በኢትዮጵያ ልጆች በማሳደግ የህይወት ሂደት ውስጥ የሴቶች ድርሻ ትልቁን ቦታ ይይዛል። በተለይም እናቶች በሞት መለየትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከትዳር አጋራቸው ከውሃ አጣጫቸው ጋር የተለያዩ ከሆነ ኃላፊነቱ ሙሉ ለሙሉ የሚመለከተው እነሱና እነሱን ብቻ ይሆናል። ታዲያ ይህ ረጅም ግዜ የሚወስደውንና የእለት ከእለት ክትትል የሚፈልገውን ልጅን አሳድጎ ለወግ ለማዕረግ የማብቃት ጉዞ እንዲህ በቀላሉ የሚገፋ አልያም የሚታለፍ አይደለም። በርካታ ያልታሰቡ የማይገመቱ መስዋእትነቶችን መክፈል የሚጠይቅ እንጂ። በመላው አገሪቱ የዚህ አይነቱ የህይወት እጣ ፈንታ የሚገጥማቸው ሴት ኢትዮጵያውያን ቁጥር በርካታ ነው።
አብዛኛዎቹ እናቶች ደግሞ በትምህርት ያልገፉ የተለያዩ ስልጠናዎች ያልወሰዱና ገቢ ማስገኛ የሚሆን ሀብት ንብረት የሌላቸው በመሆናቸውና ባስፈለጋቸው ግዜ እየመዘዙ የሚያወጡት ብር ስለማይኖራቸው የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን አማራጭ ሆኖ የሚያገኙት ያላቸውን ልምድ በመጠቀም የጉልበት ሥራ በመስራት ነው። ለምርጫ ከሚቀርቡት የጉልበት ስራዎች መካከል ደግሞ የሸክላ ሥራ አንዱ ነው። ዛሬም ድረስ ቁጥራቸው በርካታ ባይሆንም በከተማዋ አዲስ አበባ በሸክላ ሥራ ሞያ በመሳተፍ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያኖሩ እናቶች ይገኛሉ። ለዛሬም የእንዲህም ይኖራል አምድ እንግዳችን አድርገን ያቀረብናቸው እናት ከአርባ አምስት አመት በላይ በሸክላ ሥራ ያሳለፉና አራት ልጆቻቸውንም ካለማንም እርዳታ ለማሳደግ የበቁ ናቸው።
ወይዘሮ ትርንጎ ሽፈራው ይባላሉ። ውልደታቸውና እድገታቸው በሰሜን ሸዋ እንሳሮ የሚባል አካባቢ ነው። ወይዘሮ ትርንጎ የልጅነት ግዜያቸውንም እንደማንኛውም የአካባቢው የገጠር ልጅ በእረኝነትና በጨዋታ ነበር ያሳለፉት። ወቅቱን በትክክል ለይተው ባያስታውሱትም ወደ አዲስ አበባ የመጡት ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግሥት ማብቂያ አካባቢ ነበር። አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም ትዳር በመመስረት የሶስት ጉልቻን ህይወት ሀ ብለው የጀመሩት በአሁኑ መጠሪያው ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ ዜሮ ሰባት ቀጨኔ መድኃኒአለም አስራ ሰባት ማዞሪያ የሚባለው አካባቢ ነው። ወይዘሮ ትርንጎ በቤት እመቤትነት ምንም ሳይጎድልባቸው ከባለቤታቸው ጋር መኖር ይጀምራሉ። ነገር ግን በህይወት መስመር የሰው ልጅ እጣ ፈንታ አይለይምና አራት ልጆችን ከወለዱ በኋላ ገና ልጆቹ አቅማቸው ሳይጠነክር ባለቤታቸው ህይወታቸው ያልፍና አራቱንም ልጆች የማሳደጉ ሸክም እሳቸው ላይ ይወድቃል።
እሳቸውም ሀዘኑም ሆነ ብቸኝነቱ የረበሻቸው ቢሆንም አንዳች መላ መዘየድና ቢያንስ የገቢ ምንጫቸውን መፍጠር እንደሚኖርባቸው ይወስናሉ። በዚህም መሰረት ድሮ ገና በልጅነታቸው ሲመለከቱት ያደጉትንና አያቶቻቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው ይሰሩት የነበረውን የሸክላ እቃዎችን የማምረት ሥራ በአእምሯቸው ብልጭ ይልላቸዋል። እናም ምንም እንኳን ቤተሰባቸው ጋር እያሉ ልምዱን ባያዳብሩትም በልጅነታቸው ሲያዩ ስላደጉ በአካባቢያቸው ሲሰሩ ወደነበሩ የሸክላ ሥራ ባለሙያዎች በመጠጋት ራሳቸውን አስተምረውና ባለሙያ አድርገው የሸክላ ስራውን መተዳደሪያቸው በማድረግ አዲሱን የብቸኝነት ህይወት ሀ ብለው ይጀምራሉ።
የሚኖሩበት አካባቢ በርካታ በሸክላ ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች ከመኖራቸው ባሻገር በአካባቢው ለሸክላ ሥራ የሚሆነውን ግብአት በቅርበት የሚገኝበትም ነበር። ወይዘሮ ትርንጎም ይህንኑ አጋጣሚ በመጠቀም የሸክላውን አፈር ሲበረቱ ራሳቸው ተሸክመው በማምጣት፤ ካልሆነ ደግሞ በወቅቱ ግምት ለአንድ ማዳበሪያ የሸክላ አፈር ዋጋው በየወቅቱ የሚለያይ ቢሆንም እስከ ሃምሳ ሳንቲም ድረስ ለወዛደር በመክፈል እያስመጡ የሸክላ ጀበናዎችን በማዘጋጀት ለነጋዴዎች እየሸጡ ልጆቻቸውን ማሳደጉን ይያያዙታል።
ጀበናዎቹን ለማምረት ሌላው እንደ ግብአት የሚጠቀሙበት ደግሞ ስብርባሪ ገሎችን በመፍጨት ከአፈሩ ጋር መቀላቀልን ነው። ይህኛው ሥራ ለወይዘሮ ትርንጎና እንደሳቸው በሸክላ ስራ ለተሰማሩት ገዝቶም ሆነ ሰብስቦ ለማምጣት ከሚወስደው ግዜ፤ ወጪና ጉልበት በተጨማሪ በሚፈለገው ደረጃ ድቅቅ አድርጎ መፍጨቱ በራሱ አንድ አድካሚ ሥራ ነው። የሸክላ መገልገያ ቁሳቁሶችን ማምረት ከሸክላ አፈርና ከስብርባሪ ገል በተጨማሪ የእንጨትና የኩበት ማገዶ በስፋት የሚፈልግ በመሆኑ እነዚህንም አቅም ሲፈቅድ በየጫካው በመዞር ለቅሞ ማምጣት፤ ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ በግዢ ማቅረብ ለወይዘሮ ትርንጎ አንዱ የየእለት ተግባር ነበር።
የሚኖሩበት አካባቢ በርካታ በሸክላ ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች ከመኖራቸው ባሻገር በአካባቢው ለሸክላ ሥራ የሚሆነውን ግብአት በቅርበት የሚገኝበትም ነበር። ወይዘሮ ትርንጎም ይህንኑ አጋጣሚ በመጠቀም የሸክላውን አፈር ሲበረቱ ራሳቸው ተሸክመው በማምጣት፤ ካልሆነ ደግሞ በወቅቱ ግምት ለአንድ ማዳበሪያ የሸክላ አፈር ዋጋው በየወቅቱ የሚለያይ ቢሆንም እስከ ሃምሳ ሳንቲም ድረስ ለወዛደር በመክፈል እያስመጡ የሸክላ ጀበናዎችን በማዘጋጀት ለነጋዴዎች እየሸጡ ልጆቻቸውን ማሳደጉን ይያያዙታል።
ጀበናዎቹን ለማምረት ሌላው እንደ ግብአት የሚጠቀሙበት ደግሞ ስብርባሪ ገሎችን በመፍጨት ከአፈሩ ጋር መቀላቀልን ነው። ይህኛው ሥራ ለወይዘሮ ትርንጎና እንደሳቸው በሸክላ ስራ ለተሰማሩት ገዝቶም ሆነ ሰብስቦ ለማምጣት ከሚወስደው ግዜ፤ ወጪና ጉልበት በተጨማሪ በሚፈለገው ደረጃ ድቅቅ አድርጎ መፍጨቱ በራሱ አንድ አድካሚ ሥራ ነው። የሸክላ መገልገያ ቁሳቁሶችን ማምረት ከሸክላ አፈርና ከስብርባሪ ገል በተጨማሪ የእንጨትና የኩበት ማገዶ በስፋት የሚፈልግ በመሆኑ እነዚህንም አቅም ሲፈቅድ በየጫካው በመዞር ለቅሞ ማምጣት፤ ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ በግዢ ማቅረብ ለወይዘሮ ትርንጎ አንዱ የየእለት ተግባር ነበር።
ወይዘሮ ትርንጎ በልበ ሙሉነት ተመራጭ ያደረጉትን ስራ ከጀመሩት በኋላ ውጤቱን እያገኙት ሲመጡ ደግሞ አጠናክረው ይቀጥሉበታል። ብዙ ግዜ እናቶች እንኳን አራት ልጅ ይዘው አንድም ቢሆን ሰርቶ የወር ወጪ የሚደጉም ከሌለ ለበርካታ ችግሮች የሚጋለጡ መሆናቸው አይዘነጋም። በዚህ ሂደት ደግሞ እኔ ፊት ቁጭ ብሎ ረሀብ ከሚያስቸግረው ልጄ በዘመድ አዝማድ እጅ ይኑር የሚል እሳቤም ይፈጠራል። ወይዘሮ ትርንጎ ግን ለዚህ ሁሉ ነገር በር የሚከፍቱበት አጋጣሚ አልነበረም። ነግቶ በጠባ ለራሳቸውና ለፈጣሪያቸውም ይነግሩ የነበረው ቢሳካላቸው በጀበና ስራው ካልሆነም አንዳች የጉልበት ሥራ በመስራት ልጆቻቸውን ራሳቸው ለማሳደግ ነበር።
በዚህ አይነት ቀን ከሌት በመስራት ወይዘሮ ትርንጎ ለልጆቻቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ ከማሟላት ያገዳቸው ነገር አልነበረም። በወቅቱ ልጆቻቸው ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ በመሆኑ እንደ እሳቸው አገላለጽ አራቱንም የቤተሰብ ኃላፊነት የሚወጡት ብቻቸውን ነበር። አንደኛ በጠዋት ተነስቶ አንድ አባወራ ቢኖር የወር ወጪ እንደሚያስገባ ሁላ እሳቸውም ከቀኑ ግዜ የሚበቃቸውን ያህል ለገቢ ማስገኛ በወሰኑት የሸክላ ሥራ ላይ በታታሪነት ያሳልፋሉ። በሁለተኛ ደረጃ መደበኛ የሚሉትን ስራቸውን ከጨረሱ በኋላ ደግሞ አንዳንድ ግዜም በየስራቸው መሀል እንደ አንድ የቤት እመቤት በቤት ውስጥ ምግብ ማዘጋጀቱና የልጆቹን ልብስ ማጠቡም የእሳቸው ኃላፊነት ነበር። በሶስተኛ ደረጃ ከዚህ ሁሉ ባለፈ ደግሞ ወር ቆጥሮ ለሚመጣው የሚኖሩበትን የቀበሌ ቤት ኪራይ መክፈል፤ እንደ ዛሬ ዋጋ ተተምኖ በማይመጣበት ዘመን ስንት ይቆጥር ይሆን ብሎ ከዛሬ ነገ እያሉ የመብራትና የውሃ ቆጣሪ ይመጣል ብለው ቤት ውለው እየጠበቁ ይከፍሉ ነበር። በመጨረሻውም ኃላፊነት ከእነዚህ ቋሚ ስራዎች የተረፋቸውን ግዜ ደግሞ ገበያ ለመውጣትና እንደ ለቅሶ፤ ሰርግና ማህበር እንዲሁም እድርና እቁብ ያሉ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን የሚከውኑበት ነው።
ወይዘሮ ትርንጎ ዛሬም ልጆቻቸው ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ቢሆኑም እንደድሮው የቤቱ ኃላፊ በመሆን ሁሉንም ነገር የሚከውኑት ራሳቸው ናቸው። አሁን ላይ የእሳቸው ውጣ ውረድ መድከምና መንገላታት እንደተጠበቀ ሆኖ ወይዘሮ ትርንጎን የሚያስከፋቸው ግን የኑሮ ውድነቱ ሲሆን ያለውን የኑሮ ውድነትም እንዲህ ይገልጹታል።
ድሮ በንጉሱ ዘመንም ሆነ በደርግ ግዜ የጀበናው መሸጫ ዋጋ ርካሽ ቢሆንም እኛም ለሆዳችን የምንሸምተው ጤፉ፣ ሽሮውና በርበሬው በተመሳሳይ ርካሽ ነበር። ለምሳሌ እኛ በዛ ወቅት አንድ ጀበና እንሸጥ የነበረው እንደ ጥራቱና እንደ ገበያው ውሎ አርባም ሃምሳም ሳንቲም ነበር። ከዚህ አልፎ እኔ የማስታውሰው አንድ ብር ከሃምሳ ገብቶ በጣም ተገርመን ጉድ ጉድ ስንል ነበር። ይህም ሆኖ እኛ ጀበናውን በአርባና በሃምሳ ሳንቲም የምንሸጥ ቢሆንም ለሃያ አምስት ኪሎ ጤፍ ከነማስፈጫው እንከፍል የነበረው አስራ አምስት ብር ብቻ ነበር። በተመሳሳይ በሁለት ብር ቅመሙን ሁሉን ችለን በርበሬ እናስፈጭ ነበር። ሽሮውና ዘይቱ፤ እንዲሁም ለወጥ ማጣፈጫ የሚገዛው ቅመምና ሌላው መብራት ውሃ ጨምሮ ሃምሳ ብር ሳንጨርስ ሁሉንም የወር ወጪ እንሸፍን ነበር።
ዛሬ አንድ ጀበና እስከ ሃምሳ ብር ለነጋዴ እያስረከብን እንገኛለን። በእርግጥ ጥርት ያለ ሲሆን ከሃምሳ ብር በላይ ያወጣል። ያላማረው ደግሞ እስከ ሰላሳ ወርዶ ይሸጣል። ወደ መስራቱ ሲገባ ግን የመተኮሻው እንጨትና ኩበት ዋጋ ቀን በቀን ጣራ እየነካ ይገኛል። ከሰላሳ እስከ ሃምሳ ሳንቲም እየተከፈለበት ይመጣ የነበረውም የሸክላ አፈር ዋጋም በአሁኑ ወቅት ትንሹ ክፍያ ሃያና ሰላሳ ብር ደርሷል። በዛ ላይ አሁን እርጅናውም እየመጣ ስለሆነ ነጋዴውም ሆነ ተጠቃሚው በሚፈልገው ደረጃ እንደ ልጅነቴ ልቅም አድርጌ መስራት አልችልም። ልጆቼ ስራውን የሚሞክሩ ቢሆንም እኔን ለመደገፍ ያህል እንጂ ያን ያህል አይደሉም። እነሱ መስራት የሚፈልጉት በዘመኑ ያለውንና የተሻለ ገቢ የሚያስገኘውን ብዙም የማያደክመውን ነው። ስለ እውነቱ እኔም ብሆን የምመርጥላቸው እንደዛው ያለውን ሥራ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቼ እንዲማሩት አላደረግኩም።
ይህም ሆኖ አብዛኛው ትርፍ የሚቀረው ከእነሱ ተቀብለው ለተጠቃሚ የሚሸጡት ነጋጌዎች ጋር መሆኑን ይናገራሉ። ሌላው ቀርቶ በበአላት ወቅት የሸክላ ገበያው እየደራ ዋጋው የሚጨምር ቢሆንም ነጋዴዎቹ ግን ከእነሱ የሚቀበሏቸው በተለመደው ዋጋ በዛ ላይ ካመረቱትም አይናቸው የገባውን መርጠው ነው። ትንሽ እክል አልያም ያለማማር ያለበት ምርት ከወጣ የሚወስድ ነጋዴ አይኖርም፤ ሊወስደው ቢስማማም በጣም በዝቅተኛ ዋጋ ነው። በአንድ ቀን እስከ አስር የሚደርሱ ጀበናዎችን በቅርጽ ደረጃ በማስቀመጥ መጀመር የሚቻል ቢሆንም አንድ ጀበና ሙሉ ለሙሉ ስራው ተጠናቆ ዘይት ተቀብቶ ለአገልግሎት ለመቅረብ ግን ከሳምንት እስከ ሁለት ሳምንት ግዜ ይፈልጋል። በመሆኑም ባለው አቅም እንኳን ቢመረት እንደ ሌላ ሥራ ከብዛት ማትረፍ አይቻልም ይላሉ።
«በአካባቢው ከእኔ ጋር ጀምረው እስካሁንም ሙሉ እድሜያቸውን ሸክላ እየሰሩ ያሉ አሉ፤ ወደ ፊትም የተለየ ነገር ካልተፈጠረ ምን አለን ብለን፤ ወይንስ ምን አግኝተን የሸክላ ስራን እናቆማለን» የሚሉት ወይዘሮ ትርንጎ ስራውን ማቆም ስለሌለባቸው ብቻ ዛሬም ድረስ እዚህ ግባ የማትባለውን ትርፍ እየጠበቁ ጀበኖቻቸውን በተለመደው አሰራር በማምረት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ወይዘሮ ትርንጎ እንደማንኛውም ሰው በአርባ ዓመታት የሸክላ ሥራ ጉዟቸው የተለያዩ ገጠመኞች ቢያስተናግዱም ከሰው እርዳታ ለመጠየቅ እጃቸውን ለመዘርጋት ያደረሳቸው አጋጣሚ እንዳልነበር ግን ይናገራሉ። እሳቸው ዛሬም በስድሳዎቹ አጋማሽ በሚገኘው እድሜያቸው ላይ ሆነው የተለያዩ ጀበናዎችን እያመረቱ በመሸጥ ዘመኑ ለፈጠረው የኑሮ ውድነት እጅ አልሰጥም ብለው ራሳቸውንና እቤት ያሉትን ልጆቻቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 16/2014 ዓ.ም