ጥር ገብቶ የካቲት እስኪተካ ድረስ የተለያዩ ታቦታት ከማደሪያቸው ወጥተው በየአካባቢው ይነግሣሉ። ንግሰትን ለማክበር ደግሞ የሚወጣው ሕዝብ ለአካባቢው ድምቀትንና ውበትን እንደሚሰጥ እሙን ነው።
በተለይ ታቦታቱ ከሚነግሱባቸው ቀናት መካከል የጥምቀት በዓል ዋዜማ ለሁሉም ሰው ራሱን ጭምር የሚያይበትና የሚመልከትበት ጊዜ ነው:: ምክንያቱም የሚወጣው ሰው ብዛት ይበልጥ ምን ያህል ውበት ለአካባቢው እንደለገሰ ማየት ግድ ነውና «እኔስ የራሴን ምን አበርክቻለሁ?» እንድንል ያስገድደናል::
በዚያ ውስጥ ሆነንም በሌሎች ማንነት ውስጥ የራሳችንን ውበት እናደንቃለን፤ አለያም እናፌዝበታለን:: ምክንያቱም ይህ ዕለት የሚደምቀው በታቦታቱ መውጣት አለያም በዘፈኑና ጭፈራው ብቻ ሳይሆን በአለባበስም ጭምር በመሆኑ ነው:: ብዙ ነገር የሚታይበት ስለሆነ ብዙዎች ጥበብን ፍለጋ የሚወጡበትም እንደሆነ ማንም ይረዳል::
እንዲያውም በአባባሉ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ አይደለም የሚባለው:: ስለዚህም ይህ ቀን ከሌሎች ዕለታት በተለይ በባህል ልብስ ለሚያምሩ ሰዎች ልዩ ስሜት ይሰጣል:: ሙያተኛውም የሥራውን ውጤት የሚያይበት ስለሆነ ዕለቱ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል:: በዕለቱ የሚታየውን የባህል ልብስ ብዛትና ዓይነት ቤቱ ይቁጠረው::
ያለው የክት ያደረገውን ሲያወጣ የሌለው ደግሞ ይህንን ጥበብ ከሚሠሩት ቤት ጎራ ይላል:: የሚያምርበትን ነገር ያስመርጣል፤ ይመርጣልም:: ጥበበኞቹ ደግሞ በምርጫቸው አለዚያም የሚያምርበትን ነግረው ፍላጎቱን ያሟሉለታል::
ከዚያ ደምቆና ተውቦ ጥምቀትን ውብ ሆኖ ያስውባል:: መቼም ይህንን ሁሉ ነገር የደረደርነው ያለምክንያት አይደለም:: አስደማቂዎቹን፤ የጥምቀት አብሳሪዎችን ለማንሳት ስለፈለግን ነው:: ማን ናቸው እነርሱ? ካላችሁ የባህል ልብስ የሚሠሩት ባለሙያዎች ናቸው::
ይህ ዕለት እነርሱ ባያስቡት ጥምቀት ጥምቀት አይሆንም ነበር:: እናም ከእነዚህ ጥበበኞች መካከል ለዛሬ አንዷን ይዘን ለመቅረብ ወደናል:: ዲዛይነርና የልብስ ጠበብቷ ወጣት ሄለን ሞገስ ትባላለች:: ይህ ጊዜ ለእነርሱ ምን ዓይነት ትርጉም እንዳለው ታስረዳለች::
በመጀመሪያ ያነሳችልን ጥምቀት ብቻ ሳይሆን በዓላት መምጣታቸው ሰዎችን ለማስዋብ ብቻ ሳይሆን የዕለት ጉሮሮንም ጭምር ለመሙያ ዕድል የምናገኝበት ነው:: እንዲያውም ከዕለቱ አልፎ ለዓመትም የሚሆን በጀት የምንይዝበት ሊሆን ይችላል:: ምክንያቱም በዓላቱ ሲያልፉ ፍላጎትም በዚያው ልክ ይቀንሳል:: እንደ ጥምቀት ዓይነት የአደባባይ በዓላት ደግሞ የሚመጡት በዓመት አንድ ጊዜ ስለሆነ የሥራ ዕድሉም እንዲሁ የተወሰነ ነው:: አሁን በአገር ደረጃ ብዙ ለውጦች እየመጡ ነው::
ለዘወትር የሚለበሱ የባህል ልብሶችም እያመረትን ስለሆነ ምንም ዓይነት ፕሮግራም ካለ መጠቀም ተጀምሯል:: ይሁን እንጂ ሥራው እምብዛም አይደለም:: ከበዓላቱ ጋርም አይመጣጠንም:: ስለሆነም እነዚህ በዓላት ለባለሙያው ልዩ ጊዜያት ናቸው ትላለች:: ይህ ጊዜ አምሮና ተውቦ ለጥምቀት ከሚወጣውም በላይ ለእነርሱ ልዩ ትርጉም እንዳለውም ታስረዳለች::
ሄለን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ስታስረዳ በሁለት መልኩ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ገቢ የሚያገኙበትን ሥራ የሚያከናውኑበት መሆኑ ነው:: ሁለተኛው ደግሞ ከእነርሱ ውጪ የሆኑ የጥበብ ሥራዎችን ለማየት የሚወጡበትና ለቀጣይ አዲስ ፈጠራን የሚያክሉበት እውቀት መሸመቺያ መድረክ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ ይህ በዓል ለሌላ ጊዜም ቋሚ ደንበኛ ለማፍራት የሚጠቀሙበት እንደሆነም ታነሳለች::
ባህልን የሚያስተዋውቁበት መድረካቸው እንደሆነም ትናገራለች:: ጥምቀት ልዩ የዝግጅትና የሥራ ጊዜያቸው ነው:: ለዚህም እኔ ወደ ቤቷ ስሄድ አሠራሯንና ባተሌነቷን በደንብ ተመልክቻለሁ:: ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነች::
እናትነትን ከሥራና ቤት መምራቱ ጋር አስተባብራ ትመራለች:: ምንም አጉድላ አታውቅም:: ደከመኝ ሰለቸኝ የሚል ነገርም የለባትም:: ምክንያቱም ወደ ቤቷ ስዘልቅ ቤቷ በጣም ጠባብ ነች:: ነገር ግን የሥራ ቦታዋ ጭምር አድርጋ ትጠቀምበታለች:: ይህ የሆነውም ልጆቿን በቅርበት ለመንከባከብ እንዲያግዛት በማሰብ ነው::
ጽጌረዳ ጫንያለው ሶፋ ላይ እነርሱን አስተኝታ ሥራዋን ታከናውናለች:: ሲነሱ ደግሞ ማድረግ ያለባትን አከናውና አሁንም ርቀት ሳትሄድ ቀጥታ ወደ ሥራ ክፍሏ ትገባለች:: ብዙ እንቅልፍ የላትም:: በተለይ እንዲህ የጥምቀት ዓይነት በዓላት ሲመጡ ላስተዋላት እውነትም ሴቶች ብርቱዎች ናቸው ያሰኛታል::
ባተሌ ሆና ለልጆቿ ማድረግ ያለባትን ታደርጋለች:: ጡት እያጠባች ጭምር ደንበኞቿን በመጡበት ሁኔታ ተቀብላ ታስተናግዳለች:: ሄለን ሥራዋን ስትከውን ከሶፋው ላይ ልጆቿን አስቀምጣ ከጎናቸው በመሆን በጠረጴዛው ላይ ዲዛይኗን በማውጣት፣ የሚሰፋውን ጨርቅ በመለየት፣ ጥልፉን በመጥለፍ ትቆያለች::
ከዚያ ልጆቿ ወደ እንቅልፍ ሲገቡላት በጠባብ ቤቷ ውስጥ በአስቀመጠችው የስፌት መኪና ወደ ልብስ ስፌቷ ትገባለች:: የሁል ጊዜ የሥራ ኡደቷ ይህ እንደሆነም አጫውታናለች:: በእርግጥ እርሷ ይህንን ብቻ አይደለም የምትሠራው:: ሹራብ ሥራን ጨምሮ የህትመት ሥራዎችም የእጇ ውጤቶች ናቸው:: ስለዚህም የብዙ ሙያዎች ባለቤት በመሆኗ ደስተኛና ሥራ የማታጣ እንስት ናት::
በሥራዋ ድካምን የሚቀንስላት እድል እንደሚገኝ የምታስረዳው ሄለን፤ በህብረት የሚመጡ ሥራዎች የተሻለ እረፍትን ይሰጣታል:: ምክንያቱም ለአንዱ የሠራችው ዲዛይን ለሁሉም ስለሚሆን:: ስለዚህም ብዙ አትደክምበትም::
ይሁን እንጂ እንጀራዋ ነውና በተናጠል የሚመጡትንም አትጠላቸውም:: እንዲያውም ይበልጥ ለመጠበብ ትጣጣርባቸዋለች:: ደከመኝን የማታውቀው ባለታሪካችን፤ በቻለችው ሁሉ በሙያዋም፣ በእናትነቷም እንዲሁም በሚስትነቷ ቤቷን ሙሉ አድርጋ ለመጓዝ የማታደርገው ነገር የለም:: ሁልጊዜ በልፋት ውስጥ ደስታዋን ትፈልጋለች::
በልፋትና በትጋት ውስጥ ሁልጊዜ ደስታ እንዳለም ታምናለች:: በዚህም ይህንን ለማግኘት ብዙ ሰዓት አትተኛም:: በተለይ እንዲህ ዓይነት በዓላት ሲመጡ ሌሊቶቹ ጭምር የሥራ ጊዜዎቿ ናቸው:: ለዚህ መሠረቷ ቤተሰቦቿ እንደሆኑ ታውቃለች:: መሥራት የምትፈልገውን ሁሉ እንድታደርግ ሁልጊዜ ያበረታቷታል::
ሁሉን ነገርም በፍላጎት እንድታከናውን ያግዟታል:: ምርጫዋንም ያከብሩላታል:: በዚህም ቤተሰብ ላይ ሆና ጭምር ሳይደክማት ታገለግላለች:: የራሷን ቤት ስትመሰርት ደግሞ ይበልጥ ጥንካሬዋንና ነጻነቷን ስላገኘች ፍላጎቷን ለማሳካት የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም:: ባለቤቷም ቢሆን ለእርሷ የቤተሰቦቿን ያህል ውድና ወርቅ ስለሆነ ቤቷን ሙሉ ለማድረግ ትጣጣራለች::
በተለይም ሙያዋን የሚደግፍላትና የሠራችውን ለሽያጭ የሚያቀርብላት ስለሆነ ደስታዋ እጥፍ ድርብ እንደሆነም አጫውታናለች:: ሄለን በዓላት ከመምጣታቸው በፊትም ሠርታ፣ ይሆናሉ ብላ ወይም ለየት ያለ ዲዛይን ስታይና ስታገኝ የምታስቀምጣቸው አልባሳትም አሉ:: ይህ ደግሞ ባተሌነቷን በብዙ መንገድ እንድትቀንስበት ያግዛታል::
የሠራችውን የባህል አልባሳት በባለቤቷ አማካኝነት ሽሮ ሜዳ ላይ ‹‹ሸዋ የባህል አልባሳት መሸጪያ›› በማለት ሱቅ በተለይ ደግሞ ባለቤቷ ከጎኗ ሆኖ ስለሚያግዛትና የእጇን ጥበብ ለገበያ ስለሚቀርብላት እጅጉን ደስተኛ ሆና እንደምትኖር ነግራናለች:: በዚህም በቅርበት እንድትገኝና ሙያዋን ተጠቅማ ቤቷን ሙሉ ለማድረግ ችላለች::
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ዝም ብሎ የመጣ እንዳልሆነ ትናገራለች:: ሙያ በልምድ እንደሚገኝ ሁሉ በትምህርትም መዳበር አለበት ትላለች:: ስለዚህም እርሷ በርካታ የትምህርት ዓይነቶችን በመስኩ ዙሪያ እንደተማረችም ነግራናለች::
ሄለን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው በተወለደችበት ደብረጽጌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ/ጊዮርጊስ አካባቢ በሚገኘው ‹‹ኑኤራ›› ትምህርት ቤት ነው:: ከዚያ መማር የምትፈልገው የሙያ ትምህርት ስለነበር በቀድሞ እንጦጦ በአሁኑ ደግሞ ተፈሪ መኮንን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በመግባት የአውቶ ኢንጅነሪንግ ትምህርትን ተምራ በዲፕሎማ ተመርቃለች::
ለመማር ላይ ያላት ፍላጎትና አቋም ልዩ የሆነው እንግዳችን ወደ ሀበሻ ልብስ ስፌት ሥራ ከመግባቷ በፊት ከአውቶው በተጨማሪ ጎን ለጎን የተለያየ ሙያዎችን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በመግባት ተከታትላለች::
ለአብነትም የሹራብ ሥራ፤ የምግብ ሙያ፤ የጸጉር ሥራና የህትመት ሥራዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸውም:: ግን ከሁሉም ወዳው የምትሠራበት የዲዛይንና ልብስ ስፌት ሥራው እንደሆነ ትናገራለች:: ሄለን ከተማረችው ትምህርት አንጻር ማንም በዚህ መስክ ላይ ትሰማራለች ብሎ አልጠበቃትም::
በተማረችው ልክ ብዙ የሥራ አማራጮች ነበሯትም:: ይሁን እንጂ ምርጫዋና እጣ ፈንታዋ የፈለገችው ላይ አድርሷታል:: ይህም በዲዛይነርነትና ልብስ ሰፊነት ሥራ ላይ መሰማራት ነው:: በዚህ ሥራም ተሰጥኦዋን በደንብ እንድትረዳውና ጥበቧን እንደፈለገችው እንድታወጣ እንዳደረጋት ታነሳለች::
የህትመት ሥራውም እንዲሁ በልብስ ላይ የሚታይ ስለሆነ ወዳው እንድትሠራ አድርጓታል:: አሁን በምትሠራው ሥራ ደስተኛና ፍላጎቷን የምታሟላበት እንደሆነም የምታምነው ሄለን፤ ማንኛውም ሙያ የተሻለ ስለሆነ ብቻ ውጤት አያመጣም:: ፍላጎት ሊታከልበት ይገባዋል:: «ደስታን ይሰጠኛል ወይ?» የሚለውን መመለስ አለበት:: ስለዚህ ሙያን መውደድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው::
ሰዎች ለሚሠሩት ሥራ እውቅና እና ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል:: ተገደው የሚሠሩት መሆን የለበትም:: ምክንያቱም ግዳጅ ያለበት ሥራ ራስን ያዋርዳል፤ ጭንቀት ውስጥ ይከታል፤ ቤተሰብን ይበትናል፤ የቤት ሰላምንም ያደፈርሳል፤ ደንበኛን ጭምር ያሳጣል:: እናም መጀመሪያ ራስን ከዚያ ቤተሰብንና ኑሮን ለማሸነፍ ሙያን መምረጥ ያስፈልጋል:: ከዚያ ሕይወትን በመልካም ጎዳና መምራት ይቻላል ትላለች:: ‹‹እናት ሆኖ በጠባብ ቤት ውስጥ ሥራውን ማከናወን ከባድ ነው::
በዚያ ላይ የቤት ውስጥ ሥራውም ትጋትን ይጠይቃል:: ይሁን እንጂ ማንኛውም ሥራ አልጋ በአልጋ ሆኖ አያውቅም:: ሁሉ ነገር የሚመቻችበትም ሁኔታ የለም:: ስለዚህም ለወደዱት ሥራ ዋጋ መክፈል ግድ ነው:: ስኬታማነትም የሚመጣው በዚህ መልኩ ስንጓዝ ነው›› የምትለው ሄለን፤ የሚወዱት ሥራ ውጤት የሚለካው በልፋቱ ልክ ብቻ ሳይሆን በደስታውም መጠን ነው:: ፍላጎት ሲደመር ሥራ ስኬት ይሆናል:: እናም በዚህ መልኩ ፈተናውን በምንወደው ሙያና ሥራ እናልፈዋለን በማለት ትመክራለች::
ሴትነት ወደ ትልቅነት መሸጋገሪያ መንገድ ነው:: ብዙ ፈተና የሚያጋጥምበትም ጊዜ ነው:: ምክንያቱም በዚህ ጊዜ እውነተኛ የአዕምሮ፣ የልብና የኅሊና ሰላም ማግኘትን ይጠይቃል:: ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ወደ ሰላም የሚያደፈርሱ ችግሮችን መፍታት ሲሆን፤ የመጀመሪያው ራስን መቆጣጠርና ትክክል ለሆነው ነገር ጠንካራ አቋም ማሳየት ነው:: በሥራ አለመሸነፍ፤ ደስታን መፍጠርና ለምን ተፈጠርኩ ብሎ ማሰብም ስኬት ላይ ያደርሰናል:: በተለይም ሴት ሲኮን እርምጃው ሁሉ ጥበባዊ ስለሆነ አሸናፊነት ሩቁ የሚያስጉዝ አይሆንም:: እናም ሴቶች መጀመሪያ ማድረግ ያለባቸው ጭንቀታቸውን ከራሳቸው ላይ ማራቅ ነው::
ከዚያ ሥራ የማይበግራቸው መሆን አለባቸው:: የደስታቸውን ምንጭ አግኝተውም መጠቀም ይኖርባቸዋል:: ይህንን ካደረጉ በቤታቸው ችግር እንኳን ቢኖር ያልፉታል ትላለችም:: ሴት ልጅ ስታገባ ሁሉ ነገሯ የሞተና ያከተመላት ይመስላታል:: ይህ ግን ትክክል አይደለም:: እንዲያውም አቅም የምታገኝበትና የራስዋን ነጻነት የምታጣጥምበት ጊዜ ነው:: ምክንያቱም ጋብቻ ማለት ሙሽራ መሆን ብቻ አይደለም::
ትዳር ሲኖር ቤት ማደራጀት፣ በቤት ውስጥ ሰላምን መፍጠር፤ ከሁሉም በላይ እናትና ሚስት መሆን አስፈላጊ ነው:: እናትነት ደግሞ ልጆችን በመያዝ ረገድ ከፍተኛ ትዕግስትና ጽናትን ይጠይቃል:: ስለዚህም በጥሩ ጊዜና በክፉ ጊዜ፣ በሕመምና በጤንነት ጊዜ ሁሉ የሚለፋበትና ቤት ሙሉ የሚደረግበትም ነው::
ይህንን ማድረግና ከዚያ ማለፍ ደግሞ ደስታን ማግኘት ነው:: ሴቶችም ግዴታቸውን ከውዴታቸው ጋር አስተባብረው ደስታን ከፈጠሩ ሕይወታቸው ብሩህ የማይሆንበት ምክንያት የለም ትላለች:: በዚህም ሴቶች ሁልጊዜ መባዘናቸውን ደስታን ለመፈለግ ማድረግ እንዳለባቸው ትመክራለች::
ያን ጊዜ ቤታቸውንም ሆነ የውጪውን ማህበረሰቡ እንደሚያስደስቱ እምነቷን ከእራሷ ተሞክሮ በመነሳት ታስረዳለች::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 10/2014