ከተወዳጅ የእግር ኳስ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የአፍሪካ ዋንጫ ለ33ኛ ጊዜ ሊካሄድ ቀናት ብቻ ቀርተውታል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት ዳግም ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት በዚህ ወቅት ካሜሮን ለሁለተኛ ጊዜ በአህጉሩ ትልቁን የእግር ኳስ ውድድር ለማሰናዳት ተዘጋጅታለች። ተሳታፊ ሃገራትም ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ፤ ብሄራዊ ቡድኖቻቸውንም እያሳወቁ ይገኛሉ።
ውድድሩን በበላይነት የሚመራው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እአአ ከ1972 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የአዘጋጅነቱን እድል በሰጣት ካሜሩን 24 ቡድኖችን ከጥር 1-29/2014 ዓ.ም ድረስ ያወዳድራል። ይህ ውድድር ዛሬ በሚጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ወራትን አስቀድሞ እንዲካሄድ መርሃ ግብር ቢያዝለትም በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ሲራዘም ቆይቶ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከ20-60ሺ ተመልካቾች የመያዝ አቅም ባላቸው ግዙፍ ስታዲየሞች ውድድሩ እንደሚጀመር ይጠበቃል። ዓለም አቀፍ የስፖርት መገናኛ ብዙሃንም ጨዋታዎቹን በቀጥታ ስርጭት ሽፋን ይሰጣሉ።
የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የሚካሄድበት ኳስ ‹‹ቶፉ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን፤ ስያሜውንም በቀለማት ካሸበረቀውና የንጉሳዊያን መለያ ከሆነው የካሜሮናዊያን ባህላዊ ልብስ የተገኘ መሆኑን ካፍ በድረገጹ አስነብቧል። ስያሜውም ባህልን፣ ጌጥን፣ ክብር፣ ቅርስና አንድነትን እንደሚያጠቃልል መረጃው ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ከዓመታት በኋላ ስትመለስ ከዚህ ቀደም ከነበረው ተሳትፎዋ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅዳለች። እቅዱን ለማሳካትና ተወዳዳሪ ለመሆንም ብሄራዊ ቡድኑ ሁለት ሳምንታትን አስቀድሞ ወደ ካሜሮን መጓዙ ይታወቃል። ከአየር ሁኔታው ጋር ለመላመድ በሚል ወደ መካከለኛው አፍሪካ ሃገር ያቀኑት ዋሊያዎቹ ዴ ዱፒዩቴ በተባለው ሆቴል ማረፊያቸውን አድርገው ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ቡድኑ በሜዳ ላይ ከሚያደርገው ዝግጅት ባለፈ በተንቀሳቃሽ ምስል ትንተና የታገዘ ትምህርት ለተጫዋቾች እየተሰጠም ይገኛል።
ከቡድኑ ውጪ የነበሩ ተጫዋቾችም ባለፉት ቀናት ቡድኑን መቀላቀላቸው ተረጋግጧል። ለግብጹ ክለብ አል ጉና የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ ቡድኑን ዘግይተው ከተቀላቀሉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆኗል። የመሃል ሜዳው ተጫዋች ያውንዴ አየር ማረፊያ ሲደርስም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሮቶኮል ኃላፊ አቶ ሚካኤል እምሩ በስፍራው በመገኘት አቀባበል እንዳደረጉለትም ፌዴሬሽኑ ጠቁሟል።
ሌላኛው በህመም ምክንያት ከቡድኑ ጋር ያልተጓዘው ተከላካዩ መናፍ አወል ምትክ የባህርዳር ከተማው የተከላካይ መስመር ተጫዋች አህመድ ረሺድ ጥሪ እንደተደረገለት ተሰምቷል። ተጫዋቹ ትናንት ወደ ካሜሮን ያቀና ሲሆን፤ ዝግጅቱንም ከዛሬ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
የዝግጅቱ አንድ አካል የሆነውን የወዳጅነት ጨዋታም በፌዴሬሽኑ ዕቅድ መሰረት ትናንት ከሱዳን ብሄራዊ ቡድን ጋር አካሂዷል። ቡድኖቹ በስምምነታቸው መሰረት ጨዋታው የአቋም መፈተሻ እንደመሆኑ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሰዓት የሚረዝሙ ሁለት ጨዋታዎችን ማምሻውን አካሂደዋል። ጨዋታውም በዝግ ስታዲየም የተካሄደ ሲሆን፤ ካሜሩናዊያን የፊፋ ዳኞች ጨዋታውን በበላይነት መርተውታል።
ዋሊያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫው በመጀመሪያው ምድብ ከአዘጋጇ ካሜሮን፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቨርዴ ጋር እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በመጀመሪያው ጨዋታም ከኬፕቨርዴ ጋር ሲገናኙ ቀጣዩን ጨዋታ ደግሞ ከአዘጋጇ ካሜሮን እና ቡርኪና ፋሶ ቤሄራዊ ቡድኖች ጋር የሚቀጥሉ ይሆናል ።
ምድቡን በተመለከተ የቅድመ ጨዋታ ግምቱን ያስቀመጠው የቢቢሲ ዘገባ፤ ኢትዮጵያ የኮንፌዴሬሽኑ መስራች ሃገር መሆኗን የምታሳይበት መልካም እድል እንደሚሆናት አስታውቋል።
ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ቡድኑን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመለሰው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ማራኪ ጨዋታ የሚጫወት ቡድን መገንባት መቻሉን፤ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ እንዲሁም በሌሎች የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ እንደታየው ከሆነም ወደ 16ቱ የመግባት እድል ያለው መሆኑንም በቅድመ ግምቱ ተቀምጧል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 22/2014