የተወለደው በታሪካዊቷ ጎሬ ከተማ ነው፡፡ አባቱ ግራዝማች ገሰሰ መንገሻ ይባላሉ፡፡ የጎንደር ተወላጅ ናቸው። እናቱ ደግሞ ወይዘሮ አስናቀች መልሴ፤ እሳቸው ደግሞ የጅማ ሰው ናቸው፡፡
አባት ከመኳንንቱ ወገን ነበሩ፡፡ ሃይማኖተኝነትን፤ ትዳርን ፤ አርበኝነትን እና አስተዳዳሪነትን በአንድ አስተባብረው የያዙ የዘመኑ ሰው፡፡ በኢሉባቦር እና አካባቢው የንጉሱ ንብረት ተቆጣጣሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ከዚያ አስቀድሞ የሊሙ አውራጃ አስተዳዳሪነት እና የአጋሮ ከተማ ከንቲባነትን ጨምሮ በብዙ ኃላፊነቶች ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡
እናቱም ቢሆኑ ከደህና ቤተሰብ የተገኙ እመቤት ናቸው፡፡ አባታቸው አቶ መልሴ ተሰማ ጅማ ከተማን ከመሰረቱ ሰዎች አንዱ ነበሩ፡፡ በእነዚህ ሁለት ሰዎች ትዳር 11 ልጆች የተወለዱ ሲሆን፣ ከነዚያ ልጆች መካከል ደግሞ አንዱ የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ሆኖ የምናወጋው ድምጻዊ ዘለቀ ገሰሰ ነው፡፡
ዘለቀ ገሰሰ የተወለደባት ጎሬ ከተማ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና ሆናም አገልግላለች፡፡ በዚህም የተነሳ ለጸጉረ ልውጦች እንግዳ አልነበረችም፡፡ ከምእራቡም ከምስራቁም ዓለም የመጡ ሰዎች በጎሬ ያልተለመዱ አልነበሩም፡፡
ዘለቀም ያደገው ከነዚሁ ጋር ነበር፡፡ የተማረበት ትምህርት ቤት መምህራን የነበሩት ህንዶች እንግሊዞች እና ሌሎች ሲሆኑ ተከራይተው የሚኖሩት ደግሞ ከነዘለቀ ቤት አጠገብ ያለን ቤት ነበር፡፡ ስለዚህም ዘለቀ እንደ ብዙሀኑ የገጠር ወጣቶች ፈረንጅ ለማየት ፊልም አላስፈለገውም ፤ ወደ ሌላ ከተማ መሄድም አላሻውም፡፡ ኋላ እጣ ፈንታው ለሚሆነው የሙዚቃ ሥራውም ሆነ የአኗኗር ስልቱ የእነሱ አስተዋጽኦ አለበት፡፡ ተማሪዎቹም ቢሆኑ ከጎሬ ዙሪያ ካሉ ቦታዎች የሚመጡ ነበሩ፤ ከበደሌ፣ ከጋምቤላ ከቡሬ ተማሪዎች ለትምህርት ወደ ጎሬ ይመጡ ነበር፡፡
የዘለቀ አባት ግራዝማች ገሰሰ እንደማንኛውም የመኳንንት ቤተሰብ ቆፍጣና ሰው ናቸው፡፡ ”አባቴ ጠዋት ተነስተው ሶስት አራት የጸሎት መጽሐፍ ነው የሚደግሙት። እሳቸው ሳይጨርሱ ደግሞ ቁርስ የሚባል ነገር የለም” ይላል ገሰሰ፡፡ ጸሎተኛም ብቻ አልነበሩም ፤ አርበኛም እንጂ፡፡
ዘለቀ የተወለደው ግራዝማች ለመጀመሪያው ኦጋዴን ዘመቻ በሄዱበት ወቅት ነበር፡፡ ስለዚህም በግራዝማች ቤት ዘፈን ብዙም የሚታወቅ እና የሚፈቀድ አልነበረም፡፡ ይሁንና እናቱ ወይዘሮ አስናቀች ከአባት በተቃራኒ ለዘብ ያሉ እና ለልጆቻቸው ፍላጎት ትኩረት የሚሰጡ ነበሩ፡፡
የእነ ዘለቀ ቤት የትልቅ ሰው ቤት እንደመሆኑ መጠን እንግዳ ይበዛበታል፡፡ ከተማዋም የታሪካዊው የጥቁር አንበሳ ጦር ዋና ማዘዣ ጣቢያ ነበረች፡፡ ስለዚህም እንግዳ እና ድግስ ብዙ ጊዜ ይኖራል፡፡ ድግስ ሲኖር እነ ዘለቀ ሙዚቃ እንዲያቀርቡ ይጋበዛሉ፡፡ የሚቀርበው ሙዚቃ ግን ትምህርት ቤት ያጠኑት እና ስለ ሀገር የሚያወሳው ብቻ ነው፡፡
እንዲህ እንዲህ እየተባለ አባትም ኮስተር እንዳሉ እናትም ለስለስ እንዳሉ ዘለቀም ሙዚቃን እንደወደደ ሕይወት ቀጠለች፡፡ የ7 ዓመት ልጅ እያለ ግን ግራዝማች ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ከኀዘን ወዲያ ማዶ ነጻነት ብቅ አለ፡፡ ሙዚቃን በደንብ ለመሞከር እድል ተገኘ፡፡ በተለይም እዚያው የሚገኙ የክርስቲያን ሚሽነሪዎች የዘለቀን ቅልጥፍና በቀላሉ አላለፉትም፡፡ እንዲዘፍን ይጋብዙት ጀመር፡፡
ስምንተኛ ክፍል ሲደርስ ወደ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ ሙዚቃን ለሚወደው ዘለቀ የተመቸች ቦታ ሆነች፡፡ እሱ እና ታላቅ ወንድሙ ጊታር መሞካከር ጀመሩ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ጎረቤታቸው ያለ ልጅ ፒያኖ ነበረው። ሌላ ድራም የሚሞክርም ልጅ ነበር፡፡ ዘለቀ ቢጤዎቹን አገኘ፡፡ ከቢጤዎቹም ጋር በግቢ ውስጥ ባለች ዶሮ ቤት ውስጥ የአፍላዎች ባንድ ተቋቋመ፡፡ የባንዱ ስም በኋላ ላይ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ታትሞ ታሪክ የሚሆነው ዳሎል ባንድ ነበር፡፡
ዘለቀ አዲስ አበባ ሲመጣ ኢትዮጵያ ዘውዳዊ ሥርዓትን ልትሰናበት አብዮት እያብላላች ነበር፡፡ ተቃውሞ እና ግርግሩ በየጊዜው ትምህርት እንዲቀጥ ያደርጋል፡፡ የትምህርት መዘጋቱ ለነዘለቀ በሙዚቃው ለመግፋት እድል ፈጠረላቸው፡፡
በሌላ መልኩ ቅድመ አብዮት በንጉሱ የመጨረሻ ዓመታት ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ በሯን ለሊበራል አኗኗር ክፍት አደረገች፡፡ የአሜሪካ ፊልም ፤ የእንግሊዝኛ ሙዚቃ፤ የምእራብ አለባበስ የወቅቱ ከተሜነት መገለጫ ነበር፡፡ በየትምህርት ቤቱም የተማሪ የሙዚቃ ባንዶች ነበሩ፡፡ ይህ ለዘለቀ እና ለዳሎል ባንድ የሙዚቃ ህይወት ማቆጥቆጥ በር ከፈተ፡፡
ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ግን የጨዋታው ህግ ተቀየረ። የደርግ እና ኢህአፓ ሽኩቻ እንኳን ለዘፈን በሕይወት ለመኖርም የሚያሰጋ ሁኔታ በሀገሪቱ እንዲፈጠር አደረገ። ደርግ እድገት በህብረት ዘመቻንም አስጀመረ፡፡ በዚህም በከተማ ያለ ተማሪ የገጠሩን ህብረተሰብ እንዲያስተምር ወደ ገጠር ይዘምታል፡፡ ዘለቀም እጣው ደረሰውና ወደ ሀረር ተላከ፡፡ ለ10 ወራት ገደማ ግዳጁን ከተወጣ በኋላ ግን ኢህአፓ ቀስ እያለ ወደ ገጠሩም እየገባ እንደሆነ ሲታወቅ እነ ገሰሰ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ሆነ፡፡
አዲስ አበባ ተመልሶ ሙዚቃውን ቀጠለ፡፡ ዘለቀና ባንዱ ስቴሪዮ ክለብ የሚባል ቦታ መስራት ጀመሩ፡፡ በኋላ ደግሞ ከአንጋፋው ምኒልክ ወስናቸው ጋር በመሆን ጣይቱ ሆቴል ቀጠሉ፡፡ለሁለት ዓመት ያህል እነ ዘለቀ ሙዚቃን ጣይቱ ውስጥ በሚሰሩበት ጊዜ የሀገሪቱ ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየተበላሸ መጣ፡፡ ሙዚቀኞችን ጨምሮ ብዙ ወጣቶች በየቦታው ይገደሉ ጀመር፡፡ ይህ ሁኔታ ቀስ በቀስ ወደ እነሱም እንደሚመጣ የተረዱት ዳሎሎች ከሀገር የሚወጡበትን መንገድ ማፈላለግ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን እሱም ቢሆን ቀላል አልነበረም፡፡ ደርግ መውጫዎችን በጥብቅ እያስጠበቀ ነበር፤ ለስደት ሲጓዝ የተገኘ ወጣትም እጣ ፈንታው መገደል ሆነ፡፡
የሆነ ሆኖ ከብዙ ጥናት እና ፍለጋ በኋላ መንገድ ተገኝቶ እነ ዘለቀ በወሎ ፤ አፋር ዞረው ጅቡቲ ገቡ፡፡ ጅቡቲ ለ9 ወራት ከቆዩ በኋላም ወደ አሜሪካ መሄድ ቻሉ፡፡ አሜሪካ ከዘለቀ በፊት ወንድሙ አዲስ ገሰሰ ቀድሞ ለትምህርት ሄዶ ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ አዲስ ለገሰ በሙዚቃ በኩል ራሱን የቻለ ታሪክ ያለው ሰው ነው፡፡ እነ ጂጂን ፤ ቴዲ አፍሮን እና ጃኖ ባንድን አሁን ለደረሱበት ቦታ ያበቃ ሰው ሲሆን የቦብ ማርሊ ልጆችን በማስተዳደርም ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የቆየ ነበር)፡፡
ዘለቀ አሜሪካ እንደገባ ወደ ትምህርት ቤት ተጓዘ፡፡ የቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተማሪ ሆነ፡፡ እንዲሁ በተሰጥኦ ብቻ የሚሰራትን ሙዚቃም በንኡስ ኮርስ መማር ጀመረ። ከዚያም ድራመር ተጫዋቻቸውን ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካ እንዲመጣ በማድረግ ባንዳቸውን አስቀጠሉ፡፡
ዶክተር አብርሀም ደሞዝ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ ጋ በመሄድ ቤታቸውን ለልምምድ እንዲፈቅዱላቸው ጠይ ቀው ተፈቀደላቸውና ከሥራ ሰዓት ውጪ እና እረፍት በሚተርፋቸው ጊዜ ልምምድ ተጧጧፈ፡፡ ከዚያም የመጀመሪያው ኮንሰርት ወንድሙ በሚማርበት ትምህርት ቤት እንዲቀርብ ሆነ፡፡ በመቀጠል ኮንሰርቱ ወደ ዋሽንግተንም ሄደ፡፡ የዋሽንግተኑ ኮንሰርት ግን ሌላ የእድል በርን የከፈተ ነበር፡፡
ኮንሰርቱን ሊታደሙ ከመጡ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ ታዳሚ በሀገሯ ልጆች ተሰጥኦ ተደነቀች፡፡ ስለዚህም ወደ አለቃዋ ቢሮ ልትጋብዛቸው ወደደች፡፡ አለቃዋ እውቁ ድምጻዊ ስቲቪ ወንደር ነበር፡፡ እሷ ደግሞ ስቲቪ ከሚያስተዳድራቸው ሶስት የሬድዮ ጣቢያዎች በአንዱ ዳይሬክተር ናት፡፡ ከስቲቪ ጋ ተገናኙ፡፡ ደስ አለው፤ ደስ አላቸው፡፡ አበረታታቸው፡፡ አምስት ሙዚቃዎችንም እንዲቀዱ አደረገ፡፡ የተቀዱትን ሙዚቃዎች ለሙዚቃ አከፋፋዮች እንዲደርስም አደረገ፡፡
የእነዘለቀ ሙዚቃ ከደረሰባቸው ቦታዎች መሀከል አንዱ ደግሞ የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሊ ቤት ነበር፡፡ ባለቤቱ ሪታ ማርሊ ሙዚቃቸውን ሰምታ ወደደችው፡፡ ከዓመት በፊት ሕይወቱ ያለፈችው ባለቤቷ ቦብ ማርሊ ከምኞቶቹ መካከል አንዱ ከኢትዮጵያውያን ድምጻውያን ጋር መስራት ነበር፡፡ ስለዚህም ወጣቶቹን ልታገኝ ፈለገች፡፡ ወደ ጃማይካ ተጋበዙ፡፡ በቦብ ማርሊ የልደት ቀንም በመቃብር ስፍራው በተዘጋጀ መርሐ ግብር ሙዚቃቸውን እንዲያቀርቡ ሆነ፡፡
ሪታ አዲስ እድል ለነዘለቀ ሰጠቻቸው፡፡ እዚያው ጃማይካ ውስጥ ሆነው ሙዚቃ እንዲሰሩ ነገሮችን አመቻቸችላቸው፡፡ በጃማይካ ገጠር ውስጥ ቤት ተከራይታ፤ ቀለብ ቆርጣ ፤ በቀን ለ8 ሰዓታት ልምምድ እያደረጉ እንዲቀመጡ አደረገች፡፡ ከሶስት ዓመታት በኋላም ላንድ ኦፍ ዘ ጁነሲስ የተሰኘ አልበማቸው ወጣ፡፡ ተወደደም፡፡
የቦብ ማርሊ ልጆች እድሜያቸው ሙዚቃ ለመጫወት ሲደርስ ሜሎዲ ሜከር የሚል ባንድ አቋቋሙ፡፡ እነ ዘለቀም ወደዚያ ባንድ ተቀላቀሉና አብረው መስራት ጀመሩ፡፡ ይህ ግንኙነት እነዘለቀን ወደ ዓለም አቀፍ ከፍታ አወጣቸው። ለ7 ዓመታት በቆየ አብሮ የመስራት ታሪካቸው ሁለት የግራሚ ሽልማቶችን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን ሰበሰቡ። ከ10 ጊዜ በላይ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ጉዞ አደረጉ፡፡ ከ7 ዓመት በኋላ ግን ባንዱ ለሁለት ተከፈለ፡፡ ዘለቀና ሌሎች ሬጌን ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር አዋህደን መስራት አለብን አሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እኛ የሬጌ ድምጻውያን ነን ስለዚህ ምንም ሳናደባልቅ በሬጌው ብቻ መቀጠል ነው ያለብን አሉ። መስማማት አልተቻለም እና ባንዱ ተበተነ፡፡
ዘለቀ የግሉን ጉዞ ጀመረ፡፡ በግሉ የመጀመሪያ አልበሙን አወጣ፡፡ ስያሜውም ካም ቱ ሚ የሚል ሆነ፡፡ በዚህ ታዋቂ አልበም ውስጥ ተወዳጆቹ ዶን ሌት ሚ ዳውን እና ሺቨር ኢን ሚን የመሳሰሉ ሙዚቃዎች የተካተቱበት ነበር፡፡ ከአልበሙ መውጣት በኋላ አሜሪካን ዞሮ ሙዚቃውን አቀረበ፡፡
ከዚያም ወደ ሀገሩ መጣ፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ኢትዮጵያን እንደ አዲስ ጎበኛት፡፡ ያ ጉብኝት ለዘለቀ አዲስ እይታ ፈጠረለት፡፡ አዲስ ተልእኮም ሰጠው፡፡ ተልእኮውም የበጎ አድራጎት ሆነ፡፡ በጉዞው ወቅት በየቦታው በትምህርት ቀን ከትምህርት ገበታ ተለይተው በጎዳና ሲንገላወዱ የሚያያቸው ህጻናት ጉዳይ እረፍት አልሰጠውም፡፡ ስለ ዚህም ትምህርት ቤት የመገንባት ዘመቻውን ጀመረ፡፡
ዘለቀ እንደሚለው ይህ በበጎ አድራጎት ላይ የመሳተፍ ዝንባሌ የመጣው ከእናቱ ነው፡፡ ”እናቴ በጣም ንቁ ነበረች። በልጅነታችን በምንኖርበት ከተማ የበጎ አድራጎት ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ እና መሪ ነበረች” ይላል፡፡ የእናቱን ፈለግ ተከተለ፡፡ ደጋጎችን አማክሮ እና ቀስቅሶ የትምህርት ቤት ግንባታን ጀመረ፡፡ ያ በአንድ ጉዞ የተጀመረ መነቃቃት በመላው ኢትዮጵያ 30 ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ተጠናቀቀ፡፡ አሁን ደግሞ አንዳንዶቹን በማሳደስ ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡
ዛሬ ላይ ዘለቀ ከሙዚቃው ባለፈ በበጎ አድራጎት ሥራም ላይ ንቁ ተሳታፊነቱን ቀጥሎበታል፡፡ በቅርቡ የአንድ ለመከላከያ ሰራዊት 5 ልጆችን ያበረከቱ እናትን ቤት አሳድሶ ጨርሷል፡፡ የአዲስ አበባ ዲያስፖራ ማህበር አባል ሆኖም በቅርቡ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ዶክተሮችን አሰባስቦ ነጻ አገልግሎት እንዲሰጡ እና መድኃኒቶችም ከመላው ዓለም እንዲሰበሰቡ ለማድረግ እየሰራ ነው። በትውልድ ከተማው ያለውን ታሪካዊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማሳደስም ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡
በባንድ 9 በግሉ ደግሞ 4 አልበሞችን የሰራው ዘለቀ አዲስ በፓን አፍሪካዊነት ዙሪያ የሚያጠነጥን አልበም እያዘጋጀ ሲሆን፣ ሰሞኑንም ከ12 ሀገራት የተሰባሰቡ የሬጌ ድምጻውያንን በመያዝም በዚሁ ሳምንት አንድ ወቅታዊ ነጠላ ዜማ ለቅቋል፡፡ ከሀገር ውስጥ ዘፋኞች ጋር በመሆንም በቅርቡ በወጣው ሀገራዊ አልበም ላይ አንድነት የተሰኘ አንድ ሙዚቃም አበርክቷል፡፡
ዘለቀ የ4 ልጆች አባት ነው፡፡ ጥሩ የትዳር ህይወት እንደነበረውም ይናገራል፡፡ ከ35 ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ ተመልሶ መጥቶ እየኖረባት ስላለችው ሀገሩ ሲያወራም በስሜት ነው፡፡ ”ዓለምን ዞሬ አይቻለሁ ፤እንደ ኢትዮጵያ ውብ ሀገር አላየሁም” የሚለው ዘለቀ “በኢትዮጵያዊነቴ በጣም ነው የምኮራው” ሲልም ያክላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር እንዳለንም ይናገራል፡፡
የእረፍት ቀኑን በምን እንደሚያሳልፍ ጠየቅነው፡፡ ማንበብ እንደሚወድ እና መጽሐፍ እየጻፈ እንደሆነ ነገረን። ከዚያ በተጨማሪ ስፖርት መስራት ፤ የእግር ጉዞ ማድረግ እወዳለሁ፤ የእረፍት ቀኔንም በነዚህ በነዚህ ነገሮች ነው የማሳልፈው አለን፡፡
በመጨረሻም ለኢትዮጵያውያን የሚያስተላልፈው መል እክት ካለ እድሉን ሰጠነው፡፡ ”እኛ ጋ ዊዝደም አለ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ነን፡፡ ምእራባውያኑ ሆኑ ሌሎች ከውጭ መጥተው አያስታርቁንም ፤ ለሁሉም ሥርዓት አለን፤ የገዳ ስርአቱ ፤ ደቦው ፤ አውጫጪኙ ፣ምኑ የኛ ነው፡፡ እሱን እናሳድግ ነው የምለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዘረኝነትን መተው አለብን” የሚል መልእክት አስተላልፎ ቆይታችን ተጠናቀቀ፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ኅዳር 26/2014