ሁሌም እንደሚባለው ኢትዮጵያ የወጣት አገር ነች። በመሆኑም፣ ትኩስ የሰው ሀይል ነውና ያላት በማንኛውም ጉዳይ ቀዳሚ የመሆን እድሏ ከፍተኛ ነው።
የወጣት አገር ስንል የእድሜ ጉዳይ ብቻ አይደለም እያወራን ያለነው። የወጣት አገር ስንል ግዙፍና ትኩስ የስራ ኃይል፣ ወደ ኢኮኖሚ ሊቀየር የሚችል የሰው ሀብት … አለን እያልን ነው።
የአንድ አገር የወደፊት እጣ ፈንታ ከሚወሰንባቸው መለኪያዎች አንዱም ከአጠቃላይ ህዝቡ ውስጥ ምን ያህሉ መስራት የሚችልበት እድሜ ላይ ነው ያለው? የሚለው ነውና ወጣት የነብር ጣት …። ከዛሬው በአል አኳያ ወደ ወጣቱ ሚና እንሂድ።
በተለይ አመት መጥ የሆኑ ክብረ በአላትን፣ በተለይም ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላትን አስመልክቶ በአላቱን የማድመቅ ሁኔታ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝቶ እየተሰራ የመገኘቱ ጉዳይ ለማናችንም ግልጽ ነው። ተግባሩም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው፣ ማህበረሰቡን ብቻ ሳይሆን አገርንም እንደ አገር እየጠቀመ መገኘቱም እንዲሁ የጋራ ግንዛቤ ካገኘ ሰንብቷል።
ለወትሮው ጉዳይ ተኮር ብቻ የነበረው የምእመናን (በተለይም የወጣቱ) እንቅስቃሴ ዛሬ የእንቅስቃሴውን አይነትና መጠን እያሰፋ፣ በእውቀትና ጥበብ እየጎለበተ፣ ከነበረው እለታዊው ሃይማኖታዊ ተግባር፣ ለበአሉ ድምቀትና ውበት፣ መንፈሳዊ እርካታ ብቻ ከመስራት በበለጠ ለአካባቢ ጤና እና የመሳሰሉ መሰረታዊ የልማት ተግባራት ላይ ጭምር በመሳተፍ ስፍራን ለኑሮ ምቹ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
ትናንት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ የዋለው የጥምቀት (ከተራ) በአል ነው። ከትናንት በስቲያ ደግሞ የዚሁ በአል አካል የሆነው ከተራ (ታቦት የሚወጣበት) ነበር። በመሆኑም ከከተራ ሁለትና ሶስት ቀናትን አስቀድሞ በወጣቱ አማካኝነት የሚሰሩ በርካታ ስራዎች አሉ፤ አስፋልትን የማፅዳት፣ ሰንደቅ አላማ የመስቀል ወዘተ። ይህ አመታትን ያስቆጠረው የምእመናን ተሳትፎ ዛሬ ላይ የማልማት ወሰኑን ከእነዚህ ባለፈ አስፍቶ እስከ ዘላቂ ልማት ድረስ ዘልቋል። ለዚህ ማሳያችን ደግሞ ከትናንት በስተያና ከዚያ በፊት በነበሩት ቀናት በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ በየአካባቢው በሚገኙ ወጣቶች ሲያከናውኗቸው የነበሩት ተግባራት ናቸው።
በከተማዋ ተዘዋውረን እንደተመለከትና ወጣቱ የተሰማራባቸው ዘርፎች ውሱን አይደሉም። ተግባራቱ እንደየአካባቢው ሁኔታ የሚለያዩ ሆነው፣ ወጣቱ ወሳኝ በሆኑት ተግባራት ላይ ተሰማርቶ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
በቀጨኔ አካባቢ የተመለከትነው የመጀመሪያችን ነበር። ከቀጨኔ ወደ መነን ሲመጣ የሚታለፍ አንድ ወሳኝ ድልድይ አለ፤ የቀጨኔ ድልድይ (“ድልድዩ ጋ …” እንደሚባለው)። በዋዜማው፣ ገና በጠዋቱ እዛ አካባቢ ያሉ ወጣቶች በስራ ተጠምደው ደፋ ቀና ሲሉ ነበር የሚታዩት።
እያከናወኑ ያሉት የልማት ተግባር ከእለታዊ ጥቅሙ፣ ማለትም ለበአሉ ድምቀትና ውበት፤ እንዲሁም ለምእመናን ከሚሰጠው የመንፈሳዊ፣ ህሊናዊ እርካታና ደስታ የሚተናነስ አይደለም።
ያከናወኗቸው ተግባራት የድልድዩን ግራና ቀኝ ግድግዳ መሰል ብረትና ብረቱ የቆመበትን መሰረት በማፅዳትና የተለያዩ ቀለማትን (ጥቁርና ነጭ) በመቀባት፤ አስፋልቱ ግራና ቀኝ ላይ ክረምት አመጣሽ የአሸዋ፣ አፈርና ድንጋይ “ክምር” መቆፈርና በአካፋ እየዛቁ ከአካባቢው አርቆ መጣል፣ መንገዶች ግራና ቀኝ ለጉዞ አስቸጋሪ የሆኑ የዛፍ/ቅጠላቅጠል ምንጣሮ፣ ማንኛውንም ለእንቅስቃሴ እንቅፋት የሆነን ነገር ሁሉ ማስወገድ ወዘተ ናቸው። ይህ ከዚህ በፊት ብዙም የማይታይ የወጣቶች እንቅስቃሴ በዛች አካባቢ ብቻ ሳይወሰን ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊስፋፋ፤ የሚመለከታቸው አካላትም ስራው ተዘውታሪ እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ማሳሰብ ተገቢ ነው። በአካባቢው የሚገኙና አስፋልትን የሚያህል መንገድ ገንዘባቸውን ወጪ አድርገው እየገነቡ ያሉት አቶ ግርማ በለውን የመሳሰሉትም ሊበረታቱ ይገባል።
የአካባቢው ነዋሪ፣ የእንቅስቃሴው ተሳታፊና የአይን ምስክሩ ፍሬው በቀለ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረገው ቆይታ እንደተናገረው፤ ወጣቱ እያደረገ ያለው ከእለታዊ ጠቀሜታ ማለትም ሃይማኖታዊ ስነ ስርአቱ ድምቀትና ውበት ባለፈ ለዘላቂ አካባቢያዊ ልማትና ጥቅም አኳያ በጣም የሚያስደስት ሲሆን ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
የባለሀብቱ የልማት ተሳትፎ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው አቶ ደምመላሽ አርአያና አቶ ፍሬው በቀለ እንደሚሉት ከሆነ አካባቢውን ከማልማትና ለኑሮ ምቹ ከማድረግ አኳያ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት የባለሀብቱ አቶ ግርማ በለውን ተሳትፎ በቀላሉ መናገር አይቻልም። አሁን እያሰሩት (በጣም ተጎድቶ የነበረ) ያሉትን አስፋልት – ወደ ቀጨኔ ሲሉ፣ ድልድዩን እንደ ጨረሱ ወደ ግራ መታጠፊያውን ይዞ የሚሄደው፣ መጀመሪያም ያሰሩት እሳቸው ናቸው። አሁንም እያደሱት ያሉት እሳቸው ናቸው። ፍሳሽ ማስወገጃውን ሁሉ ያሰሩት እሳቸው ናቸው። አቶ ግርማ ለአካባቢው ያልሰሩት ስራ የለምና ሊመሰገኑ ይገባል። መንግሥትም እያገዙት ነውና ሊያመሰግናቸው፤ ሊያበረታታቸው፤ ሌሎችም አርአያነታቸውን እንዲከተሉ ሊያደርግ ይገባል።
ይህ ከላይ የተመለከትነው ቀጨኔ አካባቢ ያሉ፣ በተለይም ድልድዩ አጠገብ የሚገኙ የአጥቢያው ወጣቶች የልማት ተግባርና የጋራ ርብርብ ነው። እነሱን አስመልክተን ይህን እንበል እንጂ በአሉን፣ የአለም ቅርስ የሆነውን ጥምቀት በአልን በተዋጣለት መንፈሳዊና ባህላዊ ሥነስርአት ከማክበር አኳያ በአጠቃላይ በአገሪቱ ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች መከናወን ከጀመሩ ቆይቷል። ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ግን ለበአሉ ሲባል እየተደረጉ ያሉት፣ ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርጉት ተግባራት ከዘላቂና ቋሚ የልማት ተግባራት ጋር መተሳሰራቸው ነው።
በሌሎች በተዘዋወርንባቸው አካባቢዎችም ተመሳሳይ፣ ዘላቂ ልማትን አብሮ የማስኬድ ነገር መኖሩን የተመለከትን ሲሆን፣ መርካቶ አካባቢ እጅግ የቆሸሸንና ለጤና ጠንቅ የሆነን ቱቦ የማፅዳት ተግባር በወጣቶች ሲከናወን ተመልክተናል። ከጊዮርጊስ ወደ ፓስተር መሄጃም እንዲሁ ወጣቶች ከሰንደቅ አላማ ሰቀላ ተግባር ጎን ለጎን ከመንገድና አካባቢ ንፅህ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ሲያከናውኑ ተመልክተናልና የጥምቀት በአል ለሁለንተናዊ ሰብአዊ ትድግና እየዋለ ስለ መሆኑ ተገቢ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል።
ይህ በአንድ፣ በዚህ በጠቀስነው አካባቢ ብቻ የተወሰነ አይደለም። አሁን አሁን ተግባሩ እየተስፋፋና የአካባቢንም ችግር ዞር ብሎ የማየት ነገር እየመጣ ያለ ይመስላል። ይህ ደግሞ እራሷ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለአገር ልማት ካላት ቀናኢ አመለካከትና ተሳታፊነት አኳያ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነውና ምእመን ሊቀጥሉበት ይገባል። በየደረጃው ያለ የመንግሥት አካልም ሊያበረታታቸው፣ ሊደግፋቸውና ከጎናቸውም ሊቆም ይገባል እንላለን።
በመጨረሻም ጥምቀት በአል (ከተራ) የሶስት ትላልቅ አካላት በአንድ መገኘት ሲሆን እነሱም “ታቦቱ የጌታችን ምሳሌ፤ ካህናቱ የመጥምቁ ዮሐንስ ምሳሌዎች፤ እንዲሁም፣ መዘምራኑና ሕዝቡ ደግሞ ዮሐንስ ያጠመቃቸው ሕዝቦች ምሳሌዎች” መሆናቸውን አስታውሰን ጽሑፋችንን እናጠቃልላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም