በገጠርም ይሁን በከተማ የሚኖሩት አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ሃሳባቸውን ቤተሰቦቻቸው ላይ ጥለው የሚማሩ ናቸው:: ስለምግብና መጠለያቸው፤ ስለ አልባሳትና የትምህርት ወጪያቸው አያስቡም:: አብዛኛዎቹ ልብሳቸው ታጥቦ ምግባቸው በስሎ የሚጠብቃቸው ናቸው:: አንዳንዶች ግን ከልጅነት እስከ እውቀት የማንንም እገዛ ሳያገኙ ህይወታቸውን ለመምራት ሲጥሩ ይታያል::
የዛሬው ባለታሪካችን ከነዚህ አንዱ ሲሆን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንግዳ አድርገን አቅርበነዋል። ሚሊዮን አስራት ይባላል:: ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ልዩ ስሙ ቀጨኔ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው:: ዓይነ ስውር ነው:: በልጅነቱ በኩፍኝ ህመም ምክንያት የአይኖቹን ብርሃን ማጣቱን የነገሩት አያቱ ናቸው:: ሚሊዮን ወላጅ እናቱን እና አባቱን አያውቃቸውም::
ሁለቱም ገና እርሱ መዳህ ሳይጀምር ነው የሞቱት:: በዚህ የተነሳ ያሳደጉት ሴት አያቱ ናቸው:: አያቱ በሸክላ ሥራ የሚተዳደሩ አቅመ ደካማ ነበሩ:: በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ቤት ተከራይተው ምግቡንና ልብሱን እየቻሉ እንዳሳደጉት ይናገራል:: ከልጅነቱ ጀምሮ ዓይነ ስውር ስለነበር አስተዳደጉ እንደሌሎች ህጻናት ቀላል አለመሆኑን ይገልጻል::
በዚህ የተነሳ አያቱ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለው አሳድገውታል:: እንደልጅ አንድ ቦታ ትተውት መሄድ ስለማይችሉ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ይዘውት ይሄዱ እንደነበር ያስታውሳል:: ተወልዶ ባደገበት አካባቢ አይነስውር ልጆች ስለማይገጥሙት እርሱ ላይ ብቻ እንዲህ አይነት የጤና ችግር መከሰቱን እያሰበ በተፈጥሮው ያዝን ነበር:: ልጆች እራሳቸውን ችለው ሲጫወቱ ሲወጡና ሲገቡ እርሱ በአንድ ቦታ ተወስኖ ለመቀመጥ ይገደዳል:: አንዳንዴም በሰዎች እገዛ ይንቀሳቀሳል::
የሰፈር ልጆች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ማድረግ ባለመቻሉ ይከፋው ነበር:: ዛሬ ላይ ሆኖ የልጅነት ዘመኑን ሲያስታውስ እንደህልም ትዝ ትዝ የሚለው ከጓደኞቹ ጋር መጫወት እየፈለገ እቤት ውስጥ ተቀምጦ የሚውለውን ነው:: ሚሊዮን መማር ስለነበረበት አያቱ አይነ ስውራን ትምህርት ቤት ሊያስገቡት አምስት ኪሎ ምስራች አይነስውራን ትምህርት ቤት ይዘውት ይሄዳሉ:: አያቱ ወጪውን ሸፍነው ማስተማር እንደማይችሉ በመግለጽ ድርጅቱ እንዲያግዛቸው ይማጸናሉ:: እየተመላለሰ መማር ስለሚከብደው በአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ ቢማር እንደሚሻል ምክር ተሰጥቷቸው ወደ ቤት ይመለሳሉ::
አቅመ ደካማዋ አያት የሚሊዮን እራሱን ችሎ መኖር ያስጨንቃቸው ስለነበር አዳሪ ትምህርት ቤት ማፈላለግ ይጀምራሉ:: በመጨረሻም በራሱ በምሥራች ዓይነ ሥውራን ትምህርት ቤት አማካኝነት ምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ አይነ ሥውራን ትምህርት ቤት ያስገቡታል::
እዚያም የብሬል ትምህርቱን እየተማረ ለሁለት ዓመት ከቆየ በኋላ ሚሊዮን ድንገተኛ የጤና መታወክ ይገጥመዋል:: ሰውነቱ ላይ ሽፍ ብሎበት መቆሳሰል ሲጀምር በተለምዶ አጠራር አልማዝ ባለጭራ የሚባለው ህመም እንደሆነ ተነግሮት ነቀምት ሆስፒታል ህክምና ማድረግ ይጀምራል:: ምንም አይነት የጤና መሻሻል ባለማግኘቱ ትምህርቱን ትቶ አዲስ አበባ አያቱ ጋር ይመለሳል:: ወዲያው አያቱ ባህላዊ ህክምና ወስደውት መድኃኒት ከተሰጠው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ቁስሉ ይድናል::
ሚሊዮን ጤናው ከተሻሻለ በኋላ ተመልሶ ባኮ አይነስውራን ትምህርት ቤት ይመለሳል:: ትምህርት ቤቱ ሙሉ የጤና ምርመራ ሲያደርግለት የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደሙ እንዳለበት ይነገረውና ዳግም ሊቀበለው እንደማይችል ያሳውቀዋል:: ገና ክፉና ደጉን መለየት በማይችልበት የእድሜ ክልል ውስጥ ሆኖ ለተለያዩ የጤና ችግሮች መዳረጉ ክፉኛ ያሳዝነዋል፤ አይነ
ስውርነቱ ሳያንስ የኤች አይቪ ቫይረስ በደሙ መገኘቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበት እንደገና አያቱ ቤት ገብቶ መኖር ይጀምራል:: ብዙ ሰዎች ተደራራቢ የጤና ችግር እንዳለበት እያዩ ተስፋ ሲያስቆርጡት አያቱ ግን ያፅናኑት ነበር::
ተምሮ እራሱን አሸንፎ መኖር እንደሚችል እያበረታቱት አብረው መኖር ይጀምራሉ:: ሚሊዮን በምን ምክንያት የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደሙ እንደተገኘ አሁን ድረስ አያውቅም:: ነገር ግን ባኮ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት በነበረበት በዚያ የልጅነት እድሜው ምናልባት ከሞግዚቶች ጋር የነበረው ጥንቃቄ የጎደለው ንክኪ ተጋላጭ ሊያደርገው እንደሚችል ይገምታል::
አያቱ ሚሊዮንን የማስተማር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ብዙ ጥረቶችን ያደርጉለት ነበር:: ከቆይታ በኋላ በአይነ ስውራን ማህበር በኩል ጃንሜዳ አካባቢ በሚገኘው ጀርመን ቸርች ስኩል ይገባል:: ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በዚሁ ትምህርት ቤት ትምህርቱን መማር ይጀምራል:: ጀርመን ቸርች ስኩል ሲማር ከቤቱ እየተመላለሰ ነበር:: ትምህርት ቤቱ በወር ዘጠና ብር ለታክሲ ይሰጠው ነበር:: እርሱ ግን አያቱን እያስቸገረ ነበር የሚማረው:: በድንገት ግን ያላሰበው መከራ ይገጥመዋል:: ሰባተኛ ክፍል ሲደርስ እንዳይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት አያቱ በድንገት ያርፉና ሰማይ ይደፋበታል:: ለጊዜው በሰዎች እርዳታ ትምህርቱን እንዲከታተል ይደረጋል:: ዛሬም ድረስ የአያቱ ሞት ክፉኛ እንደጎዳው፤ ጎዳና እስከመውጣት እንዳደረሰው ይናገራል::
ሚሊዮን እስከ ስምንተኛ ክፍል በጀርመን ቸርች ስኩል ከተማረ በኋላ የዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል ትምህርቱን በበላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት ተምሯል:: አሁን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው::
ከአያቱ ሞት በኋላ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ በርካታ የሚነገሩና የማይነገሩ ፈተናዎችን ማሳለፉን ይገልጻል:: ከሁሉ በላይ የእለት ጉርስ ማግኘት ፈተና ሆኖበት እንደነበር ይገልጻል::
የቤት ኪራይም መክፈል ያቅተዋል:: ለተወሰነ ጊዜ ሰዎች እየከፈሉለት አያቱ ተከራይተውት በነበረው ቤት ውስጥ ከቆየ በኋላ የሚከፍልለት ሲያጣ ቤቱን ለቆ ለመውጣት ይገደዳል:: ከዚህ በኋላ ነበር የሚሊዮን ችግሮች ክፉኛ እየበረቱ የመጡት:: የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደሙ ያለበት፣ ማረፊያ ያጣ፤ የሚላስ የሚቀመስ የሌለው አይነስወር፤ በዚህም ላይ ተምሮ እራሱን ለማሸነፍ ሁሌም በትግል ውስጥ የሚገኝ:: ሚሊዮን በተለይም ከአስረኛ ወደ አስራ አንደኛ ክፍል ተዛውሮ በዳግማዊ ሚኒልክ ትምህርት ቤት መማር ከጀመረ ወዲህ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እየማሰነ እንደሚገኝ ይናገራል::
አንድ ቀን እየሠራ አንድ ቀን እየተማረ፣ ብዙውን ጊዜ ጎዳና ላይ እያደረ፤ ገንዘብ ሲያገኝም መርካቶ አካባቢ እየሄደ ከሃያ እስከ ሰላሳ ብር ከፍሎ ወለል ላይ እየተኛ አሳልፏል:: በዚህ ችግር ውስጥ ሆኖም ከባሰበት ይቀራል እንጂ ትምህርቱን ማቋረጥ አይፈልግም ነበር:: ከሁለት ሰዓት እስከ አስር ሰዓት ይማራል::
ከአስር ሰዓት በኋላ ደብተሩን በጀርባው ተሸክሞ እንደ ሶፍትና ማስክ የመሳሳሉ ነገሮችን እየሸጠ በሚያገኛት ገንዘብ ጉሮሮውን አብሶ እዚያው ጎዳና ላይ ከአንድ ግንብ ስር ጠጋ ብሎ ያርፋል:: ማለዳ ልብሱን ሰብስቦ ማዳበሪያ ውስጥ ከከተተ በኋላ ሰዎች ጋር በአደራ አስቀምጦ ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳል::
በዚህ መልክ ለዓመታት ህይወቱን እንደመራ ይናገራል:: ሚሊዮን አንድ ቀን ጎዳና ላይ አድሮ የገጠመውን ክስተት እንዲህ ያስረዳል:: ‹‹ከትምህርት ቤት ወጥቼ እስከ አንድ ሰዓት ድረስ ማስክ ስሸጥ አመሸሁ:: ባገኘኋት ሳንቲም እራቴን በላሁና የሌሊት ልብሴን ካስቀመጥኩበት ቦታ ወስጄ ወደ መኝታዬ ሄድኩኝ:: የምተኛው አውቶቡስ ተራ አካባቢ ጎዳና ላይ ነው:: ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ሽንቴ ሲመጣብኝ ከመኝታዬ እራቅ ብዬ ልሸና ፈለግኩና ትንሽ ሄድኩኝ:: ሸንቼ ከተመለስኩ በኋላ የመኝታዬን ቦታ ማግኘት አቅቶኝ ብዙ ተንከራተትኩኝ:: በጣም ደነገጥኩኝ:: ልብሴም ደብተሬም እዚያው ነበር::
በአጋጣሚ አንድ ሰው ወደዚህና ወደዚያ ስል አይቶኝ ምን ትፈልጋለህ አለኝ:: የማድርበት ቦታ ጠፍቶኝ ነው አልኩት:: ሰውየው ቤት ውስጥ የማድር መስሎት በዚህ ውድቅት ለምን ከቤትህ ወጣህ አለኝ:: ጎዳና ላይ እንደማድር ስነግረው በጣም እያዘነ መኝታዬን ፈልጎ ካሳየኝ በኋላ አጽናንቶኝ ሄደ::
በጎዳና ላይ ስኖር ከአንድም ሁለት ጊዜ ቦርሳዬ ከነ ደብተሩ ተወስዶብኛል:: የምለብሰው የሌሊት ልብስም ተወስዶብኝ ያውቃል፤ ግን አንዳንድ ቅን ሰዎች በሚያደርጉልኝ ድጋፍ ወዲያው እየተካሁት ህይወቴን እቀጥላለሁ:: አንድ ቀን እኔና ሌላው አይነስውር ጓደኛዬ ተያይዘን አስፓልት ስናቋርጥ ማሃል ላይ ስንደርስ ጓደኛዬ ወድቆ ለጥቂት መኪና ሊገጨን ሲል ተርፈናል::›› ጎዳና ላይ እያደረ ትምህርቱን የሚማረው አይነስውር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንድ ዩቲዩብ ላይ የህይወት ታሪኩን የሚገልጽ ዶክመንተሪ ተሰርቶ ከተለቀቀ በኋላ አንዲት እናት ለተወሰኑ ወራት የቤት ኪራይ ከፍለውለታል:: ሌሎችም አስቤዛ ገዛዝተውለት አዲሱ ገበያ አካባቢ አንዲት ትንሽ ክፍል በአንድ ሺህ ሶስት መቶ ብር ተከራይቶ መኖር ጀምሯል::
ሚሊዮን የእናቱና አባቱ ዘመዶች እንዳሉ ቢሰማም አንድም የቅርብ ዘመድ ሊረዳው አለመፈለጉ እንደሚያሳዝነው ይገልጻል:: አንዳንድ ቅን ሰዎች ስለሚያደርጉለት ትብብርም ምስጋናው ከፍ ያለ ነው::
ሚሊዮን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የኤች አይቪ መድኃኒት መውሰድ ጀምሯል:: የጤና ክትትል እያደረገ መድኃኒት የሚወስደው ከጥቁር አንበሳ ነበር:: በኋላ ግን መድኃኒቱ አልስማማው ሲል ኤች ኤፍ ከተባለ ክሊኒክ ሌላ ተስማሚ መድኃኒት እየተሰጠው መጠቀም ጀምሯል:: ድርጅቱ ለተወሰኑ ሰዎች የዱቄት ድጋፍ ቢያደርግም ሚሊዮን ግን አብስሎ መብላት ስለማይችል ከመድኃኒት ውጪ ሌላ ምንም አይነት ድጋፍ እንደማይደርግለት ተናግሯል::
የቤት ኪራይ እና የምግብ እየቻሉት ያሉት ሁለት ግለሰቦች ቃል የገቡለት እስከ ሶስት ወር ብቻ በመሆኑ ሚሊዮን ከወራት በኋላ ተመልሶ ጎዳና የሚወጣ እየመሰለው በስጋት ውስጥ ነው:: ለጊዜው ምግብ በማብሰል የምትተባበረው ቅን ሰው አግኝቷል፤ እነዚህ ሁሉ ግን ዘለቄታ ስለማይኖራቸው ሰዎች የአቅማቸውን እንዲረዱት ይፈልጋል:: በብሬል ማጣት ምክንያት ትምህርቱን እየጻፈ ሳይሆን እያዳመጠ ብቻ ለመማር መገደዱን ይናገራል::
የወረቀት እጥረትም አለበት፤ በአጠቃላይ ትምህርቱን እየተማረ ያለው አንድ አይነ ስውር ሊኖረው የሚገባውን ቁሳቁስ ሳያሟላ ነው:: በተለይም መንገድ የሚመራበት ምርኩዝ /ስቲክ/ ቢበዛ ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎት ስለማይሰጥ በየጊዜው ለመግዛት እንደሚገደድ ይናገራል:: ከዚያ ይልቅ ኬን / ብዙ ጊዜ መቆየት የሚችል ምርኩዝ/ መግዛት ቢችል ረዥም ዓመት ሊያገለግለው እንደሚችል ይገልጻል፤ ግን አቅሙ አልፈቀደለትም::
ከእርዳታ ድርጅቶችም ማግኘት አልቻለም:: ሚሊዮን ሁልጊዜ የሰው እጅ እያዩ መኖር እንደሚያሳቅቀው ይናገራል:: ቢያንስ ግን ትምህርቱን እስከሚጨርስ ድረስ የሰዎች እርዳታ የግድ እንደሚያስፈልገው ያምናል::
ለዓመታት እየተማረ ሥራ ለመሥራት ቢሞክርም ፍላጎቱን ሊያሟላ አልቻለም:: ትምህርቱንም ጠበቅ አድርጎ እንዳይዝ ተጽዕኖ ፈጥሮበታል:: ትምህርቱን ጨርሶ ሙሉ ጊዜውን ሥራ ላይ እስከሚያደርግ ድረስ የቤት ኪራይ፣ የአስቤዛ የትምህርት ቤት ወጪውን ሰዎች እንዲያግዙት ይፈልጋል::
ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ግን የአቅሙን ያህል ሰርቶ የመኖር ህልም አለው:: ልክ እንደሌሎች አይነስውር ጓደኞቹ እንደ ሶፍት ማስክና ሌሎች ቀለል ያሉ እቃዎችን እየሸጠ እራሱን ማኖር እንደማያቅተው ይገልጻል:: እንግዲህ ህይወት መልከ ብዙ ነች:: በከፍታም በዝቅታም ሀዲድ ላይ ትከንፋለች::
ሰው በእንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ሆኖም ኑሮውን ለማሸነፍ ይጥራል:: የሚሊዮን ጥንካሬ ለብዙዎቻችን ትምህርት ይሰጠናል::
ፈተናዎችን የመቋቋም ብርታቱና ጽናቱ ያንፀናል:: በስቃይ ውስጥ እየማሰነ በተስፋ የተሞላ ጠንካራ መንፈስ ያለው ሰው ነው:: ችግሩን ልንጋራውና ልናበረታታው ይገባል:: በቀጣይ ሳምንት ሌላ ባለታሪክ ይዘን እስከምንገናኝ፤ ቸር እንሰንብት::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30/2014