ከጉልበት በላይ ሁለት እግርን በፈንጂ አጥቶ ሕይወት ሙሉ አካል ላለውም ሰው ፈታኝ ነች። እግርና የግል መኪና በሌለበት ሁኔታ ረጅም ጉዞ እየተጓዙና ትራንስፖርት እየጠበቁ የዕለት ከዕለት ኑሮን መምራት ደግሞ ፈተናው ምን ያህል እንደሚያሰቃይ ያየ ይናገረው። 16 ቤተሰብ ማስተዳደር ሲጨመርበትማ ሸክሙ ፈፅሞ ሊታሰብ አይችልም።
ይህም ሳያንሳቸው ስትደግፋቸው የነበረችን የትዳር አጋር በሞት መነጠቅ ምንኛ ጨርቅን አስጥሎ እንደሚያሳብድ ለመናገር ይከብዳል። ግን ‹‹ላይችል አይሰጠው›› እንዲሉ ሆነና የዛሬው እንግዳችን ወታደር መሐመድ ሻሚል ችለውት ኖረዋል።
ለአገራቸው ልዩ ፍቅር ያላቸውና አሁን የጥፋት ኃይሎች በፈፀሙት ወረራ በብርቱ የሚቆጩት የቀድሞ ወታደሩ፤ ለእንቅስቃሴያቸው አመቺ ከሆነው ዑራኤል አካባቢ በልማት ተነስተው ቦሌ ቡልቡላ መግባታቸው ተጨማሪ ችግር ፈጥሮባቸዋል። ሰውም ናፍቋቸዋል።
በሰለጠኑበት የኤሌክትሮኒክስ ጥገና ሙያ የሚሠሩበትን እድልም አሳጥቷቸዋል። በዚህም ቤት ውስጥ የአልጋ ቁራኛ ሆነው ፀሐይ ሳያገኙ ይውላሉ። ይህም ሆኖ ግን አስከፊ ሕይወታቸውን ለማሸነፍ ይፍጨረጨራሉ። ሃያ አምስት ኪሎ ጤፍ በማትገዛው የጡረታ አበላቸው 3ሺህ 500 ብር የቤት ኪራይ እየከፈሉ መኖር ተስኗቸው ከነገ ዛሬ በውዝፍ የቤት ኪራይ ክፍያ እባረራለሁ በሚል እንቅልፍ አጥተዋልም።
በተለይ በዚህ ወቅት አካልህ ጎድሏል ሳይሉ ሲንከባከቧቸውና ከጎናቸው ሳይለዩ እንደ እህት፣ እናትና ሐኪም ሆነው ሲያበረቷቸው የነበሩ ባለቤታቸውን በሞት ማጣታቸው የመከራ ጫናውን የበለጠ አክብዶባቸዋል። ይሁንና ራሳቸውን አክመው መሥራታቸውን ቀጥለዋል። ወደ አዲስ አበባ የመጡት በአስራ ሁለት ዓመታቸው ሲሆን፤ ያመጧቸው ታላቅ እህታቸው ናቸው።
በተወለዱበት ጉራጌ ዞንም ሆነ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ብርቱ የትምህርት ፍላጎት ነበራቸው። ሆኖም ወደ አዲስ አበባ የመጡት እንደ አብዛኞቹ የገጠር ታዳጊዎች የትምህርት ዕድል ሳያገኙ ነው። ከመጡም በኋላ እህታቸው ፊደል ወይም ደብተር ገዝተው ትምህርት ቤት አላስገቧቸውም። ስለዚህ ዕድሜያቸው አለፈ። የዕድሜ አቻዎቻቸው ትምህርት ቤት ሲሄዱ ማየታቸው ለወታደሩ የመማር ፍላጎት ተጨማሪ ነበር። በዚህም እኔስ የማልማረው ለምንድነው? የሚል መንፈሳዊ ቅናት አደረባቸው። ይሁን እንጂ ያሰቡት አልሆነም።
ስለዚህም እንደአብዛኛው የጉራጌ ብሄረሰብ ተወላጆች በንግድ ሥራ ለመሰማራት አሰቡ። ሆኖም ንግዱን ለመጀመር የሚያስችል ጥሪት አልነበራቸውም። እናም ያገኙትን ሥራ መስራት ጀመሩ። ለአዋቂ ሰዎች መላላክና ጥሩ ትርፍ የሚያስገኛቸውን ስኳርና ጨው ወደ መሸጡም ገቡ። ብዙም ሳይቆዩ ጮሌነታቸውን ያየ አንድ ባለመደብር ቀጠራቸው። በመደብሩ ውስጥ ግማሽ ቀን እየሠሩ ግማሹን ቀን ለትምህርት አዋሉት።
በ13 ዓመታቸውም ትምህርታቸው አሀዱ አሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አፄ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ። እስከ 10ኛ ክፍል ያለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አብርሃም ሊንከን ትምህርት ቤት ተከታተሉ።
ባያጠናቅቁትም 11እና 12ኛ ክፍልን ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ነበር። እየሠሩ ለመማር ያደረጉት ጥረት በፈተና የተሞላባቸው ወታደሩ፤ የሱቁ ባለቤት ሳይቀር ብዙ ሰዓት እንዲሰሩለት በመፈለጉ ይፈትናቸው ነበር። በዚህም የሥራ ሰዓቱን ለትምህርታቸው በሚያመቻቸው ሁኔታ እንዲያደርግላቸው ሲጨቃጨቁ ቆይተዋል። ነገሩ አልሆንልህ ሲላቸው ደግሞ ሌላ ዘዴ ቀየሱ። ይህም ዓይናቸውን ይጥሉበት የነበረው ካዛንቺስ ፖስታ ቤት አካባቢ የሚገኘው ትልቅ የውጭ ኩባንያ ነው። እርሱን ተንተርሰው የራሳቸውን ሥራ ፈጠሩ።
ውሳኔያቸው እውን ሆነና ሄራልድ ትሪቢውን፣ ኒውስዊክ፣ ታየም፣ ኢኮኖሚክስን ጨምሮ የተለያዩ መጽሔቶችንና ጋዜጦችን ከእንግሊዝ አገር እያመጣ ወደሚያከፋፍለው ኩባንያ ይዘልቁና ያቀዱትን ሥራ ጀመሩ።
መጽሔቶቹንና ጋዜጦቹን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ማከፋፈል ጀመሩ። በዚህም ሥራው ከዕውቀት ጋር የሚሄድ በመሆኑ በጊዜው ደስታ ተሰምቷቸዋል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ በኩል በትምህርታቸው እንዲበረቱም አግዟቸዋል። ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉም ረድቷቸዋል። ግማሽ ቀን እየሠሩ ግማሽ ቀን እየተማሩ ኑሯቸውን ለመግፋት ዓይነተኛ መፍትሄም ሆኖላቸዋል።
በኢትዮጵያ የዘውዳዊ ስርአቱን ማክተም ተከትሎ ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ በኩባንያው በኩል የነበረው ሥራ እየተቀዛቀዘ መጣ። በ1967 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ኩባንያው ሙሉ በሙሉ ተዘጋ። ሱቅ ጥበቃውን በድጋሚ ሊሞክሩት ቢገቡም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ የሚያስችላቸው አልሆነም።
እናም በ1968 ዓ.ም መስከረም ወር እንደኑሮ አማራጭ አድርገው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማቋረጥ ውትድርና ተቀጠሩ። በሚያገኙት 112 ብር የወታደር ደመወዝ እስከ ቅርብ ዓመታት ባለቤታቸውን፣ ራሳቸውን፣ ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ጨምሮ 16 ቤተሰብ ከማስተዳደር አልፈው መሰረት ጥለውበታል።
‹‹እውነት ለመናገር ስቀጠር እንደ አንድ የሥራ አማራጭ እንጂ አገሬን በሙያው የማገልገል ፍቅርና ፍላጎት ኖሮኝ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱን ክህሎት ያገኘሁት ወደ ውትድርና ዓለም ከገባሁ በኋላ ነው›› ይላሉ ወታደር መሐመድ በወቅቱ ለሙያው ስለነበራቸው ስሜት ሲገልፁ። ለስምንት ወራት ደብረብርሃን ማሰልጠኛ ማዕከል የውትድርና ስልጠና ወስደው በ1969 ዓ.ም በኤርትራ ጦር ግንባር ተመደቡ። አስመራ ከተማ ውስጥ 11ኛ ሻለቃ ጦርን ተቀላቅለው ለመጀመሪያ ጊዜ በውትድርና ሙያ ሥራ ጀመሩ። የውትድርና ሕይወትን ውጣውረድ፣ አገርን ማገልገል፣ ራስን አሳልፎ ለአገር መስጠት፣ ወገንን መውደድ፣ ስለ ክብርና ስነስርዓት ተማሩ።
‹‹ለኢትዮጵያ ጦርነት አይገባትም›› የሚሉት ወታደር መሐመድ፤ ጦርነት የከፈቱባትን በብርቱ ያወግዛሉ። ውጊያው ከትግራይ የተነሳ አንድ ቡድን ነው ብለው አያምኑም። አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ጦርነቱ በነዚህ ቡድኖች የሚካሄድ ይመስለው ይሆናል።
መንግስት እንዴት እነዚህን ቶሎ ማሸነፍ አቃተው ሲል የሚደመጠውም ለዚህ ነው። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም። በተለይ በውትድርና ቆይታቸው የበሉትን በማብላት ሠራዊቱን ይደግፉ የነበሩ አገር ወዳድ የትግራይ እናቶች ምሥክር ይሆናሉ። በመሆኑም ‹‹እኛ የምንዋጋው ከምዕራባዊያኑ ነጮች ጋር ነው›› ይላሉ።
‹‹እነዚህ ክፍሎች ጦርነት የከፈቱብን ሀብታችንንም ለመዝረፍ ቢሆንም አፍሪካ ውስጥ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ በሚል ስጋት ነው። ከኢትዮጵያ መሪዎች በዕድሜ ትንሹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገር ደረጃ ያመጡት ፈጣን ለውጥ፤ በአህጉረ አፍሪካና በዓለም ያላቸው ተደማጭነት ስጋታቸውን አባብሶታል።
በዚህ ላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ታሪክ ያላት የነፃነት ቀንዲል ነች። ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ እነ አፄ ምኒልክና መንግስቱ ኃይለማርያም እንቢኝ ለአገሬ ብለው ጦርነት የሚጋፈጡ ጀግኖች መሪዎች ናቸው። መንግስቱን ብቻ ብናነሳ ስለነበርኩበት ቦንብና ጥይት እንደ በረዶ በሚወርድበት ጦርነት ውስጥ ገብቶ አዋግቷል።
ታንክ ላይ ሁሉ ወጥቶ ተዋግቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ይህንን ደግመውታል። ስለዚህ ይህ ያስፈራቸው ናቸው እየተዋጉን ያሉት›› ይላሉ የቀድሞውን ታሪክ ሲያስታውሱ። በውትድርና ሙያ የቀሰሙት ልምድ ከ11ኛው ሻለቃ ጦር አዛዥ እስከ ሜጀር ጄነራል ማዕረግ እስኪያገኙ በውትድርናው ዓለም ለማገልገል የሚያስችላቸውንና ራዕይ ያሰነቃቸው ነው።
ከተመደቡበት ጀምሮ እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ ምንም ፋታ የሌለው ውጊያ ላይ ሲሳተፉ ነበርም። እሳቸው የነበሩበት ክፍል ተወርዋሪ በመሆኑ ውጊያ ባለበት ቦታ ሁሉ መጓዝና መዋጋት የሚጠይቅ ነው። በዚህም ፋታ ሳያገኙ እንዲዋጉ አድርጓቸዋል። በውጊያው ብዙ ጓደኞቻቸውን ቢያጡም እርሳቸው ግን እስከ 1972 ዓ.ም ከጭረት ያለፈ ጉዳት አልደረሰባቸውም።
ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ከምፅዋ ነዳጅ ጭኖ አስመራ የሚመላለሰውን ኮምቮይ እያጀቡ በመመላለስ የመዋጋት ተግባራቸውን ፈጽመዋል።
ከወራት በኋላ ግን ያልጠበቁት ከባድ አደጋ ከምፅዋ 34 ኪሎ ሜትር የአሉላ አባ ነጋ ሀውልት በነበረበት ቦታ ላይ አጋጠማቸው። አደጋውም የተከሰተው እርሳቸውን ጨምሮ ሃያ ሰባት ወታደሮችን የጫነው አውቶቡስ በቦታው ላይ የተቀበረውን ፈንጂ በመርገጡ ነበር። 24ቱ ባልደረቦቻቸው በአደጋው እንደጧፍ ቀለጡ።
ይህን እንኳን የሰሙት በአስራ አምስተኛው ቀን ራሳቸውን ካወቁ በኋላ አስመራ ሆስፒታል ውስጥ ሆነው ነው። በአደጋው ሁለት እግራቸው ከጉልበታቸው በላይ መቆረጡን ተረድተዋልም። ‹‹አደጋ ደርሶብኝ ሆስፒታል ውስጥ እንዳለሁ ያወቅኩት በአስራ አምስተኛው ቀን ነው። የማቃጠል ስሜት ሲሰማኝ እጄን ሰድጄ እግሬን ላክክ ስል ሁለቱንም እግሬን አጣሁት›› ሲሉ ሁኔታውን ይገልጹታል።
ሮጦ ባልጠገቡበት ዕድሜ ሁለት እግራቸውን ማጣታቸውን ሲያውቁ ዙሪያ ገባው ጨለመባቸው። በመላ ሰውነታቸው ሰርጾ አመማቸው። በዚህ ሁኔታ መኖር በቃላት ከሚገለፀው በላይ አስፈራቸው። ‹‹የኔ ነገር በቃ ተፈፀመ›› እያሉ ለያዥ ለገናዥ እስኪያስቸግሩ ድረስ ከተኙበት አልጋ ላይ ሆነው እየተንሰቀሰቁ አለቀሱ። ከ11ኛው ሻለቃ ጦር አዛዥ እስከ ሜጀር ጄነራል ማዕረግ የመድረስ ምኞታቸውንና ተስፋቸውንም ውሃ በላው። ሁለት እግራቸውን በማጣታቸው ምክንያት ተስፋ አድርገው የነበሩትን ሁሉ ማጣታቸውን አሰቡ።
በዚሁ ምክንያት ወደፊት የሚያጡት ሁሉ እየታያቸው ሳይተኙ ሲባንኑ ሰነበቱ። አስመራ ሆስፒታል የተወሰነ ጊዜ በዚህ ሁኔታ ከቆዩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ውስጥ የተለያየ ሕክምና ሲደረግላቸው ቆዩ። ‹‹አካሉ ጎድሏል ብላ ያልተወችኝ ባለቤቴ ከጎኔ ባትኖር ሕይወቴን አጠፋ ነበር›› ሲሉም የሁኔታውን አስቸጋሪነትና ባለቤታቸው ያደረጉላቸውን ድጋፍ ይገልፁታል።
ባለቤታቸው እሳቸውን በማስታመምና ለእሳቸው እግር ሆነው ታች ላይ በማለት ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈዋል። በወቅቱ ከሚሰሩበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሥራ ገበታቸው በተከታታይ በመቅረታቸው ምክንያት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸውም ነበር። በዚህ የተነሳ ባህር ትራንዚት ቀይሯቸው የነበረ ሲሆን መሥሪያ ቤቱ ሲፈርስ ሥራ አጥ ለመሆን ተዳርገዋል። ሕክምናውን በዚህ ሁኔታ ነበር የተከታተሉት። በተለይ ሰው ሠራሽ እግር በውጭ አገር እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመሰራቱ የባለቤታቸውንም የእሳቸውንም ፍዳ አባብሶታል።
ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ደብረ ዘይት የሚገኘው አብዮታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አምባ ገቡ። አምባው የተቋቋመው ለአገራቸው ውለታ ለዋሉ ለየትኞቹም ዓይነት የጦር ጉዳተኞች እንክብካቤና ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ ነበር። ከአገር አልፎም የመላው አፍሪካን ጦር ጉዳተኞች የማገልገል ዓላማም ነበረው። ነገር ግን ሕወሓት ሲገባ አፍርሶ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ አደረገው። የዛሬን አያድርገውና ታዲያ ያኔ በዘመነ ደርግ በአምባው ለአምስት ዓመት ቆይተዋል።
የኤሌክትሮኒክስ ሙያ ትምህርት ቀስመውም በዲፕሎማ ተመርቀዋል። ያገኙት ትምህርት በስነልቦና እና አካላዊ እንቅስቃሴ የታጀበ በመሆኑ የተሰበረው ልባቸው ተጠግኖ ዳግም ተስፈኛ መሆን ችሏል። ትምህርታቸውን አጠናቀው ከአምባው እንደወጡም ቀጥታ አገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ መገናኛ መምሪያ (ሲግናል) ውስጥ ተመድበው በሬዲዮ ቴክኒሻንነት መሥራት ጀመሩ።
የሚሠሩት በሚሊቴሪ ሳይሆን በሲቪል ሲሆን፤ ከጀማሪ ቴክኒሺያንነት እስከ ከፍተኛ ቴክኒሺያንነት ደርሰዋል። እየሠሩ እያሉ አርቲፊሻል እግራቸው በመበላሸቱ መንግስት ለሦስተኛ ጊዜ ምሥራቅ ጀርመን ላካቸው። በዚህ መካከል የግንቦት 1983ቱ ለውጥ መጣ። በወቅቱ በነበረው ሥርዓት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንጂ በግላቸው የደረሰባቸው ምንም ተፅዕኖ አልነበረም። ሥራቸውን ሰርተው በሰላም ወደ ቤታቸው ይገቡ እንደነበርም ያወሳሉ። ሆኖም ሕክምና ማጣታቸውን አልሸሸጉም።
‹‹አይደለም እንደ ደርግ መንግስት ውጭ ተልኮ አርቲፊሻል ማሰራት ራሴን ሲያመኝ እንኳን ለመታከም ዕድል አልነበረኝም›› ይላሉ። ደርግ ጉዳተኛውን መልሶ ለማቋቋም እንደሳቸው የሙያ ስልጠና እየሰጠ በየሲቪል መሥሪያ ቤቱ መመደቡን የሚያስታውሱት ወታደር መሐመድ፤ በኢህአዴግ ዘመን የሕወሓት ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ሥራውን ወይ ጡረታውን ምረጡ አሉና ጡረታቸውን መረጡ።
ጦር ኃይሎች ሆስፒታል የእሳቸውን ጨምሮ የቀድሞ ሠራዊት የሕክምና ካርድም ዓይናቸው እያየ ሜዳ ላይ ተጣለ። ሕክምና ማግኘት እንደማይችሉም ይፋ ሆነ። ‹‹ሠው ሰራሽ አካል በየጊዜው ይበላሻል። ሲበላሽም ውጭ እንጂ አገር ውስጥ መሰራት አይቻልም›› የሚሉት ወታደር መሐመድ፤ ሰው ሠራሽ አካል አጥተው እሳቸውን ጨምሮ ብዙ የጦር ጉዳተኞች ቤት ውስጥ የአልጋ ቁራኛ ለመሆን መገደዳቸውን ይናገራሉ። ከጉልበት በላይ የሆነው የሁለት እግሩ አርቲፊሻል እንደማይሆንም ይጠቅሳሉ።
ይሄንን ላድርግም ቢሉ ዋጋው እጅግ ውድ በመሆኑ አይችሉትም። ‹‹ለአገርና ለወገን ሲል አካሉን ለሰዋ ባለውለታ ዜጋ ሕክምና መንፈግ ተገቢ አይደለም። ብዙዎቹ አስቀድመው በሕክምና እጦት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ቤት ውስጥ የአልጋ ቁራኛ የሆኑም አሉ። የፊት ከሌለ የኋላ አይኖርምና መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰብ አለበት።›› የሆነውን የሚያስታውሱት ባለታሪኩ፤ ለቀድሞ ሠራዊት ሳይሆን ዛሬ አገራችን ላይ በተከፈተው ጦርነት እየተዋደቁ፣ እየቆሰሉና አካላቸው እየጎደለ ላሉት ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ቢያንስ ይድረስ ይላሉ።
‹‹ወታደር እስከ ተዋጋ ድረስ አካሉ ሊጎድል ይችላል። ለእኛ ለቀድሞዎቹ ሳይሆን ለዛሬዎቹ ነግ በኔ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል›› የሚሉት ወታደር መሐመድ፤ አሁን በአመራርነት ላይ ያለው መንግስት ሕወሓት የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ያደረገውን ጀግኖች አምባ ወደ ነበረበት ይመለሳል ማለታቸውን በሚዲያ መስማታቸው ለእርሳቸው ባይደርስም ለሌሎች ትልቅ ተስፋ እንደሚሰጥ ያነሳሉ። ‹‹ምን አልባት እኛ የቀድሞ ሰራዊቶችም በሕይወት ከቆየን አምባው ወደ ነበረበት ሲመለስ ሰው ሰራሽ እግር እናገኝ ይሆናል›› የሚል ተስፋም አላቸው። አሁናዊ ሁኔታ ወታደር መሐመድ የስኳር ህመሙ ዓይናቸውን እየከለላቸው ነው። ሰው ሠራሽ እግራቸውም ከተበላሸ ብዙ ጊዜ ሆኖታል።
ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበትም በተሽከርካሪ ወንበር ነው። አንድ የቀድሞ የሥራ ባልደረባቸው የገዛላቸው ሞተር ብስክሌትም አርጅቶ ተጥሏል። ይሄው ባልደረባቸው የገዛላቸው ሠው ሠራሽ እግርም ለመፀዳጃ ቤት ብቻ ነው የሚያገለግላቸው። ስለሚጥላቸው ውጭ አይጠቀሙበትም።
የሚደግፏቸው ባለቤታቸውም በሕይወት የሉም። ስለዚህም እጅግ ከባድ ሀዘን ውስጥ ወድቀዋል። ባለታሪካችን አንዳንድ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን በመጠገን ኑሯቸውን ለመደጎም የሚፍጨረጨሩ ሲሆኑ፤ ድጎማውን ከውጭ የሚመጡ ጋዜጦችና መጽሔቶችን በማከፋፈልም የማጠናከር ሀሳብ አላቸው። ይሁንና ሥራውን የሚሠሩበት ቦታ የላቸውም።
የሚከራዩበትም አቅም እንዲሁ። ኤሌክትሮኒክሱን የሚጠግኑት እንኳን እግርና ዊልቸር ወይም መሥሪያ ቦታ ኖሯቸው ተንቀሳቅሰው ሳይሆን ጓደኞቻቸው ሲያመጡላቸው እቤት ውስጥ ብዙ ጊዜም መንቀሳቀስ ስለማይችሉ አልጋቸው ላይ ቁጭ ብለው ነው። ይህም ሆኖ በእሳቸውና በጓደኞቻቸው ቤት ያለው ርቀት ሰፊ ነው።
በዚህም አልፎ አልፎ እንጂ ብዙ ጊዜ አያመጡላቸውም። እኛም ቤታቸው ስንደርስ ይህንኑ አይተናልና ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ድረሱላቸው እንላለን። በተለይ የሚመለከተው አካል ሊቃኛቸው እንደሚገባ ሳናሳስብ አናልፍም።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 21/2014