ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ሙያዎች በርካታ ስራ ያከናወኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲራክ ሃብተማርያም የቀብር ስነስርዓት ተከናወነ፡፡
ከእግር ኳስ ተጫዋችነት፣ በስፖርት ተቋማት አመራርነት፣ በመምህርነት እንዲሁም በኢንስትራክተርነት ሲሰሩ የቆዩት ዶክተር ሲራክ ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምሮ በስፖርቱ ለረጅም ዓመታት አሳልፈዋል፡፡ ይኸውም ለተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ምርጥ ቡድን በተጫዋችነት እንዲሁም በጅማ ከተማ በአሰልጣኝነት ካገለገሉ በኋላ፤ በጅማ እርሻ ኮሌጅ የስፖርት መምህር ሆነው ሰርተዋል፡፡ ኮሌጁ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር መቀላቀሉን ተከትሎም የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ዲፓርትመንት ኃላፊ በመሆን ማገልገላቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባሰፈረው የህይወት ታሪካቸው ላይ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲመሰረትም ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለአራት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፤ በካፍ ኢንስትራክተርነም ለበርካታ የእግር ኳስ አሰልጠኞች ስልጠና ሰጥተዋል። በአሁኑ ወቅትም በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉ የነበሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲራክ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡ በቅርቡ የተሻሻለው የካፍ የአሰልጣኞች ላይሰንስ ማንዋልን በማዘጋጀት ላይ የነበሩ አንጋፋ ባለሙያም ነበሩ።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲራክ ከትናንት በስቲያ በመደበኛ የስራ ገበታቸው ላይ ሳሉ በድንገተኛ ህመም ህይወታቸው አልፏል፡፡ የቀብር ስነስርዓታቸውም ትናንት በቀራኒዮ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ በኃላፊነት ያገለገሉበት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እንዲሁም የተለያዩ የስፖርት ተቋማትም በአንጋፋው የስፖርት ባለሙያ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡ አዲስ ዘመን ስፖርትም በአንጋፋው የስፖርት ባለሙያ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን እየገለፀ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 19/2014