፡ ምክንያቱም ይህ ድርጅት በብዙ ነገር ገንብቷታል፡፡
አንዴ ማማ እውነትም የእናት ፍቅር የሚታይበት ቦታ ነው የምትለው ብርቱካን፤ የሥራ እድልን ከመፍጠሩ ባሻገር በስልጠናው የመቻልን ልኬት አሳይቶኛል። ጥንካሬንም ሰጥቶኛል፡፡ በዚህም አይበገሬነቴን እያሳየሁበት እገኛለሁ፡፡ የወረቀት መጠቅለል ሥራውን በትርፍ ጊዜዬ ስለማደርገው የሚቸግረኝ ነገር አይኖርም፡፡ ተጨማሪ ሥራዎችን እየሠራሁ ከባለቤቴ ጋር እየተጋገዝሁ ልጆቼን እያሳደግሁ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ውስጥ ላሉትም ሆነ በውጪ ለሚኖሩ እናቶች የምመክረው ማንም ሰው ያለውን መጣል የለበትም፡፡ በአገር ላይ ሠርቶ መለወጥ ከምንም በላይ ያስደስታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ልዩ ተሰጥኦውን መያዝና እድሎችን ለለውጥ መሠረት ማድረግ ይገባዋል ትላለች፡፡
እናት ወይዘሮ ልክነሽ ጌጡም እንዲሁ በተቋም ተመልምለው የገቡ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ የሻረግና ብርቱካን በሥራ ላይ የተሰማሩ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አቅመ ደካማ ብቻ ሳይሆኑ የስኳር በሽተኛም ናቸው። በዚያ ላይ የራሳቸውን ልጅ ከማሳደግ አልፈው አንዷ ልጃቸው በሞት ስትለይ የልጅ ልጆቻቸውን ጨምረው እንዲያሳድጉ ተገደዋል፡፡ እናም ሁሉንም መግበው ለማደር የማይቆፍሩት ድንጋይ የለም፡፡ ሰው ቤት በተመላላሽነት ልብስ ያጥባሉ፡፡ የጽዳት ሥራም ይሠራሉ።
ግን መቼም የአሰቡት ሞልቶላቸው አያውቅም፡፡ ሁሌ በችግር ውስጥ ቤተሰባቸው ያልፋል፡፡ በተለይም የሚበላ የሚጠጣ የማይኖርበት ጊዜ ላይ ሲሆኑ እጀግ ያማቸዋል። እርሳቸው የስኳር በሽተኛ ሆነው ሳለ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው መመገብ ምን ያህል ከባድ እንደሆነም ያለፈበት ይናገረው፡፡ ግን ዓመታትን በዚህ ሁኔታ አሳልፈዋል፡፡ አሁን ግን አንዴ ማማ ደርሶላቸዋል። ቢያንስ የተወሰነ ድጎማ ስለሚያገኙ በትንሹም ቢሆን እፎይ ብለዋል፡፡
ወይዘሮ መሳይ ዘውዱም እንዲሁ በአንዴ ማማ የሚደገፉ እናት ናቸው፡፡ የዲስክ መንሸራተት ተብለው በህክምና እየተረዱ ያሉ ሲሆኑ፤ ቤታቸውን ለመሙላት ያለአባት ልጃቸውን ለማሳደግ ይጥራሉ፡፡ ሰው ቤት እየሠሩ ነበር የልጃቸውንም ሆነ የእርሳቸውን ሆድ የሚሞሉት፡፡ ነገር ግን አሁን በህመማቸው ምክንያት ይህንን ማድረግ አልቻሉም፡፡ በአንዳንድ ሰዎች እገዛ ነበር አንዴ ማማ እስኪያገኛቸው ድረስ የኖሩት፡፡ አሁን ደግሞ ክፍለከተማ መርጧቸው በድርጅቱ እንዲረዱ ሆነዋል፡ ፡ በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ እነዚህና መሰል እናቶች የሚደገፉበት ይህ ፕሮጀክት ወረቀትን አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ እናም ተቋማት ለዚህ በጎ ተግባር እጃቸውን እንዲዘረጉ መልዕክታችንን እያስተላለፍን ሀሳባችንን ቋጨን፡፡ ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2014