ለዘመናት የስፖርት ቤተሰቤ ጥያቄ የነበረው የዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ምላሽ አግኝቶ አበረታች እንቅስቃሴ መታየት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። በተለያዩ ክልሎች በተለያየ መጠን ከሚገነቡት ስታዲየሞች ባሻገር በመንግስት በጀት ግዙፍ የኦሊምፒክና የዓለም ዋንጫ ስታዲየም በአዲስ አበባ ከተማ በመገንባት ላይ ይገኛል። ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተካሄደ ይገኛል።
ከ62 ሺህ በላይ ተመልካቾችን በወንበር የመያዝ አቅም ያለው የብሄራዊ ስታዲየም ግንባታ ታህሳስ/2008 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ የመዋቅር ስራው ተጠናቆ በአሁኑ ግዜ ማጠቃለያ የሆነው ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል። ግንባታው አሁን ያለበትን ሂደትም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አመራሮች በስፍራው ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል። በጉብኝቱም ወቅት የግንባታው አማካሪ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር መሰለ ኃይሌ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደም በአካል በመገኘት የስታዲየሙን ግንባታ ተመልክተው አቅጣጫ ካስቀመጡ በኋላ የግንባታው በጥሩ ሁኔታ አየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል። በቀጣይም የስታዲየሙን ግንባታ የማጠናቀቅ ስራው ከውጫዊ የማስዋብ ስራው ጎን ለጎን እንዲሰራ በማድረግ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ፤ በዚህ ወቅት እየተከናወነ ያለው በስታዲየሙ የውስጥ ክፍሎች ያሉ ስራዎች ሲሆኑ በዚህም በርካታ ለውጥ መኖሩን የተመለከቱ መሆኑን ይገልጻሉ። የውሃ መተላለፊያ ግንባታውን ጨምሮ የተዘረጉ፣ የተገጠሙ፣ በውጪ በኩልም ሌሎች የተሰሩ የግንባታው አካል የሆኑ በርካታ ስራዎች ጥሩ በሚባል ሂደት እያለፉ ይገኛሉ። የዚህ ስታዲየም ግንባታ ለሃገርም ጭምር መልካም የሚባል ምልክት በመሆኑ በሚኒስትሩ በኩል በትኩረት ክትትል እየተደረገበት መሆኑንም ያረጋግጣሉ።
ከግንባታው ጋር ተያይዞ በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች ማጋጠማቸው ግንባታው በሚፈለገው ፍጥነት እንዲሁም በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዳይጓዝ ምክንያት መሆኑ ይስተዋላል። ለግንባታው ማከናወኛ የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ከውጪ ሃገራት የሚገቡ
መሆኑን ተከትሎ በመጓጓዣ ላይ የገጠሙ ችግሮች፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም የተወሰኑ እቃዎች በውጪ ሃገራት በትዕዛዝ ተሰርተው የሚገቡ መሆኑ እንዲሁም በስታዲየሙ ግቢ ውስጥ በነበረው የሰፋሪዎች በወቅቱ አለመነሳት ምክንያት ግንባታው እስካሁን መድረስ ከሚገባው ደረጃ ላይ ሊገኝ አልቻለም።
እነዚህ ችግሮች አስቀድመው ይታዩ የነበሩ ሲሆን፤ ጥቂት የሚሆኑት ግን ሊፈቱ አልቻሉም። ከእነዚህ መካከል በዚህ ወቅትም በግንባታው ላይ በተለይ ክፍተት ሆኖ የቀጠለው ከውጪ ምንዛሪ ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑን ሚኒስትሩ ይጠቁማሉ። ግንባታውን
በማከናወን ላይ በሚገኘው የቻይናው ተቋራጭም ይኸው ጉዳይ እንደ ጥያቄ ሲነሳ ቆይቷል። የውጪ ምንዛሪው ገንዘብ የተፈቀደ ቢሆንም እስካሁን ክፍያው ባለመጠናቀቁ በግንባታው ላይ የራሱን የሆነ ተጽእኖ ፈጥሯል። ይህንንም ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር እንዲለቀቅ ለማድረግ እንደሚሞከር ተስፋቸውን አንጸባርቀዋል።
ይህ ግዙፍ ስታዲየም ራሱን ችሎ ካረፈበት ስፍራ ባሻገር ዙሪያውን የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶችን የሚያስተናግድ እንዲሁም የተለያዩ ግልጋሎቶችን የሚሰጡ ግንባታዎች ይከናወኑበታል። ይሁን እንጂ እነዚህ ግንባታዎች ከሚሰፍሩባቸው ከአንዱ አቅጣጫ ህገወጥ ሰፋሪዎች መሬቱን ወረው ይዘውት ቆይተዋል። እነዚህ ሰፋሪዎች በተለያየ መንገድ እንዲነሱ ቢደረግም የእምነት አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ተቋም ግን ምትክ ቦታ ባለማግኘቱ ስፍራው ነጻ ሊሆን አልቻለም።
ይኸውም ሌላው በግንባታው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር የቀጠለ ጉዳይ መሆኑ በሚኒስትሩ ተመላክቷል። ጉዳዩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የሚመለከት ሲሆን፤ በሚኒስትሩ በኩል ንግግር ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ደብዳቤ ከመጻፍ ባለፈም ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ተይዟል። ከዚህ በኋላም ምላሽ ካልተገኘ ሚኒስትሩ በአካል በመቅረብ ጥያቄውን ለማቅረብ መወሰኑንም አስረድተዋል።
ገንዘቡ የሚለቀቅ ከሆነም በተቋራጩ በኩል የሚነሳው ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ በተረጋጋ ሁኔታ ስራው የሚቀጥል ሲሆን፤ የእምነት ተቋሙ ተቀያሪ ቦታ አግኝቶ ሲነሳም በስታዲየሙ ዙሪያ ያለው ግንባታ ተጠናቆ በቅርብ ስራ ላይ እንዲውል ለማድረግ ጥረት የሚደረግ ይሆናል ሲሉም ተስፋቸውን አንጸባርቀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 20/2021