ባለፈው ሳምንት የተከበረውን የእጅ መታጠብ ሳምንት ምክንያት በማድረግ ሰይፉ ፋንታሁን በኢቢኤስ ቲቪ ላይ ከአርቲስት ሚካኤል ታምሬ ጋር አንዲት አጭር ጭውውት አሳይቷል።ሰይፉ የእጁን ንጹህነት አይቶ ሊበላ ሲል አርቲስት ሚካኤል ይከለክለዋል።የሰይፉ እጅ በባትሪ መሰል ነገር (የጤና ባለሙያዎች የሚጠቀሙት መሰለኝ) ሲታይ ብዙ ነገሮች ይታያሉ።ባለሙያዋ እያሳየችው በሚገባ ከታጠበ በኋላ እጁ ላይ ስታበራ እነዚያ ነገሮች አይታዩም።
ኮቪድ-19 አፍላ በነበረበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ትምህርቶች በየመድረኩ፣ በመገናኛ ብዙኃን እና በየአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሁሉ ይሰጡ ነበር።ማንም ሰው ወደየትኛውም አገልግሎት ሰጪ ተቋም እጁን ሳይታጠብ አይገባም፤ ወይም እጁን ሳኒታይዘር ሳይቀባ አይገባም ነበር።ይህ አሁን አሁን እየተዘነጋ ነው።በትልልቅ ሆቴሎችና በባንኮች አካባቢ ብቻ ነው የሚታይ።
ምንም እንኳን ተቋማዊ የሆነው ቁጥጥር ቢቀንስም፣ ምንም እንኳን በኮቪድ ላይ የነበረን ፍርሃት የቀነሰ ቢሆንም (ኮቪድ-19 ባይጠፋም) አንዳንድ የመከላከያ መንገዶቹ ግን ልማድ ሆነውልን ቀርተዋል።እነዚህ የመከላከያ መንገዶች ሌሎች ነገሮችንም እንደሚከላከሉ አይተንበታል።ከራሴ ልማድ ልነሳ።
በተለይም በሰሞኑ የጥቅምት ብርድ ጠዋት ከቤት ስወጣ ወዲያውኑ ነው ማስክ ማድረግ ነው ትዝ የሚለኝ።የማደርገው ማስክ ብርድ እየተከላከለ ጥቅሙን ለመድኩት።እንዴ ቀጩንም ይከላከላል፤ ወቅቱስ ጥቅምት አይደል፤ ቆፋናም የሚያደርገው ጥርም ይመጣል።
ከቤት ስወጣ ማስክ የማደርገው ምንም ሰው አጠገቤ በሌለበት ነው።ኮቪድ-19 ትዝ ብሎኝ ሳይሆን ብርድ እንዳደርገው አስገደደኝ ማለት ነው።ስለዚህ በእንዲህ ዓይነቱ የነፋስና የብርድ ወቅት የከንፈር መሰነጣጠቅን እየተከላከልን ነው ማለት ነው።
ሌላው በማስክ ያገኘሁት ጥቅም ደግሞ ከርቀት የሚመጣ መጥፎ ሽታን መከላከል ነው።መጥፎ ሽታ ሲሸተን አፍንጫ መያዝ አይመከርም።አንዳንዶች ሽታ አይከላከልም ይላሉ።እኔ ግን ይከላከላል ባይ ነኝ።አይመከርም የሚባለው ግን ሽታው ከገባ በኋላ መያዝ ነው እንጂ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከሆነ መጥፎ ሽታን በከፊልም ቢሆን ይከላከላል።
ማስክ ገና ብርቅ በነበረበት ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያየሁት አንድ ቀልድ ነበር፤ ቀልዱ ከቀልድነት ያለፈ ቁም ነገር ላይኖረው ይችላል።
‹‹ማስክ የጠቀመኝ ብቻዬን ሳወራ ሰው እንዳያየኝ ነው›› ብሎ ነበር አንዱ።የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ብቻዬን የሚያስቅ ነገር ሲያጋጥመኝ ያ ቀልድ ትዝ ይለኛል።አንዳንድ ሰው ብቻውን የሚያወራበት አጋጣሚ ወይም ብቻውን ፈገግ የሚልበት አጋጣሚ ይፈጠራል።እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ የሌሎች ሰዎችን ትኩረት ይስባሉ፤ ‹‹እብድ ነው እንዴ!›› ያሰኛል።ማስክ እንዲህ ዓይነት ገመናዎችንም ይሸፍናል ማለት ነው።
ማስክ ጉንፋንን በመከላከል ከፍተኛ ጥቅም ሰጥቷል።እንደሚታወቀው ኮቪድ-19 ገና አፍላ በነበረበት ጊዜ ብዙ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሠሩ (እንደየሥራው ባህሪ) ፈቅደው ነበር።አንዳንዶቹም አሰናብተው ነበር።በዚህ ምክንያት ብዙ ሰው ከቤት መዋል ጀምረ።እናም በዚያን ወቅት ማህበራዊ ገጾች ላይ መነጋገሪያ የነበረው የጉንፋን መጥፋት ነው።ይሄ ማለት መከላከያ ዘዴዎቹ ጉንፋንንም እየተከላከሉ ነበር ማለት ነው።
የጤና ባለሙያዎች በወቅቱ ይናገሩ እንደነበረው ጉንፋን በእጅ ንክኪም ይተላለፋል፤ ጉንፋን የከፋ ጉዳት ስለማያደርስ ነው አጀንዳ ያልሆነው እንጂ የሚተላለፈው በትንፋሽ ብቻ አልነበረም።እናም አለመጨባበጡና አለመጠጋጋቱ ጉንፋንንም ሲከላከል ነበር።
በብዙ ሰዎች ‹‹ኮሮና ከገባ ወዲህ ጉንፋን እንኳን አልያዘኝም›› ሲሉ ይሰማል፤ የዚህ ምክንያቱ ሌላ መለኮታዊ ክስተት ሳይሆን በኮቪድ-19 ምክንያት የጉንፋኑንም የመከላከያ መንገድ ስለተጠቀሙ ነው።በዚያ ላይ ደግሞ የጉንፋንና የኮቪድ-19 የመከላከያ መንገዶች ተቀራራቢ ናቸው።ጉንፋን ቀላል ስለሆነ ነው ትኩረት ያልተሰጠው እንጂ በኮሮና መከላከያ መንዶች መከላከል እንደሚቻል የጤና ባለሙያዎች የነገሩን ሀቅ ነው።
ከማስክ በተጨማሪ ሌላው የለመድነው በጎ ልማድ ደግሞ እጅን መታጠብ ነው።መግቢያዬ ላይ እንዳልኩት ባለፈው ሳምንት የእጅ መታጠብ ሳምንት ተብሎ ተከብሯል።
እጅ መታጠብ ደግሞ ኮቪድ-19 እና ጉንፋን ብቻ ሳይሆን በጣም ብዙ በሽታዎችን ነው የሚከላከል።እጅ ደግሞ ቫይረስ ብቻ ሳይሆን ባክቴሪያ እና ሌሎች የጀርም ተህዋሶችን ሁሉ ይይዛል።ስለዚህ እጃችንን ስንታጠብ የምንከላከለው በቫይረስ የሚተላለፉ በሽታዎችን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ነገሮች ሁሉ የሚተላለፉትን እየተከላከልን ነው ማለት ነው።
እንግዲህ የእጅ መታጠብ ሳይንሳዊ ጥቅሙ ይህ ከሆነ በኮቪድ-19 አፍላነት ወቅት የነበረው አስገዳጅ የእጅ መታጠብ ትዕዛዝ ልማድ እንዲሆንብን አድርጎናል።ከዚህ በፊት አስተውለው የነበረው ነገር አሁን ብዙም የለም።
ከዚህ በፊት እጅን ሳይታጠቡ የመመገብ ልማድ ሁሉ ነበር፤ ወይም ደግሞ ጠረጴዛ ላይ ያለውን ለመጠጥ የመጣ ውሃ በብርጭቆ ቀነስ አድርገው ጣታቸውን የሚያስነኩ ነበሩ።ያ ዓይነት አስተጣጠብ ካለመታጠብ በምንም አይለይም።አሁን ግን የዚህ ዓይነት ድርጊት ብዙም አይታይም።እንዲያውም ያለሳሙና የሚታጠብ የለም።ከዚህ በፊት ሰዎች በሳሙና የሚታጠቡት ከበሉ በኋላ የወጡን ቅባት ለማስለቀቅ ነበር፤ አሁን ግን ከምግብ በፊትም ሆነ በኋላ በሳሙና ነው።
ሌላው ልማድ የሆነው ነገር ሳኒታይዘር መቀባት ነው።ብዙ ሰዎች (በተለይም ሴቶች) ታክሲ ውስጥ ለረዳት ብር ከሰጡ በኋላ ከቦርሳቸው ሳኒታይዘር አውጥተው ይቀባሉ።ይህ ድርጊት የኮቪድ-19 ፍራቻ ብቻ አይሆንም፤ ልማድ ጭምር ነው።ለምሳሌ ርቀትን መጠበቅ አሁን አሁን ተዘንግቷል፤ ሳኒታይዘር መቀባት ግን እየተፈጸመ ነው።ስለዚህ ይሄ ሳኒታይዘር የመቀባት ልምድ ሌሎች በሽታዎችንም ይከላከላል ማለት ነው።ብር በሚያደርገው ዝውውር ከብዙ ሰው እጅ ላይ ስለሚያርፍ ብዙ ነገር ይኖረዋል፤ በዚያ ላይ ብር ከቦርሳ፣ ከኪስ ስለሚወጣ ብዙ ጀርም ይይዛል።በዓይን የሚታዩ ቆሻሻዎች እንኳን አሉት።ስለዚህ የሳኒታይዘር ልምድ ከብር ላይ የሚመጡ ጀርሞችን ይከላከላል ማለት ነው።
የኮቪድ-19 ሌላኛው በረከት ደግሞ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው።በፈጠራ ሥራዎች በኩል ያበረከተልን በጎ ልምድ በመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ተነግሮለታል።በእግር የሚሰሩ የእጅ መታጠቢያዎች ለሌላ ጊዜም ቢሆን አስፈላጊ ናቸው።ማስክ ለመሥራት በመሞከር የተለያዩ የጥልፋጥልፍና ሌሎች የዕደ ጥበብ ሥራዎች ተሠርተዋል።
‹‹ችግር ብልሃትን ይወልዳል›› እንዲሉ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እነዚህን በጎ ልማዶች ብናዳብርም ወረርሽኙ ግን አሁንም እንዳለ ነው።ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎችን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ራሱ ኮቪድ-19 አሁንም ሥጋት ነው።
ባለፈው ዓርብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በኩል ከፍተኛ መዘናጋት እየታየ መሆኑን አሳውቋል።ጥናት እና የሰዎች አስተያየት ዋቢ ባናደርግም ሁላችንም በየቦታው የምናስተውለው ነው።በተለይም ርቀትን መጠበቅ ሙሉ በሙሉ የተዘነጋ ይመስላል።የአፍና አፍንጫ መሸፈኛም ቢሆን እንደ ባንክ እና መድኃኒት ቤቶች ውስጥ አስገዳጅ ስለሆነ እንጂ በሌሎች ቦታዎች እየተዘነጋ ነው።ታክሲዎች ውስጥ ረዳቱንና ሾፌሩን ጨምሮ የማያደርጉ ሰዎች ማየት አዲስ አይደለም።
በኮቪድ-19 ምክንያት ያዳበርናቸውን በሽታን የመከላከል ዘዴዎች ልማድ እናድርጋቸው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2014