ፍፁም ለሕይወቷ ሰስታ አታውቅም። የተገኘችበት ጦርነት አካሏንና ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም ምስሉን በካሜራዋ ለማስቀረት ቅድሚያ በመስጠት የተጣለባትን ኃላፊነት በቆራጥነትና በጀግንነት ስትወጣ ቆይታለች።
በተለይ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ የጥፋት ቡድኑ በሴቶች ላይ ያደረሰውን ግፍና በደል በካሜራዋ በማስቀረት ብቸኛዋ ሴት ነበረች። የፊቷ ቀለም ከአለባበሷ ጋር ተዳምሮ ስትታይ ፈረንጅ ያስመስላታል።
ሆኖም በሙያዋ አሜሪካንን ጨምሮ የባህር ማዶውን ዓለም ደጋግማ የመጎብኝት ዕድል ብታገኝም በአባቷም በእናቷም ንፁህ ኢትዮጵያዊ ሀበሻ መሆኗን ትናገራለች። በመልኳ የተነሳ አገር ውስጥ በየጊዜው የሚገጥማት ገጠመኝ የከፋ ባይሆንም አስቸጋሪ እንደነበርም ታስታውሳለች።
በቅርቡም በሕግ በማስከበር ዘመቻው ወቅት የገጠማት ይሄው ነበር። አማርኛ አቀላጥፋ መናገሯ ከከፋ አደጋ እንደታደጋትም ነግራናለች። የዛሬ እንግዳችን ዕውቋና አንጋፋዋ የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ፀሐይ ንጉሴን በዚሁ ዙሪያ አነጋግረን የሚከተለውን ጽሑፍ አጠናቅረናል።
ፀሐይ በሙያው የተሰማራችው ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ነው። አብዛኛውን የሥራ ጊዜዋን ያሳለፈችው ደግሞ አሁን እየሰራችበት በምትገኘው በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው። ከሥራ ቆይታዋ በኢትዮ-ኤርትራ እና በቅርቡ በተካሄደው የሕልውና ዘመቻ የተሳተፈችበት ታሪክ ይጎላል።
በሁለቱም ጦርነቶች መካከል በተገኘችበት ወቅት ቅልጥ ባለ ጦርነት መካከል ለሕይወቷ ሳትሳሳ በካሜራዋ ምስላቸውን ቀርፃ የማስቀረት ዕድል አግኝታለች። ለፀሐይ ሁለቱም ጦርነቶች ስማቸው ተመሳሳይ ይሁን እንጂ በእጅጉ ይለያያሉ።
የጦርነት ደግ የለውም ቢባልም እንደ ሕልውና ዘመቻው በሴቶችና በንብረት ላይ የከፋ ድርጊት የተፈፀመበት ጦርነት በዓለም ላይ መካሄዱን አይታም ሰምታም አታውቅም። እንዲህ ዓይነት አሰቃቂና ዘግናኝ፤ ደግሞም አሳፋሪ ድርጊት የተፈፀመበት የጦርነት ግጭት ወደፊትም ይኖራል ብላ አታስብም።
ከዚህ አንፃር የኢትዮ ኤርትራው ጦርነት በብዙ አንፃር የተሻለና በሰለጠነ መንገድ የተካሄደ ነው ብሎ መናገር እንደሚቻልም ትጠቅሳለች። ፀሐይ ወጓን የጀመረችልን ሁለቱ ጦርነቶች እንዴት እንደሚለያዩ በመግለፅ ነው።
ቀደም ሲል ምንም ያክል በደም የተገመደ ግንኙነትና የሚያስተሳስራቸው ታሪክ ቢኖርም ኢትዮጵያና ኤርትራ የተለያዩ ሁለት አገራት ነበሩ። ጦርነቱ ጠመንጃ ተይዞ የሚካሄደውም በነዚህ ሁለት አገሮች መካከል ነው። ውድመት ይደርስበት የነበረው ንብረትም ሆነ ተጎጂ ይሆን የነበረው ሰው በጦርነት ውስጥና በዚሁ ክልል አካባቢ የሚገኝ ብቻ ነበር። አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ሕፃናትና ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገም አልነበር።
በአጠቃላይ የኢትዮኤርትራ ጦርነት በየትኛውም ዓለም ላይ ያለና የተለመደ ነበር ማለት ይቻላል። የሕልውናው ጦርነት ግን ሀገርን በካዱ በጥፋት ኃይሎችና በአገር ወዳድ ሕዝቦችና በመንግሥት የሚካሄድ በመሆኑ ከዚህ በእጅጉ ይለያል። ከኤርትራውያኑ ጋር የቀለም ልዩነት አለን ባይባልም ታድያ፤ በሕልውናው ጦርነት ግን ባንዳዎችን ሰበብ አድርጎ ከሚዋጋን የውጭ ጠላትም ጋር ነበር።
“ጦርነቱ አስከፊ የሚያስብለው በአሸባሪው ቡድን የተደረገው አካሄድ የሰለጠነ መንገድ የተከተለ አልነበረም። የጥፋት ቡድኑ ሙሉ ትኩረቱን ያደረገው ማውደም ላይ ብቻ ነበር። በዚህም የትኞቹንም የልማት ተቋማት አውድሟል። ከአፀደ ሕፃናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ያሉ የትምህርት ተቋማትን እና የጤና ጣቢያዎችን ከጥቅም ውጪ አድርጓል።
የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ እንዲሁም ከሆቴል ጀምሮ የሕዝብ መገልገያዎች፣ መኖሪያ ቤቶች ሁሉ አልቀሩትም።” እነዚህ ተቋማት የእነሱም ልጆች የሚማሩባቸውና የሚታከሙባቸው እንዲሁም የሚጠቀሙባቸው ቢሆኑም የትምህርትና የጤና ተቋም መገልገያ ቁሳቁሶች ኮምፒውተር፣ መቀመጫዎች ተሰባብረዋል ትላለች። ሌላው ቀርቶ ከሸክላ ድስትና የእንጀራ መሶብ አንስቶ ቴሌቪዢን እና ሌሎች ዕቃዎች በጥይት ተመትተው፣ ተሰባብረው፣ ደቅቀው በየቦታው ይታያሉ። የመኪናና ንብረት ቃጠሎ ሁሉም ቦታ አለ።
ሌላው ቀርቶ አንድ ጭነት መኪና ሙሉ የተከካ ሽሮ፣ እህል ያቃጠሉበትን ሁኔታ አይታ ምስሉን ቀርፃ አስቀርታለች። ሸዋ ሮቢት በቃላት ከሚገለፀው በላይ እጅግ ወድማለች። ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ወድሟል። ባለቤቱ ከነልጆቹና ከነሚስቱ ከፎቁ ሥር ቆፍሮ ተደብቆ በመተኛት ቢተርፍም ፎቅ ቤቱ ከነሙሉ ዕቃው ዓመድ ሆኗል። ከሸዋ ሮቢት ጀምሮ ሁሉም የጤና ተቋማት ወድመዋል።
አልሰበር ያለ አልጋ ተቀምጦ ቢታይም ኮምቦልቻ ላይ ከተገነባና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ስድስት ወር የሆነውን ሆስፒታል ከነቁሳቁሱ ዓመድ እንደሆነ አስተውላለች። ‹‹መርሳ ሆስፒታል ወድሟል። ሐኪምም መድኃኒትም የለም። ሆኖም ግራ የገባቸው ቤተሰቦቿ አንድ ታማሚ በጋሪ አምጥተው ሜዳው ላይ ቁጭ አድርገዋት ሳይ ከልቤ አዘንኩና አለቀስኩ›› ብላናለች ፀሐይ።
ወገል ጤና ደላንታ ወረዳ ውስጥ ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ በመውደማቸው መንቀሳቀስ አቅቷቸው በዱላ እየታገዙ ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩ ታማሚዎችም አንጀቷን በልተዋታል። ከሚሴ የነበሩ ሁለት ትላልቅ ሆቴሎች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን ወሎ ሐይቅ አካባቢ ያስተዋለችው ደግሞ ከዚህ ተቃራኒውን ነው። ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ ዘመድ አዝማድና እነሱን ያለ ሁሉ ተጠራርጎ ጦርነቱን ሽሽት አንድ ቦታ መሽጎ ነበር። ቦታው ቀጥ ያለ ዳገት ነው።ዳገቱ ርዝመቱ ተወጥቶ አይልቅም።
መኪና ስለማይገባ እነሱ የወጡት ላባቸው እየተንጠፋጠፈ ረጅም መንገድ ተጉዘው ነው።ሰዎቹ እዚህ ቦታ የተደበቁት የጥፋት ቡድኑ አይደርስብንም ብለው አስበው ነበር። ሆኖም እንዳሰቡት አልሆነም። ፀሐይ ከቦታው ስትደርስ፤ አንዲት ልጅ ያቀፈች ሴት ብቻ ስትቀር ሁሉንም ፈጅተዋቸው አግኝታ ምስሉን በካሜራዋ ማስቀረት ችላለች። ሰዎች ሙታንን መቅበር እንኳን አልተፈቀደላቸውም ነበር። ማልቀስም አይፈቀድላቸውም ነበር።
ብዙ ቦታ እንዲህ አድርገዋል። ብዙዎች ኢንተርቪው ሲደረጉ የጥፋት ቡድኖቹ ዕውነት ለቅቀው የሄዱ ሁሉ አይመስላቸውም ነበር። አሁን እዚህ ነበሩ እያሉ ዙሪያ ገባውን በፍርሃት ይገላምጣሉ።
እነ ፀሐይ ሲደርሱ ግን ከየጎጇቸው እየወጡ ወገን መጣልን ብለው እልል ሲሉ እና አሁን ማልቀስም ሆነ የሞተብንን መቅበር እንችላለን ሲሉ እንደነበር ታስታውሳለች።
በአጠቃላይ ሞት እንደ ቀላል ነገር ነው የሚታለፈው። በየቦታው የጅምላ መቃብር በብዛት ይታያል። ወሎ ዩኒቨርስቲ አካባቢም እንዲሁ የጅምላ መቃብር ይታያል። ከሞት የተረፈው ሌላው ሰው ደግሞ ከቀብሩ አጠገብ ቁጭ ብሎ ሕይወቱን ለማቆየት ሸንኮራ ሲበላ ስታይ የማይታምን ትንግርት ይመስላል ትላለች ምስሉን በካሜራዋ እንዳስቀረች እየተናገረች። ‹‹ጥፋቱ ሲታይ በቀጥታ ለውድመት ብቻ የተዘጋጀ ጦርነት ነው የሚመስለው።
የንብረትና የዘር ማጥፋት ተፈፅሞበታል›› የምትለው የካሜራ ባለሙያዋ በተመልካቹ አዕምሮ ለምን እንዲህ ይሆናል? ለምን አስፈለገ? የሚል አስደማሚ ጥያቄ ያስነሳ መሆኑንም ትናገራለች። ‹‹ድርጊቱን ስመለከተው በእኔ አእምሮም ያቃጨለው እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ ነበር›› ብላናለች። የሕልውና ዘመቻው በግ፣ ዶሮ፣ ውሻ ሁሉ በጥፋት ቡድኑ በጥይት ተደብድቦ የተገደለበት ጦርነት እንደነበረም አልዘነጋችውም።
የጥፋት ቡድኑ ግፍና ጭካኔ በፍፁም ልኬት አልነበረውም። በተለይ ገጠር ውስጥ ብዙ አረጋውያን ሴቶች ሆን ተብሎ የጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ መደረጉን ታዝባለች። አቅምና ጤና የሌላቸው ደካማ እናቶች እንጨት ሰብረው፣ ውሃ ቀድተው፣ ወፍጮ ቤት በመሄድ እህል አስፈጭተው የሚያቀርቡላቸውን ልጆቻቸውን እንዲያጡ ተደርጓል። በተጨማሪም ሰሜን ሸዋ ዞን መዘዞ አካባቢ የታዘበችውንና የገጠማት ጥሩ ማሳያ ይሆናል ብላ አጫውታናለች። እንዳወጋችን ታድያ መዘዞ አካባቢ እንዳጋጠማት አንዲት ዕድሜያቸው የገፋ እናት የነበራቸው አንድ ልጅ ነበር። እሳቸው አቅመ ደካማና ታማሚ በመሆናቸው ውሀ ቀድቶና እንጨት ሰብሮ ከማምጣት ጀምሮ እህል አስፈጭቶና ሁሉን ነገር ገዝቶ የሚያቀርብላቸው እሱ ነበር።
‹‹ነገር ግን አትግደሉብኝ ብዬ እየወደቅኩና እየፈረጥኩ ብለምናቸውም አልማሩልኝም ገደሉብኝ›› አሉኝ ብላናለች። አዛውንቷ እንደነገሯት ከሌሎች ጎረምሳ ልጆች ጋር አንድ ቤት ውስጥ ሰብሰብ ብለው አግኝተዋቸው ነው ከፊታቸው የገደሉባቸው። ፀሐይ እንደምትለው እኝህ እናት ጎስቋላ ናቸው። ያለቻቸው የለበሷት አንዲት ቀሚስ ብቻ ነች። እሷም አርጅታለች።
ከአንድ ብርድ ልብስ ውጪ የሌሊት ልብስ ስለሌላቸውና ሌሊትም ቀንም እሷን ስለሚለብሱ ተቀዳዳና ተጣጥፋለች። በዚህ ላይ አካባቢው ብርዳማ ነው። እንኳን ያለ ብርድ ልብስ ብርድ ልብስ እንኳን ተደራርቦ ተለብሶ ብርዱ እጅግ ያንዘፈዝፋል። እንጨት ሰብሮ በማምጣት የሚያሞቃቸው ልጃቸው ነበር። ግን ደግሞ አብዝቶ የሚያሳዝነው የጥፋት ቡድኑ አባላት እጅግ ሰብዓዊነት በጎደለው ሁኔታ አንድዬ ልጃቸውን መግደል ሳያንሳቸው ያቺን የነበረቻቸውን አንዲት ብርድ ልብስ እንኳን ጨክነው ወስደውባቸዋል።
ፀሐይ ስታገኛቸው አዛውንቷ የሚለብሱት አጥተው በብርድ እየተንዘፈዘፉ ነበር። ‹‹የማደርግላቸው ባጣና ሁኔታውን ማየቴ ቢያመኝ ለጊዜው በኪሴ ውስጥ በአጋጣሚ ይዣት የነበረችውን አንዲት መቶ ብር ሰጠኋቸው›› ሰትል ፀሐይ አጫውታናለች። ባለሙያዋ ሌላው ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላበት ነው የምትለው የጥፋት ኃይሎች በሴቶች ላይ ፈፅመው ያየችውን ግፍና በደል ነው። የቡድኑ አባላት ያረከሱትና ያዋረዱት በየትኛውም የዕድሜ ደረጃ የሚገኙ፤ በየትኛውም ሁኔታ ያሉ የህይዋን ዘሮችን በሙሉ መሆኑን መታዘብ ችላለች።
በተለይ ሕሊናቸውን ስተው ጎዳና የወጡ፣ የአእምሮ ዘገምተኞች፣ ዓለም በቃኝ ብለው የመነኑ መነኮሳትንና በሸክም ፀበል የመጡ ሕመምተኞችን ደፍረው ማየቷ ድርጊታቸው እጅግ ሰብዓዊነት የጎደለው፣ ጤናማ የሆነ ሰው ያደርገዋል ተብሎ የማይታሰብ መሆኑን ትገልፃለች።
‹‹ከዚህ ቀደም የወሲብ ስሜት ከፍቅርና በሌላኛው ተቃራኒ ጾታ በመሳብ ወይም በመውደድ የሚመጣና ከፍላጎት ጋር የተያያዘ ይመስለኝ ነበር›› የምትለው ባለሙያዋ ሆኖም የጥፋት ቡድኑ ሕሊናውን ከሳተ፣ ከአዕምሮ ዘገምተኛና ዓለም በቃኝ ካለ፣ ዕድሜያቸው ከ80 በላይ ከመሆን አልፎ ሰውነታቸው የደከመ አዛውንቶች ጋር ማድረጋቸውን ስትሰማ እነዚህ የጥፋት ቡድኖች ከሰው የተለዩ አውሬዎች አድርጋ እንድታሰብ ያስቻለት መሆኑንም አጫውታናለች። ‹‹ምንም ያህል በቀል ቢኖራቸውም እንዲህ ከሰው ግብር የሚያስወጣ አይሆንም›› ስትልም ድርጊታቸውን ኮንነዋለች።
እንደታዘበችው ታድያ የቡድኑ አባላት እንደዚህ ዓይነቶቹን የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተፈራረቁ በተደጋጋሚ ጊዜ ደፍረዋቸዋል። በተለይ ሕሊናቸውን ያልሳቱት አዛውንት ሴቶች በድርጊቱ ራሳቸውን የበለጠ ከመሳታቸው የተነሳ ሲጠየቁ በማን ምን እንደደረሰባቸው እንኳን መናገር ተስኗቸው ነበር።
እየተፈራረቁ ብዙ ሆነው በተደጋጋሚ እንደደፈሯቸው ለጋዜጠኞች ይናገሩም የነበረው ሁኔታዎች ከተረጋጉ፣ ሕክምና ካገኙና ብዙ ከቆዩ በኋላም ነበር። ሰሜን ሸዋ መዘዞ ላይ በተደጋጋሚ ተፈራርቀው የደፈሯት የአዕምሮ ዝገምተኛ ሴት ከተደፈረች በኋላ ሀፍረተ ሥጋዋን እንኳን መሸፈን የማትችል እንደነበረች ታዝባለች። ተደፍሬ ከምኖር ብለው ራሳቸውን ያጠፉም አሉ ብላናለች ፀሐይ። አንዲቱ ራስዋን ማጥፋቷን ሰምታለች። ሰው እየተገደለ አንደፈርም ብለው ትንቅንቅ የሚገጥሙ ጀግኖች ሴቶች ቁጥርም ቀላል አልነበረም።
ወልድያ ላይ አንዲት ወጣት ክብሬን አላስነካም ብላ ከደፋሪው ጋር ስትታገል የያዘው ጥይት በድንገት ጭኗን ቢያቆስለውም፤ ቁስሉ ተሰፍቶላት በጥሩ ሁኔታ ላይ የምትገኝ ጀግና ወጣት ሴትም ገጥማታለች። ሸዋ ሮቢት ደብረ ሲና፣ መዘዞ፣ ዋድላ ደላንታና በየሄዱበት ካጋጠሟቸው በጦርነቱ ድል የቀናቸውም ብዙ ነበሩ።
የጥፋት ቡድኑን አባላት በኮንሶ ሹል ድንጋይ፣ በማጭድ በመጥረቢያና ዱላ ከኋላ በመምታትና የእጅ በእጅ ትንቅንቅ በመግጠም የተሻለ መሣሪያና መኪኖች የቀሙና ያስጣሉ አሉ። በዚህም ፋኖው ያደረገው አስተዋፅዖ በሁሉም ቦታ የጎላ መሆኑን አይታለች። አንድ በፍርድ አኩርፎና አምልጦ ጫካ የገባና ወደ እነሱ እንዲገባ በተደጋጋሚ ከእጅ መንሻ ጋር ያባብሉት የነበረ አገሬን አልክድምና አላስነካም ብሎ ወጣቱን በማሰባሰብ ታግሎ ድል ለመቀዳጀት የበቃም ጎልማሳ ምስል የማስቀረት ዕድል አግኝታለች።
ከመኪና ጀምሮ በርካታ መሣሪያ ማርኳል። ስለ ምርኮ ከተነሳ ለጥፋት ቡድኑ ቁስለኞችና ምርኮዎች የሚደረገው ክብካቤ ከነሱ የተገላቢጦሽ መሆኑን ከአንደበታቸው መስማቷንና በዓይኗ ማየቷን አጫውታናለች። ንፁህ መኝታ፣ ምግብ፣ ጉልኮስ ተሰጥቷቸውና ቁስላቸው ታጥቦና ታሽጎላቸው ሕክምና ያገኙበትን ምስልም ለማስቀረት በቅታለች። ፀሐይ በሁለቱም ጦርነቶች አስገራሚ ገጠመኞች አሏት። የኢትዮ-ኤርትራውን እናስቀድም።
በዚህ ጦርነት ዛላአምበሳ ላይ ግራ ቀኙ በቁጥቋጦና የታጀበ ቀጥ ያለ የድንጋይ ዳገት ላይ በልቧ እየተሳበች ፎቶ ማንሳት ይጠበቅባት ነበር። ታድያ የሆነ ነገር አየችና ቆመች። ይሄኔ ከኋላዋ የነበረ ወታደር ‹ልታስመችን ነው› በማለት ቀና ብሎ በኩርኩም መትቶ አስቀመጣት። በዚሁ ግንባር ሌላ ጊዜ ዋሻ ውስጥ ስትሠራ መሣሪያውን አጠገቡ አቁሞ ተረጋግቶ መፃፍ የሚያነብ አንድ ወታደር አግኝታ ምስሉን ማስቀረት ችላለች። ተኩስ በሚፋለሙበት ሁኔታ በስጋት ውስጥ ሆኖ መጽሐፍ ማንበብ የደረሰ ፅናቱ በአግራሞት አስደምሟታል። ይሄን ከዛሬ ጋር ስታነፃፅረው ጦርነቱ ምን ያህል የተረጋጋ እንደነበረም ለመታዘብ አስችሏታል። በሕልውና ዘመቻው ግዳጅ በሄደችባቸው ስፍራዎች ሕይወቷን የተፈታተኑት በርካታ ገጠመኞች እንዳሏትም አጫውታናለች።
ገጠመኞቹ የፊቷን ቀለም ከፈረንጆች ጋር በማመሳሰል የውጭ ዜጋ እንደሆነች ይቆጥሯትም እንደነበር አውግታናለች። ፀሐይ እንደምትለው እንድምታቸው አሜሪካና የውጪው ዓለም በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩት ከነበረ ጫና ጋር ተያይዞ የመጣ ስጋትን መሠረት ያደረጉም ነበሩ። ደሴ ሲገቡ መግቢያው ላይ ከፍተኛ ጭንቅንቅ ነበር። ፍራሽ ተሸክሞ ፌስታል አንጠልጥሎና ጓዙን ሸክፎ የሚገባው የሚወጣው ሰው ቁጥር ብዙ ነበር። በዚህ ላይ መሣሪያ ስጠኝ አልሰጥም የሚሉ አመራሮችና ወጣቶች እሰጣ ገባ ለጉድ ነው። ተኩስም እዛም እዚህም ሲንጣጣ ይሰማል።
አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሆኑ መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ተዘጋግተዋል። እንደ አራድኛው ደሴ ተቀውጣለች። ምን እንደሆነ ምክንያቱ መረጃ የሚሰጥም አልነበረም። ሆ! እያለ በመኪና ተጭኖ የሚሄደው ወጣትና ሠራዊት ብዙ ነበር። ተኩሱ ሲቀልጥ ነፍሱን ለማዳን ሁሉም እግሬ አውጭኝ አለና ከባልደረቦቿ ጋር ተጠፋፉ። የእሷ እግር የጣላት ጠባብ የወሎ ጭሳጭስ ቤት በር ትንሽ ነበረች። በፍፁም አንድ ወታደርና እሷን ማስገባት ስለተሳናት በሥርዓት የተቀመጠውን ጭስ ረጋግጠውና ደፋፍተው ለመሸሸግ ሞከሩ።
በዚሁ መካከል ‹‹ሁኔታዎች ይረጋጋሉ። ነገሮች እንዲህ ሆነው አይቀጥሉም። ይሄ ትዕይንት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለታሪክ ያስፈልገዋል›› የሚል ሀሳብ መጣላት። ‹‹ወጥቼ ምስሉን መቅረፅ ያዝኩ›› ትለዋለች። ሆኖም ከዚያም ከዚህም ያዛት የሚል ድምፅ ሊያሰራት አልቻለም። እነሱ ናቸው አገራችንን የሚያጠፏት ብለው አስቆሟት። መታወቂያና ከድርጅቷ ያመጣችውን ደብዳቤ ብታሳይም አላመኗትም። ፖሊስ ጣቢያ ይዘዋት ሄዱ።
በዚህ አንዱ ከፈረደ ሌላው የማርያም ጠላት በሚያደርግበት ቀውጢ ጊዜ ተርፋ ፖሊስ ጣቢያ በመሄዷ ፈጣሪዋን አመሰገነች። ኮምቦልቻ ጥሩ ምስል ለማግኘት ፎቅ ላይ በወጣችበትም ጊዜም ‹‹እዚህ ውስጥ ፈረንጅ ገብታለች›› በሚል በብዙ ሕዝብ መከበቧን ታወሳለች። እሷን ፈረንጅ አውርዳት እያሉ መጮሃቸውንም ትጠቅሳለች። ሕጋዊ ወታደር ደርሶ መታወቂያዋን ስትሰጠው እንኳን ማመን አቅቶት እንደነበር ትጠቅሳለች። ‹‹ጋራው ላይ ተኩስ ስለነበር የሚተኮስበትን ዒላማ ለጠላት የምሰጥ ነው የመሰላቸው›› የምትለው ፀሐይ የከተማውን ምስልና ሰውን ማንሳቷን ብትነግራቸውም ሊሰሟት እንዳልቻሉም ታስታውሳለች።
መታወቂያዋንና ደብዳቤዋን አሳይታ በብዙ መከራ እንዳመኗትና ሕዝቡ እንደተበተነም አጫውታናለች። ሌላው የፀሐይ ገጠመኝ የወታደር የተቃጠለ መኪና አይታ ልትቀርጽ ስትል መርሳ አካባቢ የገጠማት ነው። ወታደሮች በመኪና ሲያልፉ ስትቀርጽ ሲያይዋት በፍጥነት አዙረው ወደ እሷ መጡ። በጣም ተቆጥተውና መሳሪያቸውን አነጣጥረው ነበር። ስታስረዳቸው እንደተለመደው ቶሎ አላመኗትም።
እያቅማሙ መታወቂያዋንና ደብዳቤዋን በሞባይላቸው ቀርፀው ምስሉን እንድታስቀር ፈቀዱላት። ፀሐይ በሙያዋ ያካበተቻቸው ገጠመኞች እዚህ ተነግረው የማያልቁ በመሆኑ የዛሬውን እዚህ ላይ ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 24/2014