ሕይወት ምንጊዜም በውጣ ውረድ የተሞላች ናት። የእለት ከዕለት ኑሮውን አልጋ በአልጋ ሆኖለት የሕይወት ዘመኑን የሚገፋ የትኛውም ዓይነት ምድራዊ ሰው የለም። ገንዘብ ቢኖረው በሕይወቱ የጤና ወይም ሌላ አንዳች እንቅፋት ይገጥመዋል።
ቁም ነገሩ እንዲህ ዓይነቱን መሰናክል እያለፉ ሰው የመሆንና የሰው ልጅ ‹‹ጥረህ ግረህ ብላ›› ተብሎ ከፈጣሪው የተሰጠውን ትዕዛዝ በመተግበር በሕይወት ለመኖር ጥረት በማድረግ የመፍጨርጨሩ ጉዳይ ነው።
ብዙዎች ሕይወታቸውን የሚገፉት በዚህ መንገድ ነው። የቂርቆሷ ወይዘሮ ሰላም ይታይህ /የተለወጠ/ ሕይወታቸውን በዚህ መንገድ እየገፉ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ። በደላላ አማካኝነት በገቡበት በሰው ቤት ሥራ በአሰሪያቸው ሌሊቱን ሲደበደቡ ያነጉ ነበር፡፡ ተስፋ ሳይቆርጡ የገቡበት ሌላኛው ቤት ግን መልካም አሰሪ ገጠማቸው፡፡ ወይዘሮ ሰላም መልካሟ አሰሪያቸው በትዳር ካጣመሯቸው ባለቤታቸው የ18 ዓመት ወንድ ልጅ ለማፍራት በቅተዋል።
የሚበጅሽ ትዳር እንጂ ትምህርት አለመሆኑን እኛ እናውቅልሻለን ብለው በታዳጊነታቸው የሞገቷቸውን ወላጆቻቸውን በመሸሽ ከሁለት ተመሳሳይ ችግር ከገጠማቸው ጓደኞቻቸው ጋር ከጎንደር አዲስ አበባ ከመጡ 30ኛ ዓመታቸውን ደፍነዋል። በዚህ ቆይታቸው እንዲሁ እኔ ነኝ የማውቅልሽ በሚሉ ደላሎችና ሰዎች ግፊት የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ውስጥ ተዘፍቀው ቆይተዋል።
በዚሁ ሳቢያም ሳያውቁት ለኤች አይ ቪ ኤዲስ ለመጋለጥ በቅተዋል። ሳያስቡት ለቫይረሱ መጋለጣቸውን መስማታቸው ከማስደንገጥ አልፎ ለተወሰነ ጊዜ የአልጋ ቁራኛ አድርጎና ተስፋ አስቆርጧቸው ነበር። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን የሰሙት ያውም በለስ ቀንቷት ወደ ውጪ የወጣች የቀድሞ ባልደረባቸውና ጓደኛቸው ጠርታቸው ወደ አሜሪካ ለመሄድ ፕሮሰስ (ሂደት) በጀመሩበት ወቅት መሆኑ የበለጠ ስሜታቸውን ጎድቶታል።
ይህ ቢሆንም ወይዘሮዋ በጥረታቸው ከዚህም አገግመው ቀሪ የሕይወት ዘመናቸውን ለመኖር ዛሬም እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ። ዛሬ የምናጋራችሁም የእኚህኑ ወይዘሮ ተስፋ ሳይቆርጡ በሕይወት ለመኖር የተደረገና አሁንም እየተደረገ ያለ ጥረት ነው።
ወይዘሮ ሰላም ተወልደው ያደጉት ሰሜን ጎንደር ዞን ወገራ በተሰኘ ገጠር አካባቢ ነው። እናት አባታቸው ሀብት ሞልቶ የተረፋቸው ቢሆኑም የትምህርት ጥቅም ያልገባቸው ነበሩ። አብዝተውም በትዳር ያምናሉ።
ሴት ልጅ ለዚሁ ትዳር ከሚያገለግላት ግብረ ገብና የቤት ውስጥ ሙያ ውጭ አደባባይ ወጥታ ከወንዱ እኩል ትምህርት መማር የለባትም የሚል አቋም ነበራቸው። ትምህርት ቤት መዋሏ በጎ ስነምግባሯን ይሸረሽርና ያባልጋታል ብለውም ያስባሉ። ወይዘሮዋ ደግሞ ራሳቸውን ማወቅ ከጀመሩበት ጀምሮ በአካባቢያቸው የሚማር ሴት ልጅ አይተው ባይሆንም በተፈጥሯቸው ትምህርት የሚወዱ ነበሩ።
ለትምህርት ከደረሱ ጀምሮም ትምህርት ቤት እንዲያስገቧቸውም ሲወተውቷቸው ነው የቆዩት። ሆኖም ሊያስተምሯቸው ስላልቻሉ ከሌሎች ተመሳሳይ ችግር ካለባቸው የአካባቢያቸው ታዳጊዎች ጋር በመመካከር ከወገራ ጠፍተው ጎንደር ከተማ ውስጥ ይመጣሉ። እዚህ የተመኙትን ትምህርት የሚያውቋቸው ዘመዶቻቸው ጋር ተቀምጠው እስከ ሦስተኛ ክፍል ይማራሉ።
ትምህርት ለመቀጠል አመቺው አዲስ አበባ ከተማ ነው የሚል ወሬ በመስማታቸውም እየሰሩ ትምህርታቸውን ከአራተኛ ክፍል ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ።
አሁን ድረስ እየኖሩበት ያለው ቂርቆስ ሰፈር ባለ ደላላ አማካኝነት ሳሪስ ሰው ቤት ይቀጠራሉ። በገቡ ማግስት እንኳን ትምህርታቸውን ሊማሩ ለሕይወታቸውም አደጋ ይገጥማቸዋል። ነገሩ እንዲህ ነው። አሰሪያቸው ሁለት ልጆች አሏት። ባለትዳርም ነች። ታዲያ ለአዳር ሥራ የሄደውን ባሏን እግር ጠብቃ እቤቷ በገቡ ማግስት አብረዋት ቁጭ ብለው ቢራ እንዲጠጡ ትጠይቃቸዋለች።
እሳቸው ደግሞ የገጠር ልጅ በመሆናቸውና ጎንደር ከተማ ውስጥ ሦስት ዓመት ቢቀመጡም ዘመዶቻቸው ከቤት ወደ ትምህርት ቤት፣ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ብቻ ስለሚፈቅዱላቸውና ቢራ ጠጪዎች ስላልነበሩ ቢራ ጠጥተው አያውቁም። መልኩንም አይተውት አያውቁም።
እናም አልጠጣም ይሏታል። ከዚያም መደብደብ ይጀምራሉ። ጎረቤት እንዳያስጥላቸው፣ በሩን ዘግተው ነበር የምትደበድባቸው። እሳቸው ሲጮሁና ሲያለቅሱ፤ እሷ ቢራዋን በመጎንጨት የቤቷን ሳሎን እያዞረች ስትደበድባቸው ሌሊቱ ይጋመሳል። ‹‹ንጋቱ ወገግ ሲል ሲደክማትና ቢራው በስካር ጥሏት ስትተወኝ እግሬ አውጪኝ ብዬ በርሬ ወጣሁ›› የሚሉት ወይዘሮዋ ለአዲስ አበባ ከተማ አዲስ በመሆናቸውና ቂርቆስ የምትለዋን ስም እንጂ ደላላው ያለበትን አካባቢ ያለመያዛቸው ከደረሰባቸው ጥቃት ጋር ቀኑን ሙሉ እንዳንከራተታቸው ያስታውሳሉ።
ማደሪያቸው ያሳስባቸውና ዱር አድሬ ዱርዬ ይጫወትብኛል ብለው በመስጋታቸው 11 ሰዓት አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ይገባሉ። ፖሊስ ደላላውን አፈላልጎ ያገኝላቸዋል። ሴትየዋ እንዲህ ማድረግ ልማዷ መሆኑና የአእምሮ ችግር ያለባት መሆኑም ይታወቃል። ሁለተኛ እሷ ጋር ሰው እንዳያስቀጥር ማስጠንቀቂያ ይሰጠውና ደላላው የሰው ቤት ሥራ ያስቀጥራቸዋል።
የሰው ቤት ሥራ ተመችቷቸው ነበር። ሰውነታቸው እንዲያምርና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ አድርጓቸዋል። ብዙ ጊዜም ተመላልሰው ጎንደር ያሉ ቤተሰቦቻቸውን መጠየቅ አስችሏቸዋል። የገቡባት አንዲት ሴት በተለይ የአገራቸውን ልጅ ድረዋት ለተወሰነ ዓመታት በትዳር ቆይተዋል። አንድ ልጅም ወልደዋል። ልጁ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ያለች አክስቱ ጋር ተቀምጦ እየተማረ ይገኛል። ዘግይቶ ትምህርት ቤት በመግባቱ በ18 ዓመቱ ሰባተኛ ክፍል ደርሷል።
አባቱን የፈቱት አገራችን እንግባ ስላላቸው ተመልሼ ገጠር አልገባም በማለታቸው ነበር። ትዳራቸውን ፈትተው የገቡባቸው ባልና ሚስቶች ያሉበት ቤት እክል ገጥሟቸዋል። ባልየው ለብቻው የወለዳቸው ሁለት ጎረምሳ ልጆች አሉት።
ሴትየዋ ደግሞ ከእሱ የወለደቻቸው ሁለት ትናንሽ ልጆች ነበሯት። እንዳጫወቱን ታዲያ አንደኛው ጎረምሳ ሲያልፉ ሲያገድሙ እየጎተተ ሥራ አላሰራሽ አላቸው። በተለይ አሰሪዎቻቸው ሳይኖሩ መኝታ ክፍላቸው ድረስ እየመጣ እጅግ ያስቸግራቸው ነበር። በኋላ ከጎረቤት እንደሰሙት ሰዎቹ ሰራተኛ የማይበረክትላቸው በዚህ ምክንያት ነው። ብዙዎቹን አስረግዟል።
ማርገዛቸው ሲታወቅ ደግሞ አሰሪዎቹ ያባርሯቸዋል። አንድ ቀን በፍልጥ መቱት። አባትየው ደርሶ ምንድነው ቢላቸው ዕውነቱን ነገሩት። እየሳቀና ‹‹ጎንደሮች አትነኩም›› እያለ በወር ደሞዛቸው ላይ ተጨማሪ የአንድ ወር ደሞዝ ጨምሮ ሰጣቸው። እንዲህ ቢሆንም ሁኔታው ስላላማራቸውና አሁን ያሉበት ቂርቆስ አካባቢ የምትኖር ሴትዮ ‹‹ከእንግዲህ የሰው ቤት ይቅርብሽ፣ እኔ በአንድ ጊዜ የሚለውጥ ሥራ አስገባሻለሁ። ሥራውን እስካስገባሽ ደግሞ በወር 30 ብር እየከፈልኩሽ የኔን ጠላ ታመላልሻለሽ›› ስላለቻቸው ከዚያ ቤት ወጡ።
ሴትዮዋ አሁን በሚኖሩበት ጀርባ ቤት ተከራይታ የምታሰራቸው ሴተኛ አዳሪዎች ነበሯት። የእሳቸው ሥራ ከሴትየዋ ጋር ጠላ እያመጡ ለእነዚህ ሴቶች መስጠት ነበር። ሆኖም ጠላውን ወደ ሴቶቹ በሚያመጡበት ወቅት ወንዶች እየቆነጠጡ ያስቸግሯቸዋል። ይሄንኑም ለአሰሪያቸው ይነግሯታል።
‹‹ታዲያ ምን ችግር አለው። ጥሩ እኮ ነው። እኔን ወርቅ በወርቅ ያደረጉኝ እነሱ ናቸው›› አለችኝ የሚሉት ወይዘሮዋ፤ አሁን የሚኖሩበት ጨርቆስ ሰፈር ጀርባ ቤት ተከራይታ ከምታሰራቸው ሴት አዳሪዎች ጋር እንዲሰሩ ታግባባቸዋለች።
ቁም ሳጥኗን ከፍታ በሥራው አካበትኩት የምትለውን ልብስና ወርቅ ታሳያቸዋለች። በዚህ ሁኔታ ተታልለው ወደ ሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ይገባሉ። ሆኖም እንዳለቻቸው ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑላቸውም። ልጃቸውን አዘግይተው ትምህርት ቤት ያስገቡበት ምክንያትም አንዱ ይሄ ነው።
ልጃቸው ነፍስ ሲያውቅ የሚሰሩትን ሥራ እንዳያይና ሥራ ቦታቸው እንዳይመጣ ቄራ አካባቢ የምትኖር አክስታቸው ጋር አስቀመጡት። አሁንም ከአክስታቸው ጋር ሆኖ እየተማረ ይገኛል። እንደነገሩን ሥራው ሌላው ቀርቶ ይሄን ልጃቸውን እንኳን ለማስተማርና ለማኖር አላስቻላቸውም። ይባስ ብሎ ለበሽታ ዳርጓቸዋል።
እንዳጫወቱን ሥራው ቡጢው፣ እርግጫው፣ ጥፊው፣ ስድቡ፣ ማመናጨቁ መከራ ነበር። ‹‹ብዙ ወንዶች የሚጣሉን ከከፈሉት በላይ በነፃ ሲጠቀሙብን ከላያችን ላይ ተነሱልን ስንላቸው እንቢ ብለው ነው›› የሚሉት ወይዘሮዋ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ ደንበኛቸው በሹል ድንጋይ አይናቸው ስር መቶ ያደረሰባቸውንና ጠባሳ ሆኖ የቀረውን አደጋ ለአብነት አሳይተውናል።
ዓይናቸው የጠፋ፣ ጥርሳቸው የረገፈና የተለያየ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ጓደኞች እንዳሏቸውም ነግረውናል። ሥራው በርካታ ሴቶችን ለኤች አይቪ በማጋለጥም ረገድ ጎጂ መሆኑን አጫውተውናል። ሴተኛ አዳሪዎች በአብዛኛው ወሲብ በሚፈፅሙበት ጊዜ አፈፃፀሙን ወንዱ ነው የሚወስነው።
በእርግጥ ከጊዜ በኋላ ስለ ኤች አይቪ ግንዛቤ እያገኙ በመጡበት ወቅት ሴቶች ደንበኛቸውን በኮንዶም እንዲጠቀሙ ይጠይቁ ነበር። ነገር ግን ቀደም ባሉት ጊዜያት ይህ ዓይነቱ ግንዛቤ ስላልነበራቸው እሳቸውን ጨምሮ ብዙዎቹ ‹‹ይሄን ያህል ገንዘብ እንሰጣችኋለን ባዶውን እናድርግ›› ቢሏቸው እምቢ አይሉም። በሴተኛ አዳሪነት ሥራ ላይ ተሰማርተው በነበሩበት ወቅት እሳቸውም ብዙ ጊዜ በዚህ መልኩ ከደንበኞቻቸው ጋር ወሲብ ፈፅመዋል።
ለኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ የተጋለጡትም በዚህ አጋጣሚ ሳይሆን እንደማይቀርም ይገምታሉ። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ በማያውቁበት ከ12 ዓመታት በፊት በየጊዜው ያማቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሰውነታቸው እየመነመነና ክብደታቸውም እየቀነሰ መምጣቱን ያስታውሳሉ። ራሴን ሆዴን፣ ጨጓራዬንና ጉንፋን እያሉ ለተከታታይ ቀናት ተኝተው የሚውሉባቸው ቀናት እንደነበሩም በፍፁም አይዘነጉትም። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ብዙ ጊዜ ኖረዋል። ሥራው ውስጥ እያሉ የወለዷቸው አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ልጆቻቸው ሲሞቱባቸውም የሞታቸው መንስኤ ኤች አይቪ መሆኑን አልጠረጠሩም።
የሩቁ ቀርቶ የቅርብ ዓመታቱን አስታውሰው እንዳወጉን አምስት የቅርብ ጓደኞቻቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው በኤች አይ ቪ ሞተዋል። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን ያወቁት አንዲት እዚሁ አሁን ያሉበት ቦታ በሴተኛ አዳሪነት የምትሰራ ባልደረባና ጓደኛቸው ውጭ ልትወስዳቸው በነበረበት አጋጣሚ ነው።
ጓደኛቸው በደላላ አማካኝነት በሰው ቤት ሥራ ተቀጥራ አረብ አገር ሄዳ ነበር። ቀልጣፋና ጎበዝ ስለሆነች ከአንዱ አገር ወደ ሌላው ሀገር ስትንፏቀቅ ቆይታ በለስ ይቀናትና አሜሪካ ትገባለች። ይሄኔም እጅግ የሚዋደዱና ብዙ ነገር አብረው ያሳለፉ ጓደኛሞች በመሆናቸው ልትወስዳቸው ሁኔታዎችን ታመቻቻለች። እሷ ጋር ለመሄድ ምርመራ ሲያደርጉም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ይነገራቸዋል።
‹‹በየጊዜው ሲያመኝ ቢቆይም፣ ሰውነቴ ቢመነምንም፣ ኤች አይ ቪ ይይዘኛል ብዬ አልጠበኩም። ቫይረሱ እንዳለብኝ ሲነገረኝ እጅግ ደነገጥኩ። ሰማይና ምድሩ የተደፋብኝም መሰለኝ›› ሲሉ መርዶውን የሰሙበትን ሁኔታ ያስታውሳሉ፤ ወይዘሮ ሰላም።
መርዶው ሲነገራቸው ዕድላቸውን አብዝተው አማረሩ። ፈጣሪያቸውን ወቀሱ። ባህር ማዶ ካለችው ከጓደኛቸው ጋር በስልክ ተላቀሱ። ለወራት ተስፋ በመቁረጣቸው ራሳቸውን ከአካባቢያቸው ሰዎች አግልለው እንደነበርም ይናገራሉ።
የሴተኛ አዳሪነቱን ሥራም ይሄኔ ነው እርግፍ አድርገው የተውት። ቡና አብሮ መጠጣት፣ መርፌ፣ ምላጭና እንደቢላ ያሉ ስለታማ ነገሮችን መዋዋሳቸውን አቆሙ። በሁኔታቸው ግራ የተጋቡትና ሳቂታ፣ ተጫዋች፣ ግልፅና ከነሱ ጋር የነበራቸው ማህበራዊ መስተጋብር የጠበቀ መሆኑን የሚያውቁት ጎረቤቶቻቸውና የአካባቢው ማህበረሰብ ባልተለመደ ባህርያቸው በእጅጉ ተገረመ። ‹‹በእርግጥ ጫት በፊትም አልቅምም።
አረቄ አለመጠጣቴን፣ ጥሬ ሥጋ መብላት ማቆሜን በአጠቃላይ ካልበሰሉ ምግቦች መታቀቤን ያዩ ጎረቤቶቼ በድርጊቴ አኮረፉኝ›› ይላሉ። እንዲህም ሆኖ የበሬ ግንባር ለምታክልና ከአንድ አልጋ በላይ በማታዘረጋ ቤታቸው በየቀኑ የሚከፍሉትን የ40 ብር የቤት ኪራይ ለመሸፈን የሚያስችላቸውን ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸው ነበር።
ኑሯቸውን ለመደጎም አልጋ ማከራየታቸውን፣ አንሶላ ማጠባቸውን፣ የጉልበት ሥራ መሥራታቸውን ቀጠሉ። በአካባቢው በአብዛኛው ውሃ ስለሚጠፋ አንሶላ አንዳንዴም የብርድ ልብስ ለማጠብ ባለ 20 ሊትሩን በረኪና በ30 ብር አብዝቶ መግዛት ስለሚያስፈልጋቸው ህመማቸውን ዋጥ አድርገው ተጉ። ቫይረሱ እንዳይጎዳቸው ሲወስዱት የነበረው መድሃኒት ሲያስቸግራቸው ቆዬ። ጥሩ ምግብ መብላት፣ ማረፍና የተወሰነ ጊዜ መተኛት ይፈልጋል። ሆኖም ቤታቸውና አካባቢያቸውም ሆነ የኑሮ ሁኔታቸውም ለዚህ አመቺ አልነበረም።
ሌላው ቀርቶ ከስድስት ሰዓት በፊት መተኛት የሚያስችላቸውና አረጋግቶ የሚያውላቸው አልነበረም። የተቀቀለ ድንች በሚጥሚጣ እንዲሁም ክሽን ብላ በዘይት የተሰራች ጎመን በዳቦ በመሸጥ ሕይወታቸውን ለማቆየት ግድ ይላቸው ነበር። ያም ሆነ ይህ ሁኔታውን ተላመዱት። ዘንድሮ ፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት መውሰድ ከጀመሩ ስምንት ዓመታቸውን አጠናቅቀዋል። ጤናቸው ተሻሽሏል። ነገር ግን የራሳቸው ቤት የላቸውም።
በደሃ ደሃ ተለይተው ቀበሌ ካመለከቱ አሥር ዓመት ሆኗቸዋል። ድጋሚ ቢጠይቁም ቅድሚያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ነው ተባሉ። ባለፈው ዓመት ገና ደግሞ እንደገና የሌሎቹ ተቃጠለ። እናም አሁን ቀበሌ ላሉት እንጂ ለእናንተ አይሰጥም ተባሉ። በምን አግባብ እንደሆነ ባያውቁም አንዳንዶች ቤት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲሚያስተውሉ ይናገራሉ።
ወይዘሮ ሰላም በሚገጥሟቸው መሰናክሎች ሳይረቱ የነገ ሕይወታቸውን ለማሳመር እየተፍጨረጨሩ የሚኖሩ ጠንካራ ሰው መሆናቸውን እኛም በዚህ አጋጣሚ ለመገንዘብ ችለናል። በመሆኑም ጥረታቸው በድጋፍ እንዲታገዝ ለባለድርሻ አካላት እያሳሰብን ጽሑፋችንን በዚሁ ደመደምን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2014