የተገኙት ከታዋቂ ቤተሰብ ነው። የገብሩ ቤተሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከሚታወቁት መካከል ዋነኛው ነው። አባታቸው ከንቲባ ገብሩ ደስታ በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት የጎንደር ከተማ የመጀመሪያ ከንቲባ ናቸው።
ዲፕሎማት፣ የመጀመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት፣ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ሆነው ሰርተዋል።
እህታቸው ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ በበኩላቸው ባለብዙ ሙያና ዝነኛ ነበሩ። አርበኛ፣ ደራሲ፣ የሴቶች መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛ ነበሩ ። ከዚህ ቤተሰብ ውስጥ ነው እንግዲህ የዛሬዋ ጉዳያችን እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የተገኙት።
የመታወቂያ ስማቸው የውብዳር ነው። ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ያልተቀበልናቸው በሚል ስያሜ በጻፈው መጽሀፍ ላይ እንደተገለጸው፤ የያኔዋ የውብዳር የዛሬዋ እማሆይ ጽጌ ማርያም የትውልድ ዘመን ታህሳስ 4 ቀን 1915 አ.ም ነው። አባታቸው ከንቲባ ገብሩ ደስታ ሲባሉ እናታቸው ደግሞ ካሳዬ የሌምቱ ይባላሉ። ወለጋ የተወለዱት እማሆይ እድገታቸው ግን አዲስ አበባ ነው። ነገር ግን ከዚያ በኋላ የእማሆይ ህይወት ብዙ ሀገራትን ያካለለ ሆኗል።
አንድ ቀን የእማሆይ ጽጌ ማርያም ታላቅ እህት የሆኑት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ልጅ ሆነው አልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን ፊት ቀረቡ። ወ/ሮ ስንዱ በእጃቸው በድብ ቅርጽ የተሰራ አሻንጉሊት ይዘው ነበር። በድፍረትም ይህ አሻንጉሊት የተሰራበት ሀገር ይላኩኝ ስትል ልጅ እግሯ ስንዱ አልጋወራሹን ጠየቀች። አልጋወራሹ አሻንጉሊቱን ተቀብለው ካዩ በኋላ የስዊዝ ስሪት እንደሆነ አዩ። እሺ አሏት። ደፋሯ ስንዱ ጥቄዋን አላቆመችም ፤ የምሄድበት ሀገር አማርኛ እንዳይጠፋኝ እህቴ የውብዳርም አብራኝ ትሂድ አለች። እሱም ተፈቀደ።
በጅቡቲ በኩል በመርከብ ወደ ስዊዝ ተጓዙ። እንዳለጌታ በመጽሀፉ ስለጉዞው እንዲህ ይላል። ”የውብዳር በስድስት አመቷ የመርከብ ጉዞ የፈጠረባትን ስሜት ፤ በባህሩ ላይ የተረዳችውን አዲስ ነገር ፤ ተፈጥሮ ከራሷ ጋር የምታደርገውን ጨዋታ ዘግይታም ቢሆን በሙዚቃ ገለጸችው። በልቧ ላይ የታተመው ትዝታ ፤ አድጎና ጎልምሶ ከእድሜዋ ጋር ደርጅቶ የ‹‹ባህሩ ዜማ›› The song of the sea የሚል ሙዚቃ ወጣው። ያለፈችበትን ህይወት ፤የህይወቷን ቁራጭ ገጽታ ለፒያኖዋ ነገረችው። ፒያኖዋ የነገረችውን ነገረን”።
ስንዱ እና የውብዳር በስደት ጉዟቸው መጀመሪያ የደረሱት ፍላድ የሚባል ሰው ጋር ነበር። ፍላድ ለብዙ አስርት አመታት በኢትዮጵያ የኖረ ነው። አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላ ምሽግ ካሰሯቸው ነጮች መሀከልም አንዱ ነው።
የወዳጁን የከንቲባ ገብሩን ጥያቄ ተቀብሎ ሁለቱን ኮረዳዎች ሊያሳድግ ተረከበ። የፍላድ ቤት ኑሮ ተስማማቸው። የሀገር እና የወገን ናፍቆት እየቀዘቀዘ መጣ። እንዲያውም በአንድ ወቅት አባታቸው ሊጎበኟቸው በመጡ ጊዜ የውብዳር አባቷን ፈጽማ ረስታቸው ነበር። እርግጥ አባት ስሜቱን ይረዱታል። ምክንያቱም እሳቸውም በተመሳሳይ መንገድ ከቤተሰባቸው ተለይተው በኢየሩሳሌም በስዊድን እና በጀርመን በነጮች እጅ ያደጉ ነበሩና ።
እነ ስንዱ በፍላድ ቤት ያገሩን ቋንቋ ከተማሩ በኋላ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ተላኩ። የገቡበት ትምህርት ቤት ደግሞ ተማሪዎች እረፍት ጊዜ ሲኖራቸው እንዲሞካክሩት ተብሎ ፒያኖ ተቀምጦ ነበር። እዚያ ፒያኖ ላይ ከሚጫወቱት ተማሪዎች የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ልጅ ቫዮሊን ስትጫወት አይታ የውብዳር መንፈሳዊ ቅናት ቀናች። እንደሷ ለመሆን ፈለገች። ፈልጋም አልቀረች። ተማረችው። ደግሞ ሌላ አይነስውር ሰው ቫዮሊን ሲጫወት አይታ እሱንም መሆን ፈለገች። በገና በአል ላይ የገና አባት ቫዮሊን እንዲሰጧት ፈለገች። ተሰጣትም። ቫዮሊን የሚያስተምር አንድ ሰውም ተቀጠረላት።
እህቷ ስንዱ ትምህርቷን ጨርሳ በጤና ፤ በህግ፤ በቋንቋ እና ሌሎችም ባለዲፕሎማ ሆና ወደ ሀገር ቤት ስትመለስ የውብዳርም አብራ ተመለሰች። ስንዱ ወደ ስራ ስትገባ የውብዳር ደግሞ ያልጨረሰችውን ትምህርት እንድትጨርስ ወደ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተቀላቀለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጣልያን ለዳግማዊ ወረራ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። የከንቲባ ገብሩ ቤተሰብ ወደ አርበኝነት ገባ። በተጋድሎ ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ። በግዞት ወደ ጣልያኗ አዚናራ ደሴት ተላኩ። ለአንድ አመት ታሰሩ። ከዚያ ሲመለሱ ቤተሰቡ ሀዘን በረታበት። ወንድማቸውን ጨምሮ ብዙ አርበኞች ሞተዋል።
የውብዳር ከዚያ በኋላ ሀገር ውስጥ የመቆየት ፍላጎት አልነበራትም። ወደ ውጭ ለመሄድ ፈለገች። በጥያቄዋ መሰረት ወደ ካይሮ ተላከች። በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የቫዮሊን ትምህርቷን አጠናክራ ቀጥላ በንጉስ ፉአድ ፊት ዝግጅት እስከማቅረብ ደረሰች። ነገር ግን የካይሮ አየር አልስማማ ሲላት ከሁለት አመት በኋላ ወደ ሀገሯ ተመለሰች። ከዚያም ወደ እንግሊዝ ለመሄድ ጥያቄ አቀረበች። በእንግሊዝ የንጉሳዊ ቤተሰብ ወጪዋ ተሸፍኖላት ለመሄድ ዝግጅት ላይ እያለች ግን ከበላይ አካል በመጣ ትእዛዝ ነው ተብሎ ጉዞው ቀረ።
ይህ አጋጣሚ የየውብዳርን ህይወት መስመር ሙሉ ለሙሉ ቀየረው። ከባድ የመንፈስ ስብራት ገጠማት። ለ15 ቀን ምግብ ሳትቀምስ እንዲሁ በወፍራም ቡና ስትተክዝ ቆየች። ኑሮ እንደቀድሞው አልሆን አለ። ምናኔን ማሰላሰል ያዘች። ከእናቷ ጋር ወደ ግሸን ማርያም የሄዱ ጊዜ ካልመነኮስኩ ብላ በስንት ምክር ተመለሰች። ሀሳቧን ግን አልቀየረችም ነበር። ሰንብታም ቢሆን አደረገችው። መነነች። ገና በ25 አመቷ እማሆይ ጽጌ ማርያምም ተባለች። የእማሆይ ጽጌማርያም መመነን ብዙ ድንጋጤ ፈጠረ።
ለምናኔያቸው ምክንያት ብዙ መላምት ይሰነዘራል። በ6 አመቷ ከቤተሰብ ተነጥላ ስደት ኑሮን መጀመሯ ከሚለው አንስቶ የፍቅር ጓደኛዋ ሌላ ሴት በማግባቱ ነው እስከሚል መላምት ይሰነዘራል። እማሆይ ግን ስለ እንግሊዙ ጉዞ መሰረዝም ሆነ ስለምናኔያቸው ምክንያት ብዙ መናገር አይፈልጉም። ከእናታቸው ሞት በኋላ ግን በጃንሆይ እገዛ እማሆይ ኑሯቸውን በኢየሩሳሌም ገዳማት አድርገዋል።
እማሆይ በምናኔ እያሉም ቢሆን ግን እጃቸው ከፒያኖ ብዙም አልራቀም። በክላሲካል ሙዚቃ አድናቂዎች ዘንድ በብዙ የሚደነቁ በርካታ ስራዎችን አበርክተዋል። እንደ ታዋቂው ግርማ ይፍራሸዋ ያሉ ረቂቅ ሙዚቃውን አብጠርጥረው የሚያውቁ ጠበብት የእማሆይ ስራዎች ኦሪጅናል እና አምሳ የማይገኝላቸው ናቸው ይላሉ።
ብዙዎቹ ስራዎቻቸውም ከግላዊ ህይወታቸው ጋር የተያያዘ መሆናቸውን ይናገራሉ። ሌላኛው የሙዚቃ ሀያሲ ሰርጸ ፍሬስብሀት በበኩሉ እማሆይ ሙዚቃውን እንደ መደበቂያ ይጠቀሙበት ነበር ይላል። በሙዚቃቸው ውስጥ ጥልቅ ስሜቶች እንደሚንጸባረቁ ይገልጻል።
ሰርጸ በአንድ ወቅት አርአያ ሰብ ለተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንደተናገረው፤ የመጀመሪያው አልበማቸውንም በዘመነ ጃንሆይ ንብረትነቱ የቤትሆቨን በሆነ ፒያኖ ጀርመን ሀገር የተቀረጸ ሲሆን፣ገቢውንም ለበጎ አድርጎት ስራ አውለውታል። ከዚያ በኋላም የተደነቁ ቅንብሮችን የሰሩ ሲሆን በምንኩስና ህይወታቸው ጸንተው እስካሁንም ኢየሩሳሌም ይኖራሉ። በነገው እለትም 99ኛ አመት የልደት በአላቸውን ያከብራሉ።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2014