ኢትዮጵያ መስራች በሆነችበት የአፍሪካ ዋንጫ ከዓመታት በኋላ ዳግም በተሳታፊነት ተመልሳለች፡፡ በዚህ ውድድር በምድብ አንድ የተደለደለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ዝግጅቱን ለመጀመር አስቀድሞ ጉዞውን ወደ ካሜሮን ያውንዴ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፤ ልምምድ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ጥር 1/2014 ዓም በሚጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሆነው ብሄራዊ ቡድኑ ውድድሩ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ወደ አዘጋጇ ሃገር ካሜሮን ያቀናው ከአየር ሁኔታው ጋር ተላምዶ ዝግጅቱን እንዲያደርግ ነው፡፡ ቡድኑ ማረፊያውን ባደረገው ያውንዴ ሲደርስም በሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን፣ በከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች የታጀበ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ከጥቂት እረፍት በኋላም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ብሄራዊ ቡድኑ ቀላል እንቅስቃሴ በማድረግ ወደ ልምምድ የገባ ሲሆን፤ እስከ ውድድሩ መጀመሪያ ድረስም ልምምዱን የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ ካሜሩን ያቀኑት ዋሊያዎቹ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአሸኛኘት ስነስርዓት እንደተደረገላቸው የሚታወስ ነው፡፡ በስነስርዓቱም ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የመልካም ምኞታቸውን ለቡድኑ አስተላልፈዋል፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተንቀሳቃሽ ምስል ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹በዚህ ውድድር ስትሳተፉ ከመጀመሪያዎቹ ተርታ አይደለንም በማለት ከዝቅተኛ ስሜት እንዳትነሱ አደራ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ ዋንጫ ላይ ለመድረስ እያንዳንዱ ቡድን እድል የተለያየ ቢሆንም ስንወዳደርግን ኢላማ አድርገን የምንነሳው ከፍ አድርገን፣ ዋንጫንም በማሰብ መሆን አለበት፡፡ እንደዚህ ሲሆን ነው የምትችሉትን ወኔ ለመሰነቅ የምትችሉት›› ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው፤ ቡድኑ በአሸናፊነት መንፈስ መጓዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ሌሎች ቡድኖች ጠንካራ በመሆናቸው አንችልም የሚል መንፈስ ሳይኖራቸው በቁርጠኝነት ‹‹እናሸንፋለን፤ እንችላለን›› በሚል ወደ ውድድር መግባት አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ወሳኝ ሲሆን፤ ቡድኑ ሳይደናገጥ ተልዕኮውን ለመፈጸም በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ቡድኑ የሃገር መልካም ገጽታን ማሳየት እንደሚገባው የጠቆሙት ደግሞ፤ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ናቸው፡፡ በንግግራቸውም ‹‹ለውድድሩ የሚያስፈልገው ጊዜ እና ወጪ ሃገሪቷ ባጋጠማት የህልውና ማስከበር ዘመቻ ምክንያት እንደሚፈለገው ባይሰራበትም ልኡኩ ወደ ስፍራው ሲጓዝ ሃገራዊ አንድነትን የሚያንጸባርቁ ዝግጅቶችን በማድረግ፣ ኢትዮጵያዊ የአልሸነፍ ወኔን በመላበስ ጠንካራ ተወዳዳሪ ከመሆን አልፎ የስፖርት ዲፕሎማሲ የሚፈቅደውን ህጋዊ አሰራር በመከተል ገጽታችንን ለአፍሪካዊና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማስተላለፍ ይጠበቅባችኋል›› ብለዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 19/2014