ልጅነት አታላይ ነው። በትምህርት የታገዘ ግንዛቤ ካልታከለበት የወደፊቱን ያበላሻል። በጓደኛ ግፊት ብቻ አይወድቁ አወዳደቅ ላይ ይጥላል። የወደፊቱን ዕጣ ፈንታ ብልሽትሽቱን ያወጣዋልም። የተበላሸውን ለማስተካከል ደግሞ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል።
በተለይ ብዙ ወጣት ሴቶች እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ የሚገቡት ከዚህ የተነሳ ነው። በዚህም ዕድሜያቸውን ሁሉ በልጅነታቸው ያበላሹትን በማስተካከል ላይ ያሳልፉታል። ለዛሬ ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችውን ወይዘሮ የሕይወት ተሞክሮ ልናስነብባችሁ ወድደናል። ወይዘሮዋ እናት ካሳሁን ትባላለች።
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን አዴት ከተማ ተወልዳ አድጋለች። ብቸኛውን አንድ ወንድ ልጅ ጨምሮ ሰባት ልጆች ላላቸው ወላጆቿ ሦስተኛ ልጅ ነች። ሆኖም ከእሷ በላይ ያሉት ሁለቱ ወንድምና እህቷም ሆኑ እሷ እርሻውና የቤት ውስጥ ሥራው አላደርሳችሁ ስላላቸው አልተማሩም። በዚህም አብዛኛውን የልጅነት ዘመኗን የፈጀችው በሥራ ነው። ‹‹የምጫወተው እዚያው ከብት ከማግድበት ሥፍራ ነበር›› የምትለው ባለታሪካችን፤ ጉልጓሎው፣ አረሙ፣ ውሃ መቅዳቱ፣ እንጨት ሰበራው፣ እንጀራ ከመጋገር ጀምሮ ያለው የቤት ውስጥ ሥራ አድካሚ እንደነበር ታነሳለች። ወላጆቿ ጥሩ ባለሙያ እንድትሆንላቸው በሥራ ኮትኩተው እንዳሳደጓትም ትናገራለች። በ15 ዓመቷ የዳሯትም ይሄን ሙያዋን ታሳቢ አድርገው ነበር። በተለይ እንጀራ የመጋገር ሙያዋ የገቢ ምንጭ ማግኛ ሆኖላታል። በትዳሯ ከአምስት ወር በላይ ባትቀመጥም ራሳቸውን ችለው ጎጆ እስኪወጡ የተቀመጡባቸው የባለቤቷ ወላጆች የሴት ቁንጮ መሆኗን መስክረውላታል። አለመማሯ ከአብሮ አደግ ጓደኛዋ ግፊት ጋር ተደማምሮ በለጋ ዕድሜዋ በወሲብ ንግድ እንድትሰማራ ያደረጋት እንግዳችን፤ ዛሬ ከዚህ ሁኔታ ወጥታ መሿለኪያ አካባቢ በሚገኘውና በተለምዶ ካታንጋ በሚባለው ብርሃነ ሠላም ሰፈር አልጋ ማከራየትን ጨምሮ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች። ድንች ቅቅል በሚጥሚጣ፣ ዳቦ በጎመን ቅቅል ትሸጣለች። የሀበሻ ጎመኑን በጥሬው ገበያ አውጥታ የምትሸጥበትም ጊዜ አለ። የምትገዛው እዚያው ሰፈር ውስጥ ካሉ ቸርቻሪዎች በመሆኑ ብዙም ትርፍ የላትም። ርቃ እንዳትሄድና ረከስ ካለበት ቦታ አምጥታ እንዳታተርፍ ደግሞ ሕፃን ልጆቿን የሚይዝላት አታገኝም።
በመሆኑም ይህንኑ ሥራ ተግባሬ ብላ ቀጥላለች። በእርግጥ እንደቀደመው ጊዜ አትጠጣም፤ አትቅምም። ስለዚህ ለጫትና ለሲጋራ ብላ የምታወጣው የለም። ይሁን እንጂ አልሸሹም ዞር የሆነባት ነገር አለ። እንጀራ ስለማትጋግር አንዱን 10 ብር፤ አንዱን ዳቦ 3ከ 50 መግዛት ይቸግራታል።
ጨው እንኳን ቸግሯት የሚያውቅበት ቀን አለ። በየሰው ቤት እየዞረች አንሶላና ልብስ ታጥባለች። ድንጋይ ትሸከማለችም። በቃ የሚቀራት የጉልበት ሥራ የለም። ሁለት ልጆቿን ጨምሮ ከራሷ ጋር ሦስት ቤተሰብ የምታስተዳድረው በዚሁ ሥረዋ ነው። ሥራውን የምትሠራው ከዋናው አልጋ ማከራያትና የፅዳት ሥራ በኋላ ነው። ከምታከራየው ስምንት ተደራራቢ አልጋ ውስጥ አንዱን ማለትም ከሥር ያለውን ሁለት ሕፃናት ሴት ልጆቿን ይዛ ታድርበታለች። ዋጋው በቀን 30 ብር ሲሆን፤ የእሷም ደሞዝ ከዚህ ብር ነፃ ሆና ከነልጆቿ በአልጋው ላይ ማደሯ ብቻ ነው። ይህ ሲሆንም በሰካራም ሽንት የራሰውን አንሶላና ብርድ ልብስ ጨምሮ ቤቱን ማፅዳቱ አይቆጠርላትም። ሌላው ቀርቶ በሠፈሩ በአብዛኛው ውሃ ስለሚጠፋ ለ20 ሊትር ጀሪካና ውሃ ከነተሸካሚው 30 ብር አይወራረድላትም።
በሁለት ወር አንዴ መንግሥት ላሠራው መፀዳጃ ቤት ማስመጠጫ የሚወጣውንም 40 ብር የቤቱ ባለቤት ሳትሆን እሷው ነች የምትሸፍነው። ከበላይዋ ያለውን ሰባት አልጋ ተከራይተው የሚያድሩት የተለያዩ ዓይነት ወንዶችም ቢሆኑ በአንድ ክፍል ውስጥ በዚህ ሁኔታ ማደሯም ያስጨንቃል። ነገር ግን ስለተላመደችው
አትፈራም። ‹‹ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል›› እንዲሉ እንኳን እሷ ሕፃን ልጆቿም የሚፈሩ አይመስሉም። አሁን ላይ ያኔ ወደ ሥራው ስትገባ ብዙ ወንዶችን ስቦ በዙርያዋ ያሽከረክር የነበረው ፀሐይ የመሰለው የልጅነት ወዘናዋ ጠውልጎ የወጣትነት ፊቷ ገርጥቷል። አማላይ የነበረው ድንቡሽቡሽ ገላዋም ሟሿል። ሌት ከቀን ያገኘችውን ለመሥራትና ኑሮዋን ለማሸነፍ ስትባዝን በውርጭና ብርድ የተገረፈውና በቀትር ፀሐይና እሳት የተለበለበው ፊቷ ማዲያት አበላሽቶታል። ነገር ግን ቅላቱ አልተደበቀም፤ ውብ እንደነበረችም አልሸሸገውም። አስከፊው የሴት አዳሪነት ሕይወት ካረገባት የኑሮ ማጥ ውስጥ ዛሬም መውጣት አልቻለችም። ምክንያቱም በወር ውስጥ ትቀየሪያለሽ የተባለችው አልሆነም።
ወትዋቿ ዕድለኛ ሆና ስትለወጥ እሷ ግን የሕይወት ኮንፓሷ ግራ ይሁን ቀኝ ጠፍቶባት ታች እላይ በማለት እየባዘነች ነው። እንደ አብሮ አደጓ አልፎላት በተሻለ ሁኔታ መኖር ብትመኝም አሁን ያለችበት የኑሮ ሁኔታ ሊያራምዳት የሚችል መስሎ አይታያትም። በእጅጉ ተስፋ ቆርጣለች። ነገር ግን ከሁለት ሕፃናት ልጆቿ ጋር ዛሬን ለማደር መፍጨርጨሯን አላቋረጠችም። እንዳወጋችን ባሏ ያለፍላጎቷ ታግባውና በቤተሰብ ይምጣላት እንጂ በዕድሜ አቻዋ አይደለም። ስለዚህም ጥላው አዲስ አበባ ከተማን በወሬ ሰምታ ከነገረቻት አንዲት ጓድኛዋ ጋር በመሆን በሌሊት ጠፍተው ገቡ። ስትመጣ ከአባቷ ለትራንስፖርት 150 ብር ሰርቃ ነበርና መርካቶ አውቶቡስ ተራ አልጋ ቤት አደሩ። በእርግጥ ጓደኛዋም ከወላጆቿ ማሳ ላይ ተረፈ ምርት እየሰበሰበች በመሸጥና በማጠራቀም ብዙ ገንዘብ ይዛ ነበር። በዚህም ለአልጋም ሆነ ለምግብ አልተቸገሩም። ጠዋት እዚያው አውቶቡስ ተራ አጠያይቀው ያገኙት ደላላ ሥራ አስቀጠራቸው። ሁለቱም የተቀጠሩት ሰው ቤት ሲሆን፤ ተቃቅፈው ተላቅሰው ነው የተለያዩት። የሚገርመው እስከ ዛሬ በዓይነ ሥጋ ተገናኝተው አያውቁም። በስልክም እንዲሁ።
ያም ሆነ ይህ እሷ እዚያው አውቶቡስ ተራ የሚገኝ ትራንዚት የሚባል ሆቴል እንጀራ ጋገራ ሥራ ጀምራለች። በቀን 70፤ ገበያ ያለ ዕለት ደግሞ 100 እንጀራ ትጋግራለችም። በዚህ መልኩ በሆቴሉ በወር 60 ብር እየተከፈላት ሁለት ዓመት አሳለፈች። ወደ ትውልድ ቦታዋ ዘልቃም ቤተሰቦቿን ጠይቃ ተመልሳለች። እንደገና ተመልሳ ስትመጣ ደግሞ ላም በረት አካባቢ ያለች አንዲት ባለ ሆቴል ቤት ውስጥ እንዲሁ በእንጀራ መጋገር ተቀጠረች። እዚህም ደሞዙ መቶ ብር ነበር። ሰዎቹም እጅግ መልካም ናቸው።
እሷ እንጀራ የምትጋግረው ባለሆቴሏ ሴትዮ መኖርያ ቤት ውስጥ ሲሆን፤ ጉልበቷን ሳትቆጥብ ሴትዬዋን በሌላ ሥራ ብታግዛትም እንደልቧ ታርፋለች። እንደ አሁኑ ትኋንና ቁንጫ ሰውነቷን በሚበዘብዝበት ሳይሆን ንፁሕ መኝታ ላይ ትተኛለችም። ትበላና ትጠጣለችም። በእጅጉ ደስተኛ ነበረች። ሁለቱ ቤቶች አራት ዓመት እንጀራ ጋገራ ስትሠራ የተቀጠረችው ጠቅላላውን በመሆኑ የቤት ኪራይም ሆነ የምግብ ወጪ አልነበረባትም። በዚህም ጥሩ ጥሪት ቋጥራለች። ‹‹ቤተሰቦቼ ያላቸው ቢሆኑም አዲስ አበባ ከተማ የሚኖር ሀብታም ይመስላቸዋል። እነሱ ከኔ ባይፈልጉም ይሉኝታ ይይዘኛል›› የምትለው ወይዘሮ እናት፤ ሁለት ዓመት እንጀራ ጋግራ የቋጠረችውን ይዛ ወደ ቤተሰቦቿ ትሄዳለች። ‹‹በዚህ ወቅት ነው ሕይወቴ ትርጉም እንዲያጣ ላደረገውና አሁን ለምኖርበት አስከፊ ሁኔታ ለመዘፈቅ የበቃሁት›› ትላለች ገጠመኟን ስታስታውስ። አንዷ የሰፈሯ ልጅ አዲስ አበባ ያለችው እህቴ ጋር ይዘሽኝ ካልሄድሽ ሞቼ እገኛለሁ አለቻት። እህቷ የምትሠራው ለካ እዚህ አሁን እሷ በምትኖርበትና የተረገመ በምትለው ቦታ ነበር። ‹‹እህትሽ ምትሠራበትን አላውቀውም። አዲስ አበባ ሰፊ ነው። ሰው ተፈልጎ አይገኝም›› ብትላትም አልሰማቻትም። ስልኳን ይዣለሁ ይዘሽኝ ካልሄድሽ ብላ ወጥራ ያዘቻትም። ስለዚህም ምርጫ ስላልነበራት ይዛት ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች። እንደደረሱ ሲደውሉላት በፍጥነት መጣችና ተቀበለቻቸው። እሷ እህቷን አስረክባት ወደ ምትሠራበት ቤት ላምበረት ልትሄድ ስትል እኔ ጋር ማደር አለብሽ ብላ አላስኬድ አለቻት። አይሆንም ብትላትም ‹‹አብረን አድገን አንድ ምንጭ ውሃ ጠጥተን›› እያለች ተማፀነቻት። የምትኖርበት ቦታም ይዛቸው ሄደች። ‹‹ለኔ ባትመጣ ይሻለኝ ነበር።
ያቺን ልጅም ባላመጣት ኖሮ ደግ ነበር›› የምትለው ወይዘሮ እናት፤ አንድ አልጋ ብቻ በምታዘረጋው ቤቷ ውስጥ የነበረውን የራሷን አልጋ ለቃ አስተኛቻት። ክብካቤዋ ምስጡሩ ምን እንደሆነ በወቅቱ ባይገለጽላትም አንድ ነገር ከእርሷ የሚፈለግ ዓይነት ነበር። እህቷን ይዤ በመምጣቴ ነው እንዳትል ለእህቷ መምጣት ይሄን ያህል ቁብ አልሰጠችውም። ጠዋት ልትሄድ ስትነሳ ይሄን ይዛ ቁጭ አድርጋ የት እንደምትሠራና ምን እንደምትሠራ ጠየቀቻት።
ላምበረት አካባቢ እንጀራ ጋገራ እንደሆነ ሳትደብቅ ነገረቻት። እሷ ሥራ እንደምታስገባትና ሥራው ሳትደክምና እንደ እንጀራ ጋገራው በእሳት ሳትለበለብ በአንድ ወር ውስጥ የምትቀየርበት እንደሆነ አስረዳቻት። ራሷን ምትጠብቅና የምትንከባከብበት ቆንጆ ሥራ መሆኑንም ገለጸችላት። ሆኖም ምንድነው እያለች ብትወተውታትም ሥራውን አልነገረቻትም። በዚህ ልቧ የተንጠለጠለውና በውስጧም ምን በወጣኝ እንዲህ ዓይነት ሥራ እያለ በ100 ብር እንጀራ በመጋገር በእሳት የምለበለበው ያለችው ወይዘሮዋ የአሠሪዎቿን ስልክ ለአብሮ አደጓ በመስጠትና አብሮ አደጓ የሰጠቻትን ስልክ በመቀበል የምትሠራበትን ቤት አድራሻ ከነገረቻት በኋላ ወደ ምትሠራበት ቤት ትሄዳለች። አሠሪዎቿ ጋር ከመድረሷ አብሮ አደጓ ስልክ ደውላ ጥሩ ሥራ ስላገኘችላት እንድትመጣ ትነግራታለች። ልቧ በዚህ ሥራ የሸፈተው እናትም ሁለትና ሦስት ቀን እንኳን ተረጋግታ መቀመጥ አልቻለችም። ተነስታ ወደ አብሮ አደጓ ጋር ሄደች። ሆኖም የጓጓችለት ሥራ ሴት አዳሪነት ሆኖ አገኘችው። የገዛ አብሮ አደጓ እንዲህ ላለው ሥራ ስላጨቻት ተበሳጫች። በተለይ ገጠር ባሉት ዘመዶቿ ዘንድ ፍፁም ተቀባይነት የሌለውና የተወገዘ መሆኑ በድርጊቷ ተናደደች።
አሻፈረኝ ብላ የሰው ቤት ሥራ እንዲያስገባት ደላላ ጋር ልትሄድ ብትልም አብሮ አደግ ሆዬ ግዴለሽም በአጭር ጊዜ የምትቀየሪበት ሥራ ይሄ ነው ብላ እግሯ ላይ በመውደቅ ትለምናትና ታባብላት ጀመር። ከአሠሪዎቿ ጋር ሥራውን መልቀቋን ነግራ ተሰናብታቸው በመምጣቷና አማራጭ በማጣቷ ለጊዜው ልሞክረው ብላ ገባችበት። ያሰበችው ቀርቶ ያላሰበችው ምድራዊ ገሐነም ሆነባትም። ቀይ ፊቷ ፍላጎታቸው ሴት አዳሪ መሆኗን እንኳን አላስረሳውም። እንዲያውም እኛ እያለን እንዴት ከሌላ ወንድ ጋር እናይሻለን በሚሉ ወንድ ደንበኞቿ ቦክስና ጥፊ በለዘ። በማታውቀው ምክንያት እንዳትሞት እንዳትሽር በየቀኑ ትደበደባለችም።
‹‹አብሬው ተኝቼ ጥርሴ በከንፈሬ እስኪ ወጣ በቡጢ የመታኝና በኮንቦርሳቶ በተከፈለው ሌላ ቤት ውስጥ በሚነድ የከሰል ማንደጃ ፍም ላይ የወረወረኝም አጋጥሞኛል›› ትላለች አስከፊነቱን ስታወሳ። እንዳስተዋልናት የወጣትነት ውበቷ ያለጊዜው ረግፏል። ፊቷ በማዲያት ተጠባብሷል። በረዶ ይምስላል እየተባለች የምትደነቅበትና የምትሞካሽበት ጥርሷ በጫት ተበላሽቷል። ከ35 ዓመቱ የዕድሜ ዘመኗ 10ሩን በዚህ ሁኔታ ነው የኖረችው። አራት ዓመቱን በሰው ቤት እንጀራ ጋገራ ሠራተኝነት አሳልፈዋለች። ዘንድሮን ጨምሮ ቀሪውን ስድስቱን ዓመት ደግሞ ከአስከፊው ሴት አዳሪነት ሕይወት ወጥታ አልጋ ማከራየትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ታከናውናለች።
በዚህ ወቅት በፊት ትሠራው የነበረውን የሰው ቤት እንጀራ ጋገራ ሥራ አጥብቃ ተመኝታዋለች። ሆኖም ከነልጇ የሚቀጥራት አጥታለች። ከሴት አዳሪነት ሕይወት መውጣቷን የሰሙም አምነው ሊቀጥሯት አልቻሉም። ባሏን መፍታቷም ቆጭቷታል።
ከገጠር የሚመጣውን ሁሉ ስለሱ ሳታሰልስ ትጠይቃለች። በቅርቡ በመኪና አደጋ ቢሞትም ነፍሱን ይማረውና ትዳር መመስረቱንና ሁለት ልጆች መውለዱን እንዲሁም ቢጠሩት የማይሰማ የናጠጠ ሀብታም መሆኑን ሰምታለች። ሀብቱ እንዲህ ዓይነቱን የስቃይ ኑሮ ሳታይ ሀብቷ ሆኖ የተደላደለ ኑሮ ሊያኖራት የሚችል እንደነበር በማሰብ በገደቢስ ዕድሏ ታዝናለች። ዕለት በዕለት የወሲብ ንግድ የሚከናወንበት ሰፈር ደስ አይላትና አይመቻትም። በተለይ ለሕፃን ልጆቿ ይሄን እያዩ ማደጋቸው ጥሩ እንዳልሆነ ታስባለች። ስለ ሁኔታውም ዘወትር ትጨነቃለች።
በዚህም ለብረሃነ ሠላም ቀበሌ 20/21 ቤት እንዲሰጣት አመልክታለች። የደሀ ደሀ ብሎ ከመዘገባት ቢቆይም የፈየደላት የለም። በተለይ ኮቪድ ገናና በነበረበትና በመጣበት ወቅት ብዙዎች ቢደገፉም እሷ ግን ማንም አልደረሰላትም። ሥራ አቁማና ቁራሽ ዳቦ የሚሰጣት አጥታ ከነ ልጆቿ ለበርካታ ቀናት ድፍት ብላ አሳልፋለች። ሆኖም እናት ከእዚያ ቤት እና ሠፈር፤ ደግሞም ብርቱ የድህነት ቀንበር ከተጫነው ሕይወቷ ለመውጣት መፍጨርጨሯን አላቋረጠችም። ግን የሌሎች ድጋፍ ያስፈልጋታል። ሁለት ሕፃናትን ከመመገብ አልፎ ማስተማር በሰማይ የሚያፀድቅ ብቻ ሳይሆን በምድርም የህሊና እርካታ ይሰጣልና ደግፏት። በተለይ የሠፈረ ሰላም 21/20 ቀበሌ አንዲት መጠለያ ቤት በመስጠት ልጆቿን አስተማሪ ካልሆነው የሴት አዳሪነት ስፍራ ታደጉላት መልዕክታችን ነው።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014