
ግለሰቡ ከቤቱ ተነስቶ ሩቅ አገር ሄዶ ለቅሶ ለመድረስ ጉዞ ጀምሯል:: የሁለት ቀናት ጉዞ በመኪና የአንድ ቀን ጉዞ ደግሞ በእግሩ አድርጎ በሦስተኛው ቀን ለቅሶ ቤቱ ደረሰ:: አድካሚ ጉዞ:: የተፈጥሮ አቅምን የሚፈትን ጉዞ:: ቀን በቀን ለለመዱት የቀለለ ለከተሜው ግን የከበደ ጉዞ ነበር:: የለቅሶ ቤቱ አዳር ደግሞ እጅግ ያልጠበቀው ሆኖ ተቸገረ:: እንቅልፍ በአይኑ ውልብ ሳይል ያለፈ ሌሊት ከቁንጫ ጋር ግብግብ የተገጠመበት ሌሊት:: የራሱን ቤት እያሰበ በናፍቆት ውስጥ ገባ:: “ለካንስ በአንድ አዳር የራስ ቤት ይናፍቃል” አለ:: በእንቅልፍ ሰረገላ በሰላም ተሳፍሮ የሚያልፍበት የራሱ ቤት ትዝ አለው:: በምናቡ ጉዞ አድርጎ ቤቱ ገብቶ የሚያርፈው እንቅልፍ ውልብ እያለበት በብዙ ተስፋ ከሩቅ ያለችውን ቤት ናፈቀ:: እንቅልፍ ያስናፈቀው ቤት:: ይህ ሰው ለቅሶውን ጨርሶ ወደ ቤቱ ጉዞ ጀመረ፤ በጉዞ ሁሉ አእምሮውን የተቆጣጠረው እንቅልፍ ነበር:: በእንቅልፍ ውስጥ ታልፎ የሚገኘውን እረፍት እያሰበ ፈጣሪን እያመሰገነ::
እረፍቱ የሚሰጠው ጥንካሬን በቃል መግለጽ ተቸገረ:: እንቅልፍን አክብሮ ማሰብና፤ አክብሮ መያዝ:: በብዙ የናፈቀው ሆነ፤ አይደርሱም የለምና ቤቱም ደረሰ:: ቤቱ ገብቶ ሌሎች ፕሮግራሞቹን ሰርዞ በእንቅልፍ ለሚያሳልፈው ጊዜ የሚመገበውን አዘጋጅቶ እንቅልፍን ጀመረ:: ከቁንጫ ጋር በሚደረግ ትግል አንድ ቀን ያጣውን እንቅልፍ ለማጣጣም ሁለት ቀናት እንደሚያስፈልጉት አሰበና በተከታታይ ሁለት ቀናት ከራሱ ጋር ሆነ:: እንቅልፍ ከተፈጥሮ ስጦታዎች መካከል የተሰጠ ለራስ ከራስ በሆነ ቅኝት ውስጥ ስንሆን ብቻ በአግባቡ የምንጠቀመው:: አምስት ሚሊዮን ያህል ሰዎች የተሳተፉባቸው 153 ጥናቶች በቂ እንቅልፍ የማያገኙ ሰዎች ለስኳር በሽታ፣ ደም ግፊት፣ ከልብ ጋር ለተያያዙ በሽታዎች እንዲሁም ከልክ ላለፈ ውፍረት ተጋላጭነታቸው የሰፋ እንደሆነ ያስረዳሉ::
በቂ እንቅልፍ ማግኘት ከበሽታ ከመከላከልም ባሻገር የማስታወስ አቅምን እንደሚጨምር ጥናቶች ያስረዳሉ፤ የተፈጥሮ ስጦታ፤ ነገር ግን ለራስ ከራስ የሆነ እሳቤን የሚፈልግ:: ግለሰቡ ተፈጥሮ ስለሰጠችን ችሮታዎች እያሰበ ከእንቅልፍ ያጣውን በእንቅልፍ መለሰው:: ተፈጥሮ አስገድዳ እንቅልፍን ሰጠችን:: ወደን ሳይሆን ተገደን እጅ የምንሰጥበት ጉዳይ ነው፤ እንቅልፍ:: እንቅልፍ ለራስ ጊዜ የመስጠት ማሳያ ነው::
በተፈጥሮ አስገዳጅነት የሚሆን ለራስ ጊዜ መስጠት:: እውቁ አልበርት አንስታይን “ወደ ተፈጥሮ በጥልቀት ተመልከት ሌላውን ነገር በሚገባ መረዳት የምትችልበትን አቅም ታገኛለህ” ይላል:: ተፈጥሮን በጥልቀት አይተን ትምህርት ከምንወስድበት ነገሮች መካከል አንዱ እንቅልፍ ነው:: ይህ ጽሑፍ ለራስ በራስ ስለሚሰጥ ጊዜ ነው:: እንቅልፍ በተፈጥሮ አስገዳጅነት ለራሳችን ጊዜን ለመስጠት የምናደርገው ነው:: ተፈጥሮ አስገድዳ የምታደርገው ነገሮች እንዳሉ ሆነው ለራሳችንም የተተውም ነገር መኖሩን ስንረዳ ከእኛ የሚጠበቀውን ለመወጣት::
እንቅልፍ የተፈጥሮ አስገዳጅነት የሚታይበት ነው:: ተፈጥሮ አስገድዳ ከምታስደርገን ነገሮች ወጥተን ራሳችን አስበን ለራሳችን ልናደርግ ስለሚገባው ነገር ማሰብ ስላለብን ቁልፍ ነጥቦችን እናነሳለን:: በዚህ የመነሻ ታሪካችን ሁለት ተፈጥሮ አስገድዳን የምናደርጋቸውን መደበኛ የህይወታችን አካላት እንመልከታለን፤ እነርሱም እንቅልፍና ሞት:: እንቅልፍ በየቀኑ የሚሆን ሞት ደግሞ በህይወት ዘመን አንዴ:: የምናብ ባለታሪኩ ግለሰብ ለቅሶ ሊደርስ ጉዞ ያደረገ ነው:: ሞት ምድርን ላንመለስ የምንሰናበትበት ሲሆን ከእዚያ መለስ ግን ለዋናው ሞት የሚያበቁ መጠነኛ ሞቶች ሊገጥሙን ይችላሉ:: በመጠጥ ሆነ ባልተገባ መንገድ ጤናውን እየጎዳ ያለ ሰው ለዋናው ሞት ቀድሞ እየሞተ እንዳለ እንረዳለን::
እንቅልፍ ማጣትም አንዱ ሊሆን ይችላል:: ዋናው ፍሬ ነገራችን ሞትም ሆነ እንቅልፍ ሁለቱ የተፈጥሮ መገለጫዎች ናቸው፤ በተለይም አስገድደው የወደዱትን የሚያደርጉ:: የሰው ልጅ ለራስ ከራስ መርሆችን ነድፎ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ግድ የሚሉት:: በእንቅልፍ ደረጃዎች ውስጥ አንዱ ከሞት ጋር ተመሳሳይ የሆነ እንቅልፍ ደረጃ ነው:: እንቅልፍ ከ60 እስከ 100 ደቂቃዎች ርዝማኔ ያላቸው ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው ደረጃ በመተኛት እና አለመተኛት መካከል የሚገኝ ሰውነታችን ቀስ በቀስ ለቀቅ እያለ የሚመጣበት ደረጃ ሲሆን ሁለተኛው ክፍል ደግሞ በዝግመት ሙሉ በሙሉ ወደ እንቅልፍ የምንገባበት ነው። ሶስተኛው ደረጃ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የምንተኛበት ክፍል ሰውነታችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከሌሎች እንቅስቃሴዎች ውጭ የሚሆንበትና መነሳት የሚባል ነገር የማይታሰብበት ደረጃ ነው። ሰዎች በየዕለት ዕለት የእንቅልፍ ጊዜያቸው በእነዚህ ደረጃዎች ሥር የሚያልፉ ሲሆን የደረጃዎቹ መዛባት ለጤና መታወክ ሚና እንዳለውም ይነገራል። ሁለቱም የተፈጥሮ ኃይላቸውን ተጠቅመው ለሰውነታችን የሚሰጡትን ትርጉም መነሻ በማድረግ በእረፍት እንገልጻቸዋለን::
እንቅልፍ ተኝቶ የተነሳን ሰው እረፍት አድርጎ የተነሳ አድርገን እንቆጥራለን፤ ደግሞም ትክክል ነን:: የሞተን ሰው በባህላችን ሞተ ሳይሆን ‘እከሌ አረፈ’ እንላለን:: በተፈጥሮ አስገዳጅነት የሚሆን እረፍት በእንቅልፍና ሞት ውስጥ:: ዛሬ በምንመለከተው ጽሑፍ ውስጥ ራሳችን ለራሳችን ልንፈጥር ስለሚገባው እረፍት እንመለከታለን:: ለራስ ከራስ ሊሆን የተገባቸው በቀላሉ ልናደርጋቸው የሚገቡን ነገሮች ቦታ ባለመስጠት ለራሳችን ያጎደልነውን እንመለከታለን:: መመልከታችን ወደ መፍትሄ እንዲያደርሰን ውሳኔው የግላችን መሆኑን መረዳትም ይገባናል:: ለራስህ ከአንተ የሚቀርብ የለም:: ለአንቺ ከአንቺ የሚቀርብ የለም:: ለራስ ከራስ ብለን ወደ ተፈጥሮ ተመልክተን ልናስተካክላቸው የሚገቡ ነገሮችን ስለማስተካከል::
ባሉበት እየረገጡ ከመቆየት መውጣትን የሚጠይቅ:: ባሉበት መቆየት ‘በራሴ ላይ ለውጥ ማድረግ እፈልጋለሁ ራሴን መቀየር ይገባኛል’ ብሎ የሚያስብ ሰው ለውጥን የማድረግ እድሉ ሰፊ ነው:: በተቃራው እንደ እምነት ባይያዝም በተግባር ግን የመለወጥን ጉዞ የማያደርግ ሰው ባለበት ለመቆየት የወሰነ ነው:: ባለበት የሚረግጥ፤ ባለበት የሚቆይ:: ለራስ ከራስ ማበርከት የሚገባን አንዱ ነጥብ በየጊዜው እየተለወጥን የመሄዳች ጉዳይ ነው:: በነገሮች ሁሉ እያደጉ መሄድ የህይወት መርህ ማድረግ ትርፉ ወደር የለውም:: በባህሪም ሆነ በክህሎት ማደግን ግብ ማድረግ የጤናማነት ማሳያ ነው:: ህይወት ያለው ነገር በእድገት መስመር ላይ ስለሆነ በየጊዜው እያደገ መሄዱ የግድ ነውና::
ባለንበት ዘመን በስፋት ሥራ ላይ እየዋሉ ያሉ መተግበሪያዎች /applications/ በአይነታቸው ተለይተው ይቀርባሉ:: ስራን የማቀላጠፍ እገዛን የሚያደርጉ ራሳቸውን ችለው በአንድ በኩል ይቀርባሉ:: መተግበሪያዎቹን ወቅታዊ በማድረግ በየወቅቱ የተሻሻሉ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል:: የመተግበሪያው ሰሪዎች አሻሽለው የሰሩትን ለማግኘት አፕዴት (update) እንላለን:: በቀጣይም እንዲሁ አዳዲስ ነገሮች ሲኖር አፕዴት ይደረጋል::
ኮምፒውተራችንም የሚገጥሙት የኮምፒውተር አዋኪ ቫይረሶች ሆነ እክሎችን ለመጋፈጥ እንዲችል በአምራቹ አማካኝነት በየጊዜው የሚላኩ ማስተካከያዎች አሉ:: አንዳንዴ ማስተካከያዎችን በተደጋጋሚ ውትወታ ስንጭነው አንዳንዴ ተገደን ልናደርገው እንችላለን:: ይህ ስለምንጠቀምባቸው ቁሳቁሶች ነው፤ ስለ እኛስ? የሰው ልጅ ከግዑዝም ሆነ ከሌሎች ፍጥረቶች በሙሉ ልዩ የሆነ ነው::
ተጽእኖ ፈጣሪነቱን አቅዶ በመተግበር አቅሙ ውስጥ ይገኛል:: የሰው ልጅ እንደ ሰው ልጁነቱ በአግባቡ መንቀሳቀስ የሚችል ይሆን ዘንድ ሊረዳው የሚገባውን አቅም መጨመር አስፈላጊነቱ ግልጽ ነው:: በመጠጥ ሆነ በሌሎች መንገዶች አቅምን ከመግደል አቅምን ማሳደግ ትኩረትን ይሻል:: ዛሬ ራሴን በምን አፕዴት ላድርግ፣ የምራመደው የተግባር እርምጃስ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ይገባል:: ጂም ሮህን የተባሉ ግለሰባዊ አቅምን በማበልጸግ ዙሪያ ንግግር በማድረግ የሚታወቁ ሰው “ከስራህ ይልቅ በራስህ ላይ እንዴት በርትተህ መስራት እንደምትችል ተማር፤ ያኔ ስራህም ይለወጣል::” ይላሉ::
ለራስ ከራስ ለራስ ከራስ ማለት እያንዳንዱ ሰው ግለሰባዊ አቅሙን ለማሳደግ ቀዳሚውን ኃላፊነት በመውሰድ ራሱ ላይ የሚሰራው ሥራ ማለት ነው:: ሪቻርድ ፓስኬል / Richard Pascale/ የተባሉ ሰው መሪነትን ሲተረጉሙ “መሪነት ማለት በሌላ በምንም መንገድ ሊሆን ያልቻለን ነገር እንዲሆን ማስቻል ነው” ይላሉ:: ከእርሳቸው ትርጉም ውስጥ ‘በምንም መንገድ ሊሆን ያልቻለን ነገር ወደ እያንዳንዱ ግለሰብ እናምጣው’::
ሌሎች ሰዎች በብዙ መንገድ ሞክረው አልሆን ያለ ነገር እንዲሆን ያደረገን ሰው መሪ የምንለው በውስጡ ባለው የማድረግ አቅም ነው:: እያንዳንዱ ግለሰብም ለሌላ ሰው የከበደን ነገር በራሱ አቅም በተወሰነ ደረጃ ሊያከናውነው ይችላል፤ ልዩነት የግለሰባዊ አቅም ልዩነት ነው:: አንዱ ከሌላው ሰው ጋር ያለው አንጻራዊ ለውጥ:: ጥያቄው አንጻራዊው ለውጡ ምክንያት ምንድን ነው? የሚል ነው:: በእድሜ፣ በጾታ እንዲሁም በክብደት እኩል የሆኑ ሰዎች አንድን ችግር ቢጋፈጡ እኩል መፍትሄ ሊሰጡት አይችሉም:: የአንዱ ምላሽ ከሌላ እንዲሁም ለመፍትሄ ፍለጋ የሚሄዱበት መንገድም ሊለያይ ይችላል:: አንድ ሰው ያለው ተጽእኖን የመቋቋም አቅም ሌላ ሰው የለውም::
አንጻራዊ አቅም አንድ ሰው ከሌላ ሰው በተለየ ሁኔታ ያለውን አንጻራዊ አቅም መነሻ ያደርጋል:: ለሆነ ሰው አስቸጋሪ የሆነ ነገር ለሌላ ሰው አስቸጋሪነቱ ይጨምራል ወይንም ይቀንሳል:: ለራስ ማሰብ ሲመጣ የራስን አቅም ማሳደግ ቀዳሚው የሚሆነው ለእዚህ ነው:: ተግባራዊነትን የሚጠይቁ የህይወት ጥያቄዎች በየፌርማታው የሚገጥም ስለሆነ:: ጥበብ ከእያንዳንዱ ሰው በሚወስነው ውሳኔ ውስጥ የሚጠይቅ ስለሆነ::
ጉዳዩ አካላዊ ይሁን መንፈሳዊ እንዲሁም ስሜትን መግዛት በውስጥ አቅም ላይ የተመሰረተ ምላሽ ነው እንደ ግለሰብ መስጠት የሚቻለው:: በጥሩ እንቅልፍ የዳበረ ግለሰብና በእንቅልፍ እጦት ውስጥ የሚቸገር ሰው እኩል ስሜታዊነት አይታይባቸውም::
የእውቀት እንዲሁም የጥበብ አቅማቸው ይለያያልና:: የግሪክ ፈላስፋ የነበረው አርስቶትል የራስን አቅም መገንባትን የተመለከተውን ጉዳይ ፍሮንሲስ/Phronesis ወይንም ተጨባጭ ጥበብ/practical wisdom በሚለው ውስጥ ያካትተዋል:: ለራስ ከራስ ብሎ ራሱን ለመገንባት ደቂቃዎችን የሚሰጥ ትኩረቱን የማይነፍግ ሰው በተጨባጭ ጥበብ ውስጥ ነው:: በተጨባጭ የሆነውን ነገር የወሰነው፤ በተጨባጭ ነገም የሚሆነውን ነገር ይወስናል:: ለራስ ከራስን ተጨባጭ ለማድረግ የግንዛቤ ለውጥ አስፈላጊ ነው:: ለራስ ጊዜ የመስጠትን አስፈላጊነት መረዳት::
በተጨባጭ የተግባር ሰውም መሆን:: ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመራመድ የሚከተሉትን ሦስት ነጥቦችን እንተግብራቸው:: ሦስት ነጥቦች ለተግባራዊ እርምጃ ለራስ ከራስ ብሎ ተነስቶ ራስን በመገንባት መንገድ ለመራመድ ሊደረጉ የሚገባቸው አያሌ ነጥቦች ቢኖሩም በአጭሩ በሦስት እንመልከታቸው፤ ግብ ማድረግ በግለሰባዊ ሆነ በቤተሰባዊ ህይወታችን ውስጥ ግብ የምናደርጋቸው አያሌ ጉዳዮች አሉ:: ለቤት አስቤዛ ለመግዛት ስናስብ ካለን የገንዘብ አቅም አንጻር ግብ እናደርጋለን::
‘እንትን ይህን ያክል ኪሎ ብገዛ፤ እንትን ይህን ያህል ሊትር ወዘተ’ ብለን እናቅዳለን:: የግል አቅምን መገንባት ጉዳይም እንዲሁ በመደበኛነት የእቅዳችን አካል ሊሆን የተገባው ነው:: ግለሰቦች ባላቸው ውስጣዊ አቅም ለሌላው መፍትሄ ይሆናሉ፤ ወይንም ጎጂ:: ግብ ማድረግ ካለንበት ድክመት ወደ ጥንካሬ እንድንወጣ የሚያደርግ መሆን አለበት::
ከህግ በላይ ለመኖር፤ እሴት ጨማሪ ለመሆን:: ፕልቶ እንዳለው “መልካም ሰዎች በአግባቡ ለመመላለስ ህግ አያስፈልጋቸውም፤ ክፉ ሰዎች ግን በህግ ውስጥ መሽሎኪያ ይፈልጋሉ::” መደበኛ በሆነ ትምህርት ልጆችን መላክ አንድ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ጎን ለጎን ሌሎች ክህሎቶችን ልጆች እየያዙ እንዲያድጉ ለማድረግ፤ በባህሪም እንዲታነጹ ወዘተ ግብ ማድረግን ይጠይቃል:: ራሳቸውን ችለው ውሳኔ መወሰን የሚችሉበት እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችም እንዲሁ ግብ ያደርጋሉ:: በአብዛኛው ራስ ላይ መስራት ግብ የሚደረገው የተሻለ ደመወዝ ለመከፈል የሚያበቃ ትምህርት ይዞ ለመገኘት ታሳቢ ያደረገ ነው:: እየሰራን ያለነውን ስራ ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ሁሌም ተገቢ ቢሆንም ራስን ማሳደግን ከደመወዝ ጋር ብቻ ሰፍቶ ማየት ግን ስህተት ነው:: አቅም ማሳደግ የሚያመጣው ጥቅም ብዙ ቢሆንም መነሻና መድረሻው ግን ደመወዝ አይደለም:: ሌላው የተሳሳተ ራስን ማሳደጊያ እቅድ የሚኖረን አንድ ችግር ከተፈጠረ በኋላ ያንን ችግር ለመቅረፍ ነው::
የሰውነት ክብደት ጨምሮ መቀነስ ሲታሰብ ስፖርት እንዲሁም ሌሎች የመፍትሄ መንገዶች ታሳቢ ይደረጋሉ:: ነገር ግን የፈራነው ነገር ከመከሰቱ በፊት እቅድ ተደርጎ ቢተገበር የተሻለው መንገድ እርሱ ነው:: ለራስ ከራስ የሚሆን ስጦታ መካከል አንዱ ምናልባትም ቀዳሚው ራስን ለማሳደግ የሚሆን ነው:: በወጀብ ማእበል ውስጥ ጸንቶ መቆም፣ አልበርት አንስታያን “ህይወት ሳይክል እንደመጋለብ ነው፤ ሚዛንን ለመጠበቅ የግድ ወደፊት መሄድን የሚጠይቅ” ይላል:: ወደፊት በጽናት መግፋት አስፈላጊ መሆኑን የሚያመለክት:: በጊዜ አጠቃቀም ጉዳይ የሚቆጭ አንድ ሰው አለ::
ይህ ሰው የዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረ ህንዳዊ ሰው ነው:: እጅግ በጣም ለጊዜ አጠቃቀም ቦታ የሚሰጥ ነው:: “ሰው እንዴት 30 ደቂቃ ማርፈድን እንደ ተለመደ ነገር ሊቆጥር ይችላል?” ሲልም ይናገራል:: ፈጽሞውኑ ለመቀበል የሚቸግረው ነገር ነው:: “ወጀብም ሆነ ማእበል ቢኖር፤ ዝናብ መጠኑን ጨምሮ ዶፍ ዝናብ ቢሆን፤ በመንገድ ላይ እየሄደ ያለ አንድም ሰው ቢቀር እኔ ግን በዝናቡም በዶፉም አልፌ በሰዓቴ ቀጠሮዬ ቦታ መድረስ አለብኝ ብዬ አምናለሁ” ይላል:: የዚህ ሰው የማስተማሪያ ሰዓት በሰዓቱ ጀምሮ በሰዓቱ እንደሚጠናቀቅ ሁሉም ተማሪ መረዳቱ አለው::
ይህ ሰው ማስተማር ከጀመረ በኋላ ክፍል ውስጥ መገኘት ያለው ትርጉምም እንዲሁ ግልጽ ነው:: በወጀብ ማእበል ውስጥ ጸንቶ ያለ ሙት ላይ መድረስ:: ኦሎምፒክ በመጣ ጊዜ ሩጫን የሚጀምሩ አያሌ ሰዎች አሉ:: ሁሉም ግን በዚያው ጸንተው ሲዘልቁ አናስተውልም:: በወረት ተጀምረው በወረት የሚያልቁ አያሌ ነገሮች አሉ:: በወጀብ ማእበል ውስጥ ጸንቶ መቆምን የሚጠይቅ ሩጫ::
ለራስ ከራስ የሚሉ ሰዎች ራሳቸውን ለማስለመድ እንዲሁም ለማሰልጠን ያሰቡትን ወደ መፈጸም ሲመጡ ሊያስቡት የሚገባውን ነገር በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ያሰብኩትን ወደ ውጤት አደርሳለሁ ብለው ነው:: ልዩነትን መለካት ጊታር የሚባለውን የሙዚቃ መሳሪያ ለመለማመድ እቅድ አድርጎ የጀመረ ሰው በጊዜ ሂደት እንደመጀመሪያው ጊዜ ጊታሩን ተጫወት ቢባል ይቸግረዋል:: እንደ መጀመሪያው ጊዜ እያበላሸ ድምጽ ማውጣት ይከብደዋል:: በጊዜ ሂደት የሚቸገረው ማበላሸት እየሆነ ይሄዳል:: መኪና መንዳት እየተለማመደ ያለም ሰው እንዲሁ ነው::
ለራስ ከራስ ልናደርጋቸው የሚገቡን ነጥቦችን ዘርዝረን ማደግን ስናስብ አሁን ያለንበትን አስቀምጠን ወደፊት የምንደርስበትን ግብ አድርገን እንነሳለን:: በሂደት ያለውን ለውጥ ማወቃችን ራስ ላይ የመስራትን አስፈላጊነት እንድንረዳ ስለሚረዳን ልዩነትን እየለኩ መሄድ ተገቢ ነው:: ሯጮች ብዙ ልምምድ ካደረጉ በኋላ ያሉበትን አቅማቸውን ለማወቅ የስፖርት ውድድር ያደርጋሉ::
በውድድሩም የሰሩት ልምምድ የሰጣቸውን ጥቅም ይረዳሉ:: አንዳንዴ በልምምድ ወቅት የደረሱበት የመሰላቸው ነገር በውድድር ወቅት የሚቀራቸው ነገር መኖሩን ይረዳሉ::
ለራስ ከራስ በሚሰራው ስራ ውስጥም ያለን እየመሰለን የሌሉን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ:: በተጨባጭ አካላዊም፣ ስነ-ልቦናዊም እንዲሁም መንፈሳዊ አቅማችን በየጊዜው ያለበትን ደረጃ በማወቅ መሆን ወዳለበት ለማድረስ መስራት ያስፈልገናል:: ልዩነቱን እየለኩ መራመድ::
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014