
“ለምክር ቤቱ አባላት ላረጋግጥላችሁ የምሻው አገሬ ጥንትም በዚያ ሁሉ ባላንጣ ፊት እንዳሸነፈችው ሁሉ ታሸንፋለች፡፡” አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ተወካይ፤ በዚህ ንግግራቸው ጥንት- ባላንጣ- ታሸንፋለች! የሚሉት ጎልተው ወጥተዋልና እኛም ጉዳያችንን እርሱን አድርገን እናንሳ፡፡ እነዚህ ቃላት እንደ ኦሎምፒክ የሁሉንም ቀልብ የሳቡ ናቸው፡፡
ኦሎምፒክ የዓለም ዓይኖች በትኩረት የሚከታተሉት ከፕላኔታችን ስፖርታዊ ትዕይንቶች መካከል ከቀዳሚዎች ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ ሚዲያዎች እንደ አገራቸው ነባራዊ ሁኔታ በሰፊው የሚሸፍኑት፡፡ ኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ትኩረት እንደምናደርግ ሌሎች አገራትም እንዲሁ ውጤት ከሚጠብቁበት ዘርፍ አንጻር ትኩረታቸውን አድርገው ዓይናቸውን ያደርጋሉ፡፡ ወርቅ በመጣ ቁጥር የደስታ ችቦ ይለኮሳል፡፡ ሁሉም ወርቅ ግን እኩል የደስታ ስሜትን አይፈጥርም፡፡ አንዳንዱ ወርቅ ይለያል፡፡ ከወርቆች ሁሉ ልዩ የሆነ ወርቅ፡፡
የአንድ አገር ዜጎችን በአንድ ሳምባ እየተነፈሱ መሆኑን የሚያረጋግጥ ወርቅ፡፡ እርሱም ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ የተገኘው ወርቅ ነው፡፡ እንዲህ ባለጊዜ ዜጎች በእምባ ይራጫሉ፤ ከአንድ ወርቅ በላይ የሆነ ትርጉም አለውና። ስሜትን ሰቅዞ በመያዝ የአንድ አገር ሕዝብን ወደ አንድ መድረክ በመሰብሰብ በአንድ ሳምባ እንዲተነፍሱ የሚያደርግ ቅጽበት፡፡ ሲንጋፖር የመጀመሪያውን ወርቅ በኦሎምፒክ ስታገኝ የነበረውን ክስተት አስታከን ወደ ርዕሰ ጉዳያችን እንግባ፡፡
ቀድሞ የማሌዢያ ፌደሬሽን አካል የነበረችው፤ ራሷን ችላ ከቆመች ስልሳ ዓመታት በቅጡ ያልሞላት ሲንጋፖር በኦሎምፒክ መድረክ የደስታ ሲቃ ውስጥ የገባችበት ልዩ ወቅት ነበር፡፡ የመጀመሪያውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዋን በጆሴፍ ስኩሊንግ በኩል ያገኘችበት ጊዜ፡፡ በወቅቱ ሲንጋፖራውያን እጅግ ተደስተው፤ በደስታ ብዛትም ታላቅ ስካር ውስጥ ነበሩ፡፡
ዳዊን ሊም ከስታንፎርድ ግራጅዌት ስኩል ኦፍ ቢዝንስ ለተማሪዎች ወቅቱን አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ አሉ፤ ‹‹የ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች መካከል ለእኛ ሲንጋፖራውያን በጣም ወሳኝ የሆነውን ሊያደርግ ደቂቃዎች እየቆጠሩ ነው፡፡ የወንዶች የዋና ውድድር የመጨረሻው ትንቅንቅ፡፡ እውነታውን በቀጥታ ልንገራችሁ እኔ የስፖርት ሰው አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ይህ ውድድር ልዩ ነበር፡፡ የውድድሩ ስም መዋኘት ነው፡፡ ውድድሩን እንደሚያሸንፉ ግምት የተሰጣቸው ስፖርተኞች አሉ፡፡ አንዱ ከአሜሪካ ሌላው ከደቡብ አፍሪካ፡፡ ከባድ ትንቅንቅ ሊሆንበት ያለው ውድድር፡፡
የእኔ ልብ የማሸነፍ እድል ከተሰጣቸው ከሁለቱ ስፖርተኞች ጋር ሳይሆን ከወጣቱ ስፖርተኛ ጆሴፍ ስኩሊንግ ጋር ነው፡፡ እርሱም ሲንጋፖር ከምትባል ትንሽ ሀገር ተወክሎ ግዙፍ አገራትን የሚገጥም፡፡ ውድድሩ ተጀመረ፤ ትንቅንቁ ሆነ፤ ጆሴፍ ስኩሊንግ ቀዳሚ ሆነ፡፡ ለእኛ ሲንጋፖራውያንም የመጀመሪያው ወርቅ ሜዳልያ ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ነጻ አገር በሆንን በ50ኛው ዓመት ላይ የመጀመሪያውን ወርቅ አገኘን፡፡ በወቅቱ ብሔራዊ መዝሙራችን ሲዘመርና ሰንደቅ ዓላማችን ከፍብሎ ሲውለበለብ ይሰማኝ የነበረው ክብር አሁንም ይሰማኛል፡፡ የሚሆነውን እያየሁ አለቅስም ነበር፡፡
ምናልባትም በአገራችን ገና ወጣት በሆነው ታሪካችን ውስጥ ትልቁ ክብር የተሰማን ቀንም ነበር፡፡ በውድድሩ ውስጥ በጣም የሚጠበቁት ባለብዙ ልምዶች ነበሩ፡፡ ነገርግን ልጃችን ጆሴፍ ሕልም አሸናፊ ሆነ፡፡ ዳዊት ጎልያድን እንደገጠመው አይነት ሕልም፡፡ ትንሿ አገር ትልልቆቹን እንድታሸንፍ ያደረገ ሕልም፡፡ በእዚያ ቀን ዮሴፍ ህልሙን አሳካ፤ እንዲሁም መላው ሕዝባችን በእርሱ ላይ ያለውን ህልምም አሳካ፡፡
… አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ አገር እንዴት የሚገነባ ይመስላችኋል? አገር እንደ ዮሴፍ ባሉ ታሪኮች ላይ ይገነባል። ስለ ሕልም በሆኑ ታሪኮች፣ የእናንተ ሕልም፣ የእኔ ሕልም፣ የቤተሰቦቻችን፣ የማኅበረሰባችን ነገርግን መድረስ ወዳለብን ለመድረስ በደምና በላብ በአስቸጋሪ መንገድ ውስጥ እያለፍን የምናከናውነው ሕልም፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሕልም ነበረው፡፡ ልጃችን ጆሴፍ ሕልም ነበረው፡፡ አገር እንዲህ በመሰሉ ሕልሞችና ሕልመኞች የምትገነባ ነች፡፡
ሕልም፣ ሥነ-ምግባር እና ዋጋ መክፈል አገር የሚገነባባቸው ምሰሶዎች ናቸው፡፡ የዛሬ 50 ዓመት ሲንጋፖር ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ተላቃ አዲስ ነጻ አገር ነበረች። የተፈጥሮ ሀብት የሌላት፡፡ ከሦስተኛው ዓለም ተርታ የምትመደብ፡፡ ዛሬስ? ዛሬ ታሪክ ተቀይሯል፡፡ እንደ ጆሴፍ አይነት ሕልም ያላቸው ሰዎች እንደ አገር በፈጠሩት የጋራ ሕልም የተነሳ፡፡›› የደስታቸው ምክንያቱ እንደ አገር ለመቆም ያደረጉት ጥረት መሳካቱ እንደ አገር የመቆጠር እድል እንዳገኙም ተሰምቷቸው ስለነበር ተናገሩት፡፡
ተናጋሪው አገር በመገንባት ዙሪያ ደጋግመው ያነሱት “የጋራ ሕልም”ን ነው፡፡ የጋራ ሕልም፣ የጋራ ተስፋ እና በጋራ ጥረት ውስጥ መገኘት፡፡ የኢትዮጵያን አክራሞት በጸጥታው ምክር ቤት አንጻር ስንመለከት የጽሑፉ መግቢያ ያደረግነውን የአምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴን ንግግር እናገኛለን፡፡ አምባሳደሩ አገራቸውን ወክለው በጸጥታው ምክር ቤት ያደረጉትን ንግግር ሲቋጩ “ለምክር ቤቱ አባላት ላረጋግጥላችሁ የምሻው አገሬ ጥንትም በዚያ ሁሉ ባላንጣ ፊት እንዳሸነፈችው ሁሉ ታሸንፋለች” አሉ፡፡ ሦስት ቃላትም ጎልተው ከአምባሳደሩ የመዝጊያ ንግግር ውስጥ እናገኛለን ጥንት-ባላንጣ-ታሸንፋለች!
በጥንት ጀምረን፤ በባላንጣ አልፈን በታሸንፋለች እንቆጫለን፡፡ መዳረሻ መልዕክታችን “እንደ ተበላ ዕቁብ … ወይስ?” በሚለው ጥያቄ ውስጥ ይገኛል፡፡
ጥንት
ያለፉት ብዙ ትላንቶች ጥንት በሚለው ቃል ውስጥ ያላቸው ድርሻ ብዙ ነው፡፡ ከጥንት ታሪካችን ተነስተን ዛሬ ላይ ስንመጣ የጋራ ሕልምን ፍለጋ የከፈልነው ዋጋ ብዙ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ የጥንት ስልጣኔያችን ዛሬ ላይ እየተጎበኘ ለአገር ገቢ እያስገኘ ሲሄድም በጥንት ውስጥ የተሰወረ አቅማችንን መፈለጉ ለነገ የሚባል እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ የእርስበርስ ጦርነት በጥንት ታሪካችን ውስጥ የበዛውን ገጽ ይዞ ዛሬም ተከትሎናል፡፡ በዓለም መድረክ ላይ እውነት ይዘን በቀረብን ጊዜ ባገኘነው ምላሽ ያዘንባቸው የታሪክ ምዕራፎች እንዲሁ በጥንት ትርጉም ውስጥ ስፍራ አላቸው፡፡ ጥንትን በጋራ ሕልማችን እንየው ስንል የጎደለብን ብዙ ሆኖ ይሰማናል፡፡ ዛሬም እንደትላንቱም ሆኖ፡፡ በዕቁብ መንደር ትርጉሙ የሚገኝ፡፡
ለአንዳች ጉዳይ ዕቁብ የገባው ሰው የዕቁብ ዕጣ በወጣ ቁጥር ዓይኑን በዕድሉ ላይ ያደርጋል፡፡ ዕድል ቀንቶት ዕቁቡ እርሱ ቤት የገባ ቀን ደስታው ወደር የለውም፡፡ የዕቁቡ ደስታ ግን በቀሩት የዕቁቡ ወቅቶች ላይዘልቁ ይችላሉ፡፡ የወጣው ዕቁብ የተበላ ዕቁብ ነውና በተስፋ አይደገፈም፡፡ ዕቁቡ ገንዘብ ይዞልኝ ይመጣል ሳይሆን ገንዘብ ከእኔ ይጠበቃል በሚል ስለሚተካ ዕቁቡ ድካም የሞላበት ይሆናል፡፡ ‘ይህ ዕቁብ አልቆና ተገላግዬ’ ወደማለቱም ይገባል፡፡
ጥንት ውስጥ አሸናፊነታችን መኖሩን በዓለሙ መድረክ የተናገሩት አምባሳደሩ እንደ ሕዝብ በጥንቱ ውስጥ ያለንን ትርጉም ተናገሩ፡፡ ይህን የአምባሳደሩን መልዕክት ከወዲህ አስቀምጠን አንድ ዕድልን እናንሳ፡፡ ወደ አሜሪካ የመሄድን እድልን፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ አሜሪካ መሄድ እንደሚችል እና እንዲመዘገብ በአንድ ትንግርተኛ ቀን መልዕክት ቢደርሰው ከአንድ ቤት ምን ያህል ሰው ይመዘገብ ይሆን? ከአንድ ወረዳስ?ከአንድ ክልል? ከመላ አገሪቱስ? ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይስ ተቆጥሮ ይገኝ ይሆን? በስተመጨረሻ ኢትዮጵያ የሚቀረው ሰው በጣት የሚቆጠር ይሆን? ግምታዊ ምላሹን ለራሳችን እናድርገውና እንቀጥል፡፡
አሸናፊነት የስሌት ውጤት መሆኑ እሙን ነው፡፡ እንደ አገር ድል ማድረግ ሲታሰብ ድል የሚያደርገው ጉዳይ ድህነት፣ ዕውቀት ማጣት፣ ሥራ አጥነት፣ ያልተገባ ባህሪ ወዘተ እያልን ልንዘረዝር እንችላለን፡፡ በጥንት ትርጉማችን ውስጥ ያለው አሸናፊነት በእኒህ ነጥቦች አንጻር ዛሬ ራሳችንን ስንፈትሽ የምናገኘው ምላሽ የሚሰጠን ትርጉም ምንድን ነው? የጋራ ህልማችን እንደ ተበላ እቁብ ወይንስ… ምን…?
የሲንጋፖር የመጀመሪያው የኦሎምፒክ ወርቅ ለተናጋሪዋ እንስት የሰጣቸው ትርጉም “የጋራ ሕልም” የሚል መሆኑን መግቢያ ላይ አንስተናል፡፡ አሜሪካውያን ለአገራቸው ዜጋ የሚያደርጉት ጥንቃቄ ለጋራ ህልማቸው የሚፈጥሩትን መናበብ በሚገባ አሳይቶናል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በጥንት ስሌት ውስጥ አሸናፊነት አለን፡፡ አምነን ልንቀበለው የሚገባ አሸናፊነት፡፡ በጦርሜዳ የሆነ አሸናፊነት፡፡ እንደ ላሊበላ በመሰሉ ድንቅ ቅርሶች ውስጥ አልፎ የሚታይ ድንቅ አሸናፊነት፡፡ በጥንቱ ውስጥ ያለው አሸናፊነት ግን በአሁናዊ ቁመናችን ውስጥ የሚኖረው ትርጉም በጥያቄ ውስጥ ነው። አሁናዊ ውስጣችን እንደተበላ ዕቁብ ወይንስ … ?ብሎ የሚያስጠይቅ ነው፡፡
በጥንቱ ታሪካችን ውስጥ ኢትዮጵያውያን ከአገር ለትምህርት ወጥተው ውጭ አገር ሲቀሩ የአዕምሮ ችግር እንዳለባቸው ይቆጠር ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ በተገኘው ቀዳዳ ከአገር ወጥቶ መገኘትና ኑሮን ማደላደል ቀዳሚው የመቀየሪያ መንገድ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ፈጣሪ ከእኛ ጋር መሆኑን ማሳያ ተደርጎም የሚቀርብ ነው፡፡ ተስማምተን አገራችንን በጋራ ሕልም መገንባት ሳንችል መቅረታችን ይታያል፡፡ አንባቢው ስለራሱ እንዲያነብ እመክራለሁ፤ ስለራሱ ብቻ፡፡ አጠገቡ ካለው ሰው ጋር ስላለው የጋራ ሕልም፡፡ በጋራ ሕልሙ ውስጥ ስለሚፈጥረው የጋራ አገር፡፡ ተግባብቶ ስለሚኖርበት። በጥንት ውስጥ የነበረውን አሸናፊነት ባላንጣም ቢኖር ከአሸናፊነት የማያጎድል፡፡
ባላንጣ
በግጥም፣ ስነቃል እና በሌሎችም መንገዶች ልዩ ልዩ መልዕክቶችን ማስተላለፍ የተለመደ ነው፡፡ በአሁን ዘመን በሕዝብ ማመላለሻ መኪናዎች ላይ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ተለጥፈው እንደምናየው፡፡ እረኞች በግጥምና በዜማ ወቅታዊ ሁኔታውን ለቀጣይ የሚያስተላልፉበት መንገድ የኖረ ልማዳችን ነው፡፡ ትኩረትን ካገኙ ይዘቶች መካከል ደግሞ ጀግናን ማወደስ፣ ባላንጣን አሳንሶን ማቅረብ፣ ፍቅርን መግለጽ፣ ተስፋን ማስረዳት ወዘተ ይገኙበታል፡፡
ሕይወታችንን ለመምራት ስንራመድ ባላንጣ መንገዳችን ላይ የሚገጥመን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከመሬት ተነስቶ ባላንጣ የሚሆን እንዳለ ሆኖ በሥራ አጋጣሚ ወይንም በጥቅም ግጭት ባላንጣነት ይፈጠራል፡፡ የአገራችን ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ባላንጣነትን ሲያብላላ ከነበረ አስተሳሰብ መነሻ ያደረገ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ብሔርን መሰረት ባደረገው የፖለቲካ ውቅር ውስጥ ባላንጣነት ማዕከላዊ ነጥብ ሆኖ የተሠራበት ሆኖ ይታያልም፡፡ መተባበር፣ መደጋገፍ፣ ተያይዞ ማደግ ወዘተ ከሚሉ ሃሳቦች ይልቅ በተቃራኒው ያሉ ጠላትነትን ማዕከል ያደረጉ አስተሳሰቦች በሰፊው ሲሰራጩ ኖረው ዛሬ ውጤቱን እያጨድን እንገኛለን፡፡
ባላንጣነት በበዛባት አገር ውስጥ የጋራ ሕልም ጠፍቶ የጋራ ኑሯችን እንደ ተበላ እቁብ ቢሆን እንዴት ሊገርመን ይችላል፡፡ ከሰሞኑ ከተሰሙ ዜናዎች መካከል አንዱ የቀድሞ የሠራዊት አባላት ወደ ሠራዊቱ እንዲቀላቀሉ የቀረበላቸው ጥሪ ይገኝበታል፡፡ ጥሪው የቀረበላቸው የቀድሞ የሠራዊት አባላት እንዲያሟላ የተለያዩ መስፈርቶች ቀርቦላቸዋል፤ ከእነዚህ መካከልም ‹‹የአገሪቱን ሕገመንግስት መቀበል›› የሚለው አንዱ ነው፡፡ ትኩረትን የሚስብ መስፈርት፡፡ ለምን?
የቀድሞ ሠራዊት አባላት በተለይም በደርግ ዘመን የነበሩት አሁን ያለውን ሕገመንግስት ለማንበር እየመጣ ያለውን ኃይል ለመመከት ሲዋደቁ የነበሩ መሆኑ ይታወሳል። ባላንጣቸው እንደሆነ የሚያምኑትን ኃይል ሕገመንግሥት ተቀብለው እንዲቀላቀሉ የቀረበው ጥያቄ ላይዋጥላቸው ቢችልም ሕገ መንግሥቱ እስኪተካከል ድረስ የግድ ገዢ ሕግ አስፈላጊ በመሆኑ ሊከበር ይገባዋል በሚለው ሙግት መመላለስን ይጠይቃቸዋል፡፡
ባላንጣነት የፖለቲካ ስሪታችን የጦር ሠራዊታችን የጋራ ሳምባ እንዳይኖረው ያደረገ የትላንት ጉዟችን ውስጥ ሚዛን የደፋም ነው፡፡ ይህ ሲሆን እንደ ተበላ ዕቁብ ጀርባቸውን ለአገራቸው የሰጡ ወጣቶች ሆኑ አዛውንቶች ቢኖሩ እንዴት ሊገርመን ይችላል? የጸጥታው ምክር ቤት ፊት የቀረቡት አምባሳደሩ ባላንጣ ብለው የጠሯቸው የውጭ ኃይሎች በባላንጣነት ስሜት በመካከላችን የኖሩበትን ርቀትም እንድናይ ያስፈልጋል፡፡
የጋራ ህልም ላይ እንድንደርስ ካስፈለገ በውስጥም በውጭም ያለው የባላንጣነት ጦስን መመርመር አይከፋም፡፡ በሃይማኖት አክራሪነት የፈጠርነው ባላንጣነት ያሳጣን ስሌቱ ምን ያህል ነው? ስፖርታችንን ለማስተዳደር በሄድንበት ርቀት ውስጥ የተፈጠረው ባላንጣነትስ? በፖለቲካው መድረክስ? በንግድ ማህበረሰቡ መካከልስ? በሁሉም ስፍራ?
የጋራ ሕልም በተበላ እቁብ ስሌት ውስጥ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ስለዚህ በነገ ውስጥ በሚታይ የጋራ ተስፋ ቆሞ ማሰቡ አይከፋም፡፡ በባላንጣነት ውስጥ የጋራ ሕልም ቦታ የለውም፡፡ ወዳጄ ሆይ ከሰውጋር ወጥተህ የምትገባ እንደመሆንህ በዙሪያህ የበዙ ባላንጣዎች ይኖራሉ፡፡ ባላንጣዎችህ የምትቆፍረውን ጉድጓድ በደፈኑብህ ጊዜ ተስፋ ቆርጠህ ለመቀመጥ አትስነፍ፡፡ ባላንጣህን ልታሸንፈው እንደምትችል አምነህ ተነሳ እንጂ፡፡ መዳረሻህም ጉድጓድ ርሆቦት ሊሆን እንደሚችል አምነህ ተነሳ፡፡ በአንተ ላይ እንዲሆን የማትፈልገውን በሌላው ላይ ባለማድረግ ፍቅር በመላበት መንገድ የአንተን ሩጫ ሩጥ፡፡ የሞራል ልዕልና ለሕይወትህ የሚሰጠውን ትርጉም አይተህ ሕይወትን በራስህ መንገድ ምራት፤ በመልካሙ መንገድ፤ በሕልም መንገድ!
አንዳንዱ ባላንጣ በአንተ ስኬት የሚቀና ነው፡፡ አንተ ወደ ስኬት ከሄድክበት ነገር ትምህርት የሚወስድ ሳይሆን እንዴት አንተን ወደ እርሱ ደረጃ ዝቅ አድርጎ ማቅረብ እንደሚችል በማሰብ የሚሰራ፡፡ አንዳንዱ ባላንጣ ዓይንህን በጨርቅ አስሮ ላሞኝህ የሚል ነው፡፡ በራሱ ልክ የሚያስብ፡፡ እንደ እርሱ ወርደህ አታስብ፡፡ አንዳንዱ ባላንጣ በበዛ ንግግር ውስጥ እውነትን መቅበር የሚችል ሲሆን፤ እመኑኝ እውነት መቼም ቢሆን ተቀብራ አትቀርም፡፡ እውነት ከሞት መነሻ ጊዜ አላትና፡፡
የጋራ ህልምን እንደ ቤተሰብ እንደ ማኅበረሰብ እንደ አገር እንዲኖረን በምናስብበት ጊዜ ባላንጦቻችንን በሞራል፤ በእሴት፤ በሥራ ትጋት በልጠን በመገኘት መሆን አለበት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ጎራ ሆነን ጦር የተማዘዝንበት ያለፉት የታሪካችን ምዕራፎች ፈውስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መውጫ መንገዱም አንዱ የሌላውን ቁስል ከሚያክምበት፤ ያነሳነው ብረት ተቀጥቅጦ ለእርሻ በሚውልበት መንገድ ነው።
የጋራ ሕልምን ፍለጋ አስቸጋሪ መንገድ ቢሆንም ፈውሳችን እዚያ ውስጥ በመሆኑ መበርታት አማራጭ የለውም፡፡ የጋራ ሕልም በሌለበት የተገነባ አገር የለም፤ ሊገነባም ሆነ ሊጸና አይችልም፡፡ ባላንጣዬ ስለምን ከአጠገቤ አደባ ብለህ ጠይቅ፡፡ ምላሹ ሕልም አልባ ሊያደርግህ የሚል ነው፡፡ የነፍስ ወከፍ ቅዥት ሲበዛ የጋራ ሕልም ይጠፋል፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ በዓመታት መካከል የነፍስ ወከፍ ቅዠታችንን ለመጫን የሄድንበት ርቀት ማሳያ፡፡
ባድማ ዝምታውን ሰብሮ ቢናገር በአንድ ወቅት አንድ አገር የነበሩ ዜጎች እንዴት ደማቸው በተለያየ ጎራ ፈሰሰ ብንል ምላሹ የጋራ ሕልም አለመኖር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አንዳችን የያዘነው እውነት ለሌላችን የተበላ ዕቁብ ሆኖ፤ ሕልማችን ሁሉ እርስበርሱ ተጋጭቶ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ከፊታችን ያሉት እንደ አገር መምከሪያ መድረኮች የጠፋውን ሰው ፍለጋ ላይ እንደሚያተኩሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከሕልም የጠፋው፤ ከጋራ ሕልም የጠፋው፤ ከጋራ ተስፋ የጠፋውን አንድ ሰው ፍለጋ፡፡ ሁሉም ዜጋ እኩል ዋጋ ኖሮት የጠፋውን በመፈለግ ወደ ውጤት የሚደረስበት ወቅት፡፡ የአሸናፊነት ማረጋገጫ፡፡
ታሸንፋለች
ወዳጄ ሆይ ወደ ኦሎምፒክ የሚተመው አሸናፊነትን ፈልጎ ነው፡፡ በንግድ ውድድር የተሠማራውም እንደ እዚያው። ጦር የተማዘዘውም ሆነ ደጀኑም እንዲሁ፡፡ አሸናፊነት በሁሉም ዘንድ የምትፈለግ ነገር ግን ለሁሉም የማትሆን ናት። አሸናፊ መሆን የሚገባቸውን ነጥቦችን በመዘርዘር ወደ አሸናፊነት እንመራችኋለን የሚሉት መጽሐፍት በርክተዋል። ከመጽሐፍቱ ቁጥር በላይ ደግሞ ተሸናፊነት ሰማይ ምድሩን ይዞታል፡፡ ጥያቄው ተሸናፊነትን እንዴት እንመልከተው የሚለው ላይ ነው፡፡
በተጽዕኖ ምክንያት ተስፋ ቆርጦ እጁን ሰጥቶ የውስጡን ጥያቄ በሱስ ውስጥ የሚደብቀውን ምን እንበለው? እውነታውን ካልካድን ተሸናፊ ነው፡፡ ዛሬ የተሸነፈ ለነገ አይነሳም ማለት ባንችልም ዛሬ ግን መሸነፉን መቀበል አለብን፡፡ ሌላ ማሳያ፤ ዓመታትን በትምህርት ላይ ጨርሶ ከዩኒቨርስቲ ዲግሪውን ይዞ አዘፍኖ ወይንም አዘምሮ የተመረቀ ሰው የምስክር ወረቀቱን የማይመጥን እውቀት ይዞ ሲገኝ ምን እንበለው? አሸናፊ ወይንስ ተሸናፊ፡፡ ለአንባቢው ፍርዱን እተወዋለሁ፡፡ በትዕግስት ማሳለፍ የሚገባንን ግጭት ወደ ግብግብ ቀይረን አላስፈላጊ ምስቅልቅል ውስጥ ሲገባ ግጭት ውስጥ ለገባ ቤተሰብ ሆነ ለተጋጮቹ ድምር ውጤቱ ምንድን ነው? አሁንም ፍርዱን ለአንባቢው እተወዋለሁ፡፡
ማሸነፍን ማወጃችን ተገቢነት አለው፡፡ እንደ አገር አሸናፊነት መገለጫችን ወደሚሆንበት መድረስ አለመቻላችን ግን ልንጠይቀው የሚገባ ነው፡፡ እንዴት ከአሸናፊነት ጎደልኩ?እንዴት እንደ አገር በልመና የምንመላለስ ሆንን? እንዴት የተነቃቁ የፈጠራ ባለቤቶች ሳይኖሩን ቀሩ? እንዴት ፋብሪካዎቻችን ለእኛ የሚበቃ ማምረት አልቻሉም? እንዴት መከባበር በመካከላችን ስፍራን አጣ? እንዴት የሃይማኖት አባቶች ሚናቸው በአገር ደረጃ የሚደመጥ ሳይሆን ቀረ? እንዴት እንደ ትውልድ ከቁም ነገር ራቅን? እንዴት? እንዴት? … ወዘተ፡፡
ጥበብ አሸናፊነትን ተጎናጽፎ ስለመኖር ትጣራለች፡፡ አስተዋይነትን የለበሰ ሰው በአሸናፊነት የሚመላለስ ነውና ፍሬው ለብዙዎች ይደርሳል፡፡ በምንለውና በሆነው መካከል ልዩነቱ ቢሰፋ የአሸናፊነት ስብከታችን ፊደል ብቻ ሆኖ ይቀራልም፡፡ እናም አሸናፊነት ያሻናል! እንደ ግለሰብም፣ እንደ ቤተሰብ፤ እንደ ማኅበረሰብና እንደ አገር!!!
አሸናፊነት እውን ይሆን ዘንድ አክብረን ያልያዝነውን ነገር ፈልገን ማግኘት አለብን፤ የጋራ ሕልምን፡፡ ራዕይ የሌለው ሕዝብ መረን ነው፤ የጋራ ሕልም የሌለው፡፡ በዕቁብ ላይ ሁለት ጎልተው የወጡ ሕልሞች አሉ፤ እቁብ የደረሳቸው የሚያልሙት እና ዕቁብ ያልወጣላቸው አሻግረው የሚያዩት።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/2014