ዓለም ሁሌም በክፋት ሀሳብ ውስጥ ናት። ቸር መስለው ሌሎችን የሚጎዱ፣ የሚሰጡ መስለው የሚነጥቁ በርካታ የጭቃ ውስጥ እሾኮች አሏት። ከነዚህ ውስጥ አንዷ ደግሞ አሜሪካ ናት። አሜሪካ ስትነሳ ከኢኮኖሚና ከቴክኖሎጂዋ በላይ ማንም የሌለው ክፋትና ራስ ወዳድነቷ አብሮ ይጠቀሳል።
በአገራችን ስታደርጋቸው የቆየቻቸውና እያረገቻቸው የምትገኝ የድጋፍ የሚመሰሉ ጥፋቶች ለእዚህ በማሳያነት ሊቀርቡ ይችላሉ። የጭቃ ውስጥ እሾህ በመሆን የኢትዮጵያ ወዳጅ መስላ ብዙ ደባዎችንና ጥቃቶችን ፈጽማብናለች። የቅርቡን እንኳ ብንጠቅስ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጽ ጋር ተደራደሩ አለች፤ ከድርድር አመቻችነትና ከታዛቢነት አልፋም አደራዳሪ ካልሆንኩ ብላ ሰነድ አዘጋጅታ ልታፈራረም ቃጣት።
የግብጽና የአሜሪካ ግንኙነት የት ድረስ እንደሆነ ለምታውቀዋ ኢትዮጵያ የአሜሪካ አደራዳሪነት ምን ሊያስከትል እንደሚችል ግልጽ ነው። እናም ኢትዮጵያ ያ ድርድር ቀፈፈኝ ማለቷ አሜሪካን ሳያማት አልቀረም። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ላይ የማትልከው የላትም። የኢትዮጵያ ጠላቶች ያለቻቸውን ሁሉ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ማስነሳት ውስጥ ገብታለች።
ኢትዮጵያ በአገር ክህደት ወንጀል እና በአሸባሪነት ከፈረጀችው ትህነግ ጋር ቅቤ መጥበስ ውስጥ መግባቷ ሌላ ምን ያመለክታል። እንደ ትህነግ ሁሉ የኢትዮጵያን መንግሥት ለመጉዳት የማትፈነቅለው ድንጋይ ላለመኖሩ ከትህነግ ጋር የፈጠረችው ወዳጅነት ያስገነዝባል። በትግራይ ክልል በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሰበብ ሕወሓትን ቀና እንዲያደርግ የገባው የመገናኛ መሣሪያ ለእዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
በክህደት ወንጀሉ ሳቢያ በረሃ ውስጥ ጠውልጎ የነበረው ትህነግ ቀና ቀና ማለት የጀመረው በእርዳታ እና በእርዳታ ውስጥ በገቡለት ድጋፎች ነው። ውሻ በበላበት እንዲሉ ክህደት መገለጫው የሆነው ይህ ቡድን ለአሜሪካ በማደር አሁንም ኢትዮጵያን ከዳ። ለሃያ ሰባት ዓመታት ያደረገው አልበቃ ብሎት ኢትዮጵያውያንን ጨፈጨፈ፣ ንብረታቸውን እየዘረፈ ወደ ትግራይ አጋዘ፤ የተቀረውን አወደመ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን አፈናቀለ። ይህ ሁሉ የሆነው የአሜሪካና ምዕራባውያኑ ድጋፍ ይዥጎደጎድለት ከጀመረ ወዲህ ነው።
የኢትዮጵያም ትግል ከምዕራባውያኑ ጋርም ጭምር እየሆነ መጣ። ያሳለፍንው አንድ ዓመት እውነትን ሽተን ለምንታገለው ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የፈተና ወቅት የሆነብን ትግሉ ከትህነግ ጋር ብቻ ባለመሆኑ ነው። ትግላችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪም ድጋፍ ከሚያደርጉለት ከምዕራባውያን በተለይም ከዋናዋ አሜሪካ ጋር ሆኗል።
አሜሪካና ትህነግ ይመሳሰላሉ። የአሜሪካ የክፋት ሀሳቦች ከሕወሓት የክፋት ሀሳቦች ጋር አንድ ናቸው። ሁለቱም ራሳቸውን እንጂ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚበጅ አንድም ነገር የላቸውም። ትህነግ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር ለማድረግ ሲኦል መግባት ካለብኝ እገባለሁ ያለ ቡድን ነው/ይህን በግልጽ ያስቀመጠ ቡድን ነው/ ፤ አሜሪካም የአሜሪካ ጥቅሞች የምትላቸውን ከማስጠበቅ ወጪ ሌላ አጀንዳ የላትም። የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የአገር ሉዓላዊነት ወዘተ የሚሉት ለአሜሪካ የይስሙላ ስለመሆናቸው በዚህ አንድ ዓመት በሚገባ ማየት ችለናል።
ሕወሓት በ27ቱ ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ኢትዮጵያን አሲዞ ከኃያላኑ ጋር ያልፈጸመው ድርድር የለም። አሜሪካኖቹና ምዕራባውያን አገሮች የዚህ ጥቅም ተጋሪዎች አልነበሩም ተብሎ አይወሰድም። ሕወሓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዘርፎታል የሚባለው ብዙ ቢሊየን ዶላርስ የተቀመጠው በእነዚሁ አገሮች አይደል።
እነዚህ አገሮች ባለፉት ሶስት ዓመታት ከሕወሓት ወደካዝናቸው የገባ ገንዘብ አለመኖሩ ሳያማቸው የቀረም አይመሰለኝም። የዛሬው የአሜሪካና የምዕራባውያኑ ፍርደ ገምድልነትም ይህንኑ ጥቅም ማስቀጠልን ያለመ ነው። እናም አሜሪካ ጥቅሟን ለማስጠበቅ አይታዘዘኝም ያለችውን መንግሥት አውርዳ ሕወሓትን ካልሆነም ከእሱ ያልተለየን አሻንጉሊት መንግሥት ለመመስረት እየሰራች ናት።
አሜሪካኖች ሽማግሌ ሊሆኑ ሞከሩ፤ አልሆነም፤ አስፈራሩ፤ አልሆነም፤ ማዕቀብ መጣል ውስጥ ገቡ ፤ አልሆነም። አሁን ደግሞ ግልጽ ጦርነት ሊባል የሚችል ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ ውስጥ ገብተዋል እየተባለ ነው። ሕወሓት ለውጊያው የሳተላይት መረጃ እየደረሰው ያለውም በዚህ መልኩ መሆኑ እየተጠቆመ ነው። ይህን መረጃ ደግሞ ከአሜሪካ ካልሆነ በቀር ከሌላ አካል ሊያገኝ አይችልም እየተባለ ነው። በእርግጥ ይህ ሆኖ ከሆነ ደግሞ አሜሪካኖቹ በትህነግ በኩል ሆነው እያዋጉ ናቸው ማለት ነው። ከዚህም አሜሪካኖቹ ከጭቃ እሾህነት ወደ አዋጋኒት እንደተሸጋገሩ እንረዳለን።
አሜሪካ የራሷ ጉዳይ የሌላት እስኪመስል ድረስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ስታቦካና ስትጋግር ትታያለች። በሕወሓት የስልጣን ዘመን እንዲሁም ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰው ስቃይ ለአሜሪካ ምኗም አይደለም። በቀጣይም የሚሆነው ይሄው ነው። አሜሪካ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ስቃዩ እየጎለበተ ሲሄድ የእሷና የትህነግ እንጀራ እንደሚበስል ነው የምታስበው።
የአሜሪካና አውሮፓውያኑ ፍላጎት በሕወሓት መሪነት ኢትዮጵያን በመቆጣጠር ምስራቅ አፍሪካን መቆጣጠር ከዛም አፍሪካን እንዳሻቸው መዘወርም ነው። ለዚህ ሁሉ ደግሞ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ግድ ይላቸዋል። ለዚህ ሁሉ ክፋታቸው ደግሞ ከሀዲውና አሸባሪው ሕወሓት አስፈልጓቸዋል።
ያኔ በበርሊኑ ጉባኤም የታየው ይሄው ነበር፤ አውሮፓውያን በአፍሪካ ላይ አነጣጠሩ። ጣሊያን ኢትዮጵያን መረጠች፤ እንዳሰበችው ግን አልሆነም፤ ይባስ ብሎ በኢትዮጵያ ነጻነት የመላው አፍሪካ አርነት ወጣ እንጂ። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀኝ እጅ እንደሆነች ያምናሉ፤ ለዛም ነው የክፋት ሀሳባቸውን ይዘው ከሸረኛው ቡድን ጋር የሚያሴሩት።
አሜሪካ በቅርቡ ደግሞ በአዲስና ባልተለመደ የክፋት ሀሳብ መጥታለች። የሕወሓት ወራሪ ቡድን ከአማራ ክልልና ከአፋር ክልል ለቆ እንዲወጣ የሚያዝ ቀጭንትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር። ከዚህ ትዕዛዝ ኋላ ምን እንዳለ አናውቅም። የአሜሪካ ሀሳብ ለኢትዮጵያውያን መልካም ሆኖ አያውቅም። አሜሪካ መንግሥታችን የተራመደባቸው ጠንካራ የሉዓላዊነት መንገዶች አላፈናፍን ሲላት የቀየሰችው የማስመሰያ ሀሳቧ እንደሚሆን መጠርጠሩ አይከፋም ባይ ነኝ።
በክፋት ሀሳቧ አገርና ታሪክ አውድማ የራሷን ቤት የምትሰራ ዘመነኛ ወንበዴ ናት..አሜሪካ። ጠላትን አሳምሮ ማወቅ ትልቅ ነገር ነው። የቱንም ያህል አሜሪካ ጥሩ ነገር ብታደርግ በጥርጣሬ መመልከት ይገባል። የምሳ ነጻ የለም / ኖ ፍሪ ላንች/ ነው የሚባለው፤ በእያንዳንዱ ለጋስነቷ ውስጥ ይዛ የምትቀርበውን አስቀድሞ ማወቅ ይገባል።
የአሜሪካ ጉዞ መጨረሻው የት ጋ እንደሆነ አናውቅም። ጉዞዋ ምንም ይሁን ምን እኛ ግን በአንድነትና በሕብረት በመቆም የክፋት ሀሳቧን መና በማስቀረት ታሪክ ማድረግ ይጠበቅብናል። ለእዚህ ደግሞ ምስጋና ለጀግኖች አባቶችና እናቶች ተሞክሮው አለን። አገሩን የሚወድ ዜጋ ሁሉ ከመንግሥት ጎን በመቆም ይህን የአሜሪካና አጋሮቿን ደባ ማክሸፍ ይጠበቅበታል። ጊዜው የአባቶቻችንን አደራ የምንፈጽምበት ነው። የአባቶቻችንም አደራ ደግሞ አገርና ሕዝብን መጠበቅ ነው። በዚህ እውነት ውስጥ በመቆም ህልውናችንን ማስቀጠል ይኖርብናል።
ይሄ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን ክብርና ሉዓላዊነታችንን ላለማስደፈር የሄድንባቸው የችግር ጎዳናዎች ከሕመማቸው እኩል አጠንክረውናል ብዬ አስባለሁ። ያለፉት አንድ ዓመት መከራዎቻችን ጥንካሬን ያገኘንባቸው ስለመሆናቸው የአሜሪካና የምዕራባውያኑ ዛቻና ማስፈራሪያዎችና ጫናዎች ምስክሮች ነው። አሁንም ቀጣይ ጫናዎችን በመቋቋም አገራችንን የማሻገር ሌላ የቤት ስራ እንዳለብን እንገዘብ። የአሜሪካ የክፋት ሀሳብ ማለቂያ የለውም። ትናንት ስታስብ ነበር፤ ዛሬም እያሰበች ነው። ነገም ምን እንደምታስብ አናውቅምና ይህን ሁሉ ለመቀልበስ ክንዳችንን ማጠንከር ይኖርብናል እላለሁ፡ አበቃሁ፤ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 1/2014